በቁምላቸው አበበ ይማም(ሞሼ ዳያን)
fenote1971@gmail.com
በዚች ምድር ላይ እንደ ከሀዲውና እፉኝቱ ትህነግና ገዢው ቡድን እጅግ ሚስጥራዊ የሆነ ድርጅትና ስብስብ የለም ። አቅጣጫውን የሳተ “ጥንካሬው”ና “ስኬቱ” የተመዘገበው በርዕዮት አለም ጥራትና መርህ ሳይሆን በሚስጥር በጨለማ በሚፈጽመው ደባና ሴራ ነው ። በለውጡ ማግስት ጨርቄን ማቄን ሳይል ዳና ሳያሰማ መማጸኛ ከተማው የመሸገው ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓም የፈጸመውን ትውልድና ታሪክ ይቅር የማይለውን ክህደት በሰሜን ዕዝና በሀገር ላይ ለመፈጸም ነበር ።
በትጥቅ ትግሉ 17 አመታትም ሆነ አገዛዝ ላይ በነበረባቸው 30 አመታት ሚስጥራዊ ደባውንና ሴራውን እያፈራረቀ ተጠቅሞባቸዋል። የገዛ ሀገሩንና ሕዝቡን በድቅድቅ ጨለማ በአደናጋሪ ማንነት እንደ ትህነግ የገዛ ድርጅት እግር እስኪቀጥን ቢፈለግ አይገኝም። ስለድርጅቱም ሆነ ገዥ ቡድኑ እውነተኛ ማንነት አይደለም ሕዝቡ የራሱ ከፍተኛ ካድሬም ምንም እውቀት የላቸውም። በልበ ሙሉነትና በእርግጠኝንት ስለ ገዥው ቡድን ማንነትና ምንነት አፉን ሞልቶ የሚናገር የለም።
ስለድርጅቱ የተጻፉ በጣት የሚቆጠሩ መጽሐፍትም የሚስጥራዊነት ትብታቡን ማፍታታት ያልቻሉ ናቸው። ሚስጥር ላለማውጣት የተማማሉና ቃል ኪዳን የገቡ ነው የሚመስለው። ከድርጅቱ የተባረሩም ሆነ የተሰናበቱ መስራች አባላት ሳይቀሩ ይህን መሀላ ጠብቀው ኖረዋል። የአንዳንዶቹ ሚስጥር ደግሞ እንደ መቃብር የተዘጋበት ነው። ስለሞትና ስቃይ መልዓኩ ጌታቸው አሰፋ ማንነትና ምንነት ከተባራሪ ወሬና ፎቶ በስተቀር ይህ ነው የሚባል የሚጨበጥ መረጃም ሆነ ማስረጃ የለም ። ስለ የቀድሞ የመረጃና ደኅንነት አገልግሎት ኃላፊ የሞት መልዓኩ ጌታቸው አሰፋ የሚታወቀው ነገር እጅግ በጣም ጥቂት ቢሆንም እውነት ስለመሆኑ ምንም አይነት ማረጋገጫ የለም። ስለሱ የወጡ በጣት የሚቆጠሩ ፎቶዎች ሳይቀሩ እርስ በርስ የተለያዩና የሚያምታቱ ናቸው። ከሰሞኑን ስለመሞቱ የወጣውን መረጃ አምኖ ለመቀበል የሚያስቸግረው ከዚህ የግርታ ማዕቀፍ የተነሳ ነው። በዚህ ድንግዝግዝና ተሁኖም ዘመንፈሱ ጌታቸው አሰፋ ማን ነው!? ስል እጠይቃለሁ ። መልስ ፍለጋ ስጎለጉል ከቢቢሲና ከኢትዮ ቲንክ ታንክ የቀራረምሁትን እነሆ ፦
ጌታቸው አሰፋ በ1940ዎቹ መጨረሻ ላይ በመቐለ ከተማ፤ ቀበሌ 14 በተለምዶ ‘እንዳ አቦይ ፍቐዱ’ የሚባል ሰፈር ነው የተወለደው ። እስከ 8ኛ ክፍል እዚያው መቐለ ከተማረ በኋላ 9ኛ ክፍልን ለመቀጠል ወደ አዲስ አበባ መጣ። የ፪ኛ ደረጃ ትምህርቱን በዊንጌት ትምህርት ቤት መከታተል ቢጀምርም በማቋረጥ 1969 ዓ.ም ላይ የትጥቅ ትግሉን ተቀላቀለ። ወዲያው በመንግሥት ላይ ድንገተኛ ጥቃቶችን የሚሰነዝር ቡድንን ተቀላቀለ። በትጥቅ ትግል ላይ በነበረበት ወቅት በአልታዘዝም ባይነትና ግትርነቱ የተነሳ ሶስት ጊዜ ከደረጃው ዝቅ ተደርጎ እንዲሰራ ተደርጓል። ይሁንና 1980ዎቹ መጀመሪያ ላይ የህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል ሆኖ እስከመመረጥ ደርሶ ነበር።
የደርግ መንግሥት ከተገረሰሰ በኋላ ደግሞ በ1983 ዓ.ም በአገር መከላከያ ኃይል ውስጥ የኦፕሬሽን ኃላፊ ሆኖም ተሹሞ ነበር። ከአምስት ዓመታት በኋላ ደግሞ የፌደራል ፖሊስ ምክትል ኮሚሽነር ሆኖ “አገልግሏል”። በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ወቅት ለወቅቱ ጠቅላይ ሚኔስትር መለስ ዜናዊ ተጠሪ የነበረው የማእከላዊ ዕዝ አዛዥም ነበር።ግንቦት 1993 ዓ.ም ላይ የብሔራዊ መረጃ እና ደኅንነት ኃላፊ የነበረው አቶ ክንፈ ገብረመድህን መገደልን ተከትሎ የደኅንነት ቢሮ ኃላፊ ሆኖ ተሾመ።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ከገዥነት እንዲነሳ እስከተወሰነበት ዕለት ድረስ የደኅንነት መሥሪያ ቤቱን ለ17 ዓመታት ቀጥቅጦ ገዝቶታል። ያለ አዛዥ ያሻውን አድርጓል፤ ገድሏል። ገልብጦ ገርፏል፤ አካል አጉድሏል። ዘር እንዳይተኩ አድርጓል። ወንድ ልጅ ሳይቀር እንዲደፈር አድርጓል። ጥፍር ነቅሏል። በወንድ ልጅ ብልት የሁለትና የሶስት ሊትር የላስቲክ ውሀ አንጠልጥሏል። በደረሰባቸው ስቃይ ብዙዎቹ ለአእምሮ ህመም ተዳርገዋል። ሽባ ሆነዋል። እግራቸው ተቆርጧል። በማዕከላዊ፣ በቃሊቲ፣ በቅሊንጦ፣ በሸዋ ሮቢትና በሌሎች “ማረሚያ” ቤቶችና ስውር ማሰቃያ ቦታዎች ህልቆ መሳፍርት የሌለው ግፍ ፈጽሟል። አስፈጽሟል።
በእስክንድር ነጋ ፣ በአንዷለም አራጌ ፣ በሀብታሙ አያሌው ፣ በከፍያለው ፣ በዳባ ገሬ ፣ በወልቃይት ሕዝብ፣ በዋልድባ አባቶች እና በሙስሊም ወንድሞቻችን ላይ ለመስማት የሚሰቀጥጥና ለማየት የሚዘገንን ግፍ ፈጽሟል። ከሁለት አመታት በፊት “የፍትሕ ሰቆቃ” በሚል በኢቲቪና በሌሎች ቴሌቪዥኖች የተላለፈው ዘጋቢ ፊልም፤ የጌታቸው ሽፈራው “የሰቆቃ ድምጾች”፤ የአንዳርጋቸው ጽጌ “የታፋኙ ማስታወሻ”፤ የአንዷለም አራጌ ፤ የሀብታሙ አያሌው ፤ ወዘተረፈ ግለ ማስታዎሻዎች ለዚህ እማኝ ናቸው። የሞት መልዓኩ ጌታቸው በጄኔራል አደም መሐመድ ከተተካ በኋላ የትህነግ ገዥ ስብስብ የትግራይ ክልላዊ መንግሥት የደኅንነት አማካሪ አድርጎ በመሾም ለኢትዮጵያ ሕዝብ ያለውን ንቀትና ጥላቻ አረጋገጠ። ምን ታመጣላችሁ በሚል እልህ፤ በወንጀል ተጠርጥሮ በሕግ የሚፈለገውን በላኤ ሰብ ይባስ ብሎ የህወሓት እና የኢህአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል አድርጎ መርጦት አረፈ።
ወላጅ አባቱ ሻለቃ አሰፋ በንጉሡ እና በደርግ ዘመን የትግራይ ክፍለ አገር የስለላና ምርመራ ፖሊስ ምክትል አዛዥ ነበሩ። ሻለቃ አሰፋ በደረግ አደረጃጀቶች ውስጥ በተፈጠረ አለመግባባት በመቀሌ ከተማ ውስጥ ተገድለዋል። የሞት መልዓኩ ጌታቸው የትግል አጋሮች እንደሚሉት ከሆነ በልጅነቱ ጠንካራ ተማሪ ነበር። የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን በማቋረጥ 1969 ላይ የትግራይ ሕዝብ ነፃ አውጪ ግንባር የትጥቅ ትግል ከተቀላቀለ በኋላ አፋር ክልል ውስጥ ካዳሓራ በተሰኘ ሥፍራ ነበር ወታደራዊ ስልጠና የወሰደው።1970 ዓ.ም ላይ ህወሓት ውስጥ የተከሰተው መከፋፈል “ሕንፍሽፍሽ” ተሳትፈሃል ተብሎ ለእስር ተዳርጎ እንደነበር በስም ያልተጠቀሱ የቢቢሲ አማርኛ ምንጮች ገልጸዋል። በምሕረት ከእስር የተለቀቀው ጌታቸው በተለያዩ አውደ ውጊያዎች ተሳትፏል። በትጥቅ ትግል ወቅት በብዛት ይሰጠው የነበረ ተልዕኮ መረጃ ማሰባሰብ፣ ማደራጀትና መተንተን እንደነበር ይነገራል ።
በተለያዩ ጊዜያት ከፓርቲው ለመገለል ቢቃረብም፤ በቅርብ ጓደኛው መለስ ዜናዊ አማካኝነት በትግሉ እንዲቀጥል ይደረግ ነበር። ዛሬ ላይ ሆነን ስናስበው መለስ ለምን ይከላከለው እንደነበር ይገባናል። ለምሳሌ እነ ዶክተር አረጋዊ በርሄ ከድርጅቱ ጋር የተቆራረጡበት የማርክሳዊ ሌኒናዊ ሊግ ትግራይ (ማሌሊት) ምስረታ መድረክ ላይ እሱም “አላመንኩበትም”ብሎ አቋም ይዞ እንደነበር ይነገራል። በመለስ አግባቢነት ግን በአባልነት ሊቀጥል ችሏል። ሆኖም የደኅንነት ቢሮ ኃላፊ ከሆነ በኋላ ወደ መጨረሻ አካባቢ መለስ ዜናዊ ጋር የነበረው መልካም ግንኙነት ባልታወቀ ምክንያት ሻክሮ እንደነበረ እነዚሁ የቢቢሲ ምንጮች ይናገራሉ ። ከመለስ ሞት በኋላም በትህነግ ግምገማዎች ላይ የድርጅቱ ከፍተኛ አመራሮች ላይ ጠንካራ አስተያየቶችን ይሰነዝር ነበር።
የድርጅቱ ስራ አስፈፃሚ ሆኖ በተመረጠበት 12ኛው የህወሓት ጉባኤ ላይ በድርጅቱ አመራር የሰፈነውን ሥርዓተ አልበኝነትና ሙስና ጠቅሶ አመራሩን በድፍረት ወርፏል ተብሎ ይነገርለታል። በለውጡ ዋዜማ ኢህአዴግ አካሄድኩ ባለው ‘’ጥልቅ ተሃድሶ’’ ላይ ከግንባሩ ከፍተኛ አመራሮች ጋር አለመግባባት ፈጥሮ ነበረ። አህያ ቢራገጥ ጥርስ አይሳበርም ሆኖ እንጅ እውነተኛ መተጋገልና መቆራረጥ ቢኖር ኖሩ ለ46 አመታት የጥፋት መንገድን ባልመረጠ። ተነግሮ የማያልቅ ግፍ በዜጎቹ ላይ ባልፈጸመ፤ መጨረሻውም ጥፋትና ቀውስ ባልሆነ። በየትኛው የቅስም ልዕልና ነው ጌታቸው የውንብድና አጋሮቹን ከፍ ዝቅ ያደርግ የነበረው።
የሰኔ 16ቱን የቦንብ ፍንዳታ በማስመልከት የቀድሞው የፌደራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ አቶ ብርሃኑ ጸጋዬ፤ ‘’ወንጀሉን በዋናነት የመሩትና በገንዘብ የደገፉት የብሔራዊ ደኅንነት እና መረጃ ኤጀንሲ የቀድሞው ኃላፊ /አቶ ጌታቸው አሰፋ/ ናቸው’’ ብለዋል። አቶ አብዲ ሞሃመድ /አብዳሌ/ የሶማሌ ክልል የቀድሞ ፕሬዚዳንት የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድን የመጀመሪያዎቹን 100 ቀናት አስመልክቶ ሐምሌ 5 ቀን 2010 በሰጠው መግለጫ ላይ ስለ አቶ ጌታቸው አሰፋ ሲናገር ‘’ጌታቸው ሙሰኛ ፣ ሌባ እና ራሰ ወዳድ ነው። አዲስ አበባ ላይ ተቀምጦ የክልል መስተዳድሮችን ይሾማል።’’ ሲል ስሞታ ቢያቀርብም ጉድና ጅራት ከኋላ ነው እንዲሉ አብዲሌ በክልሉ የፈጸመው ግፍ ከጌታቸው የሚተናነስ አንዳልነበረ ውሎ አድሮ መሰማቱ አልቀረም።
የቀድሞው የአሜሪካ የኮንግረስ አባል ማይክ ኮፍማን ለአሜሪካ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ማይክ ፖምፔዮ እና ለግምጃ ቤት ኃላፊው ስቲቭ ሙንችን ጥቅምት 13፣ ቀን 2010 ዓም በጻፉት ደብዳቤ፤”አቶ ጌታቸው አሰፋ በርካታ ነጹሐን እንዲገደሉ፣ እንዲጠለፉ፣ እንዲሰቃዩ፣ እንዲጉላሉ፣ እንዲታሰሩ እና ከአገር ተሰደው እንዲሄዱ አድርጓል። በየትኛውም መስፈርት አቶ ጌታቸው ወንጀለኛ እና የሰብዓዊ መብት ጣሽ ነው’’፤ ማለታቸውን እናገኛለን። በአንድ ራስ ሁለት ምላስ እንዲሉ ይቺ አሜሪካ ናት በሱዛን ራይስ እየተመራች የትህነግን መቃብር ድንጋይ በማንከባለል እንደ አላዛር መሲህ ሆና ልታስነሳው ከንቱ ሙከራ እያደረገች ያለው።
በላኤ ኢትዮጵያው ጌታቸው ከኢትዮጵያ አልፎ የቀጠናውን ጂኦ ፓለቲካ እስከ መበየን የሚያደርስ ተጽዕኖ እንደነበረው የጁሊያን አሳጁ ዊኪሊክስ አደባባይ በሰጠው መረጃ በግልጽ ሰፍሮ ይገኛል። ‘’ የኤርትራ መንግሥት በተባበሩት መንግሥታት የጸጥታው ምክር ቤት የተጣለበትን ማዕቀብ ተከትሎ፤ የኢትዮጵያ እና ሱዳን አዋሳኝ ድንበርን የአሸባሪዎች መፈንጫ ለማድረግ እየጣረ ነው።’’ ብሎ ማዋሸኩን ታህሳስ 2002 ዓ.ም ላይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ድረ-ገጽ ጠቅሶት ነበር። ጌታቸው የዋዛ ሰው አይደለም ። በወርሃ ሰኔ አዲስ አበባ ላይ ከአሜሪካው ልዩ መልእክተኛ ዶናልድ ያማማቶ ጋር ፊት ለፊት ተገናኝቶ በተወያየበት ‘’እንደ ኦሮሞ ነጻነት ግንባር እና የኦጋዴን ብሔራዊ ነጻነት ግንባር የመሰሉ ሰርጎ ገብ አማጺያን ዙሪያ አሜሪካ ያላትን አቋም ኢትዮጵያ ማወቅ ትሻለች’’ እስከማለት ደርሶ ነበር። እንዲሁም ሰኔ 1 ቀን 2001 ዓ.ም በወቅቱ በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ከነበሩት ኢረቭ ሂክስ ጋር ለአራት ሰዓታት የቆየ ውይይት አድርጎ ነበር። “የኦነግ እና ኦብነግ እንቅስቃሴ ለኢትዮጵያ ውስጣዊ ደኅንነት አስጊ ስለመሆኑ ፤ የአሜሪካ ድምጽ ሬዲዮ ሚዛናዊ ያልሆነ ዘገባ፤ የቀድሞ የህወሓት አባል እና የመከላከያ ሚኒስትር የነበረው ስዬ አብረሃ በተቃዋሚነታቸው ውስጥ ተጽእኖ ፈጣሪነታቸው እየጨመረ መምጣቱ እንዳሳሰበው ሹክ ማለቱን ዊክሊክስ ዘርግፎታል። ምርጫ 97ን ተከትሎ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ሆነው ተመርጠው የነበሩትን ዶክተር ብርሃኑ ነጋ ‘’ጽንፈኛ’’ ብሎ ማሳጣቱን ይኸው መረጃ አመልክቷል።
ኢትዮጵያ ከአሜሪካ ጋር ያላት ግንኙነትም እንደማይዋጥለት ይሄው አፈትላኪ መረጃ ያስታውሳል። ይሁንና ጥቅምት 26 ፣ ቀን 2002 ዓም ጌታቸው አሰፋን የያዘ በወቅቱ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር በነበረው ስዩም መስፍን የሚመራ የልዑክ ቡድን ወደ አሜሪካ አቅንቶ ከውጪ ጉዳይ ሚኒስትሯ ሂላሪ ክሊንተን ጋር ተወያይቶ ነበር። የጸጥታ ትብብር፣ ዲሞክራሲያዊ አስተዳደር እና የኢኮኖሚ ማሻሻያ ጉዳዮች ለውይይት ቀርበው የነበረ ሲሆን፤ ሂላሪ ክሊንተን የአፍሪካ ቀንድ አለመረጋጋት ለኢትዮጵያ ሌላ ጫና እንደሆነ በመጥቀስ በሁለቱ አገራት መካከል ያለውን የጸጥታ ትብብር ማድነቋን ይኸው የዊኪሊክስ መረጃ ያትታል። ሂላሪ ክሊንተን ወደ ዋሽንግተን ዲሲ ላቀናው የኢትዮጵያ ልዑክ፤ የኢትዮጵያ መንግሥት ለሶማሊያ ጸጥታ አስከባሪ ኃይሎች ስልጠናዎችን እንዲሰጥ እና ለሶማሊያ የሽግግር መንግሥት የማይቋረጥ ድጋፍ እንድትሰጥ ማሳሰቧንም ያስታውሳል።
እንደ እልባት
ሰልጣን ላይ ያለው ዴሞክራቱ የባይደን አስተዳደር በተለይ ሱዛን ራይስና የእሷ ደቀመዝሙር የሆነው የውጭ ጉዳይ ሚንስትሩ አንተኒ ብሊከን የከሀዲው ትህነግ አገዛዝ መወገድ እንደ እግር እሳት የሚለበልባቸው የቀጣናውን ተላላኪያቸውን ባልጠበቁት ሁኔታ ማጣታቸው ነው ።
በትግራይ ክልል ያለከልካይ እንደልባችን ገብተን እንውጣ ሲሉ ደጋግመው የሚያላዝኑት ለሰብዓዊ እርዳታና ለዜጎች ደህንነት ተጨንቀው እንዳልሆነ ተፈቅዶላቸው ከገቡ በኋላ ያደረጉትን አይተናል። ዛሬም 70 በመቶ የሚሆነውን የዕለት ደራሽ እርዳታ ከ4 ነጥብ 2 ሚሊዮን ለሚሆነው ሕዝብ በሌለ አቅሙ እርዳታ እያቀረበ ያለው የኢፌዲሪ መንግስት ነው ። አሜሪካንን ጨምሮ ሌሎች ለጋሾች እያቀረቡት ያለው ከሲሶ በታች ነው ። ያለ ገደብ መንቀሳቀሱን የፈለጉት ከአንድ ሁለት አመራሮቹ ጋር በየሸለቆውና በየዋሻው የተበተነውን ትህነግ መልሶ ለማደራጀት አልያም እነ ጌታቸውን ለማስመለጥ እንዳይሆን ጥብቅ ጥንቃቄ ማድረግ ያሻል። የጌታቸው አሰፋ መሞትም በዲኤንኤ ወይም በፎረንዚክ ተረጋግጦ ለሕዝብ ይፋ ሊሆን ይገባል። ካልሞተም መንግስት ከክትትል እንዳይዘናጋ ያነቃዋል። እንዳየነው ጌታቸው በስማ በለው ሞቱን ሰምተን ብቻ እጃችንን አጣጥፈን የምንቀመጥለት ተራ ሰው አይደለም።
ሀገራችን ኢትዮጵያ በጀግኖችና ሀቀኛ ልጆቿ ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትኑር !!!
አሜን።
አዲስ ዘመን መጋቢት 25 ቀን 2013 ዓ.ም