እየሩስ አበራ
የታፈነ ምሬት፣ ሊፈነዳ የደረስ መተንፈሻ ያጣ የህዝብ ብሶት … ያሳስባል:: ለኢትዮጵያ ህዝብ የጭንቅና የውጥረት ጊዜ ነበር:: ከትናንት ዛሬ የተሻለ ለውጥ እንደሚመጣ በማሰብ ለውጥን እየናፈቀ ቆይቷል:: 27 ዓመታት የወለዱት ምሬትና ብሶት ውስጥ የቆየው የኢትዮጵያ ህዝብ ዳር እስከ ዳር በአንድ መንፈስ ተነቃንቋል:: እየታገለ ትግሉ ሳይቋረጥ ከዛሬ ነገ ለውጥ ይመጣል ብሎ በማሰብ በተስፋ እየተጠባበቅ የነበረበት ያ ወቅት!::
የቁርጡ ቀን ደርሶ ያሰበው እስከሚሳካለት ትዕግስቱ አይሎ በፅናት እየተጠባበቀ ያለበት ወቅት ላይ ነበር፤ ይሆናል ተብሎ ለመገመት የሚያዳግት ክስተት ተከሰተ:: መጋቢት ወር ሊሰናበት ሲል መቼ ቢሆን የጊዜ ጉዳይ እንጂ የማይቀየር ነገር የለምና ያልታሰበው ሀገሪቱን በሞኖፖል የያዘው አካል ከተሰቀለበት የስልጣን ማማ የመልቀቁ ዜና ተሰማ:: ይኼኔ ነበር በመላው ሀገሪቱ ደስታና ፈንጥዝያ የሆነው፤ ልክ የዛሬ ሦስት ዓመት:: ይህ ነበር ዛሬን በሀሳብ ሰረገላ በትዝታ ጎዳና ወደ ኋላ እንድንቃኘው ያስገደደኝ::
ለውጥን ሲናፍቅ የቆየው፣ ነጻነት ለመጎናጽፍ ጭላንጭል ፍለጋ ሲዋትት የነበረው ህዝብ በመተባበርና በአንድነት ታግሎ ያመጣው ለውጥ ከማየት በላይ ደስታን የሚፈጥርለት ነገር አልነበረም:: ከጫፍ እስከ ጫፍ ላሉ ኢትዮጵያውያን የበራው የለውጥ ብርሃን ነገ የተሻለ ለመሆኑ ማሳያ ሆኗል:: በህዝብ ጫንቃ ተቀምጦ የህዝብ ፍላጎት ወደ ጎን ብሎ ስልጣንን የሙጥኝ ያለ አካልን ከስልጣኑ ማማ ማውረድ በቀላሉ የሚታሰብ ባይሆንም ማድረግ ተችሎ ሲገኝ ግን ለውጥ በመሻት፣ ነጻነትን መፈለግ የቅንጦት ሳይሆን የትግል ውጤት በመሆኑ የሚፈጥረው ደስታ ከውስጥ የሚያስፈነጥዝ ሆኖ ቢሆን ምንም አያስገርምም::
በተለይ ለውጥ የሚያስፈልገው በስልጣን ላይ ያለው አካል በህዝብና ለአገሩ የማይበጅ ከሆነ ስልጣኑን የሰጠው ህዝብ ነውና የሰጠው ስልጣን መልሶ መቀበሉ የማይቀር ነው:: ስልጣን የህዝብ ማገልገያ መሆኑን በመረዳት በሚገባ ህዝቡን ከማገልገል ይልቅ ሀገር መበዝበዝና ህዝብን መበደል ሥራዬ ብሎ ከተያያዘው ህዝቡ በቃኝ ያለው እለት ይቺ ቅጽበት መጥታ የነበረው እንዳልነበረ በማድረግ እንዲያየው ታደርገዋለች::
በስልጣን ላይ የነበረው አጥፊው የህወሐት ቡደን አስቀድሞ ስልጣኑን ቢለቅም እንኳን ተመልሶ ዳግሞ ወደ ስልጣን መምጣት የሚችልበት መንገድ ቀደሞውኑ በማመቻቸት ካልሆነም ደግሞ ሀገር ለማፍረስ የሚችልበት ስትራቴጂ ነድፎ ስልት ቀይሶ ነበር:: በመሆኑም ብሔር ከብሔር፣ ጎሳ ከጎሳ፣ ሃይማኖትን ከሃይማኖት በማጋጨት ሀገር ማፍረስ ሴራና ተንኮል ከሽፎበታል:: ይባስ ብሎ የጥፋት ቡድኑ መከላከያ ላይ በከፈተው ጥቃት ምክንያት መንግሥት ህግ የማስከበር ዘመቻ ማካሄዱ የሚታወስ ነው::
ሀገራችን አጣብቂኝ ውስጥ ገብታ ኃይለኛ ቀውስ በነበረበት በዚያን ሰዓት ሀገሪቱን ለማስተዳደር የተቀበለው መንግሥት ሀገርን አረጋግቶ ወደ ሥራ ለመግባት እጅግ በርካታ ውጣ ውረዶች መሰናክሎች ተጋርጠውበት ከፊቱ ተደቅነው ነበር:: የለውጡ ጅማሮ ኢኮኖሚ የወደቀበት እየፈራረሰች ያለች ሀገር ተረክቦ ወደ መስመር ለመመለስ በርካታ ሥራዎች የሚጠይቅ ነው:: የለውጡ መንግሥት ጅማሮ በይቅርታና በእርቅ የታጀበ ነበር:: በሀገር ውስጥ ያለው ያለፉ ጥፋቶች ሁሉ በይቅርታ በማለፍ የተጀመረ እስከ ጎረቤት ሀገር ድረስ ሰላም ለማውረድ ያሰበ ነበር:: ከኤርትራ ጋር 20 ዓመታት ተቋርጦ የቆየውን ግንኙነት በማደስ በሁለት ህዝቦች መካከል ያለው ወንድማማችነት እንዲጠናከረ ተደርጓል::
የኢትዮጵያዊያን የአንድነት አሻራ ያረፈበት ታላቁ የህዳሴ ግድብ በመጀመሪያ አስፈላጊውን ሁሉ ሥራ ከተሰራ በኋላ በ2012 ዓ.ም የመጀመሪያ ዙር የውሃ ሙሌት እንዲሞላ ሆነ፤ ጨልሞ የነበረው ተስፋ የብርሃን ጮራ ፈነጠቀበት:: በኢትዮጵያውያኑ ልብ እንደገና ተስፋ ለመለመ:: በቅርቡ የወጣው የግድቡ ግንባታ ሂደት መረጃ 79 በመቶ ያህል መጠናቀቁን አመልክቷል። ከአምስት እስከ ሰባት ዓመት የግንባታ ጊዜ የተያዘለት ግድቡ በተለያየ ምክንያት በተያዘለት የጊዜ ገደብ ሊጠናቀቅ አልቻለም።
ለውጥ ሰንቆ ከተነሳው በርካታ ተግባራት ውስጥ ሸገርን በማስዋብ ፕሮጀክት ውስጥ የተካተተ የአንድነት ፓርክ እና የሸገር ፓርክ ግንባታ በሚያምር ሁኔታ ተጠናቆ ሥራ መጀመሩ የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው:: በገበታ ለሀገር ፕሮጀክቶችም የተመረጡት የእንጣጦ ፓርክ፤ ወንጪ፤ የኮይሻና የጎርጎራ ፕሮጀክቶች ውስጥ የእንጦጦ ፓርክ የተጠናቀቀ ሲሆን፤ በክልል ያሉት በጥሩ ጅማሮ ላይ ያሉ መሆኑን አይቶ ማመንን የሚያስችል ሥራዎች እየተሰሩ መሆኑን መካድ አይቻልም::
ለውጥ ከአንድ ሥርዓት ወደ ሌላ ሥርዓት መሸጋጋርን የሚያሳይ ድልድይ ነው:: ይህ ድልድይ ተገንብቶ ሁሉም ሰው በእኩልነት የነጻነት አየር እንዲተነፍስ ማድረግ ግን በቀላሉ የሚታለፍ ሳይሆን በእሳት የመፈተን ያህል ከባድ ሊሆን ይችላል:: በተለይ በኛ ሀገር ለረጅም ጊዜ የተለያዩ የሀሳብ ነጻነት ታፍኖ ለቆየበት ሀገር ለውጡ ይዞት የሚመጣው ቱሩፋት እንዳለ ቢታወቅም ከዚያ ባሻገር ወደ የለውጥ ሂደት የሚደረገው ጉዞ አልጋ በአልጋ አይሆንም:: በመሆኑ እጅግ በርካታ በሆነ ውጥንቅጥ ውስጥ ሆና እየተናወጠች የቆየች ሀገር በለውጥ ጎዳና ወደፊት እንድትገሰግስ የማድረጉን ሂደት ቀላል ሳይሆን ውስብስብና አስቸጋሪ ያደርገዋል::
ሁላችንም የተሻለ ነገን ለማየት በጋራ በመስራት ኃላፊነታችንን መወጣት ይጠበቅበናል:: ወሳኙ ጉዳይ ደግሞ ፅናት ነው:: ስልጣኑን የለቀቀ ስግብግብ መቼም ቢሆንም በዓለም ላይ ተሰምቶ የማያልቅ ወንጀልን ከመፈፀም ወደ ኋላ እንደማይል አሳይቷል:: ያበደ ውሻና ተስፋ የቆረጠ ነፍስ የሚያርጉትን አያውቁም፤ ጥፋታቸው ወሰን የሌለው የሆነው ለዚሁ ነው:: መቼም እነርሱ ጋር ስለወንድምም ሆነ ስለልጅ፣ ስለእህትም ሆነ ስለእናት ማሰብ ብሎ ነገር የለም:: በህዝብ መነገድን ዛሬም ቀጥለውበታል:: ነገር ግን የነቃ ህዝብ አዋቂ ነው:: ከአራት አስርት ዓመታት በላይ የተቀለደበት ህዝብ ዛሬ መንቃት አለበት::
ስልጣን ላይ ወጥተው ታይተዋል:: ከዚህ በኋላ ይበቃቸዋል:: የትግራይ ህዝብም ይህንን መገንዘብ አለበት:: በእርሱ ስም እየተጠቀሙ ንግዳቸውን እንዲቀጥሉ ሊፈቅድ አይገባም:: አሁን የተስፋ ብርሃን አለ:: ያንን ብርሃን መከተል ያስፈልጋል:: በብርሃኑ ውስጥ የሚያጋጥሙ ጋሬጣዎችን ደግሞ በፅናት ማለፍ ከተቻለ ኢትዮጵያን ያደገች አገር ማድረግ ብዙ አሳሳቢ አይሆንም::
አዲስ ዘመን መጋቢት 26 ቀን 2013 ዓ.ም