ታዋቂው ገጣሚ ፀጋዬ ገብረመድህን እንደሚለው የሰው ልጅ ከሁለት ነገር ይማራል፤ አንድም “ሀ” ብሎ ከፊደል፣ አልያም “ዋ” ብሎ ከመከራ:: የመጀመሪያዎቹ ተማሪዎች ነገን የሚያስቡና ስለነገው ብሩህ ተስፋ ያላቸው ናቸው:: ሁለተኞቹ ግን ከሚደርስባቸው ችግር የሚማሩ ናቸው:: ይህ የሁለተኛው ትምህርት ግን ዋጋ ያስከፍላል፤ ከዚያም አልፎ ሁለተኛ እድል የማይሰጥ ሊሆን ይችላል:: እኛ ደግሞ ከመልካም አጋጣሚዎች መማር እያቃተን መከራ እንዲመጣ የማንቆፍረው ጉድጓድ፣ የማንፈነቅለው ድንጋይ የለም::
እነዚህን እድሎች ስንመለከት በቅድሚያ የምናገኘው ሰፊውን መልካም አጋጣሚ ነው:: እንደሚታወቀው ኢትዮጵያ የቀደመ የስልጣኔ ታሪክ ያላት አገር ናት:: አሁን ዓለምን በእጃቸው በማድረግ እንዳሻቸው መዘወር የሚፈልጉ ሃገራት ስማቸው በማይነሳበትና ስልጣኔን ባልተረዱበት ዘመን ኢትዮጵያ የስልጣኔና የእድገት አቅጣጫ አመላክታቸዋለች:: ዛሬም ድረስ አሻራቸው ጎልቶ የሚታይ የስልጣኔ ሃውልቶችንም ለታሪክ ምስክርነት አኑራለች::
በተለያዩ እይታዎች የገነነ ታሪክ የነበራት አገራችን ያንን ገናና ስምና ስልጣኔ ማስጠበቅና ማሳደግ ሳትችል ቀርታ የታሪክ አስታዋሽ ብቻ ሆና ቆይታለች:: ልጆች የአባቶቻቸው ታሪክ ነጋሪ እንጂ አስቀጣይ መሆን ሳይችሉ በመቅረታቸው ልክ እንደ ደካማ አትሌት ሁሉም ከኋላ እየተነሳ ቀድሞ ሲሄድ ቆመን ማየት ከጀመርን ሰነባብተናል:: እነቻይና፣ ጃፓን፣ ኮርያና የመሳሰሉ አገራት ደግሞ እንደ ማርሽ ቀያሪው አትሌታችን በፍጥነት ጥለውን ከጫፍ ሲደርሱ አይተናል::
ጥለውን ሲያልፉም ቆሞ ከማየት በዘለለ እነሱ ጋ ለመድረስ የሞከርንበት ጊዜ አናሳ ነው:: ይልቁንም እርስ በርሳችን “ባንተ ወይም ባንቺ ምክንያት ነው የቀደሙኝ” የሚል የእናቴ መቀነት አደናቀፈኝ አይነት የማይረባ ምክንያት ከወደፊቱ የማሸነፍ እድል ይልቅ ላለፈው ሽንፈት ሰበብ በመደርደር የምክንያት ሰዎች መሆን የዘወትር ተግባራችን ሆኗል::
በሌላ በኩል ደግሞ በስልጣኔያቸው ትልቅ ደረጃ ላይ የነበሩና ቆም ብለው ማሰብ ባለመቻላቸው በደረሰባቸው ክፉ እጣ ለከፋ ውድቀት የተዳረጉትን እነ ሶርያንና የመንንም ማየት አልቻልንም::
አሁን ያለንበት ወቅት ካደጉት አገራትም ሆነ ከወደቁት ተምሮ ምርጫችንን ለማስተካከል ትክክለኛው ወቅት ነው:: በአንድ በኩል በርካታ እድሎች ከፊታችን አሉ:: አገራችን ወደብልፅግና ለምታደርገው ጉዞ የሚያግዙ ሰፋፊ እድሎች ከፊት ቆመዋል:: ለምሳሌ ከዚህ ቀደም አንቆ ያስቀራት ህወሓት መራሹ ስርዓት መወገዱ አንድ ትልቅ አጋጣሚ ነው:: ይህ ስርዓት ጥቂቶች እንደልብ የሚሆኑበትና አብዛኛው ግን የበይ ተመልካች እንዲሆን ያደረገ አፋኝ ስርዓት በመሆኑ በእኩልነት ማደግ ከባድ ነበር:: አሁን ግን ይህ የኢ-ፍትሃዊነት ዘብ የነበረው ሃይል በመወገዱና ከዚህ በኋላም የመመለስ እድሉ በመሞቱ ፊትን ወደልማት ማዞር ይገባል::
ሌላው መልካም አጋጣሚ ያለፉ ሶስት አመታት የለውጥ ሂደቶች በአጭር ጊዜ ስራ መለወጥ እንደሚቻል አስተምረውናል:: በነዚህ ወቅቶች ከህወሓት መራሹ ስርዓት የተሻገሩ በርካታ ፈተናዎች ቢኖሩም፤ አያሌ የልማት ተስፋዎችን ማየት ችለናል:: ለምሳሌ በአሁኑ ወቅት በምግብ ራሳችንን ለመቻል የተጓዝንበት ርቀት በአጭር ጊዜ ከድህነት እንደምንወጣ ያሳየን ነው:: በልማት ፕሮጀክቶች አፈጻፀም፣ በግብርና ስራችን፣ ወዘተ ላይ የታዩት አመርቂ ስኬቶች ለዚህ ማሳያዎች ናቸው::
የታላቁ ህዳሴ ግድባችንም አንዱና ትልቁ የስኬታችን እና የእድገት ተስፋችን ነው:: ይህ ፕሮጀክት የመሰረት ድንጋይ ከተቀመጠለት አስር አመት ቢሞላውም እነሆ ፕሮጀክቱን መጨረስ እንደሚቻል የታየው ከለውጡ ወዲህ ነው:: ፕሮጀክቱ ባለፉት ጊዜያት ያጋጣሙት በርካታ ፈተናዎችን አልፎ አሁን ላይ ከጫፍ ደርሷል:: ይህም የመቻል ትልቁ ማሳያችን ነው::
በኢኮ ቱሪዝም፣ መስክም ቢሆን ባለፉት ሶስት አመታት የጀመርናቸውን ስራዎች መስራት ከቻልን በአጭር ጊዜ አንደኛውን የነኮርያን እና የነቻይናን መንገድ መከተል እንደንምችል የሚያሳይ ነው:: በአዲስ አበባ በሸገር ፕሮጀክት ላይ የታየው ተስፋ ሰጪ ስራ በገበታ ለሀገር በሶስት ፕሮጀክቶች እየሰፋ መጥቷል::
ይህም ለዘርፉ እድገት ብቻ ሳይሆን ለሀገራዊ ለውጥ ትልቅ ስኬት የሚያጎናጽፍ ነው:: ችግሮቻችንን እያስወገድን እነዚህን ስራዎች ማጠናከር ከቻልን እውነትም የነቻይናን መንገድ መከተላችን እንደማይቀርም የሚያመላክቱ ናቸው::
በአንጻሩ ግን የውድቀት መንገድም ከፊታችን እንዳለ እንገነዘባለን:: ይህ መንገድ የጥፋት መንገድ ነው:: ይህ መንገድ ከፊቱ በርካታ መፈናቀሎች፣ ሞቶችና የጭለማ ጉዞዎች ያሉበት ነው:: ይህን መንገድ እንድንመርጥ የሚፈልጉ በርካታ የውጭ ሃይሎች አሉ:: መንገዱን መም ረጥ ወይም አለመምረጥ ግን የኛና የኛ ጉዳይ ብ ቻ ነው::
አሁን…አሁን በዚህ በተቀደደልን የጭለማ መንገድ እንድንጓዝ በርካታ ጠላቶችንን ከኋላ ይገፉናል:: አንዳንዶቻችንም ድግሱ ሳይገባን በዚህ የተቀደደ ቦይ ለመፍሰስ እንጥራለን:: ለዚህ በተለያዩ አካባቢዎች እየተፈጠሩ ያሉ አገርን የማፍረስ ውጥኖች ማሳያዎች ናቸው:: እነዚህ ሃይሎች በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ በንፁሃን ዜጎች ላይ ቁማር በመጫወት ለፖለቲካ ትርፍና ለኢትዮጵያ ውድቀት ሌት ተቀን ይሰራሉ:: ነገር ግን እኛ ምርጫችንን ማስተካከል ይጠበቅብናል፤ የቻይናንና የጃፓንን መንገድ አልያም የየመንና የሶርያን:: የሚያዋጣንን መንገድ በመምረጥ ለልጆቻችን ብሩህ ተስፋን እናስቀምጥ::
አዲስ ዘመን መጋቢት 26 ቀን 2013 ዓ.ም