ኢያሱ መሰለ
ከጠዋቱ አስራ ሁለት ሰዓት አካባቢ ነው:: ቦታው አዲስ አበባ ከሜክሲኮ አደባባይ ወደ ጦር ሃይሎች በሚወስደው ጎዳና ደጃዝማች ባልቻ አባነፍሶ ሆስፒታል አጠገብ ነው፤ ወደ መስሪያ ቤቴ ለመሄድ ትራንስፖርት ወደምሳፈርበት ቦታ በማምራት ላይ እገኛለሁ:: የጽዳት ሰራተኞች ጎዳናዎችን ያጸዳሉ:: እራፊ ጨርቅ፣ ላስቲክና ማዳበሪያ ሰውነታቸው ላይ ጣል ጣል ያደረጉ የጎዳና ተዳዳሪዎች በየጥጋ ጥጉ ተኝተዋል:: መንጋቱን ሲጠባበቁ የነበሩ ሰዎች የየእለት ተግባራቸውን ለማከናወን ወዲህ ወዲያ ማለት ጀምረዋል:: በዚያች ቅጽበት የአንዲት እናት እንቅስቃሴ ትኩረቴን ሳበኝ:: ሴትየዋ ባለሞተር ዊልቸር ላይ ተቀምጣ ሽቅብ ወደ ልደታ ቤተክርስቲያን ትወጣለች:: ከዊልቸሩ ፊት ለፊት ጧፍና ሻማ አስቀምጣለች:: ቤተክርስቲያን ለመሳለም የሚሄዱ ሰዎች እያስቆሟት የሚፈልጉትን ነገር ሲገዟት አስተዋልኩኝ:: ባለሞተሩ ዊልቸር አካል ጉዳተኛ መሆኗን ይናገራል::
ኑሮዋን ለማሸነፍ ማለዳ ወደ ስራ በመሰማራት ላይ ያለችውን እናት ለአንድ አፍታ ቆም ብዬ ከጤነኛ ሰዎች ጋር አነጻጸርኳት:: ችግራቸው ምንም ይሁን ምን ሙሉ ጤንነት ይዘው በየጎዳናው እየቆሙ አላፊ አግዳሚውን ምጽዋት የሚጠይቁ ሰዎችን በአዲስ አበባ ጎዳናዎች ማየት የተለመደ ሆኗል:: እንዲህ ዓይነት ሰዎች በሚበዙበት ከተማ ያጋጠማትን የጤና እክል ምክንያት ሳታደርግ ሰርታ ለመኖር የምትጥር ምስኪን እናትን መመልከት ያስገርማል:: ከራሷ አልፋ ሌሎችን የምታኖር መሆኗ ሲታሰብ ደግሞ የበለጠ ጥንካሬዋን ያሳየናል::
በልጅነቷ ድንገት በገጠማት የጤና እክል ምክንያት ሁለት እግሮቿ ከጥቅም ውጭ ስለሆኑ ቆማ መሄድ አትችልም:: ሰራተኛ ሳትቀጥር ዘመድ ሳይረዳት ሶስት ልጆቿን ተንከባክባ አሳድጋለች:: ጧፍና ሻማ በመሸጥ በምታገኛት አነስተኛ ገቢ አምስት ቤተሰቦቿን ታስተዳድራለች:: የደረሰባት የአካል ጉዳት ምክንያት አድርጋ እጇን ለልመና መስጠት አልፈለገችም:: ከልጅነቷ ጀምሮ እራሷን ችላ ለመኖር የሚያስችሏትን ስራዎች ሰርታ ለማደር ጥራለች:: ለበርካታ ዓመታት የአዲስ አበባን የኑሮ ውድነት ተቋቁማ ቤተሰቦቿን በቤት ኪራይ አኑራለች:: ቤተሰቧን ለማኖር በውጣ ውረድ ውስጥ የምታልፈው አካል ጉዳተኛ ሴት ጥረቷና ትጋቷ አስተማሪ በመሆኑ የዚህ አምድ እንግዳ ላድርጋት አስቤ ፈቃደኝነቷን ጠየኳት:: ሳታቅማማ እሺታዋን ገልጻልኝ ወደ ወጋችን ገባን::
አስረበብ ይግዛው ትባላለች:: ተወልዳ ያደረገችው ደቡብ ጎንደር ዞን ጋይንት ከሚባል ቦታ ነው:: አሁን በአዲስ አበባ ልደታ ክፍለ ከተማ ወረዳ አስር ነዋሪ ነች:: አካል ጉዳተኛዋ እናት በልጅነቷ ጤናማ ሆና እንደተወለደች ትናገራለች:: እንደማንኛውም ልጅ ከአካባቢው ልጆች ጋር እየተጫወተችና ለቤተሰቦቿ እየተላላከች ማደጓን ታስታውሳለች:: ቤተሰቦቿ ለትምህርት ያላቸው ግንዛቤ አናሳ በመሆኑ የልጅነት ጊዜዋን በስራ እንዳሳለፈች ትናገራለች:: የግብርና ስራዎችን በማገዝ፣ ውሃ በመቅዳት፣ የቤት ውስጥ ስራዎችን በመስራትና ታናናሾቿን በመንከባከብ ወርቃማውን የልጅነት እድሜዋን ያለትምህርት አሳልፋለች::
አስረበብ የ15 ዓመት ታዳጊ እያለች የገጠማት ድንገተኛ ክስተት የአካል ጉዳት እንዳስከተለባት ትናገራለች:: ሁኔታውን እንዲህ ታስረዳለች:: በግብርና ስራ የሚተዳደሩት አባቷ ከሰፈራቸው ራቅ ባለ ቦታ በስራ ተጠምደዋል:: የአስረብብ እናት ስራ ላይ ላሉት ባለቤታቸው ምሳ አዘጋጅተው አስረብብን አስይዘው ይልኳታል:: የእናቷን ትእዛዛ ለመፈጸም ከቤት ወጥታ ወደ ተላከችበት ቦታ በመሄድ ላይ ያለችው ታዳጊ ገና ከቤቷ ወጣ እንዳለች አደገኛ አውሎ ንፋስ ይነሳና በአቧራ ያፍናታል፤ ነፋሱ ብርቱ ስለነበር ግፊቱ እንዳይጥላት በመስጋት ባለችበት ቦታ ቁጭ ትላለች:: ለተወሰነ ጊዜ መንገዱን ያፈነውና በተቀመጠችበት ቦታ አቧራ እያስነሳ ሲጦዝ የነበረው አውሎ ነፋስ ይከስማል:: አስረብብ ከተቀመጠችበት ልትነሳ ትሞክራለች:: ነገር ግን ሁለቱም እግሮቿ አልታዘዝ ይሏታል፤ መነሳት አቅቷት እዚያው ቁጭ ትላለች:: ባለችበት ሆና የሰዎችን እርዳታ ለማግኘት ድምጽ ታሰማለች:: ድምጧን የሰሙት እናቷ እየሮጡ ሄደው ልጃቸውን አፋፍሰው ሊያነሷት ሲሞክሩ ያቅታቸዋል:: እየሮጠች ስትሄድ የነበረችው ልጃቸው ከመቅጽበት ከወደቀችብት መነሳት ሲያቅታት ግራ ተጋብተው እሪታቸውን ሲያቀልጡት ሰዎች ደርሰው ያነሷትና ወደ ቤቷ ይወስዷታል:: ቤተሰቦቿ ይሻላታል በማለት ለጉዳዩ ብዙም ግምት ሳይሰጡ ይቀራሉ:: ኋላ ግን ወጌሻ እያስመጡ እግሯን ማሳሸት ይጀምራሉ:: አስረብብ ሊሻላት አልቻለም:: ከዚያም ወደ ጸበል ይዘዋት ይሄዳሉ፤ እዚያም ለረዥም ጊዜ እየተቀመጠችም እየተመላለሰችም ስትጸበል ብትቆይም ምንም አይነት የጤና መሻሻል ሳታሳይ ትቀራለች:: የቤተሰቦቿ የኑሮ ደረጃና አቅም አስፈላጊውን ህክምና በሙሉ ለማድረግ እንዳላስቻላት የምትናገረው አስረብብ ከተወሰነ የጸበል ክትትል በኋላ ቤተሶቦችዋ እቤት አስገብተው እንዳስቀመጧት ትገልጻለች:: ተስፋ የተጣለባት ብላቴና ገና በልጅነቷ ምክንያቱ በውል ባልታወቀ ህመም እንደዋዛ እግሮቿ ተሳስረው እቤት ለመቀመጥ ትገደዳለች::
እቤት በተቀመጠችባቸው ዓመታት የወደፊቱን ህይወቷን በማሰብ እራሷን ችላ የምትኖርበትን ስራ አማራጭ ፈልጋ በአካባቢዋ ሰርታ ለመኖር የሚያስችላትን እደ ጥበብ መለማመድ ትሞክራለች:: እንደ ሌማት፣ መሶበወርቅ፣ ወስከንባ የመሳሰሉ ከስንደዶ የሚሰሩ ባህላዊ ቁሶችን በመስፋት እየሸጠች የራሷን ወጪ ከመሸፈን አልፋ መጠነኛ ገንዘብ ማጠራቀም ትጀምራለች:: ባጠራቀመችው ገንዘብ ቅድሚያ ለጤናዋ በመስጠት የህክምና ክትልል ለማድረግ ወደ ደሴ ሆስፒታል ትሄዳለች:: በሆስፒታሉ የጤና ምርመራ ካደረገች በኋላ ጉልበቷ ላይ ጉዳት እንደደረሰባት ይነገራታል:: የህክምና ጥረቷ ውጤት ሳያመጣ ይቀርና ታዳጊዋ ተስፋ ቆርጣ ወደ ቤቷ በመመለስ የጀመረችውን የእጅ ስራ መስራቷን ትቀጥላለች::
አስረበብ የምታዘጋጃቸውን ባህላዊ ቁሶች የምትሸጠው በርካሽ ዋጋ በመሆኑ ወጪዋና ገቢዋ አልመጣጠን ይላል:: ወደ አዲስ አበባ ብትሄድ የእደ ጥበብ ውጤቶቿን በተሻለ ዋጋ መሸጥ እንደምትችልና በጎ አድራጊ ድርጅቶች የሙያ እገዛ ሊያደርጉላት እንደሚችሉ ተነግሯት ተወልዳ ያደገችበትን አካባቢ ትታ ትመጠላች::
የአዲስ አባባ ህይወት ግን እርሷ እንዳሰበችው ቀላል ሆኖ አላገኘችውም:: ለጥቂት ጊዜ ቤት ተከራይታ የእጅ ስራዎቿን እየሰራች ለመኖር ሞከረች፤ ግን የሚቻል አልሆነም:: ለስራው የሚያስፈልጉ ግብዓቶችን ማግኘትና የተሰሩ እቃዎችን ለገበያ ተደራሽ ማድረግ ሌላ ፈተና ይሆንባታል:: በዚህ ምክንያት አስረብብ ትቸገራለች:: የእለት ጉርሷን መሸፈን ያቅታትና ለልመና ትዳረጋለች:: የሰው እጅ እያዩ የመኖር ፍላጎት የሌላት አካል ጉዳተኛዋ ሴት በአጭር ጊዜ ውስጥ ሳትፈልግ ከገባችበት የልመና ህይወት ወጥታ እየነገዱ ለመኖር መፍጨርጨር ትጀምራለች::
ኑሮን ብቻዋን ስትጋፈጥ የነበረችው ታታሪዋ ወጣት በአጋጣሚ ከተዋወቀችው የአካባቢዋ ሰው ጋር ትዳር ትመሰርታለች:: ባለቤቷ የቀን ስራ እየሰራ እርሷም ጧፍና ሻማ እየነገደች ተጋግዘው መኖር ይጀምራሉ፤ በዚህ መሃል ሶስት ልጆች ይወለዳሉ:: አስረበብ ልጆቿን እያጠባች፣ ልብሳቸውን እያጠበች፣ ምግብ እያበሰለች ታሳድጋለች:: ልጆቿን ያለማንም አጋዥ አሳድጋ እያስተማረች መሆኗን የምትናገረው አስረበብ ከጓደኞቻቸው አንሰው እንዳይታዩ መስዋእትነት እየከፈለች መሆኗን ትናገራለች::
አዲስ አበባ ከመጣች ከሃያ ዓመት በላይ እንደሆናት የምትናረው ታታሪዋ ሴት ከቤት ኪራይ ወጥታ ቀበሌ በሰጣት ቤት ውስጥ መኖር ከጀመረች ገና ሁለት ዓመቷ ነው:: የቤቷ ጥበት ከእርሷ የጤና ችግርና ከቤተሰቧ ብዛት አንጻር አመቺነት እንደሌለው ትገልጻለች:: በተለይም የመጸዳጃ ቤት ፈተና እንደሆነባት ትናገራለች:: ነገር ግን ሁሉንም ተቋቁማ እየኖረች ነው:: ዛሬ በዚህች ትንሽ ቤት ውስጥ አምስት ቤተሰቧን ሰብስባ የምታኖረውና ልጆቿን የምታስተምረው ጧፍና ሻማ በመነገድ ብቻ ነው:: ባለቤቷ የቀን ሰራተኛ በመሆኑ ስራ ከሚሰራበት ይልቅ የማይሰራበት ጊዜ እንደሚበልጥ ትናገራለች:: ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እንደውም ስራ እየሰራ አይደለም ትላለች::
አስረብብ ከቀበሌ እስከ ክፍለ ከተማ ችግሯን አስረድታ ቤት ለማግኘት በርካታ ውጣ ውረዶችን ማሳለፏን ትናገራለች:: በተለይም ሃላፊዎችን ለማግኘት ስትል ፎቅ ላይ የምታደርገው ምልልስ ከፍተኛ እንግልት እንዳበዛባትና ለአካል ጉዳተኛ አመቺ እንዳልነበር ታስታውሳለች:: ከብዙ ጥረት በኋላ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ችግሯን ተረድተው ስላደረጉላት ቀና ትብብር ግን ምስጋናዋ የላቅ እንደሆነ ትገልጻለች::
አስረበብ ‹‹አዲስ ጉዞ›› የተባለ በጎ አድራጊ ድርጅት በሰጣት ባለሞተር ዊልቸር ላይ ተቀምጣ ስራዋን ታከናውናለች:: ጠዋት ከሌሊቱ አስራ አንድ ሰዓት ተኩል ጧፍና ሻማወዋን በዊልቸሯ ላይ ጭና ቤተክርስቲያን መግቢያ በር ላይ ትቀመጣለች:: እስከ ስድስት ሰዓት ከሰራች በኋላ ወደ ቤቷ ትገባለች:: ማታ እንደአስፈላጊነቱ በምህላ ሰዓት እቃዋን ይዛ በመውጣት ከሸጠች በኋላ አምሽታ ወደ ቤቷ ትገባለች:: አስረበብ በሰባ አምስት ብር የምትረከበውን እስር ጧፍ ቸርችራ መቶ ብር ታጣራዋለች:: የንግስ በዓል እና ልዩ ፕሮግራም ሲኖር በርካታ ጧፍና ሻማ በመሸጥ የሌላውን ቀን የሚያካክስ ገቢ እንደምታገኝ የምትናገረው ታታሪዋ እንስት በአዘቦት ቀን ግን አንድ እስር እንኳን ሳትጨርስ የምትውልበት አጋጣሚ እንዳለ ትገልጻለች:: አብዛኛውን ጊዜ ልደታ ቤተክርስቲያን በር ላይ ተቀምጣ ትሸጣለች:: አልፎ አልፎ ደግሞ ከርቸሌ ሚካኤል ድረስ እየሄደች ትሸጣለች:: ቤተሰቦቿን ለማኖር ስትል ጸሃይና ዝናብ እየተፈራረቁባት እንደምትሰራ የምትናገረው እናት መጠለያ ባለው ቦታ ቁጭ ብሎ የመስራት ሀሳብ እንዳላት ገልጻለች:: ነገር ግን የቦታና የገንዘብ አቅም ህይወቷን በተሻለ ደረጃ ለመምራት እንቅፋት እንደሆኑባት ትጠቅሳለች::
ባለፈው ዓመት የኮሮና ቫይረስ መከሰቱን ተከትሎ የቤተክርስቲያን ተሳላሚዎች ቁጥር መቀነስ በገቢዋ ላይ ተጽዕኖ እንደፈጠረባት የምትናገረው አስረበብ አሁን የተሻለ ገቢ እያገኘች እንደሆነና የቤተሰቦቿን የእለት ጉሮሮ መሸፈን እየቻለች መሆኑን ታስረዳለች:: የሶስት ልጆቿን ፍላጎት ለማሟላትና አስተምራ ለቁም ነገር ለማብቃት ቀን ከሌሊት እየተጋች መሆኗን ትገልጻለች::
አስረበብ አሁን ስጋት የሆነባት ከበጎ አድራጎት የተሰጣት ባለሞተር ዊልቸር ባትሪው እየደከመ መምጣቱ ነው:: ሞተሩ ቻርጅ እየተደረገ ጥቅም የሚሰጥ መሆኑን የምትገልጸው ታታሪዋ ሴት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አቅሙ እየደከመ መጥቷል ትላለች:: ባትሪው ከቆመ ስራዋ የሚስተጓጎል መሆኑንና ቤተሰቧ ለችግር የሚጋለጥ መሆኑ የሁልጊዜ ስጋቷ እንደሆነ ትገልጻለች:: የሞተሩ ባትሪ አስር ሺህ ብር እንደሚገዛና ከሶስት እስከ አራት ዓመት ብቻ አገልግሎት ሰጥቶ የሚቆም መሆኑን የተናገረችው አስረበብ ከእጅ ወደ አፍ የሆነው ኑሮዋ በዚህ ምክንያት ይደናቀፋል የሚል ስጋት ይዟታል:: ይህች ምስኪን እናት ይህን ችግሯን የሚቀርፍላት አካል ቢኖር ስራዋን ያለ ስጋት እየሰራች ቤተሰቦቿን የምታስተዳድር መሆኑን ትገልጻለች:: ለዚህም የበጎ አድራጎትና የቀና ሰዎችን ትብብር ትፈልጋለች::
እስከ አሁንም ሰዎች የሚሰጧት ገንቢ አስተያየትና ሞራል ስራዋን ጠንክራ እንድትሰራ እንዳደረጋት የምትናገረው አስረበብ አሁንም ሰርታ ለመኖር የምታደርገውን ጥረት እንዲያግዟት ትመኛለች:: የልጆቿ የትምህረት ደረጃ ከፍ ሲል በዚያው ልክ ፍላጎታቸውም እንደሚጨምር የምትናገረው ብርቱዋ እናት ከምንግዜም በላይ ልጆቿን አንድ ደረጃ ላይ ለማድረስ ጠንክራ መስራት ያለባት ጊዜ አሁን መሆኑን ትናገራለች:: ለዚህም በጎ አድራጎት ድርጅቶችና ቅን ሰዎች ስራዋን እንዲያግዟት ትጠይቃለች
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 9/2013