ራስወርቅ ሙሉጌታ
የሰው ልጅ በምድር ሲኖር ይነስም ይብዛ ይወጣውም አይወጣው ሊገጥሙት የሚችሉ በርካታ ችግሮች መኖራቸው የማይታበል ሀቅ ነው። አንዳንዱ ከባድ የሚባል ችግር ደርሶበት ተጋፍጦት የሚያልፍ ወይንም ደግሞ ከችግሩ ጋር አብሮት የመኖርን ክህሎት የሚያዳበር ሲሆን በተቃራኒው ደግሞ ሌሎች ለቀላል ችግሮች እንኳን መፍትሄ መሻት ተስኗቸው ራሳቸውን ለተለያዩ ጉዳቶች ሲዳር ጉ ይስተዋላሉ። ችግር አይግጠመኝ አይባልምና ለመሆኑ ምንም አይነት ችገር ቢገጥመን ለማለፍ ምን ማድረግ ይጠበቅብናል ስንል የማህበራዊ ልማትና አመራር ባለሙያ ከሆኑትና በቲቪ ዘጠኝ የክሊፍ ሞቲቬሽን ወይም አፋፍ ለመድረስ ዝግጅት አዘጋጅና አቅራቢ አቶ ዘላለም ይትባረክ የሰጡንን አስተያዬት እንደሚከተለው ይዘን ቀርበናል።
ችግር ስንል ማነስ፣ መጥፋት፣ መቋረጥ፣ መጋጭት፣ መሳሳት፣ መበላሸት ወዘተ እንደማለት ሲሆን ሁሉም አሉታዊ፣ ተቃራኒ፣ ኔጌቲቭ ወይም የሙሉና በጎ ነገር ተቃራኒ በሙሉ ችግር ከሚለው ቃል ጋር አቻ ትርጉም አለው፡፡ ምን አልባትም የሥራ ማጣት፣ የገንዘብ መጉደል፣ የኑሮ ጣጣ፣ የግንኙነት መደፍረስ፣ የትዳር መናጋት፣ ውድቀት ወይም ኪሳራ ወዘተ በሙሉ መገለጫዎች ናቸው፡፡
ችግርን መፍቻ ብልሃቶች
ምንም አይነት ችግር ቢገጥመን ለመፍታት ሁለት መንገዶችን መጠቀም ያለብን ሲሆን የመጀመሪያው ራሳችንን ማረጋጋት ይሆናል። ለዚህም የአዕምሮአችንን ችግር የመፍታት ተፈጥሮአዊ ክህሎትና አቅሞች ከሚያጎለብቱ ተመካሪ ዘዴዎች መካከል ጥሩ የእንቅልፍ ሌሊትን ማሳለፍ፣ ሙዚቃ ማዳመጥ፣ መደነስ፣ መጫዋቻ ጌሞችን መጠቀም፣ በዮጋ ልምምድ መሳተፍ፣ አጃ፣ ለውዝ ወይም ቸሪኦስ መመገብ እና ከችግሩ ስነ-ልቦናዊ ርቀትን መፍጠር መቻል ተጠቃሽ ናቸው። በሁለተኛ ደረጃ መሬት ያለውን ችግራችንን ለማስወገድ ደግሞ የሚከተሉትን ብልሃቶች መጠቀም ተገቢ ነው።
1ኛ. ችግሩን ለይቶ ወይም ነጥሎ ማዬት
የብዙ ቀላል የሆኑ ችግሮች መወሳሰብ ምክንያት የችግሩ ፈጽሞ አለመለየት ሳይሆን በሌሎች ችግሮች መከለሉ ነው።
በመሆኑም ያለንበትን ወይም የተያዝንበትን ማንኛውንም ችግር ነጥለን ከሌሎች ጋር ካለው ዝምድና ውጭ ብቻውን ማዬት፤ ይህም የችግራችንን መንስኤ መነሻ ውጤትና መድረሻ ለማወቅ ከመርዳቱ ባለፈ ከስሩ፣ ከምንጩ ለማድረቅና ለመፍታት የሚያስፈልገንን የብልሃት አካሄድ እንድናውቅ ይረዳናል፡፡
ችግሩን ነጥለን ካላየነው ግን በደንብ በተገቢው ችግራችንን ከመሰረቱ ስለማናውቀው ችግሩ ሊገዝፍብን
ከመቻሉ ባለፈ ምን መፍትሔ ማድረግ እንዳለብን አናውቅም፡፡ ይህም በግምት በመሰለኝ አይነት አካሄድን እንድንሞክር እንድንሳሳት ከማድረጉ ባለፈ መፍትሔው ጋር እስክንደርስ ድረስ በብዙ መንገድ፣ አድካሚ ሙከራና ውጣ ውረድ እንድናልፍ ያደርገናል፡፡
2ኛ. ራስን ከችግር በላይ ማድረግ
ችግርን ከመለዬት ቀጥሎ ልናደርገው የሚገባን ነገር ካለንበት ከማንኛውም ችግር እኛ እንደምንበልጥ መረዳት ነው። ይህም ችግሩ ምንም የከፋና ከባድ ቢሆንም አቅልለን እንድንመለከተውና እኛ ችግር ብቻ ሳይሆን መፍትሔንም የያዝን እንደሆንን እንድንገነዘብ የሚያስችል ድጋፍን ይሰጠናል፡፡
ይህ እሳቤ ካለንበት ማንኛውም ችግርና ችግሩ ከሚያደርስብን ችግር በላይ የምንበልጥና ቅድሚያ ለራስ እንድንል ያደርገናል። በተጨማሪ ራሳችንን እንድንጠብቅ ችግሩ ከነገርና ሁኔታ አልፎ እኛንም ይዞን እንዳይሄድ ይረዳናል። ያለበለዚያ የአንዳንድ ችግሮች ጥልቀትና ስፋት ከእኛ በላይ ከሆኑ ጉዳታችን ከውጭ አልፎ ወደ ውስጥ ስለሚገባ አደገኛ ከመሆኑ በላይ ለማገገም ከባድ ነው የሚሆነው።
ሁለተኛ ራሳችንን ከችግራችን በላይ አድርጎ መመልከት ያለንበትን ወይም የገጠመንን ማንኛውንም ችግር የከፋና ከባድ ቢሆንም አቅልለን ማዬት እንድንችል ይረዳናል። ምክንያቱም እኛና ችግራችን በማለት ተፈጥሮአዊና ዓለማዊ ወይም ሰው ሰራሽ የሚባሉትን ንጽጽሮች እንድናይ ይረዳናል። ሦስተኛ እኔ የችግር መገኛ ብቻ ሳልሆን በእኔ ውስጥም መፍትሔም ጭምር አለ ብሎ ለማሰብ ራስን ከችግር በላይ አድርጎ ማዬት አስፈላጊ ነው።
3ኛ. መፍትሔው ላይ ማተኮር
እንግዲህ ችግሩን ነጥለን ከመረመርንና በኋላ ራሳችን ከችግሩ በላይ ማድረግ ከመቻል ቀጥሎ በሦስተኛ እርምጃ የምናደርገው መፍትሔ ላይ ማተኮር ነው። ችግሩ ሊሰጠው በሚገባው ትኩረት ደረጃ ለይተን ከተረዳነው በኋላ፤ ችግሩን ወይም የተጎዳነውንና የደረሰብንን ወደ ጎን በማድረግና በመተው ቀጥሎ ችግሩ እንዳይቀጥልና እንዳያድግ ምን ላድርግ፣ ምን ልሥራ ብለን ለመፍትሔ ማዘጋጀት ይሆናል። ለዚህም መፍትሔውን ከችግሩ ነጥሎ ከችግር በላይ በሆነ አስተሳሰብ በንፁህ አዕምሮ ያጋጠመንን ችግር ለመፍታት መሞከር ይኖርብናል።
ያለበለዚያ በቅድሚያ በችግሩ ተጎድተን አሁንም ደግመን ችግሩን ብቻ በማሰብ የምንቆዝም ከሆነ ሁለተኛ የድጋሚ መጎዳት ይሆንብናል። በመሆኑም አይኖቻችንን፣ ትኩረታችን ወይም ያለንን ሁሉ አቅምና ጉልበት አሟጠን ካለንበት ችግር ላይ በመንቀል መፍትሔ ላይ ብቻ ትኩረት ማድረግ አለብን።
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 5/2013