ጽጌረዳ ጫንያለው
አንዳንዶች ካለመረዳት በመነጨ ስሜት ስለሚጓዙ በአገራቸው እንዲደራደሩ ሆነዋል ይባላል። ሌሎች ደግሞ ርሃባቸው ይታገስላቸው ዘንድ አገራቸውን ችላ ብለው ለቀናዊ የፍላጎት እርካታቸው ሲታገሉ ድርድር ውስጥ እንደገቡ ይወራሉ። በሌላ በኩል ደግሞ ፖለቲካው በራሱ የፈጠረው ገደብ የለሽ የሥልጣን ጥማት በአገር ድርድር እንዲጀምሩ ገፋፍቷቸዋል የሚሉም አልጠፉም። እርግጥ ነው፤ እጠየቃለሁ የሚለው ጉዳይ ራሱ ለድርድር የሚያበቃ ጉዳይ እንደሆነም ይጠቀሳል። ግን ምንስ ቢሆን በሰው መደራደር ይቻላል? እንደ እኔ ከሆነ በፍጹም አይታሰብም። ምክንያቱም ሰውነት ከራስ ይጀምራል።
ራሱን ከሰው አሳንሶ የሚያስብ ካልሆነ በስተቀር የሰው ህይወትን ቀብድ አስይዞ የሚደራደር የለም። ዛሬ እየሆነ ያለው ደግሞ ይኸው ነው። በሰው ህይወት ስልጣንን ለማስጠበቅ ይሰራል፤ በሰው ህይወት ለመደበቅ ይሞከራል፤ በሰው ህይወት ላለመጠየቅ ይታተራል፤ በሰው ህይወት አንተ ብቻነህ ፈዋሼ ለመባል ደፋ ቀና ይባላል። ሰው የሚያስብለው ታዲያ የትኛው ነው? መልሱ ግልጽ ነው። ይህንን የሚያደርጉ አካላት ሰው ለመሆን ብዙ የሚጎላቸው ይመስለኛል። ሰው ያልሆነ ሰው ደግሞ ስለአገር ቀርቶ ስለ ራሱ ማሰብ አይችልም። ምክንያቱም ሰው ከእንስሳ የሚለየው በማሰቡ እንደሆነ እሙን ነው። እናም እነዚህ ሰዎች ብዙ ያልተረዱትና የማያገናዝቡት ነገር አለ ብዬ አምናለሁ። ፖለቲካ ያለ አገር ምንም እንደሆነ አያውቁም። ግን ፖለቲከኛ ነኝ ይላሉ። ጥቅምም ቢሆን ያለ አገር እንደማይከበር አይረዱም። ምክንያቱም አገር ሰው እንደሆነ አያውቁም።
ማወቅ እና መማርም አገር ሲኖር የሚመጣ እንደሆነ አልተረዱም። ምክንያቱም ተምረው ሳይሆን የሰው ስቃይ ላይ ተንተርሰው ያለፉ ናቸውና። ስለዚህም እነርሱ መንታ ምላሶች ናቸው። ከአንደበት የሚወጣው ልብን ያቀልጣል። ውስጣቸው ግን ለራሳቸው የኖረ፣ የሞተም ነው። አገርን ከመቼውም በላይ እንታደጋት፤ እንትናን አስወጥተን እንትናን ካስገባን አገር ትረጋጋለች የሁልጊዜ መፈክራቸው ነው። እኛ ብንሆን ኖሮ ይኸኔዬ ጸጥ ረጭ እናደርገው ነበርም መለያቸው ነው። ታዲያ አገር ከተፈለገ ለምን ሰላማችንን አይሰጡንም፤ ለምን እንዲያረጋጋ መንግስትን ብቻ ይከሱታል፤ እነርሱው ፈጣሪ እነርሱም አዳኝ መሆን ከቻሉ ለምን ጸጥ ረጭ አድርገው መፍትሄ አምጪ አይሆኑም ? ምክንያቱም እነርሱ ይህንን አይፈልጉም። የእነርሱ አላማ በማበጣበጥ መክበር ብቻ ነው ።
እነርሱ የተዘራ ስንዴ ላይ እንክርዳድ ይዘራሉ፤ የቀናውና መስዋትነት የተከፈለበት ላይ ጠማማ እንጨታቸውን ይተክላሉ። ለእነርሱ ክብራቸው ጥቅማቸው እንጂ አገራቸው መቼም አይሆንም። እኛ ብንሆን እንሰራው ነበር ብለው የማይሰሩትና ያልሰሩት ሲሰራ የሚተቹ፤ ከጠላት ጋር የሚያብሩ ናቸው። እናም እነርሱን ማሳፈር የሚቻለው የማይሠሩትን ትቶ ከሚሠሩት ጋር ብቻ ለመተባባር፤ ስለ ጠላት ከማሰብ ስለ ወገን ብርታትና ጥንካሬ ማሰብን ማስቀደም ሲቻል ብቻ ነውና ይህንን ማድረግ ከምንም በላይ ያስፈልጋል።
ከጉዳያችን ጋር በተያያዘ መውአዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት የጻፈውን የኢትዮጵያዊያን አይነትን ላንሳ። ከእነርሱ ጋር የሚመሳሰሉትንም ጭምር በደንብ ያብራራልናል። በአሁኑ ጊዜ አራት ዓይነት ኢትዮጵያውያን አሉ ይላል። እነርሱም ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ፤ ኢትዮጵያም በእነርሱ ውስጥ ያለች፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ፣ ኢትዮጵያ ግን በእነርሱ ውስጥ የሌለች፤ ከኢትዮጵያ የወጡ፣ ኢትዮጵያ ግን ከእነርሱ ልብ ያልወጣችና ከኢትዮጵያ የወጡ፤ ኢትዮጵያም ከእነርሱ ልብ የወጣች ናቸው። በባህሪያቸውም የመጀመሪያው ልባቸው ውስጥ ያለችው ኢትዮጵያ ልዩ ናት። በሀገራቸው ውስጥ ሆነው፣ ችግሯን እና መከራዋን ሁሉ አብረው ተቀብለው፤ ቢያዝኑም ሳይማረሩባት የሚኖሩ ናቸው።
በቀበሌው፣ በአስተዳደሩ፣ በአመራሩ፣ በአሠራሩ፣ በኢኮኖሚው፣ በኋላ ቀርነቱ ወዘተ ምክንያት እርሷን አይለኳትም። በዓይናቸው የሚያዩትን ገጽታ በውስጣቸው ያለችውን ኢትዮጵያ ገጽታ የማይቀይርባቸውም ናቸው። ምክንያቱም የእነርሱ ኢትዮጵያ ታላቅ ናት፤ ኩሩ ናት፤ ጀግና ናት፤ ነጻና ውብ ናት። ሥልጡን ናት። ሲሠሩ፣ ሲደክሙ፣ ሲያለሙ፣ ሲሠው፣ ሲከፍሉ፣ በልባቸው ላለችው ኢትዮጵያ ነው። በሚያዩዋት ኢትዮጵያ እንጂ በልባቸው ባለችው ኢትዮጵያ አይማረሩም።
ሁለተኛዎቹ ደግሞ ከዚህ በተቃራኒ የሚቀመጡ ናቸው። በኢትዮጵያ ውስጥ አሉ። አንዳችም የኢትዮጵያ ጠባይ፣ ባህል፣ ፍቅር፣ ክብር፣ አመል፣ ስሜት፣ ወኔ፣ ቅንዐት በልባቸው ውስጥ የለም። ለእነርሱ ኢትዮጵያ መልክዓ ምድር ብቻ ናት። ቦታ ብቻ ናት። ኢትዮጵያ ብትወድቅ ብትነሣ፣ ብትሞት ብትድን፤ ቢያልፍላት ባያልፍላት፣ ብታድግ ብትደኸይ አይገዳቸውም። ሊጠቅሟት ሳይሆን ሊጠቀሙባት ብቻ ይፈልጓታል። ስለ እነርሱ እንድትኖር እንጂ ስለ እርሷ እንዲኖሩ አይፈልጉም። ለእርሷ አይሠውም፤ ለእነርሱ ግን ይሠዋታል።
ሦስተኞቹ ደግሞ ከመጀመሪያው ጋር ተቀራራቢነት ያላቸው ናቸው። ወደውም ሆነ ሳይወዱ ከሀገር የወጡ ናቸው። በአካል ከሀገር ርቀዋል። በልባቸው ግን ኢትዮጵያን ፀንሰዋል። ደማቸው፣ ጠባያቸው፣ እምነታቸው፣ አመላቸው፣ ባህላቸው፣ ስሜታቸው ኢትዮጵያ ውስጥ ነው። ስሟን ሲሰሙ አንዳች ነገር እንደ ኤሌክትሪክ ይነዝራቸዋል። ልጆቻቸውን፣ ቤታቸውን፣ አቆጣጠራቸውን፣ ሃሳባቸውን፣ ምኞታቸውን፣ ጸሎታቸውን ሁሉ ኢትዮጵያዊኛ አድርገውታል። ለእነርሱ የጊዜ ጉዳይ ነው። አንድ ቀን ነፍሳቸውም ሥጋቸውም እዚያው ኢትዮጵያ እንደሚሆን ያምናሉ። ቢሞቱ እንኳን ሥጋቸው እንዲመለስ ይፈልጋሉ።
የመጨረሻው ከሁለተኛው ጋር የሚቀራረብ ነው። ባህሪያቸው ዝምድናን ይሰጣቸዋል። ውጪና ውስጥ የሚለው ነው የሚለያቸው። ኑሯቸው በውጪ ስለሆነ ኢትዮጵያም ከእነርሱ ወጥታለች። ምናልባትም መልካቸው ብቻ ካልሆነ በቀር አንዳችም ከሀገራቸው ጋር የሚያመሳስላቸው ነገር ላይኖር ይችላል። ለእነርሱ ኢትዮጵያ በምሥራቅ አፍሪካ የምትገኝ አንዲት ሀገር ብቻ ናት። ብትኖርም ሆነ ብትሞት ስሜት አይሰጣቸውም። አይኖሩባትም፤ አትኖርባቸውም።
«ብረሳሽ ቀኜ ትርሳኝ፣ ባላስብሽ ምላሴ ከትናጋዬ ትጣበቅ» የሚል ምሕላ የላቸውም። ኢትዮጵያን ከልባቸው ማውጣት ብቻ ሳይሆን ከልጆቻቸው ልብ እንዳትገባ ሆኑ ይጥራሉ። በዓለም ባሉ ቋንቋዎች ሁሉ እንዲናገሩ ሲያግዟቸው ኢትዮጵያ ውስጥ የሚነገር ቋንቋን አንዱንም እንዲናገሩ አይፈልጉም። እንደውም አልፈው ተርፈው አንተ ኢትዮጵያዊ አይደለህ ተብለው ቢጠየቁ በፍጹም በለው የሚሸመጥጡ አይነት ሰዎች ናቸው።
ታዲያ ለኢትዮጵያ የትኛው ይበጃል፤ ምን ይደረግ ከተባለ ሁለት መንገዶችን መከተል ይገባል ባይ ነኝ። የመጀመሪያው አንድና ሦስተኛ ላይ የተቀመጡትን ኢትዮጵያዊያንን ማብዛት ሲሆን፤ ለዚህ ደግሞ ከትምህርትና ከሥራ የጀመረ ተግባር ያስፈልጋል። ልጅን በዚህ ባህሪ እየኮተኮቱ ማሳደግም ይገባል። ሌላው ደግሞ አስመሳዮችን መለየትና ወደ እውነታው የሚያመጡ መድረኮችን መፍጠር ይገባል። የተሻለ ማምጣት የሚቻለው የተሻለ መሆንን የሚፈልግ ሲኖር ነውና አገራዊ አገልግሎቶችን በመፍጠር የውዴታ ግዴታ ሥርዓትን መዘርጋት ተገቢ ነው። ምክንያቱም አገራዊ ፍቅርን ለማምጣት ለአገር መስራትን ማለማመድ ይገባልና።
በአሁኑ ወቅት በአገር ጉዳይ የሚደራደሩ ክፉዎች ኃይል አግኝተው ቅኖች የተሸነፉ ይመስለናል። ወንጀለኞች ደስታ ተጎናጽፈው ንጹሐን እያለቁ እንደሆነም ይሰማናል። ግን ጥቃቅን ብርቱ ድምጾች መኖራቸውን ማየት ይገባናል። ሁሉም የዋጠውን ጨለማ ማየት ብቻ ላይ ማተኮር የለበትም። በዚያ ውስጥ ብርሃን አሳልፎ ማየትና ያንን ብርሀን ማጎላት ይገበዋል እንጂ። ምክንያቱም የማያልፍ ቀን የለም። ሰኞ ብሎ እሁድ መሆኑ እንደማይቀር ሁሉ አንድ ቀን ይነጋል። የኢትዮጵያም ትንሣኤ ይኖራል። እናም ያንን እየሻቱ መስራት ጠላትን ማሳደድና ተደራዳሪዎችን ማሳፈር ይገባል። ነገ የትንሳኤ ቀን እንደሚሆን ለትውልዱ መንገርና ከጨለማው ሳይሆን ከብርሀኑ እንዲቋደስ ማስተማርም ያስፈልጋል። ኢትዮጵያን በብርሃን የምናይበት ቀንን፤ በአገር የሚደራደሩ የሚያፍሩበትንና ከስህተታቸው የሚመለሱበትን ቀንን አምላክ ይስጠን። ሰላም!
አዲስ ዘመን መጋቢት 25 ቀን 2013 ዓ.ም