አዲሱ ገረመው
በተለምዷዊ ትርጓሜ፤ “ሥነ-ጥበብ” ወይም “አርት” በጥቅል “ክኂሎት” የሚል ትርጓሜ ሲይዝ፤ በተለይ የ“ደስታ” ወይም የ“ተዝናኖት” ምንጭ መሆን የሚችልን ነገር የመፍጠር ችሎታ እንደሆነ ተደርጎ ይተረጎማል:: የአንድ ሥነ-ውበት ሙያ ባለቤት የሆነ ሰው “የሥነ-ጥበብ ሰው” (አርቲስት)፣ የሚሠራው ሙያ ወይም የጥበቡ ውጤት ደግሞ “ሥነ-ጥበብ” (አርት) ሊባል ይችላል::
በዘመናዊው ዓለም ትርጓሜ መሠረት “ሥነ-ጥበብ” የሚለው ቃል ሰፊና በርከት ያሉ መልኮችን እንዲሁም የመገናኛ ብዙሃን ዓይነቶችን ያካትታል:: ሥዕልና ቅርጻ ቅርጽ፣ ኪነ-ሕንጻ፣ ሥነ-ጽሑፍ፣ ሙዚቃ፣ ዳንስና ቴአትር እንዲሁም የተለያዩ የመልቲ ሚዲያ ዓይነቶች (እንደ ሲኒማ ያሉትን) ይይዝና “ሥነ-ጥበብ” የሚል የስም ብያኔ ይይዛል::
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባህል፣ ኪነ ጥበብና ቱሪዝም ምክትል ቢሮ ኃላፊና የዘርፉ ምሁር አቶ ሠርጸ ፍሬስበሐት እንደሚሉት፤ “ሥነ-ጥበብ” ረቂቅ ሰብአዊ ስሜቶች በትዕምርት የሚቀረፁበት ፈጠራ ነው:: ማኅበራዊ እውነታን፤ በምስል የሚያንጸባርቅና ሰዎች ስለ ዓለም ያላቸውን ውበታዊ ግንዛቤ የሚገልጽ ክዋኔ፤ “ሥነ-ጥበብ” ይባላል:: የሰውን ልጅ ደመ-ነፍስ፤ ስጋዊ (ሥግው) የሚያደርግ ኪናዊ ክዋኔ ነው:: ሥነ-ጥበባት፤ ‘ውበት’ ለሚባለው ረቂቅ “ዲበአካላዊ” ወይም “ረቂቅ” ሐሳብ (Metaphysical ideal)፤ ምናባዊ አካል ፈጥረው የሚታይ፣ የሚዳሰስ፣ የሚሰማ ያደርጉታል::
ሥነ ጥበብ የተመልካችን ወይም የአድናቂውን አእምሮ ከሚገመተው በላይ የመቆጣጠር እና በገሀዱ ዓለም ላይ ላሉ ነገሮች ከሚሰጠው ትርጉም በላቀ፤ በምናብ ለተፈጠረው ጉዳይ ቀልቡን እንዲሰጥ ተጽዕኖ ማሳረፍ ይችላል::
“ሆን ተብለው የተዋቀሩት የምናብ ፈጠራዎች፤ የነባራዊው ዓለም ውክልናዎች (አስተማስሎዎች) (construction of representations) የተመልካቹን ወይም የአድማጩን የዓለም ዕይታ (world view) በተጽዕኗቸው ሥር ማድረግ ይችላሉ” ይላሉ አቶ ሠርጸ::
እንደ እርሳቸው ሙያዊ ማብራሪያ፤ ሥነ-ጥበብ፤ የሰው ልጅ ብቻ የሚፈጥረው ሲሆን፣ “ዩኒቨርሳል” የሚሆነው ደግሞ በየትኛውም ዓለም በሚኖር ማህበረሰብ ውስጥ ተጽዕኖ ማሳደር ስለሚችል ነው::
“ሰው” እንደ ሁለት ዓለማት ሥነ ፍጥረት
አቶ ሠርጸ እንደሚሉት፤ “ሰው” እንደ ሁለት ዓለማት ሥነ ፍጥረት መታየት ይችላል:: የመጀመሪያው “ተፈጥሯዊው ዓለም” (Natural World) ይባላል:: ይኸኛውን ዓለም፤ የሰው ልጅ በተፈጥሮ ያገኘው፣ ሲወለድ የተቀበለው፣ የለመደውና አብሮት የሚኖረው አካባቢው ነው::
ሁለተኛው ደግሞ “ማኅበራዊው ዓለም” (Social World) ነው:: የሰው ልጅ እርሱ ራሱ፤ በአስተሳሰቡ፣ በአብሮ መኖሩና በዘመናት ፍልስፍናው እያሻሻለው ወይም እያጠፋው የመጣው ራሱ የፈጠረው ዓለም ነው:: በዚህ መሠረት ስለ ሥነ-ጥበብ እና ባህል ስናወሳ፤ ስለ ሁለተኛው ዓለም ማለትም ስለ “ማኅበራዊው ዓለም” በስፋት እየተነጋገርን ነው::
የሥነ ጥበብ እና ባህል ቦታው በዚህ የሰው ልጅ አስተሳሰብ በፈጠረው ዓለም ውስጥ ነው:: ይሁን እንጂ፤ ሥነ-ፍጥረትን እና የሰው ልጅን ፍጥረታዊ ቁም ነገር መመርመራችን በተወሰነ መልኩ ከአንደኛው ዓለም “ከተፈጥሯዊው ዓለም” ሐሳቦችም ጥቂት ማንሳታችን አይቀርም::
ከዚህ አልፈን፤ ጠንከር ወደሚለው የአሪስቶትል አስተሳሰብ ከሔድን፤ “ይህችን ‘ጎደሎ ዓለም’ (Imperfect world) ‘ምልዕት’ ወይም ‘ፍጽምት’ መስላ እንድትታይ፤” የሆነችው በ‘ሥነ-ጥበብ’ ሆኖ እናገኘዋለን::
የአእምሮ ዕድገት መለኪያ፣ የሰው ልጅ ከእንስሳት ተለይቶ እንዲቆም ምክንያት የሆኑት ነገሮች ሲዘረዘሩ፤ የሰው ልጅ የሥነ-ጥበብ ባለቤት መሆኑም አንዱ መለያው ሆኖ ይጠቀሳል::
ታላቁ ደራሲ ከበደ ሚካኤል እንዳሉት፤ “የሰው ልጅ በብርቱ ወደሚደክምለት የቁሳዊ ሀብት ኀሰሳ፤ አንድ ቀን ቢደርስና በቁሳዊ ሀብት እርካብ ላይ ቢወጣ፤ ደስታው ፍፁም ይሆናል ተብሎ አይገመትም:: ከቁሳዊነት ያለፈውን የዚህን ሰው ፍላጎት ማሟላት የሚችሉት እንደ ሥነ-ጥበብ ያሉት መንፈሳዊ ኃይሎች ናቸው::”
ኢማኑኤል ካንት፤ “ሰው ለምቾቱ የሚሆኑትን ነገሮች ካገኘ በኋላ የሕይወቱ ዓላማ በእነዚህ ነገሮች ብቻ ከተፈጸመ፤ በሥጋዊ ባህርይ ብቻ ተወስኗል ያሰኛል:: ይህም ከእንስሳት ምንም ያህል የተራራቀ ሆኖ አይገኝም:: …ከጥበባት የሚገኘው ደስታ፤ ለተከበረው ሥነ-ፍጥረት ለሰው ልጅ የመጨረሻው ፍስሐ እንደመሆኑ መጠን፤ ጥበባቱ በቀላሉ የሚገኙ አይደሉም:: ሰውም ከጥበባቱ የመነጨውን ደስታ በሙሉ ሊደርስበት የሚችለው ስሜቱ በጣም የተራቀቀ ሲሆን ነው” ይላል::
ከእነዚህ ምልከታ ተነስተን “ሥነ-ጥበብ” ማለትም ውብ የሆነውን ነገር ሁሉ የሚያስወድድ ስሜት መሆኑን መረዳት ይቻላል:: ውብ ነገር ማለት ደግሞ ከውስጡ ምንም ነገር ሳናገኝበት የሚያምር በመሆኑ ብቻ የምንወደው ነው::
የመገናኛ ብዙሃንናና ሥነ ጥበብ ግንኙነት
“ጥበባት፣ የጥበብ ሰው እና መገናኛ ብዙሃን” የሚለው ጉዳይ የተለመደ እና በኪነ ጥበቡ ዓለም ያሉ ባለሙያዎችም ሆኑ የጥበብ አድናቂዎች የሚስማሙበት ሐሳብ መሆኑን አቶ ሠርጸ ይናገራሉ:: ምክንያቱም የሚዲያው ሰው በተለይ ኪነ ጥበባዊ ውጤቶች በሆኑ ነጥቦች ላይ የሰ ላ ሂስ ከመስጠት ይጀም ራልና ነው::
“ሒስ፤ ከራሱ ከጥበቡ ተወስዶ፣ ለጥበቡ መዳበር የሚሰጥ ክትባት ነው፤” ይላሉ:: በተጻፉ ሁለት መሥመሮች መሐል፣ ያልተጻፈውን ሦስተኛ መስመር የምታሳውቀን ሒስ በመሆኗ ባለሙያው ጥበብን በሂስ ማዳበር እንዳለበት ያመላክታሉ::
ሒስ “ያመጣዋል” ተብሎ የተጠበቀው ውጤት የመሳካት ዕድሉ በጣም ያንሳል:: የተሰጠው ሒስ እና የሒስ ባህል፣ ሊያነቃው የሚገባ ማኅበረሰብ፣ “የዳኝነት ቦታ ካልያዘ” ሒሱ ተገቢው ቦታ ላይ አርፏል ለማለት ይቸግራል::
የጥበብ ሰው በባሕርዩ ማግኘት የሚፈልገውን “ያለ አንዳች ጥርጥር ምሉዕ ተቀባይነት የማግኘት ፍላጎቱን” ብቻ በማሳካት ጥበቡን ይጎዳዋል:: ታዲያ ሒስ በኪነ ጥበብ ሰው እና በሐያሲው መካከል ብቻ የተካሔደች ሙግት ሆና ብትቀርስ? ለሚለው ጥያቄም፤ የጥበብ ታዳሚውን፣ ተመልካቹን፣ አድማጩን በእንግሊዝኛው `Audience` የምንለውን አካል ማንቃት፣ ማሳወቅ፣ መራጭ እና ዳኛ እንዲሆን ማድረግ የተገባ መሆኑን አቶ ሠርጸ ያስረዳሉ::
የሚዲያ ሰው ከሐያስያን ተጽዕኖ በላይ፣ ጥበብን የሚያሳድጋት ቁም ነገር ያለው የ`Audience` ሞጋች ባሕርይን በመፍጠር ረገድ አቅሙን ማጎልበት እንዳለበት ነው የሚያመላክቱት::
አዲስ ዘመን መጋቢት 26/2013