በአብርሃም ተወልደ
እንደመነሻ
ኢትዮጵያ- ባለፉት ሁለት አስር ዓመታት የኢፌዴሪ ህገመንግስትን ጨምሮ የተጻፉ ወርቃማ ህጎች ቢኖሯትም፣ በመሬት ላይ ያለው እውነታ ግን ሕጎቿ የተጣሱባት ፣ ዳኝነት እና ፍትህ የተጓደሉባት፣ ሰብአዊ መብቶች እና የዜጎች መሰረታዊ ነጻነቶች የተጣሱባት፣ ማህበራዊ ፍትህ የተዛነፈባት እና ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት የተዳፈነባት መሆኗን ቁልጭ አርጎ ያመለክታል።
በአንጻሩ በተለያዩ ጊዜያት ተስፋን የሰነቁ እድሎች ብቅ ብለውባት የነበረችም ናት። አንዳንዱን መልካም አጋጣሚ ባለማወቅ፣ አንዳንዶቹ ደግሞ ከለውጡ በፊት በነበረው ገዢ ፓርቲ እና መንግስት በመዳፈናቸው በአግባቡ ሳንጠቀምባቸው ቀርተናል።
ከእነዚህ መልካም አጋጣሚዎች መካከል በ1997 ዓ.ም ምርጫ ወቅት የታዩ ሕዝባዊ መነቃቃቶች እና ጠንካራ የፖለቲካ ፓርቲዎች ፉክክሮች አንዱ እና የቅርብ ጊዜ ትውስታችን ነው። ይህ ተስፋ ሰጪ ዕድል መጨረሻው እንዳይሆን ሆነ። በዚያ ምርጫ እንደ ተገፋ የቆጠረው ኢህአዴግ ከምርጫው ማግሥት ጀምሮ ያን አይነት መልካም አጋጣሚ እንዳይደገም በሚያደርግ መልኩ በተለይ በዝረራ በተሸነፈባቸው አካባቢዎች ህዝቡን አሰቃይቷል።
በዚህም ብዙዎች የማይተካውን ህይወታቸውን ተነጥቀዋል፤ አንዳንዶች ለእድሜ ልክ በሽታ እና አካል ጉዳት ተዳርገዋል። በተከታታይ በመንግሥት የተወሰዱት ጭካኔ የተሞላባቸው እርምጃዎች የታዩትን የዲሞክራሲ ጭላንጭሎች አዳፈኑ፤ ሥርዓቱም ወደ ለየለት አምባገነንነት ተሸጋገረ። ሕጎች፣ የፍትሕ አካላት፣ ሕግ አውጪው፣ የተለያዩ የመንግስት ተቋማት፣ መገናኛ ብዙሃን እና መከላከያ ሠራዊቱ ጭምር የአፈና መዋቅሩ አካል እንዲሆኑ ተደረጉ።
የለውጡ ዋዜማ
የመንግስት ግፍ ያስመረራቸው ወጣቶችና ሌሎች የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ተቃውሞ ማሰማት ጀመሩ። በተለይ በመላው ኦሮሚያ እና አማራ ክልል በተደረጉ ተቃውሞዎች ወጣቶች ስርዓቱን ከስሩ መንግሎ ለመጣል ከፍተኛ ተጋድሎ አርገዋል። በዚህ የተቃውሞ እንቅስቃሴ ፋብሪካዎች እና ተሸከርካሪዎች ተቃጠሉ፤ ለእዚህ ተቃውሞ የመንግስት የጸጥታ ሀይሎች በወሰዱት እርምጃ የበርካታ ዜጎች ህይወት እንዲጠፋ ተደረገ።
ሌላኛው የአመጹን ደረጃ ከፍ ያደረገው ደግሞ በወቅቱ በቢሾፍቱ ከተማ በተከበረው የኤሬቻ በዓል ላይ በርካታ ዜጎች ህይወታቸውን ያጡበት ሁኔታ ነው። የኦሮሞ ህዝብ ኢሬቻን እንደ ባሕሉ፣ ልማዱና ወጉ ለአዲሱ ዓመት በሰላም መድረሱን በደስታ የሚገልጽበት በአል ነው። ወቅቱ አዝመራ መድረስ የሚጀምርበት ወቅት እንደመሆኑ ፣የምስጋና፤ ወዳጅ ዘመድ እንዲሁም አብሮ አደጎች የሚገናኙበት የደስታ በዓል ነው።
ህዝቡ በአምባገነን መንግስት አልገዛም አሻፈረኝ ባለበት በዚህ ወቅት የተከበረው የኢሬቻ በአል ግን በዜጎች ላይ በተወሰደ አስነዋሪና አሳፋሪ እርምጃ ሳቢያ የደስታ ቀን መሆኑ ቀርቶ የሀዘን ቀን ለመሆን ተገዷል። በእርምጃው በርካታ የበአሉ ታዳሚዎች ተገድለዋል። በርካቶችም ለአካል ጉዳት ተዳርገዋል። በዚህ እርምጃ የሞቱትና የቆሰሉት ምን ያህል ስለመሆናቸው ያለው መረጃ አወዛጋቢ ነበር። መንግሥት የሚቆጣጠራቸዉ መገናኛ ዘዴዎች የሟቾቹን ቁጥር 52 ሲሉ፣ ማሕበራዊ መገናኛ ዘዴዎች፤ ተቃዋሚዎችና የፖለቲካ አቀንቃኞች ደግሞ ከ175 እስከ 700 ያደርሱታል።
የመንግሥት መገናኛ ብዙሃን የፀጥታ ሐይላት በከፈቱት ተኩስ የተገደለ ሰዉ የለም ይላሉ። የአይን ምስክሮች እና ተቃዋሚ ፖለቲከኞች ግን የመንግስትን መግለጫ ሐሰት በማለት በጥይት እሩምታ አያሌ ንጹሃን ረግፈዋል ሲሉ ይገልጻሉ።
ተቃውሞው እየተቀጣጠለ ሲመጣም ኢህአዴግ የለመደውን ጥልቅ ተሀድሶ ከታች እስከ ላይ ድረስ ማድረግ ውስጥ ገባ። ኢህአዴግ ለ17 ቀናት የዘለቀ ጥልቅ ተሀድሶ አደረገ። በዚሁ ወቅት በኢህአዴግ አባል ድርጅቶች መካከል ልዩነት ተፈጥሯል የሚሉ መረጃዎች ይወጡ ነበር። ይህን ተከትሎም የፓርቲው አባል ድርጅቶች መሪዎች ስለጥልቅ ተሀድሶው በመገናኛ ብዙሃን ማብራሪያ ይሰጡም ነበር። በዚሁ ወቅትም በመካከላቸው ምንም ልዩነት እንደሌለም ይገልጹ ነበር።
ነገሮች ተጋግለው ቀጠሉ። የወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩት አቶ ሀይለማሪያም ደሳለኝ የችግሩ የመፍትሄው አካል መሆን አለብኝ ብለው በገዛ ፍቃዳቸው ራሳቸውን ከጠቅላይ ሚኒስትርነት አገለሉ። የመሪነት ስልጣን በገዛ ፈቃድ መልቀቅ ለኢትዮጵያ አይደለም ለአፍሪካም በማይታሰብባት ሀገር ይህ የጠቅላይ ሚኒስትሩ እርምጃ በሀገሪቱ ታሪክ የመጀመሪያ ተባለ።
በቀጣይ አገሪቱን ማን ይመራታል የሚለው ደግሞ የመላ ኢትዮጵያውያን ጥያቄ ሆነ። የተለያዩ ግምቶች እና ጭምጭምታዎች ሲወጡ ነበር፤ መገናኛ ብዙሃኑም እንደየስሜታቸው እነማን አገሪቱን እንደሚመሩ ደረስኩበት ያሉትን ይጠቁሙ ነበር። ወቅቱ ከባድ ውጥረት የነገሰበት ነበር።
በዚያ ወሳኝ ወቅት በጉጉት ይጠበቅ የነበረው የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ለተከታታይ ቀናት ጉባኤውን ሲያካሂድ ቆየ። በመጨረሻው ቀን ስብሰባው ምሽት ላይ የኦሮሞ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት /ኦህዴድ/ ሊቀመንበር የነበሩት ዶክተር አብይ አህመድ የኢህዴግ ሊቀመንበር ተደርገው ተመረጡ።
ይህን ተከትሎም የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መጋቢት 24 ቀን 2010 ዓ.ም ባካሄደው ስብሰባ ገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ የፓርቲውን ሊቀመንበር ዶክተር አብይ አህመድን ለጠቅላይ ሚኒስትርነት አቀረበ።ፓርላማው ፓርቲው ለጠቅላይ ሚኒስትርነት ያቀረባቸውን ዶክተር አብይ አህመድን የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር አርጎ በመሾም አጸደቀ። ጠቅላይ ሚኒስትሩም ቃለ መሀላ ፈጽመው ለመላ የኢትዮጵያ ህዝብ ንግግር በማድረግ ስራቸውን ጀመሩ።
ይህ የመጀመሪያው የጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር ጆሮን ከመኮርኮር አልፎ ልብ ላይ ጠብ የሚል ሆነ። በንግግራቸው በፓለቲካ ምክንያት ከአገር የወጡና በጫካ የሚገኙ ዜጎች እና ቡድኖች ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ጥሪ አቀረቡ። ያኔ ነው ህብረተሰቡ እልል… በይ አገሬ !! …ቅጥርሽን የሚያድስ ከአለሽበት ክፉ ቀንበር የሚያላቅቅ ሙሴ መጣ በሚል ልቡንም ጆሮውንም ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የሰጠው።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ተለያዩ ክልሎች ተጉዘው መልእክት አስተላለፉ። እሳቸውን ለመቀበል የወጣው ህዝብም ድጋፉን አረጋገጠላቸው። በሀገር ውስጥ ሳይወሰኑም በተለያዩ የአሜሪካ ከተሞች እና በሌሎች ሀገሮች ከተሞች በመሄድ ኢትዮጵያውያንን አግኝተዋል። በዚህም ዜጎች በሀገራቸው ልማትና የፓለቲካ አንቅስቃሴ በነጻነት መንቀሳቀስ እንደሚችሉ በማረጋገጥ ጥሪ አቅርበዋል። በአረብ ሀገሮችም ጉብኝት ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ እስረኞችን አስፈትተው ጭምር ይዘው የመጡበት ሁኔታም አይረሳም።
ታዲያ ይህ ደስታ ብዙም ሳይሄድ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ድጋፍ በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ በተካሄደ ህዝባዊ የደስታ መግለጫ ሰልፍ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ለመግደል የታቀደ የግድያ ሙከራ ተደረገ። ምንም እንኳን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጉዳት ባይደርስባቸውም፣ እሳቸውን ብለው በወጡ የድጋፍ ሰልፉ ተሳታፊዎች ላይ ጥቃት ደረሰ። በተወረወረው ቦንብና ከቦታው ለማምለጥ ሲባል በተፈጠረው ግርግር ብዙዎች ለከፋ ጉዳት ተዳረጉ፤አንዳንዶች ህይወታቸውን አጡ።
የለውጡን ክንውን በጨረፍታ
ጊዜው እየሄደ ነገሮች መስመር እየያዙ መምጣት ጀመሩ፤አገሪቱ በብዙ ችግሮች የተወጠረችበትን ጊዜ በማለፍ የተስፋ እና የደስታ አየር እየነፈሰም መጣ። በውጭ ሆነው በትጥቅም፣ በዲፕሎማሲም ፣በሃሳብም የሚታገሉ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጠቅላይ ሚኒስትሩን ጥሪ በመከተል ወደ አገራቸው ተመለሱ፤ እንደ ኦነግ እና ግንቦት ሰባት እንዲሁም ሎሎች በሽብር የተወነጀሉ ፓርቲዎች እና ቡድኖች ተፎካካሪ ተብለው በክብር ወደ አገራቸው ተመለሱ። ወደ ሀገር ቤት ሲመለሱም መንግስትና ደጋፊዎቻቸው ያደረጉላቸው አቀባበል ደማቅና ሁሌም ሲታወስ የሚኖር ነው።
የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥሪ በፓርቲ እና በቡድን የተደራጁትን ብቻ የሚመለከት አልነበረም። በግለሰብ ደረጃ ያኮረፉም ወደ አገር ውስጥ እንዳይገቡም የተከለከሉም “ኑ ኢትዮጵያ እናንተንም ናፋቃለች!” በሚለው የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥሪ ወደ አገራቸው ተመለሱ። አክቲቪስቶች ፣ጋዜጠኞችና የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች ከእነዚህ መካከል ይጠቀሳሉ። በፓለቲካ አመለካከታቸው ሳቢያ ወህኒ ቤት ተወርውረው የነበሩትም እየተለቀቁ ህብረተሰቡን እንዲቀላቀሉ ተደርጓል።
ለውጡ ኢትዮጵያውያን አንድነታቸውን እንዲያጠና ክሩ በር የከፈተም ነው። ለእዚህም ይቅርታና ምህረት ወሳኝ መሆናቸው ታምኖበት ተሰርቶበታል።
ጠቅላይ ሚንስትሩ የመደመር አሳቤን ይፋ በማድረግ ኢትዮጵያውያን በጋራ ሆነው ሀገራቸውን ወደፊት እንዲያራምዱ አርገዋል። ለእዚህም የመደመር መጽሃፍ አሳትመዋል።
ለውጡ ለሁለት አስርት ዓመታት ጦርነትም ሰላምም በሌለበት ሁኔታ ውስጥ የቆዩትን ኢትዮጵያና ኤርትራ ግንኙነታቸውን እንደገና አንዲቀጥሉ አስችሏል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ማንም ባልጠበቀው ወቅት ኤርትራ በመሄድ ግንኙነቱን እንደገና በማስጀመር ፈር ቀዳጅ ሆነዋል። ይህን ተከትሎም የኤርትራ ፕሬዚዳንት ኢትዮጵያን ከሀያ አመት በሁዋላ ኢትዮጵያን ጎብኝተዋል።
ይህ የጠቅላይ ሚኒስትሩ እርምጃ በዲፕሎማሲ ረገድ ታላቅ ተግባር ለመሆን በቅቷል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚህ ተግባራቸው የኖቤል የሰላም ሽልማትን ለማግኘት በቅተዋል።
ለውጡ በርካታ ስኬቶች የተመዘገቡበት ቢሆንም ለውጡ በመጣባቸው እና ጥቅም በቀረባቸው ቡድኖችና ግለሰቦች አልተወደደም። እነዚህ ቡድኖች በተለይ የትህነግ የጥፋት ቡድን በቀጥታም በተላላኪዎቹም በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች በንጹሃን ዜጎች ላይ የሚያካሂደው ጭፍጨፋ የሀገሪቱ ትልቅ ችግር ሆኖ ቆይቷል።
የህዳሴውን ግድብ አስመልክቶ ከታችኞቹ የተፋሰሱ ሀገሮች ጋር ድርድሮች ቢካሄዱም፣ በተለይ የግብጽ ፍላጎት ማቆሚያ የሌለውና የግድቡን ግንባታ ማስቆምን ያለመ መሆኑ ኢትዮጵያ ግንባታውን እያካሄደች ድርድሩን ቀጥላለች። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ግብጽ እና ሱዳን የብቻ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ የሚያደርጉት ሩጫ ሌላው የአገሪቱ ፈተና ነው።
እንዲያም ሆኖ ግን ኢትዮጵያ አለቀላት ሲባል እንደገና እያበበች፣ ተበተነች ሲባል እየተሰበሰበች ብዙ ወጀቦች እያለፈች ትገኛለች። አገሪቱ ከውስጥም ከውጭም የሚፈትኗት ችግሮች እያሉ ወደ ብልጽግና የምታደርገው ጉዞ ቀጥሏል።
እንደሚታወቀው ለውጡ በብዙ ፈተናዎች እና እድሎች የታጀበ ነበር፤ ነውም። ከእነዚህም እንደ ችግር ከሚነሱት መካከል በትግራይ የህግ ማስከበር ዘመቻ እንዲካሄድ ያስገደደው የህወሓት ጁንታ በመከላከያ ሰራዊት ላይ የፈጸመው ጥቃት ቀዳሚው ሲሆን፤ የሱዳን ጠብአጫሪነት፣ የግብጽ የአባይን ወንዝ አትንኩ እኔ ብቻ ልጠቀም ባይነት ይጠቀሳሉ።
የለውጡ አመራር ለእነዚህ የውስጥ እና የውጭ ሴራዎችና የጥፋት ተልእኮዎች ሳይሸነፍ አገሪቱን ካለችበት የድህነት አረንቋ ለማውጣት መስራቱን ቀጥሏል፤ በሙስና እና ብልሹ አስራር ተተብትቦ የነበረወን የህዳሴ ግድብ ግንባታ ችግር በመፍታት አሁን ላለበት ደረጃ እንዲደርስ አድርጎታል። ሌሎች ከባባድ የኢኮኖሚ ሪፎርሞች ተሰርተዋል፤ እየተሰሩም ነው።
ለውጡን እንዲሸከሙ በሚል በርካታ አዋጆች እንዲሻሻሉ ተደርጓል። ከእነዚህም መካከል የምርጫ ህጉ ፣የበጎ አድራጎት ማህበራት ህጉ ፣ የጸረ ሽብር ህጉ ከብዙ በጥቂቱ ናቸው። በእዚህም ለውጡን ተቋማዊ ለማድረግ ተሰርቷል።
የዲሞክራሲ ስርአት ግንባታ በለውጡ ከሚጠበቁት አንዱ ነው። የምርጫ ህጉን ከማሻሻል በተጓዳኝ የምርጫ ቦርድን በአዲስ በማዋቀርና የቦርድ አባላትንም በመሰየም የተጀመረው ስራ 6ኛውን ምርጫ በዚህ አመት ለማካሄድ የሚያስችሉ ዝግጅቶች በማካሄድ ተጠናክሮ ቀጥሏል።
ይሁን እንጂ የዴሞክራሲ ስርአት ግንባታው በመንግስት ጥረት ብቻ ውጤታማ መሆን አይችልም። የህዝቡም የፖለቲካ ፓርቲዎችም ንቁ ተሳትፎ ወሳኝ ነው። በሀገራችን ምርጫ የፓርቲዎች ሚና / ምርጫ 1997 ካልሆነ በቀር / እዚህ ግባ የሚባል አልነበረም። በምርጫ ተሳትፈዋል የሚባሉ ፓርቲዎችም ቢሆን በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽ በሰጡበት ወቅት እንዳሉት የለመዱት ምርጫ ማጀብ እንጂ፤ ተፎካክሮ ማሸነፍ አልነበረም። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ምርጫውን በታቸለ መጠን ዴሞክራሲያዊ አርገን እንጠቀምበት ሲሉ አስገንዝበዋል።
እንደ አጠቃላይ ሲታይ ለውጡ በርካታ ስኬቶች ተመዝግበውበታል። ይህንንም በአብነት ለማሳየት ተሞክሯል። ስኬቶቹ የተመዘገቡት ግን በርካታ ፈተናዎችን በማለፍ ነው። ሀገራችን አሁንም በበርካታ ፈተናዎች ውስጥ ትገኛለች። ፈተናዎች አሉ በሚል ግን የሚቆም ነገር መኖር እንደሌለበት በአንድ ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስታውቀዋል። ፈተናውን ብቻ ሳይሆን ፍሬውን ማሰብ ያስፈልጋል ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደተናገሩት ሁሉ እንዳለፉት ጊዜያት ሁሉ በፈተና ውስጥ ተሆኖም በመጪው የተስፋ ዘመን ውጤታማ ለመሆን መስራት ቀጣዩ ስራ መሆን ይኖርበታል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 24/2013