ሞገስ ጸጋዬ
ኢትዮጵያና ሱዳን የረጅም ጊዜ ወዳጅ አገራት ናቸው።ሱዳን ለውስጣዊ ችግር በተዳረገችባቸው ወቅቶች ኢትዮጵያ ከጎኗ በመሆን የበኩሏን አስተዋፅኦ አበርክታለች።በዳርፉር የሰላም አስከባሪ ሃይል ከማሰማራት ጀምሮ በቅርቡ የሱዳን የሽግግር መንግስት ሲመሰረትም ጭምር ኢትዮጵያ ሱዳንን ከመፍረስ ታድጋለች።ሱዳንም ቢሆን በብዙ ጉዳዮች ከኢትዮጵያ ጎን የተሰለፈችባቸውን ወቅቶች ማየት ይቻላል።ከታላቁ ህዳሴ ግድብ ጋር በተያያዘ ከምስረታው ጀምሮ የኢትዮጵያን አቋም በመደገፍ ለግድቡ ግንባታ ትልቅ አስተዋፅኦ ስታደርግ ቆይታለች።ይሁን እንጂ በቅርቡ ይህንን አቋሟን በመለወጥ ከኢትዮጵያ በተቃራኒ በመቆም በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ኢትዮጵያን ወደመክሰስ ተሸጋግራለች።በቅርቡ ኢትዮጵያ የህግ ማስከበር ዘመቻ ውስጥ መግባቷን ተከትሎ የኢትዮጵያን መሬት በመውረር የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት የሚያበላሽ ድርጊት ፈጽማለች።ለመሆኑ የነዚህ ለውጦች ምክንያት ምንድነው? ከዚህ ጀርባስ ያለው የፖለቲካ አንድምታ እንዴት ይታያል? በሚሉና ሌሎች ጉዳዮች ዙሪያ በሱዳን የኢትዮጵያ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ከሆኑት አምባሳደር ይበልጣል አእምሮ ጋር ቃለምልልስ አድርገን ይዘን ቀርበናል፤ መልካም ቆይታ፡፡
አዲስ ዘመን፡– በህገወጥ መንገድ በሱዳን ሰራዊት የተያዘውን የኢትዮጵያ ግዛት ተከትሎ የደረሰውን ጉዳት እና አሁን ያለበትን ሁኔታ አጠር አድርገው ቢያብራሩልን?
አምባሳደር ይበልጣል፡– የኢትዮጵያ ወታደር በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል ህግ ለማስከበር በተሰማራበት ጊዜ የሱዳን ሰራዊት አጋጣሚውን ተጠቅሞ ድንበር ጥሶ በመግባት በርካታ ዜጎቻችንን አፈናቅሏል። በንብረት ላይም ውድመት ደርሷል።በእርሻ ስራ ላይ የተሰማሩ ዜጎቻችን ከስራቸው ተፈናቅለዋል፤ ስራ አጥ ሁነዋል። ንብረቶቻቸው በተለይ ትራክተሮችና ማሽነሪዎች ተቃጥለዋል። በተጨማሪም ተቀጥረው የሚሰሩ በሺዎች የሚቆጠሩ በርካታ የቀን ሰራተኞች ተፈናቅለዋል። በእርሻ ስራ ላይ የተሰማሩ ዜጎች ይዘውት ከነበረው ይዞታቸው ተፈናቅለው መደበኛ ስራቸው ተስተጓጉሎ ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡
አዲስ ዘመን፡– በኢትዮጵያና በሱዳን መካከል የተለያዩ የድንበር ውል ስምምነቶች ነበሩ። እነዚያ ስምምነቶች ምንድነው የሚሉት? አሁን ለተፈጠረው ግጭት በተለይ በሱዳን በኩል ለተደረገው ወረራ ምንድነው ያለው አስተዋፅኦ?
አምባሳደር ይበልጣል፡– የኢትዮጵያና የሱዳን ድንበር እ.ኤ.አ በ1902 በኢትዮጵያና በእንግሊዝ መንግስት መካከል በተደረገው የድንበር ማካለል ውል ነው። የ1902 ስምምነት በአጠቃላይ በወረቀት ላይ የሰፈረ ውል ነው።ይህ ገዥ ስምምነት መነሻ ነው።ኢትዮጵያም ሆነች ሱዳን ይህን ስምምነት መነሻ አድርገው ነው መስማማት የሚችሉት። አንዳንዴ እንደውም ኢትዮጵያ ይህን ስምምነት አትቀበለውም ውድቅ አድርጋዋለች ተብሎ የሚነሳበት ሁኔታ አለ።ነገር ግን ኢትዮጵያ ይህን ስምምነት ሙሉ ለሙሉ ተቀብላዋለች። ይህን ተከትሎ እ.ኤ.አ በ1903 የድንበር መከለል ስራ ተሰርቷል። ስለዚህ ይህን ውል ወደ መሬት ለማውረድ በውሉ ላይ ሁለቱ ሀገሮች የጋራ የድንበር ኮሚሽን ያቆቁማሉ የሚል አስገዳጅ ስምምነት አለ። ግን የድንበር ማካለል የሚካሄደው ሁለቱ ወገኞች የጋራ ኮሚሽን አቋቁመው መሆን ሲገባው እ.ኤ.አ በ1903 የእንግሊዝ መንግስት ድንበር የሚያጠና የራሱን ተወካይ ብቻ በመላክ በ1903 ምልክት ያደረገበት ሂደት ነበር። ይህ ጉሊያ ላይን ይባላል።አሁን በተለይ በሱዳኞች በኩል ትልቅ ውዥንብር የሚፈጥረው በኢትዮጵያና በሱዳን መካከል እንደ ድንበር ምልክት ሆኖ የምናየው የጉሊያ መስመር በመባል የሚጠራውን ነው። ይህንን የጉሊያ መስመር የኢትዮጵያ መንግስት ተወካይ በሌለበትና ኢትዮጵያ ይሁንታዋን ባልሰጠችበት ሁኔታ በተናጠል እ.ኤ.አ በ1903 የተደረገ የድንበር መስመር ነው።አሁን ካርታ ላይ የምናየው መስመር ከኢትዮጵያ መንግስት ፍላጎትና ስምምንት ውጭ በተናጠል በእንግሊዝ መንግስት የተሰመረ መስመር ነው። ከዚህ መስመር አንድ ኢትዮጵያዊ አርሶ አደር አልፎ ከተገኘ የሱዳን መንግስት ይሄው ድንበሬ ተጥሷል፤ ኢትዮጵያ ድንበሬን ጥሳ ገብታለች የሚል የመከራከሪያ ሀሳብ ያነሳሉ።ግን ይህ እውነታውን ካለመገንዘብ የመጣ ነው። ይህን የድንበር መስመር ኢትዮጵያ እውቅና አልሰጠ ችውም ። ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ እስከ 1972 ድረስ የጉሊን ላይን አልቀበለውም ብላ ውድቅ አድርጋው ነው የኖረችው።
አዲስ ዘመን፡– አሁን ያለው የሁለቱ ሀገሮች ድንበር በእንግሊዞች ብቻ የተካለለ ነው የሚል ነገር አንስተዋል፤ ስምምነት ተብሎ ሲነሳ በኢትዮጵያና በሱዳን መካከል ነው።ስለዚህ በኢትዮጵያና በጊዜው በነበሩ ቅኝ ገዥዎች መካከል የተደረገ ስምምነት ማለት ነው?
አምባሳደር ይበልጣል፡– ቅኝ ግዛት ስር ስለነበረች አጠቃላይ በቅኝ ግዛት ስራ የነበሩ ሀገሮች ነጻነታቸውን ሲያገኙ የነበረውን ድንበር ይዘው ነው የሚቀጥሉት። ሱዳንም በጊዜው በእንግሊዝ ግዛት ስር ነበረች። አጠቃላይ የአፍሪካ ሀገራትን ድንበር የወሰኑት የቅኝ ገዥ ሀገሮች ናቸው። ኢትዮጵያ ብቻ ብቸኛዋ ነጻ ሀገር ስለነበረች በጊዜው የኢትዮጵያ መንግስት ከእንግሊዞች ጋር ተደራድሮ የተካለለ ቢሆንም እ.ኤ.አ በ1903 የነበረው የድንበር ማካለል የተካሄደው በተናጠል በእንግሊዝ ተወካይ አማካኝነት ነው። ይህ ደግሞ በአሁኑ ጊዜ የሱዳን መንግስትን ይወክላል። እ.ኤ.አ. የ1972 የተደረገው ስምምነት በጣም መሰረታዊ ስምምነት ነው። እ.ኤ.አ በ1903 የተደረገውን የጉላይ ላይንን የኢትዮጵያ መንግስት አይቀበለውም። ምክንያቱ ደግሞ አድሎአዊ በሆነ መንገድ ወደ ሱዳን ባደላ መልኩ ነው ድንበሩን የከለለው። ለሱዳን ስላዳላ የኢትዮጵያ መንግስት አልተቀበለውም። ከዚህ በተጨማሪም በውሉ መሰረት የጋራ ኮሚሽን መቋቋም ሲገባው በተናጠል ነው የተደረገው።በተናጠል መደ ረጉ ብቻ ሳይሆን ድንበሩን እንድትከልል ውክልና አልተሰጣትም። የኢትዮጵያ መንግስት ሳይቀበለው እስከ 1972 ቆይቷል።
ነገር ግን በ1972 አዲስ ስምምነት የተደረገ ሲሆን በድንበር አካባቢ የሚገኝ ከዳግሎሽ ተራራ ካለው የወሰኑ ከፍል ዋና ዋና ተራራዎችን ወደ ሱዳን ግዛት በማስገባት አላግባባ ካለው አጠቃላይ አለም አቀፍ አስራር ውጭ የከለላቸውን ተስተካክሎ በአራት ትልልቅ ተራሮች አናት ላይ እንዲያልፍ ተደርጎ ተስተካከለ። ምክንያቱም በ1903 የእንግሊዝ መንግስት ስህተት ስለሰራ ማስተካከያ ተደረገበት። ወደ ሰሜኑ ክፍል ያለው ግን ዜጎች የሰፈሩበት ቦታ የለማና የተረጋጋ ኑሮ ላይ ስላሉ ሂዶ ማጥናት ይጠይቃል። ቢሮ ውስጥ ቁጭ ብሎ በውይይት የሚፈታ አልነበረም። ስለዚህ ዜጎች ያለሙት የሚኖሩበት የተስተካከሉ መንደሮች ስላሉ የጋራ ኮሚቴ ተቋቁሞ ተጠንቶ ተቀባይነት ያለው መፍትሔ ሲገኝ ድንበሩን የማካለል ስራ ይካሄዳል የሚል ስምምነት ተደርሶ ነበር።
ስለዚህ የ1972 የማስታወሻ ልውውጥ እንደሚለው ከዳግሎሽ ተራራ በስተሰሜን አሁን አወዛጋቢ የሆነው ቦታ ላይ ያሉ የዜጎች ሁኔታ በጋራ ኮሚቴ ተጠንቶ መሬት ካለው ሁኔታ ጋር ተገናዝቦ መፍትሔ ሲገኝ ድንበሩ እንደገና ይካለላል ነው የሚለው። የ1903 ውልን እንደ መነሻ እንዲያገለግል ሆኖ መሬት ያለውን እውነታ ባገናዘበ ሁኔታ የጋራ ኮሚቴ ተቋቁሞ መስከ ሂዶ አጥንቶ እንደገና ድንበሩ ይካለላል ነው የሚለው።
አዲስ ዘመን፡– እ.ኤ.አ ከ1972 ጀምሮ እስካሁን ድረስ እነዚህ ስምምነቶች መሬት ላይ መውረድ ያልቻሉባቸውን ዋና ዋና ምክንያቶች ይጥቀሱልን?
አምባሳደር ይበልጣል፡– በ1972 በተደረሰው ስምምነት ሙሉ ለሙሉ ተግባራዊ እንዲሆን ድንበሩ እንደገና እንዲካለል በማስታወሻ ልውውጥ ላይ የተደረሱ ስምምነቶች ተግባራዊ መሆን አለባቸው። አንደኛ የሰሜን ዳግሎሽ ተራራ ወይም አሁን አወዛጋቢ ሆነው ቦታ በባለሙያ የመስክ ጥናት ተደርጎበት መፍትሔ ከተገኘለት በኋላ እና ሁለቱ ወገኞች ከተስማሙ በኋላ የማከለል ስራ ይካሄዳል ነው ሚለው። ነገር ግን እነዚህ ስራዎች አልተሰሩም። የአጼ ኃይለስላሴ መንግስት እ.ኤ.አ በ1974 ከስልጣን ተወገደ። በውስጥ ችግር ምክንያት ከ1972 እስከ 1974 ድረስ ባለው ጊዜ ውስጥ ይህን ስራ ማከናወን አልተቻለም።ከ1974 ጀምሮ ደርግ በነበረበት ጊዜ ሙከራዎች ነበሩ፤ ነገር ግን በሁለቱ ሀገሮች መካከል ከነበረው ግንኙነት አንጻር በመግባባት መንፈስ ተቀራርቦ ይህን እልባት ለመስጠት ጥሩ የሆነ የፖለቲከ ሁኔታ አልነበረም ። ስለዚህ ደርግም እልባት ሳይሰጠው ቀርቷል ማለት ነው። ኢሕአዴግ ስልጣን ከያዘ በኋላ የተሻለ እንቅስቃሴ ተደርገዋል። በተለይ እ.ኤ.አ ከ2001 ጀምሮ የድንበሩን ጉዳይ እልባት ለመስጠት የድንበር ኮሚሽን የማቋቋም፣ የልዩ ኮሚቴ የማቋቋምና በሁለቱም ወገን ተቀባይነት ያለው መፍትሔ የሚያፈላልግ ልዩ ኮሚቴ ተቋቁሞ ስምምነት ከተደረሰ በኋላ የድንበር የጋራ ኮሚቴ በማቋቋም ዋናውን ችካል የማስቀመጡን ስራ የሚሰራው አካላት ተቋቁመው ስራ ጀምረዋል።
እ.ኤ.አ ከ2002 ወዲህ በርካታ ስራዎች ተሰርተዋል ማለት ነው።ለምሳሌ የልዩ ኮሚቴው ድንበር አካባቢ ሄዶ ጥናት ማድረግ ይጠበቅበት ነበር። ምክንያቱም መሬት ላይ ያለውን እውነታ አይቶ ለዛ ማስተካከያ የሚሆን የመፍትሔ ሀሳብ የሚያቀርበው ልዩ ኮሚቴው ተቋቁሞ ስራውን ጀምሮ ስምንት ዙር ውይይቶችን አድርጓል፡፡
ከነዚህ ስምንት ዙር ስምምነቶች በተጨማሪ መሬት ላይ ያለውን ነባራዊ ሁኔታ አጥንቶ የሚመጣ የመስክ ጥናት ቡድን እ.ኤ አ ከ2004 እስከ 2005 ድረስ ጥናት አደርጎ ሰነድ አዘጋጀቷል። ይህ ጥናት መሬት ላይ ያለውን እውነታ የእያንዳንዱን አርሶ አደር ይዞታ በካርታ አስቀምጦ የጂፒኤስ ንባብ ወስዶ እዛ አካባቢ ያሉ ነዋሪዎችን መዝግቦ ተመልሷል። በዚህ መረጃ መሰረት መፍትሔ ማቅረብ ይጠበቅበታል ማለት ነው።ስለዚህ አሁን የመስክ ጥናት ተካሂዷል፤ መሬት ላይ ያለው እውነታ ተለይቷል።
እ.ኤ.አ የ1972 የማስታወሻ ልውውጥ የሚለው በሁለቱ መንግስታት ተቀባይነት ያለው መፍትሄ እስኪፈለግ ድረስ ማንኛውም ዜጋ አይፈናቀልም።የእ.ኤ.አ የ1972 ስምምነትን እንጠብቃለን የሚል ስምምነት አለ። የኢትዮጵያ መንግስት በአሁን ጊዜ ሱዳን ስምምነቱን ጥሳለች ሲል ያለ ምክንያት አይደለም። በግልጽ ቀደም ሲል የነበረውን የሁለቱን ሀገሮች ስምምነት ጥሳለች። በዋናነት ጉዳት የደረሰባቸው ዜጎች ከይዞታቸው ካለሙት ከኖሩበት በሀይል ተፈናቅለዋል። ስለዚህ የ1972 የማስታወሻ ልውውጥ ተሽሯል ማለት ነው። በሁለቱ ሀገሮች መካከል ስምምነት ተደርሶ ምልክት እስኪቀመጥ ድረስ ሁለቱም በይዞታችን እንቀጥላለን የሚል ቢሆንም የኢትዮጵያ ዜጎች ከይዞታቸው በሀይል ተፈናቅለዋል። በዚህ ምክንያት ሱዳን የ1972 ስምምነትን ጥሳለች ማለት ነው፡፡
የድንበር ጉዳይ በሰላማዊ መንገድ በድርድርና በውይይት ነው የሚፈታው የሚል ስምምነት ቢኖርም የሱዳን መንግስት ግን አጋጣሚ ተጠቅሞ በሀይል የድንበር ችግርን ለመፍታት ሙከራ እያደረገ ነው።፡ በሀይል ችግሮችን ለመፍታት የተደረገ ሙከራ የአለም አቀፍ የግጭት አፈታት ስርዓትን የሚቃረን ነው።በሁለቱ ሀገሮችና ህዝቦች መካከል ያለውን የህዝብ ለህዝብ ትስስርና ዘላቂ ግንኙነትን ባላገናዘበ ሁኔታ ኢትዮጵያ አሁን ወደ ሌላ አቅጣጫ ዙራለች፤ ለመውረር ምቹ ሁኔታ አለ ብሎ በማሰብ የሱዳን መንግስት ወረራውን ፈጽሟል። ይህ ደግሞ የሁለቱን ሀገሮች መልካም ግንኙነት በአሉታዊ ሁኔታ የሚጎዳ ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡– የአለም አቀፍ ህጎች ተጥሰዋል። የተፈናቀሉ ዜጎችም አሉ፤ ነገር ግን ጉዳዩን አለም አቀፋዊ መልክ ማስያዝ ያልተፈለገው ለምንድን ነው? ኢትዮጵያ የተባበሩት መንግስታት የጸጥታው ምክር ቤት እንዲያውቀው ያላደረገችበት ምክንያት አላት?
አምባሳደር ይበልጣል፡– የኢትዮጵያ መንግስት በተለያየ ጊዜ መግለጫ ሰጥቶበታል። ሱዳን ያለውን አጠቃላይ አለም አቀፍ አሰራርንና በሁለቱ ሀገሮች የጋራ ስምምነት መሰረት በስራ ላይ የተሰማሩትን የጋራ ኮሚቴዎችን ወደ ጎን በመተው ህገወጥ ድርጊት እንደፈጸመች አለም አቀፍ ማህበረሰብ ይረዳዋል። የድንበር ጉዳይ የሚፈታው በድርድርና በውይይት ነው። ለዚህም ኢትዮጵያና ሱዳን በቂ የሁለትዮሽ ስምምነቶች አሏቸው። ባሏቸው ስምምነቶች ላይ ተመስርተው ደግሞ የጀመሯቸው ውይይቶች አሉ። ጅምር ላይ ያሉ በጥሩ ሁኔታ የነበሩ እንቅስቃሴዎች እልባት ሳያገኙ ወደ ሌላ አካል መሄድ አስፈላጊ አይደለም፡፡
መጀመሪያ ባሉ ስምምነቶች መሰረት ሁለቱ ሀገሮች በአቋቋሟቸው ስምምነቶች መሰረት ችግሩን ለመፍታት መወያየት ይጠበቅባቸዋል። ነገር ግን አዲስ የመጣው የሱዳን መንግስት ካሁን በፊት አልበሽር ስልጣን ላይ በነበሩበት ጊዜ ጀምረውት የነበረውን ሂደት ተቀብሎ ዘላቂ መፍትሄ ለማምጣት ዝግጁነት አልታየበትም።ስለዚህ የኢትዮጵያና የሱዳን ድንበር ጉዳይ ዘላቂና ሰላማዊ መፍትሔ የሚያገኘው ሁለቱ ሀገሮች በፈረሟቸው የሁለትዮሽ ስምምነት መሰረት ቁጭ ብለው ሲነጋገሩ ብቻ ነው። ከውጭ የሚመጣ ማንኛውም አይነት መፍትሄ በሁለቱ ሀገር ህዝቦች መካከል ዘላቂ ሰላምንና ወዳጅነትን ሊያረጋግጥ አይችልም።
አዲስ ዘመን፡– እርሶም እንደገለጹት በመግለጫ ዎቻቸውም እንደታዘበነው በሱዳን በኩል ለድርድር ዝግጁ የመሆን ነገር የለም። በዚህ ጉዳይ ኢትዮጵያ በቀጣይ ልትወስደው የምትችለው አማራጭ ምን ሊሆን ይችላል?
አምባሳደር ይበልጣል፡– የኢትዮጵያ መንግስት በዋናነት ቅድሚያና ትኩረት የሚሰጠው በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ነው። በግጭት የሚፈታ ነገር ዘላቂ መፍትሔ አይኖረውም ። ኢትዮጵያና ሱዳን ነገ ጦርነት ውስጥ ሊገቡና ሊዋጉ ይችላሉ፤ ነገር ግን በዚህ ውጊያ ዘላቂ መፍትሔ ማረጋገጥ አይቻልም። ከጦርነት በኋላም ሁለቱ ሀገሮች ቁጭ ብለው የወሰን ምልክቶችን ማስቀመጥ መቻል አለባቸው። እነዛን የወሰን ምልክቶች ደግሞ ሁለቱ መንግስታትና ህዝቦቻቸው መቀበል አለባቸው። ይህ የጋራ ድንበራችን ነው። ወሰናችን ነው የሚል ስምምነት በሁለቱ መንግስታት እና በሁለቱ ህዝቦች ዘንድ መኖር አለበት። በአንድ አካል በሀይል ሂደት የምትጭነው ዘላቂ መፍትሄ ሊያመጣ አይችለም፡፡
ዛሬ አቅም አለኝ ብለህ በጉልበት ሂደህ ትይዛለህ፤ ነገ አንዱ ተመልሶ መጥቶ በጉልበት ይይዛል። ይህ ደግም የማያልቅ አዙሪት ውስጥ እንድንገባ ያደርገናል። ይህ ደግሞ ከሱዳን ጋር ካለን ሁለንተናዊ ግንኙነት አንጻር የኢትዮጵያ መንግስት በምንም መንገድ ቢሆን የአይጥ እርምጃ አይወስድም። በውይይት መፈታት አለበት የሚል የጸና አቋም ነው ያለው።ነገር ግን መፍትሔ የማያመጣ ከሆነ ደግሞ ሌሎች አለም አቀፍ ህግ የሚፈቅዱልን አማራጮች ሁሉ ይታያሉ ማለት ነው።
ለሱዳን መንግስትም፣ ለሌሎች አጋር አካላት እና ለሌሎችም በተደጋጋሚ ጥሪ እያደረግንና እያሳሰብን ያለነው የሱዳን መንግስት በሀይል ከያዘው አካባቢ ወጥቶ በአሉን ሁለትዮሽ ስምምነት አማካኝነት በሰላማዊ መንገድ እንድንፈታው በተደጋጋሚ የሱዳንን መንግስት እየወተወትን ነው። ይህን ችግር በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ ለሚያነጋግሩን አካላት ይህንኑ አቋማችንን እያስረዳን ነው። የኢትዮጵያ መንግስት ጨዋ ከሆነው ከሱዳን ህዝብ ጋር ዘለቂ ግንኙነት በማለም ሮጠው ወደ ጦርነትና ግጭት መግባት አይፈልግም። በርግጥ ይህን ስናደርግ ኢትዮጵያዊያን ዋጋ እየከፈሉ ነው። ከይዞታቸውና ከስራቸው ተፈናቅለዋል። ነገር ግን ትልቁን ስዕል፣ ትልቁን የሁለቱን ሀገሮች ህዝቦች ዘላቂ ግንኙነትንና በአካባቢው ያለውን አንድምታ በማየትና በማገናዘብ ከሱዳን መንግስት ጋር ፈጥኖ ወደ ጦርነት የመግባት ፍላጎት የለንም። በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ ጥረት ይደረጋል።ይህ የማይሰራ ከሆነ መብታችንን ሌሎች አማራጮች ያረጋግጡልናል፡፡
አዲስ ዘመን፡– በአለም አቀፍ ደረጃ ያሉ ተሞክሮዎች የሚያሳዩት ባድሜን ጨምሮ የይገባኛል ጥያቄ የሚነሳባቸው ጉዳዮች ብዙ ጊዜ ከውጭ የሚመጡ ውሳኔዎች ተፈፃሚነታቸው ያን ያህል ነው።ስለዚህ የሱዳንና የኢትዮጵያ የድንበር ይገባኛል ጥያቄም ከአዲሱ መንግስት ጋር አብሮ የመጣና የሶስተኛ ወገን ፍላጎትን የማስፈጸም አንድምታ አለው ይባላል? የተፈናቀሉ ዜጎችን በተመለከተ መንግስት ምን አስቧል? የተለያዩ ሀገራት ተወካዮችን የማሳመን ስራ በስፋት ይሰራሉ፣ ይህ ምን ያህል እውነታውን ለአለም አቀፍ ማህበረሰብ እያስጨበጠ ነው ብለው ያስባሉ? ምን ያህልስ እየተረዱት ነው?
አምባሳደር ይበልጣል፡– የሱዳን መንግስት በስፋት የሚዲያ ዘመቻ እያደረገ ነው። አሁን የሱዳን መንግስት እያለ ያለው ከቀሪ ግዛቶቼ ሁሉ ኢትዮጵያ ለቃ መውጣት አለባት በማለት ኢትዮጵያን እንደ ወራሪ የማየት አካሄድ ሁሉ አለ። የተያዘብንን መሬት 90 በመቶ አስመልሰናል እያሉ ነው ያሉት። የሱዳን መንግስት ይህንን ወረራ መፈጸሙንና ስህተት እንደሰራ አለም አቀፍ ማህበረሰብ ይረዳል። በስራ አጋጣሚ የማገኛቸው ዲፕሎማቶችም ይረዳሉ። የነሱ ፍላጎት ኢትዮጵያና ሱዳን ይህን ችግር ለመፍታት ወደ ግጭት ሳይገቡ በውይይትና በድርድር እንዲፈቱት ነው። ወረራ አልፈጸምኩም፤ የራሴ ግዛት ውስጥ ነው ያለሁት ቢልም የሱዳን መንግስት በራሱ መንገድ ወረራ ማካሄዱን አረጋግጧል። ኢትዮጵያዊያንን አሰናክሎ ይገባኛል ያለውን ቦታ በሀይል እንደያዘ መግለጫ ሰጥቷል።በተለያዩ ምክንያቶች የምናገኛቸው ዲፕሎማቶችና የማህበረሰብ አካላት ይረዳል።ነገር ግን አሁንም ቢሆን ሱዳን የኔ ነው እያለች የምታቀርባቸውን ሀሳቦች ማስረዳት ይጠይቃል። የሱዳን ሀላፊዎች ኢትዮጵያና የሱዳንን አሁን የምናየውን ድንበር ስህተት በመሆኑ እ.ኤ.አ ከ1903 ጀምሮ እውቅና አይሰጠውም።ምክንያቱም ስህተት ስላለበት በሁለቱ ሀገሮች ድርድር መሻሻል አለበት።ሁለቱ ሀገሮች የሚቀበሉት አዲስ የድንበር መስመር ይኖራል የሚል ስምምነት ላይ ተደርሷል በ1972 ስምምነት።ከሱዳን ወገን በእንግሊዝ በተናጠል የወጣውን ካርታ እያሳዩ ኢትዮጵያዊያን የሱዳን ግዛት ውስጥ እንደሚገኙ የሚያሰራጩት መረጃ በተወሰነ ደረጃም ቢሆን የመምታታት ሁኔታን እየፈጠረ ነው።በኛ በኩል እውነታውን በደንብ የማስረዳት ሁኔታ ይጠይቃል ይህንንም እየሰራን ነው፡፡
አዲስ ዘመን ፡–የተፈናቀሉ ዜጎችን በተመለከተ ቢያብራሩልን?
አምባሳደር ይበልጣል፡– ዜጎች ጉዳት ደርሶባቸዋል፤ ተፈናቅለዋል ። ለሌሎች ዜጎች የስራ እድል ፈጥረው በርካታ ዜጎችን ሲረዱ የነበሩ ሰዎች ዛሬ ተረጅ ሁነዋል።በርግጥ ይህን በተመለከተ መንግስት ምን እየሰራ ነው ለሚለው ለጊዜው መረጃ የለኝም።
አዲስ ዘመን ፡– በሱዳንና በግብጽ መካከል በሂላብ ትሪያንግል የድንበር ውዝግብ አለ።ከዚህ ይልቅ ፊቷን ለምን ወደ ኢትዮጵያ ማዞር ያስፈለጋት ይመስሎዎታል? ሶስተኛ አካል ጣልቃ ገብነት አለ የሚባለውን እንዴት ያዩታል?
አምባሳደር ይበልጣል፡– እንደተባለው ሱዳን ከግብጽ ጋራ የድንበር ውዝግብ አላት። ለምን ያን ትተው ፊታቸውን ወደ ኢትዮጵያ አዞሩ ለሚለው ራሳቸው ናቸው የሚያውቁት። ውሳኔው የራሳቸው ነው። ቅድሚያ የሚሰጡት ለየትኛው ድንበር ነው የሚለው የአመራሮች ውሳኔ ነው የሚሆነው። በተለይ ደግሞ ካላቸው ቅርርብ አንፃር ነው የሚሆነው። ኢትዮጵያን የሚያሳስባት ለአንዱ ትኩረት ሰጥታ ለሌላው ትኩረት ለምን ነሳች የሚለው ሳይሆን ከኛ ጋር ያለውን ጉዳይ መፈታት ያለበት የሁለቱን ሀገሮች ዘለቂ ግንኙነት ታሳቢ ባደረገ መልኩ መሆን አለበት የሚለው ነው። የሀይል እርምጃ መፍትሔ እንደማይሆን በመረዳት በሰላማዊ መንገድና በውይይት መፈታት አለበት።ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሱዳን መንግስት የሚያሳየው የባህሪ ለውጥ ከኢትዮጵያ ጋር ያለውን ግንኙነት ትንሽ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ አቅጣጫ እየሄደ እንዳለ እንረዳለን። ይህ የተዛባ አካሄድ አስተካክሎ በዘላቂ ግንኙነት ላይ የሁለቱን ሀገሮች ግንኙነት በማገናዘብ ወደ ስላማዊ መፍትሄ ይመጣል ብለን ተስፋ እናደርጋለን፡፡
አዲስ ዘመን ፡– ከህግ ማስከበሩ ጋር ተያይዞ እስከ 50 ሺህ የሚደርሱ ኢትዮጵያዊያን ድንበር አቋርጠው ሱዳን እንደገቡ ይታወቃል።የሀገሪቷ ከፍተኛ ባለስልጣን ስደተኞችን ከጎበኙ በኋላ ሰላም ስላለ መመለስ እንደሚችሉ ቃላቸውን ሰጥተው ነበረ አሁን ምን አይነት ተጨባጭ ሁኔታዎች አሉ? በማይካድራ ዘር ተኮር ጭፍጨፋ ላይ የተሳተፉ ህገወጦች እንደነበሩ ይነገራል።ሱዳንና ኢትዮጵያ ወንጀለኛን የማስመለስ ስምምነት አላቸው።አለም አቀፍም ስምምነትም አለ፤ በዚህ መሰረት ወንጀለኞችን ለመለየት የሚያስችል ምን አይነት ሂደቶች አሉ?
አምባሳደር ይበልጣል፡– ስለ ስደተኞች ስናወራ ግምት ውስጥ ማስገባት ያለብን ጉዳይ በኦፕሬሽኑ ወቅት በንጹኃን ዜጎች ላይ ወንጀል ፈጽመው ወደ ሱዳን የተሻገሩ በርካታ የመስተዳደር አካላት፣ የሚሊሻ አባላትና ሳምሪ የሚባል የወጣቶች የወንጀለኛ ስብስብ ቡድን አብሮ ገብቷል።በርካቶች በወንጀል ስራ ላይ የተሰማሩ የሰው ህይወት ያጠፉ ወንጀል የሰሩ የአመራር አባላት አብረው ተቀላቅለው ከስደተኞች ጋር ወደ ሱዳን የገቡበት ሁኔታ አለ።የስደተኞች መጠለያ እና ያለው ስደተኛ ደግሞ እንደ ዋና የፕሮፓጋንዳ መሳሪያ ተደርጎ ተቆጥሯል።በተለያዩ ሀገሮች ተሞከሮ እንደታየው ከስደተኞች ጋር ተያይዞ ሰብአዊ ቀውስ ተፈጥሯል በሚል የአለም አቀፍ ጫና ለማምጣት ሲባል ሆን ተብሎ ሲዋጋ የቆሰለን ወንጀለኛን ልክ በዘሩ ምክንያት ጥቃት እንደተፈጸመበት አድርጎ የማቅረብ ሁኔታዎች አሉ።እኛ ስደተኞችን ሂዶ የማግኘት አማራጮች የሉንም፤ ነገር ግን የተለያዩ አለም አቀፍ ሚዲያዎች በቀጥታ እየሄዱ የሰለጠኑ የአካባቢ ሰዎችን እያናገሩ ወንጀል እንደተፈፀመባቸው አድርገው እየሰሩበት ነው። ስደተኛው ለሌላ አላማ እየዋለ ያለበት ሁኔታ ነው ያለው። ወደ ሀገራቸው መመለስ የሚፈለጉትን ደግሞ በውሸት ፕሮፓጋንዳ ተመልሳችሁ ብትሄዱ እንደዚህ አይነት ጉዳት ይደርስባችኋል እየተባሉ ወደ ሀገራቸው የሚመለሱበትን ሁኔታ የማደናቀፍ ስራዎች ይሰራሉ። ሁለተኛ ንጹሃን ወደ ሀገራቸው ለመመለስ ፍላጎት ቢኖራቸውም ትክክለኛ መረጃ እንዲያገኙ አልተደረገም፡፡
የኢትዮጵያ ሰላም ሚኒስተር ሳይቀር ወደ ሱዳን ሂደው ስደተኞችን አግኝተው በማነጋገር ስለ ሀገራቸው ነባራዊ ሁኔታ ለማስረዳት ሙከራ አድርገናል።እኔ በተደጋጋሚ ጥያቄ አቅርቢያለሁ። በትክክል ሄደን አግኝተናቸው ስለ ሀገራቸው ስለመጡበት አካባቢ አጠቃላይ ሁኔታ መረጃ እንዲያገኙ ለማድረግ ጥረት አድርገናል፤ ግን አልሆነም።የመረጃ ክፍተት አለባቸው።ይህን የመረጃ ክፍተት ለማሟላት በኛ በኩል ያቀረብነው ጥያቄ ሊሳካ አልቻለም። የሀገሩ መንግስት ካልተስማማበት ማስፈጸም አንችልም። ይህ ዜጋ የመረጃ ክፍተት አለበት፤ትክክለኛ መረጃ ማግኘት አልቻሉም።ይህን ለማድረግ ደግሞ ትብብር አላገኘንም ።በርካታ ወንጀለኞች በመጠለያ ውስጥ ቢኖሩም በዛው ልክ ወንጀል ያልሰራ ንጹሃን ደግሞ በፕሮፓጋንዳ የተበረዘ ያለበት ሁኔታ ነው ያለው።ወደ ሀገራቸው ለመመለስ ዝግጁ የሆኑ አሉ፤ እነዚህ ዝግጁ የሆኑ አካላትን በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ ከኛ ጋራ ተነጋግረው ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ ተከታታይ ጥረት አድርገናል። የሱዳንን ባለስልጣናት አገኝተናል ነገር ግን ፍቃደኞችን በምንፈልገው ፍጥነት ወደ ሀገር ለመመለስ ከሱዳንና የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ጉዳይ ኮሚሽን ድጋፍ አላገኘንም፤ ባለፈው ቅዳሜ ከሱዳን የውጭ ጉዳይ ቃለ አቀባይ ጋር በተገናኘሁበት እለት በዚህ ዙሪያ ባደረግነው ውይይት ይፈታል የሚል ቃል ገብቶልኛል። ወደ ሀገራቸው መመለስ የሚፈልጉ ነገር ግን ድጋፍ የሚጠይቁ አሉ። የነሱን ጉዳይ ክትትል እያደረግንበት ነው።በርካቶች መመለስ ፈልገው አዎንታዊ ድጋፍ ያላገኙ ስደተኞች በራሳቸው አማራጭ በእግራቸው ኡምራኮባ የሚባል በገዳሪፍ መስመር በኩል የሚገኝ የስደተኞች መጠለያ ሲሆን በጋዳሪፍ መተማ አድርገው ወደ ሀገራቸው የሚገቡበት ሁኔታ መኖሩን አንስተዋል።በቀጣይ ስራ ንጹሃን ዜጎቻችን ስለ አካባቢያቸው የተሟላ መረጃ አግኝተው ወደ ሀገራቸው የሚመለሱበትን ሁኔታ ለማመቻቸት ቀጣይ ስራ ይጠይቃል። ከወንጀለኞች ጋር ተያይዞ ወንጀለኞች ወደ ሱዳን እንደገቡ ይታወቃል።ለሱዳን መንግስት ጥያቄውን እያቀረብን ነው፤ እስካሁን አውንታዊ ምላሽ አላገኘንም ። ነገር ግን ክትትሉን እንቀጥላለን፡፡
አዲስ ዘመን፡– ከግድቡ ጋር በተያያዘ ሰሞኑን ከኢትዮጵያ በኩል የቀረበ የዳም ኦፕሬተሮች ተወካይ ላኩ የሚል ግብዣ ነበረ፤ ይህን ግብዣ ሁለቱም ሀገሮች ውድቅ አድርገውታል።አንዳንዶች እንደሚሉት ስምምነት ላይ አለመድረስ ስለሆነ ግባቸው አለመቀበላቸው የሚጠበቅ ነው።በሌላ በኩል ደግሞ ኢትዮጵያ ወደ ስምምነት ለመድረስ ያላትን ፍላጎት በአለም አቀፍ ደረጃ በግልጽ ያሳየችበት ነው የሚሉ ሀሳቦች አሉ፤ ምን ማለት እንችላለን?
አምባሳደር ይበልጣል፡– በሱዳን ወገን ሁል ጊዜ በድርድሩ ሂደትና በተለያዩ አጋጣሚዎች የሚያነሱት የኢትዮጵያ መንግስት መረጃ አልሰጠንም፤ ሊሰጠንም ፍላጎት የለውም የሚል ወቀሳ ነው። ባለፈው አመት የመጀመሪያ የውሃ ሙሌት በተካሄደበት ጊዜ የኢትዮጵያ መንግስት መረጃ ስላልሰጠኝ ውሃ እጥረት ተፈጥሮብኛል። በቀጣይነት 20 ሚሊዮን ህዝብ አደጋ ላይ ይወድቃል።የግድቡ ደህንነትም አደጋ ላይ ይወድቃል፤ ስለዚህ ገዥና አስገዳጅ የሆነ ስምምነት ላይ መድረስ አለብን የሚል አቋም ነው የምታራምደው።ይሁንና አንደኛ የድግቡን ደህንነት በተመለከተ ሱዳኖች ማመን ያለባቸውን የኢትዮጵያ መንግስት በጠቅላይ ሚኒስትራችንና በውሃና መስኖ ሚኒስትራችን ደረጃ ሱዳናውያን ስለግድቡ የፈለጉትን መረጃ የማግኘት፤ግድቡን የመጎብኘት፣ በማንኛውም ጊዜ ባለሙያዎችን የመላክና ሰነዶችን ማየት እንደሚችሉ ተነግሯቸዋል፡፡
ከሱዳናውያን የምንደብቀው መረጃ እንደሌለ በተደጋጋሚ ስናረጋግጥላቸው የቆየነው ጉዳይ ነው።ከዚህ በተጨማሪ አሁን ሁለተኛ ዙር የውሃ ሙሌት ለማካሄድ ዝግጅት ላይ ያለን በመሆኑና ከግንባታው ሂደት ጋር ተያይዞ ውሃ መለቀቅ ስለሚኖር ከመቼ ጀምሮ እንደሚለቀቅ በደብዳቤ መረጃ ደርሷቸዋል።ይህንን በአወንታዊ መልኩ ቢያዩትም አሁንም ቢሆን ገዥ ስምምነት ያስፈልጋል በሚል አቋም ላይ ናቸው።ስለዚህ የነሱ ጥያቄ ግራ የተጋባ ነው።ባለፈው አመት መረጃ ባለመስጠታችሁ ችግር ተፈጠረብን ተባለ።አሁን ደግሞ ቀደም ብለን እሄው መረጃ ስለውሃ አለቃቀቁና በቀጣይ ስራ ላይ ዝርዝር መረጃ ለመለዋወጥ ተወካይ ሰይሙ ሲባሉ ፍቃደኞች አይደለም።በአፍሪከ ህብረት አሸማጋይነት የተጀመረው ድርድር እየቀጠለ በዛ ላይ ስምምነት ተደረሰም አልተደረሰም አሁን እየሰራነው ስላለው መረጃ ለማግኘት ተወካይ ወክሉ ነው የተባለው። ነገር ግን እነሱ እንደሚሉት ተወካይ ስለላኩ ድርድሩ ይቆማል ማለት አይደለም።ይህ ደግሞ በግድቡ ላይ ካላቸው ፍላጎት ጀርባ ሌላ ጥያቄ አላቸው የሚል ጥያቄ እንድናነሳ አድርጎናል፡፡
ሱዳን ድርድሩን እያካሄደች ተወካይ ወክላ መረጃ በመከታተል ይህ ጉዳይ ያሳስበኛል፤ ጉዳት ያደርስብኛል የሚሉ ጉዳዮችን ለመፍታት መተባበር ስትችል በኢትዮጵያ በኩል የተወሰደውን ይህን በጎ እርምጃ በአወንታዊ መልኩ መቀበል አልቻለችም።ከዚህ በፊት እንደሚታወቀው ለግድቡ ከሱዳን በኩል ትልቅ ድጋፍ ነበር።አሁን ግን የግድቡ ጠቀሜታም ይሁን ሌሎች ነገሮች ባልተለወጡበት ሁኔታ የሱዳን መንግስት አቋም ተለውጧል።ይህ የሚያሳየው ሌላ አጀንዳ ከሌለ በስተቀር ግድቡም የነበረ፣አስር አመት ስንነጋገርበትና ሲከታተሉት የነበረ ነው።ዛሬ ስልጣን ላይ ያሉ ባለሙያዎችና መሪዎች ትናንት ይህ ግድብ ለሱዳን ከፍተኛ ጥቅም አለው ሲሉ የነበረ ናቸው፡፡
አጠቃላይ ሱዳን ውስጥ ያሉ ምሁራንና ባለሙያዎች ከግድቡ ጋር በተያያዘ በመንግስት ስልጣን ላይ ያሉ ሀላፊዎች የህዳሴ ግድብ ለሱዳናውያን የሚያስገኘው ጥቅም እጅግ ሰፊ እንደሆነና በአሁኑ ሰዓት የሱዳን መንግስት የሚያራምደው አቋም የተሳሳተ እንደሆነ ያስረዳሉ።ግድቡ ለሱዳን እጅግ በጣም ፋይዳ ያለውና ሰፊ ጠቀሜታም የሚያስገኘ ነው።አንዳንድ ምሁራን የሚሉት የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ማለት ለሱዳን የአስዋን ዳም ነው። ስለዚህ ግብጾች አስዋን ዳም አላቸው።አስዋን ዳም ለግብፆች ያስገኘው ጥቅም ይታወቃል።የህዳሴን ግድብ ስንገነባ ግብጾች ከአስዋን ዳም የሚያገኙት አይነት ጥቅም ሱዳናውያን ከህዳሴው ግድብ ያገኛሉ።ምንም አይነት ወጭ ሳያወጡ።እኛ በገነባነው ግድብ ሰፊ ጥቅም ያገኛሉ። ከኢትዮጵያ ተቃራኒ አካሄድ መሄድን አሁን በስልጣን ላይ ያለው መንግስት ይከተላል።ይህን ጉዳይ በድንበር ጉዳይ ላይም አይተነዋል።አጠቃላይ በቋሚነት ለኢትዮጵያ ያለው እይታ ያለውን ልዩነት ለመፍታት የሚከተለው አካሄድ አግባብነት የሌለውና የሁለቱን ሀገሮች የወደፊት የእርስ በርስ ጥቅምንና ግንኙነትን ግምት ውስጥ ያላስገባ ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡– በግድቡ ዙሪያ ያለው አቋም ከአዲሱ የሱዳን መንግስት በኋላ የመጣ ነው። የግድቡን ጥቅም ስለሚያውቁ ለግንባታ የሚሆን ቁሳቁስ ሳይቀር ድጋፍ ሲያደርጉ በነበሩበት ሁኔታ የመንግስት ለውጥ ሲመጣ የመጣው ፖለቲካዊ ለውጥ ነው ብለን ማስቀመጥ እንችላለን? እንደ ድንበሩ ጉዳይ የሶስተኛ ወገንን ጉዳይን የማስፈጸም ተልዕኮ ነው ብለን ማስቀመጥ አንችልም?
አምባሳደር ይበልጣል፡– የሱዳን መንግስት አሁን እየተከተለው ያለው አካሄድ ከመስመር የወጣ ሌላ አላማ ያለው መሆኑን መረዳት ይቻላል።
አዲስ ዘመን ፡– በሱዳን መንግስት በኩል ያለው የአቋም መዋዥቅ ህዝቡ እንዴት ይቀበለዋል? በዘለቂ ጥቅማቸው ላይስ የሚያስከትለው አሉታዊ ተፅእኖ ምንድን ነው?
አምባሳደር ይበልጣል፡– እንደተባለው ሱዳናውያን በተለይ ሱዳናውያን ጋዜጠኞች በስፋት ነው የሚቃወሙትና የሚተቹት። ይህ ግድብ ለሱዳን ሰፊ ጥቅም አለው ።የሱዳን መንግስት ከኢትዮጵያ ጋር ያለውን ልዩነት በሰላማዊ መንገድ መፍታት አለበት።ኢትዮጵያ ግጭት አትፈልግም፤ ግድቡ ይጠቅመናል፣ የድንበሩ ጉዳይም ቢሆን በሰላማዊ መንገድ ይፈታ የሚል አቋም ይዘን እየተንቀሳቀስን ነው። ይህ የህዝብ ፍላጎት አይደለም።የፖለቲከኞች ውሳኔ ነው፡፡
ህዝቡ የግድቡን ጥቅም ይረዳል።ምንም እንኳን የተዛቡ መረጃዎችን በመስጠት አጠቃላይ የ20 ሚሊዮን ህዝብ ህልውና አደጋ ላይ ሊወድቅ ነው፤ ዜጎቻችን እንዲህ ሊሆኑ ነው እየተባለ በስፋት የሚሰራጭ መረጃ ቢኖርም ህዝቡ ግን ካሁን በፊት ሲነገረው የነበረውን ይረዳል። አንዳንድ ባለሙያዎችና ጋዜጠኞች የራሳቸውን ሀላፊዎች በተለይ የውሃ ሚኒስትሮቻቸውን እስከመተቸት ይደርሳሉ። ትናንትና ስለ ጥቅሙ ስትናገሩ ነበር፤ ዛሬ ምን ተፈጠረና ነው ስለግድቡ ጉዳትና ጥፋት የሚገለፅልን የሚሉበት ሁኔታ አለ። ማህበረሰቡ ይረዳል።ትናንት ስለግድቡ በነማን ምን ሲነገረው እንደነበር ያውቃል።ዛሬ ይህ ሁሉ የአቋም ለውጥ ሲመጣ ሌላ የፖለቲካ አጀንዳ እንዳለ የሱዳናውያንን ዘላቂ ጥቅምና ከኢትዮጵያ ጋር ያለውን ግንኙነት ያላገናዘበ አቋም ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡– የሱዳን መንግስት በተለያዩ ግዛቶች ላይ ያሉ የተቃውሞ ሰልፎችን ለማስቀየርና መንግስት የገጠመውን የውስጥ ውጥረቱን ለማስቀየር ነው የህዳሴ ግድቡን አጀንዳ ያደረገው ይባላል። ወቅታዊ የሱዳን የፀጥታና የፖለቲካ ጉዳይ ምን እንደሚመስል አስተያየት ቢሰጡበት?
አምባሳደር ይበልጣል፡– እንደሚታወቀው ሱዳን በሽግግር ሂደት ላይ ናት። በርካታ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ችግሮች አሉባት። እንደሚታወቀው የዚህ ለውጥ ዋና መነሻ የነበረው የኢኮኖሚ ጥያቄ ነው።እነዚህ ችግሮች አሁንም አሉ። አሁንም በመንግስት ላይ ጫናዎች አሉ። የዳቦ፣ የነዳጅና መሰል ጥያቄዎችም አሉ።የፖለቲካው ሁኔታ በተመለከተ በርግጥ ለውጥ አለ ተቃዋሚዎች እየመጡ ያሉበት ሁኔታ ነው ያለው ።በቅርቡ እንደሚታወቀው የጁባ የሰላም ስምምነት ተቃዋሚዎችና የሽግግር መንግስቱ ስምምነት ላይ ደርሰዋል። በአንጻሩ ደግሞ ሰሞኑን ሱዳን ውስጥ የጎሳ ግጭት በየቦታው ያገረሻሉ።በፖለቲካውም ሆነ በኢኮኖሚው አሁንም ቢሆን መፍትሔ የሚያስፈልጋቸው የውዝግብ መነሻ የሆኑ ጉዳዮች በሀገሪቷ ውስጥ ይታያሉ። በኢትዮጵያና በሱዳን ተመሳሳይ የሆኑ ችግሮች ስላሏቸው ካለባቸው በርካታ የልማትና የፖለቲካ ጥያቄ አንፃር ያሉባቸውን ችግሮች ትኩረት ሰጥተው በሰላም መፍታት አለባቸው፡፡
አዲስ ዘመን፡– ስለሰጡን ሰፊ ማብራሪያ እናመሰግናለን፡፡
አምባሳደር ይበልጣል፡– እኔም አመሰግናለሁ፡፡
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 8/2013