አስቴር ኤልያስ
የሲዳማ ሕዝብ ራሱን በራሱ ለማስተዳደር ሲል ያልተቋረጠ ትግል ከማድረጉም በላይ ለዚህ ትግል ስኬት ሲሉ ሲባልም ብዙዎች የሕይወት መስዋዕትነት መክፈላቸው ይታወቃል። ትግሉ አንዴ በረድ ሌላ ጊዜ ደግሞ ጋል እያለ ሲጓዝ የነበረ ቢሆንም፤ በእነዚህ ሁሉ እንቅስቃሴዎቹ የሲዳማ ሕዝብ አንግቦ የተነሳውን የመብት ጥያቄ በጊዜው የነበሩ አመራሮች ጆሮ ሊሰጡት አልወደዱም።
ይሁንና ሕዝቡ ጥያቄው ምላሽ እንዲያገኝ የከፈለውን መስዋዕትነት በተረዳው የአገራዊ ለውጡ መንግሥት አመራር ሰጪነት የዘመናት ቋጠሮው ተፈትቶ ዛሬ ለውጡን እያጣጣመ ይገኛል።
የአገራዊ ለውጡን ሦስተኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ በአዲሱና አስረኛው የሲዳማ ክልል ውስጥ እየተደረገ ስላለው እንቅስቃሴና እያጋጠመ ስላለው ተግዳሮት መረጃ እንዲሰጡን ከሲዳማ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር እና ከክልሉ የትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ በየነ በራሳ ጋር አዲስ ዘመን ጋዜጣ ያደረገውን ቆይታ እንደሚከተለው አሰናድተነዋል።
አዲስ ዘመን፡- ከአገራዊ ለውጡ ሦስት ዓመት በኋላ በሲዳማ ክልል የታየው ለውጥ እንዴት ይገለጻል?
አቶ በየነ፡- ከሦስት ዓመት በፊትና ከሦስት ዓመት ወዲህ በምንመለከትበት ጊዜ እንደ ሲዳማ ክልል ትልቁ ጥያቄ የዴሞክራሲ ነው። ይህ ራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄ የሆነው የዴሞክራሲ ጉዳይ የመጀመሪያውን ቦታ የሚይዝ ይሆናል። በመሆኑም ለእዚህ ምላሽ ለማግኘት ሲል የሲዳማ ሕዝብ ራሱን በራሱ ለማስተዳደር ለዘመናት ከፍተኛ ትግል አካሂዷል።
እንግዲህ አንዱና ትልቁ በለውጡ የተገኘው ውጤት ይኸው ራስን በራስ የማስተዳደር ጉዳይ ነው። በዚህም ለሲዳማ ሕዝብ ትልቁ የፖለቲካ ጥያቄ የተመለሰበት ጊዜ በመሆኑ እና በአገር ደረጃም 10ኛው ብሔራዊ ክልል ሆኖ መደራጀት የቻለበት ወቅት ስለሆነ ለሲዳማ ሕዝብ ለውጡ ትልቅ ቦታ የሚሰጠውና ትልቅ ጥያቄው የተመለሰበት ሂደት ነውና በእጅጉ ደስተኛ ያደረገን ወቅት ነው።
ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ ሌሎች የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችም አሉ። ከዚያን ወዲህ እነዚህን ጥያቄዎች ለመመለስ የለውጡ መንግሥት የተለያዩ ሥራዎችን እየሰራ ይገኛል። ኅብረተሰቡን ተጠቃሚ ሊያደርጉ የሚችሉ የልማት ሥራዎች በስፋት ተሰርተዋል።
በኢኮኖሚው ዘርፍም የተለያዩ የመሠረተ ልማት ዝርጋታዎች ተጀምረዋል። ለመጀመር የታሰቡም አሉ። ለምሳሌ ከመሠረተ ልማት አንፃር ሲዳማ ውስጥ ውስን የአስፓልት መንገድ ነበር የነበረው፤ በአሁኑ ጊዜ የተለያዩ መንገዶችን በአስፓልት ለመገንባት የመሠረት ድንጋይ ተጥሎ ጨረታዎች ወጥተው ወደ ግንባታ ሂደት ውስጥ እየተገባ ያለበት ሁኔታ አለ።
ሌላው ደግሞ ትልቅ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴን ሊያፋጥንና የሥራ አጦችን ቁጥር ሊቀንስ የሚችል የኢንዱስትሪ ፓርክ ግንባታ ተካሂዶ በዚህ ዓመት ተመርቆ ወደ ሥራ ተገብቷል። እሱም የቅርብ ጊዜ ሂደት ነው።
የማህበራዊውን ዘርፍ በምንመለከትበት ጊዜ የትምህርት ሥራዎች አዲሱን ፍኖተ ካርታና እሱን ተከትሎ የመጡ የትምህርት ሥራዎችን በአዲስ መልክ ለማከናወን የተያዙ የተለያዩ እንቅስቃሴዎች እየተፈፀሙ ይገኛሉ። ይህን ተከትሎ የተለያዩ ትምህርት ቤቶችን በፌዴራል ደረጃም በክልል ደረጃም የማስፋፋት ሥራዎች እየተከናወኑ ናቸው። ይህ ብቻ ሳይሆን የትምህርት ጥራቱን በጠበቀ ሁኔታ ሕፃናትን ተጠቃሚ ሊያደርጉ የሚችሉ የትምህርት እንቅስቃሴዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ። በጤናው ዘርፍም የተለያዩ ሥራዎች እየተሰሩ ናቸው።
በአጠቃላይ እንደ ሲዳማ ክልል የሕዝቡን የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን ለመመለስ እጅግ ከፍተኛ ሥራዎች እየተሰሩ ይገኛል።
አዲስ ዘመን፡- ያነሷቸው ነጥቦች ለውጡ ያስገኛ ቸው ሊሆኑ ይችላሉ፤ ተግዳሮቶች አጋጥ መው ከሆነና እንዴትስ መፍትሄ ሊያገኙ እንደቻሉ አያይዘው ቢገልፁልን?
አቶ በየነ፡- በርግጥ አንድ ሥራ በሚሰራበት ወቅት ተግዳሮቶች መቼም ቢሆን ይኖራሉ። የሕዝቡ የልማትና
የመልካም አስተዳደር ፍላጎት እጅግ ከፍተኛ ነው። የምንወስደው ሕዝቡ ይጠይቃል። ይህን ለመመለስ አንዱና ትልቁ ተግዳሮት የጠየቀውን በሙሉ ለመመለስ አስቸጋሪ ሆኖ መገኘቱ ነው። በክልሉ በኩል የሀብት ውስንነት ጉዳይ ይኖራል፤ በአንድ ጊዜ ጥያቄዎችን ሙሉ በሙሉ መመለስ የማይቻልባቸው ሁኔታዎች ይኖራሉ። አንዳንዴ ኅብረተሰቡ የሚያቀርባቸው ጥያቄዎች ብዙ ሀብትን የሚፈልጉ ሊሆኑ ስለሚችሉ በአንድ ጊዜ ሁሉንም የልማት ጥያቄዎች መመለስ የሚቻልበት ዕድል የለም፤ ይህን እንደ ትልቅ ተግዳሮት እናየዋለን።
ሌላው ደግሞ ትልቁ ተግዳሮት ከኮቪድ ጋር ተያይዞ ያለው ነው። ኮቪድ እንግዲህ በብዙ ነገሮቻችን ላይ ጫና እያሳደረ ነው። ነገር ግን ወረርሽኙን እየተጠነቀቅን እና እየተከላከልን የመልካም አስተተዳደር ሥራዎችን፣ የልማት ሥራዎችን በኢኮኖሚውም በማህበራዊውም ዘርፍ እንቅስቃሴዎች ሳይቋረጡ እንዲቀጥሉ ለማድረግ ትግል እያደረግን እንገኛለን።
አዲስ ዘመን፡– ክልሉ የህዳሴ ግድቡን ግንባታ ከመደገፍ አንፃር እያደረገ ያለው እንቅስቃሴስ ምን ይመስላል?
አቶ በየነ፡– ክልሉ የህዳሴ ግድብ ግንባታ የተጀመረበትን 10ኛ ዓመት ከማክበር ጋር ተያይዞ የራሱን ክልላዊ እቅድ አውጥቶ እንቅስቃሴ እያደረገ ነው፤ ይህንን ሥራ የሚመራ በክልል ደረጃ የተዋቀረ ኮሚቴ አለ። ኮሚቴው ተሰብስቦ በዚህ ዓመት ከዚህ ጋር ተያይዞ የሚሰሩ ሥራዎችን ለይቶ እቅዱንም አቅርቧል። ይህም ሥራ በአስተባባሪ ኮሚቴ እየተመራ ነው።
ይህንን ሥራ የሚመራ ምክር ቤትም አለ። ምክር ቤቱም በእቅዱ ላይ ውይይት አድርጓል፤ ለአስር ተከታታይ ቀናት የሚቆይ የቦንድ ግዢ ሳምንት የታወጀ ቢሆንም፣ እቅዳችን በተለያዩ ተደራራቢ ጉዳዮች ምክንያት በታቀደው ጊዜ ማካሄድ አልቻልንም። ነገር ግን ከዚያ በኋላ የቦንድ ሳምንት አጠቃላይ በክልሉ ታውጆ ይህን የሚያስፈፅሙ በየወረዳው ያሉ አስተባባሪ ኮሚቴዎችን ጠርተን ውይይት አድርገን በእቅዱ ዙሪያ በዚህ ዓመት በምንሰበስበው ግብ ላይም መስማማት ላይ ደርሰናል።
የቦንድ ግዢ ሥራው ወረዳዎችን ጨምሮ በሁሉም የሲዳማ ክልል መዋቅሮች እየተካሄደ ነው። ሀዋሳን እንደ ምሳሌ ብንወስድ ሰሞኑን ለአንድ ቀን ከስምንት ሰዓት ጀምሮ የቦንድ ግዢ ተካሂዷል። በክልል መዋቅሮች ውስጥ ያሉ የመንግሥት ሠራተኞችም፤ አመራሩም በአጠቃላይ ቦንድ የሚገዛበትን ጊዜ ወስነናል።
ያ ሁሉ ተከናውኖ ደግሞ በምን መልኩ ነው ለማጠቃለል ያሰብነው ሲባል በከተሞች፣ በወረዳ አስተዳደሮች የተሰበሰበው ሁሉ ተሰብስቦ የተወሰነ ደረጃ በሚደርስበት ጊዜ የማጠቃለያ መድረክ በክልል ደረጃ ለማካሄድ ዝግጅት እያደረግን ነው። ይህንንም የህዳሴ ግድቡ ግንባታ የተጀመረበትን 10ኛ ዓመት ስናከብር የማጠቃለያውንም መድረክ በዚያ መልኩ አያይዘን ለማካሄድ ነው እንቅስቃሴ እያደረግን ያለነው።
አዲስ ዘመን፡– እንደ ክልል ምን ያህል ነው ለመሰብሰብ የታቀደው?
አቶ በየነ፡– በዚህ ዓመት እንደ ክልል 200 ሚሊዮን ብር ለመሰብሰብ ግብ ጥለን እየተንቀሳቀስን ነው። ከዚህም እናልፋለን የሚል ግምቱ አለን፤ እስከ 275 ሚሊዮን ብር እንሰበስባለን ብለን ከፍተኛው ግብ ጥለናል። ከፍተኛውን ነው እናሳካለን ብለን የምናስበው፤ እሱ ካልተሳካ ግን 200 ሚሊዮን ማሳካት አለብን ብለን ግብ አስቀምጠናል።
አዲስ ዘመን፡– በግድቡ ላይ ግንዛቤ የመስጠቱ ነገር ምን ይመስላል? አሁን ግድቡ ከ79 በመቶ በላይ ስለመድረሱና ሕዝቡ በዚህም ተነቃቅቶ ከቀድሞ በተለየ መልኩ ተንቀሳቅሶ ቦንድ በመግዛት እንዲሳተፍ ለማድረግ ምን የማነቃቃት ሥራ እየተሰራ ይገኛል?
አቶ በየነ፡– የቦንድ ግዢው ሊፈፀም የሚችለው ሕዝቡ ግንዛቤው ሲኖረው መሆኑ ይታወቃል። ይህንን ከክልል ጀምሮ እስከ ታች ድረስ የንቅናቄ መድረኮችን እያካሄድን በንቅናቄ ነው ለማሳካት ጥረት እያደረግን ያለነው። ለእዚህም በአካባቢው ያሉ ሚዲያዎችን ተጠቅመን የቦንድ ሳምንቱ በክልል ደረጃ ታውጇል፤ እሱ ብቻ ሳይሆን በየወረዳው እና በየቀበሌው የንቅናቄ መድረኮች ይኖራሉ። በዚህ ሂደት ውስጥ ነው ይሄንን ግብ እናሳካለን ብለን የምናስበው።
ሕዝቡ ከዚህ አንፃር በጣም ደስተኛ ነው። የህዳሴ ግድቡ ግንባታ ወደ 79 በመቶ መድረሱ ራሱ በኅብረተሰቡ ውስጥ ትልቅ ተስፋን ማሳደር የቻለ አንደኛው ምክንያት ነው። ሕዝቡ በዚህ ደስተኛ ሆኖ በዚህ ሥራ ላይ ለመሳተፍ ዝግጅት እያደረገና እየተሳተፈም ጭምር ነው። ይህንን ለማሳካት ከክልል ጀምሮ በወረዳዎች ደረጃ እንዲሁም በቀበሌዎች ደረጃ የተለያዩ እንቅስቃሴዎች እየተደረጉ ናቸው፤ የንቅናቄ መድረኮች እየተከፈቱና በዚያውም የቦንድ ግዢው እየተፈፀመ ይገኛል።
ሌላኛው ወደዚህ እንቅስቃሴ ለመግባት ተስፋ ያሳደረው የመጀመሪያው ዙር የውሃ ሙሌት መከናወኑ ነው። ይህም ያደረግነው ተሳትፎ ውጤታማ መሆኑን ያመለክታል። ቀጥለንም ዋጋ ለመክፈል ዝግጁ ነን ወደሚል መደምደሚያ ያደረሰን ሁለተኛው ምክንያት ይሄው ነው። የዚህ ዓመቱ ውሃ ሙሌት በተያዘለት ጊዜ ይከናወናል ተብሎ የተሰጠው ተስፋም የሕዝቡ ተሳትፎ እንዲጎላና በከፍተኛ ሁኔታ እንዲሳተፍ እያደረገው ያለ ነገር ነው።
እናም የንቅናቄ መድረኮቹ እየተካሄዱ ያሉት ሀገራዊ ፋይዳውን እንዲሁም ከውስጥም ከውጭም ያሉ ተግዳሮቶችን በመግለፅ ነው።
ግድቡና ውሃ ከተሞላና በሙሉ አቅሙ ወደ ሥራ ከገባ በአገሪቷ ላይ የሚያመጣውን በተለይም በገጠሩ ሕዝብ ላይ የሚመጣውን የኢኮኖሚ ትሩፋት ከማፋጠን አንፃር የሚጫወተው ሚና ትልቅ ነው። እነዚህ ነገሮች ሁሉ እየተገለፁ ነው የንቅናቄ መድረኮች እየተደረጉ ያሉት። በክልል ደረጃ የንቅናቄ ማስጀመሪያ ያደረግነውም በዚህ መልኩ ነው፤ በክልል ምክር ቤት ደረጃ የክልል የንቅናቄ ማስጀመሪያ መድረክ ሲካሄድም በእነዚህ ጉዳዮች ላይ ተግባብተናል። በዚህ መልኩ እስከ ቀበሌ ድረስ እነዚህ መድረኮች በተሳካ ሁኔታ እንዲፈፀሙና በዚያውም በአስሩ ቀን ውስጥ የቦንድ ግዢው በተፋጠነ ሁኔታ ተከናውኖ የማጠቃለያ መድረክ በክልል ደረጃ ተደርጎ ለማጠናቀቅ ታስቧል።
ይጠናቀቃል ሲባል ግን የማጠቃለያ መድረኩ ላይ ብቻ የቦንድ ግዢው ይቆማል ማለት አይደለም። እሱ ቀጣይ ተግባር ነው። የምናጠቃልለው የአስሩን ቀን የቦንድ ሳምንት መድረክ እንጂ ኅብረተሰቡ የሚያደርገው ተሳትፎ እና አስተዋፅዖ አይቆምም፤ ግድቡ እስከሚያልቅ ድረስ ይቀጥላል።
አዲስ ዘመን፡– ክልሉ አዲስ ክልል እንደመሆኑ እያለፈባቸው ያሉ መንገዶች እንዴት ይገለጻሉ? ከጎረቤት ክልሎች ጋር ያለውስ መስተጋብር ምን ይመስላል?
አቶ በየነ፡– ክልሉ በአዲስ መልክ የተደራጀ እንደመሆኑ ብዙ ነገሮች ያስፈልጉታል። አስቀድሜ እንደጠቀስኩት፤ የሕዝቡ ፍላጎት በጣም ብዙ ነው። በእርግጥ ቶሎ መፍታት የሚቻለውን ቶሎ እየፈቱ፤ ቶሎ መፍታት የማይቻለውን ደግሞ ጊዜ እየወሰዱ በዚያ ሁኔታ እየመለሱ መሄድን ይጠይቃል።
በእርግጥ ሕዝቡ ይህንን ራስን በራስ የማስተዳደሩን ነገር በጣም የጓጓለት፤ በጣምም ለብዙ ዓመታት የጠበቀውና ከ130 ዓመት በላይ ብዙዎች የታገሉለት እንዲሁም የተዋደቁለት ጉዳይ ነው ምላሽ ያገኘውና ይህ ጉዳይ ምላሽ ሲያገኝ ሕዝቡ የሚጠብቃቸው ነገሮች አሉ። አንደኛውና ትልቁ የዴሞክራሲ ጥያቄው ተመልሶለታል። ከአሁን በኋላ ክልሉ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን ለመመለስ መስራት አለበት። ከዚህ አንፃር የክልሉ የ10 ዓመት መሪ እቅድ ታቅዶና ከዚያም ደግሞ የአምስት ዓመት እቅድ ታቅዶ ቆይቷል። ከአምስት ዓመቱ እቅድ ደግሞ የአንድ ዓመት እቅድ በዚህ ዓመት ምንድነው ማከናወን የምንችለው ብለን አቅደን በሁሉም ዘርፍ እንቅስቃሴ እያደረግን እንገኛለን።
ከሁሉም ክልሎች ጋር ተቀራርበን ለመስራት አቅደን እየተንቀሳቀስን ነው። አሁን ከሁሉም ክልሎች ጋር ጥሩ የሚባል ግንኙነት አለን። ለምሳሌ ባለፈው የክልል ምስረታውን በኮቪድ 19 ምክንያት ስላላከበርን በስፋት አካሂደን እንደነበር ይታወሳል። በበዓሉ ላይ የሁሉም ክልል ማለት በሚቻል ደረጃ የክልል ርዕሳነ መስተዳደሮችና ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ከፌዴራልም ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
በዚህ መድረክ ክልሉ አዲስ እንደመሆኑ መጠን የክልሉን ልማት ለመደገፍ በብዙ ሚሊዮኖች የሚቆጠር ሀብት ጭምር ማሰባሰብ ተችሏል። በፌዴራል ደረጃም ክልሉን ለማገዝ እንቅስቃሴዎች አሉ። እኛም ከሁሉም ክልሎች ጋር ተጋግዞ ለማደግ የበኩላችንን ጥረት እያደረግን እንገኛለን። በእንዲህ ዓይነት ነው እየተንቀሳቀስን ያለነው።
አዲስ ዘመን መጋቢት 24/2013