ጽጌረዳ ጫንያለው
በአገራችን የመጣው የለውጥ ሂደት እነሆ ሦስት ዓመት ሞላው።በነዚህ ሦስት ዓመታት ታዲያ አገርን ከውድቀት የታደጉ በርካታ ሥራዎች ተከናውነዋል።ለአብነትም በኢኮኖሚው ረገድ የተሰራው ሥራ ተጨባጭ ለውጥ የታየበት ነው።በውጭ አገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውንም በአገራቸው ጉዳይ ንቁ ተሳትፎ ማድረግ የጀመሩበት ወቅት ነው።ከዚህም ባሻገር በተለያዩ ዘርፎች በተካሄዱ የሪፎርም ሥራዎች በርካታ ለውጦች ታይተዋል።በአብዛኛው ዜጎች ሲያነሷቸው የነበሩ የፖለቲካ ጥያቄዎችም መመለስ ጀምረዋል፡፡
ይሁን እንጂ ይህ ለውጥ እውን እንዳይሆን ያልተፈነቀለ ድንጋይ፣ ያልተማሰ ጉድጓድ አለ ለማለት አይቻልም።የኢትዮጵያን እድገት ከማይፈልጉ የውስጥ ኃይሎች እስከ የውጭ ጠላቶች ድረስ ለውጡን በእንጭጩ ለማስቀረት ሞክረዋል።ከዚህ አንጻር በተለይ የዜጎች መፈናቀልና ሞት ትልቅ ፈተና የሆነበት ሁኔታ ተፈጥሯል።ይሁን እንጂ እነዚህ ኃይሎች ያሰቡት ነገር ሊሳካ አልቻለም።ለውጡ አገራዊ እድገትን ለማስመዝገብ በሚያስችል ሃዲድ ላይ መጓዙን ቀጥሏል።እኛም በዚህ ዙሪያ የለውጡን ሦስተኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ አንዳንድ እንግዶችን ጋብዘናል፡፡
እንግዳችን ፒስ ኤንድ ኮንፍሊክት ሪዞሊሽን በተሰኘ የትምህርት መስክ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ የተማሩ ሲሆን፤ ሙያው ላይ በብዙ መልኩ ሰርተውበታል።ከዚያም በደቡብ ኮርያ በዲፕሎማትነት ለአራት ዓመታት አገልግለዋል።በውጭ ጉዳይም እንዲሁ በኢኮኖሚክ ዲፕሎማሲ ዙሪያ ከዚህ ያላነሰ ዕድሜ ሰርተዋል። በእነዚህ ጊዜያትም አገርን ሊጠቅሙ የሚችሉ ለውጦችን አምጥተዋል። አሁን ደግሞ የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ኤጀንሲን በዋና ዳይሬክተርነት እየመሩ ይገኛሉ፤ ወይዘሮ ሰላማዊት ዳዊት።እኛም ከሙያቸውና በኤጀንሲው እየተሰራ ስላለው ጉዳይ እንዲሁም ከውጭ ጫና ጋር በተያያዘ ላነሳንላቸው ጥያቄዎች የሰጡንን ምላሽ እንደሚከተለው አቅርበነዋል፤ መልካም ንባብ።
አዲስ ዘመን፡– የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ኤጀንሲ የተቋቋመበት ዋና አላማ ምንድነው እስካሁን ምን ምን ተግባራት አከናውኗል?
ወይዘሮ ሰላማዊት፡– ኤጀንሲው ውስጥ የዲያስፖራ ሥራውን የሚሰሩት በጣም ጥቂትና ከአምስት የማይበልጡ ናቸው።ለ15 ዓመት ያክል አገልግሎቱ እንዲሰጥ ተብሎም ነው በውጭ ጉዳይ በኩል ሲከናወን የቆየው።ይህ ደግሞ በርካታ ችግሮችን እንዲያስተናግድ አድርጎታል። ለአብነትም የዲያስፖራ ገንዘብ የሚው ልበት ቦታ ላይ፣ ኢትዮጵያ በአላት የዲያስፖራ ቁጥር ልክ ተጠቃሚ አለመሆኗ፣ የሚጠይቁት ጥያቄን የሚያስተናግድ ተቋም አለመኖርና በሰዎች ፍላጎት ላይ የተመሰረተ ሥራ መሰራቱ በዋናነት የሚጠቀስ ነው።
በእነዚህ ሁለት ዓመታት ውስጥ በተቻለ መጠን ዘመናዊና ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት ተችሏል።ይህ ሲሆን ደግሞ በሁለት መንገድ ነው። ከሌሎች አገራት ኢትዮጵያ ምን ትፈልጋለች የሚለው የመጀመሪያው ሲሆን፤ ሁለተኛው እነርሱ ምን ይፈልጋሉ የሚለው ነው።በዚህም ሁለቱን አካላት በመረጃና በተግባር በማገናኘት ነው።ምክንያቱም መርሀችንም ‹‹እኔ ለአገሬ አገሬ ለእኔ ›› የሚል ስለሆነ እርሱን ማስተግበር ነው።እናም ማን ምን ይፈልጋል በሚል በማጥናትና ዲያስፖራውን ተልዕኮ በመስጠት ተግባራት እንዲከናወኑ ያደርጋል፡፡
ዘላቂ ግንኙነት የሚኖረው አንድ አካል ብቻ ሲያደርግ ሳይሆን ሁለቱም በእኩል ደረጃ እየተጠቃቀሙ ሲቀጥሉ ነው።ስለዚህም እነዚህን ሁለት መንገዶች በአራቱ በኤጀንሲው በተቋቋሙ ክፍሎች እንዲሰሩ ይደረጋል።ወደ ለውጡ ሲገባም ከፍተኛ ለውጥ እያሳየ የመጣ ኤጀንሲ ነው።ለዚህም ማሳያው መጀመሪያ የነበሩትን ችግሮች እየፈታ መጓዙ ሲሆን፤ በማያዳግም መልኩ ተሰርቶባቸዋልም።ለአብነት መረጃ ለዲያስፖራው በጣም ወሳኝና ትልቅ ችግር ነበር።እናም በኤጀንሲው አማካኝነት ዲያስፖራው ባለበት ቦታ ላይ ሆኖ ስለ አገሩ ሙሉ መረጃ እንዲኖረው የማድረግ ሥራ ይሰራል።
ሌላው ደግሞ ዲያስፖራው ወደ ኢንቨስትንትና ቢዝነስ በሚመጣበት ጊዜ በርካታ ችግሮችን ያሳልፍ ነበር።ለዚህ ደግሞ ዋነኛ ችግሩ መረጃ ያለማግኘት ሲሆን፤ የብዙ ቦታ ቢሮዎችን እንዲያንኳኳ ይሆናል። ይህ ደግሞ ሳይሰራ እንዲመለስና እንዲማረር ያደረገው ጉዳይ ነው። እናም በመረጃ ሙሉ ሆኖ የት መሄድ እንዳለበት እንዲያውቅ በማድረግ ወደ ሥራው የሚገባበት ሁኔታ ተፈጥሮለታል።ሁለተኛው ከዚህ ጋር የተያያዘው ጉዳይ ከቢዝነስ ፕላኑ ጀምሮ እስከገንዘብ ማስገባቱ ድረስ ያሉ ሂደቶችን ተከታትለን እንዲፈጸምለት የማድረግ ሥራ በመስራትም ብዙ ነገሩን እናቀላለን።
ይህ መሆኑ ደግሞ ለአገርም ጭምር እንዲጠቅም ያደርጋል። ምክንያቱም ገንዘብ ለሌለው ሰውም ደብዳቤ አንጽፍም፤ በትክክል ቦታውና ሁኔታው ሳይኖረን ይህንን ያህል መሬት አለ አንለውምም።መጀመሪያ በተጨባጭ እዚያ ክልል ላይ ምን አለና ምን ይፈልጋል የሚለውን ካጠናን በኋላ ነው ከተስማማ እንዲሰራ የምናደርገው።ሌላው አገራዊ ጥሪዎችና አገራዊ ፕሮጀክቶች ላይ የዲያስፖራው ተሳትፎ እንዲታይና እንዲጨበጥ ማድረግ ነው።በዚህም በዋናነት የኤጀንሲው ሥራ የማህበር ልማት፣ በመዋዕለ ንዋይ ፍሰት፣ በእውቀት ሽግግር፣ በበጎ አድራጎት፣ በሀብት ማሰባሰብና በውጭ የሚኖሩ ዜጎችን መብት ማስጠበቅ ላይ ብዙ ተግባራት ፈጽሟል ማለት ይቻላል።
ዘንድሮ የተሰራውን ብቻ ተጨባጭ የሆኑትን ብናነሳ በአገራዊ ጥሪና በአገራዊ ፕሮጀክቶች ላይ የተሰሩት ሥራዎች በቂ ናቸው።እነዚህን ተግባራት እንዲያከናወን ማገዝም ነው።ለዚህም ማሳያው ህዳሴ ግድቡን በሚመለከት በ2013 ዓ.ም ብቻ በስድስት ወራት ውስጥ ከ100 ሚሊዮን ብር በላይ በቦንድ ሽያጭና በስጦታ ማበርከቱ ነው።ከገንዘቡም በላይ የኢትዮጵያን መብት በማብራራት፣ ለዓለሙ ማህበረሰብ በማስረዳትና በማሳወቅ ላይ ብዙ ተግባራት ተከናውነዋል።
ግድቡ ምንድነው፣ ለሌሎች አገራት ጭምር ያለው ፋይዳ ምንድነው፣ ሌሎች አገራት ለምን ይህንን ይቃወማሉ የሚሉና ሌሎች መረጃዎችን ከኤጀንሲው ሙሉ መረጃ በመውሰድ በተለያዩ ዓለምአቀፍ ቋንቋዎች በአደባባይና በሥራቸው አጋጣሚ ጭምር እያስረዱ መሆናቸውን በለውጦቹ ማየት ይቻላል።አሁንም ቢሆን ህዳሴውን በሚመለከት ድጋፉም ሆነ ሥራው ይቀጥላል። ምክንያቱም ህዳሴው የመልማት ያለመልማት ጉዳይ ሳይሆን በሕይወት የመኖርና አለመኖር ጉዳይ ነው።
ሌላው የአገር ጥሪ በህዳሴው ብቻ የሚያበቃ ስላልሆነ በገበታ ለሀገርም ላይ ዲያስፖራው ተሳትፎ አድርጓል። ይህም በሦስት ወር ብቻ ወደ 27 ሚሊዮን ብር ተሰብስቧል። ከዚያ በላይ የሚሰበሰብበትም ነበር።ነገር ግን ወቅቱ በግጭቶች ምክንያትና አገር ላይ በተፈጠረው ችግር ምክንያት ቀዳሚ መሆን ያለበት የሰው ሕይወትን መታደግ ነበርና ለመከላከያና ለተጎዱ ወገኖች እንዲሰበሰብ ተብሎ ይህኛው ቆሟል።በዚህም ከዚህ በላይ ማገዝ አልተቻለም።ይሁን እንጂ እነዚህ ችግሮች ሲፈቱ ዳግም ለልማቱ የሚደረጉ ተግባራት ይኖራሉ ብዬ አምናለሁ።
ወደ ሕግ ማስከበሩ ሥራ ሲገባም ዲያስፖራው ለተጎዱ ዜጎችና መከላከያ 400 ሚሊዮን ብር በሦስት ወር ውስጥ ሰብስቧል።በዓይነትም ቢሆን ከጤና ሚኒስቴር በመጣ መረጃ መሠረት መድኃኒቶችን ጨምሮ ሌሎች ቁሳቁሶችን ድጋፍ አድርጓል። በተመሳሳይ በኮሮና ጉዳይም ቢሆን እንዲሁ ዲያስፖራው ዝም አላለም ነበር።ከጤና ሚኒስቴር ጋር በየሳምንቱ ሐሙስ ሐሙስ የዲያስፖራ የሕክምና ቡድን በመሰባሰብ በኦንላይን የዓለሙን እንቅስቃሴና የኮሮናን ነባራዊ ሁኔታ በኮንፍረንስ መልኩ ሲያሳውቁ ቆይተዋል።መረጃንም በቀላሉ ይለዋወጡ ነበር።ይህ ደግሞ አገር ምን ማድረግ ያለባትን ቀድማ እንድትዘጋጅ አድርጓል። ከሙያዊ እገዛ ባሻገርም መጀመሪያ አካባቢ ኪቶችንና የመከላከያ መሣሪያዎችን ለማግኘት ባልተቻለበትና አገራት ለእኔ ብቻ በሚሉበት ወቅት ዲያስፖራው ከተለያዩ ቦታዎች ገዝቶ በመላክ አገር ከዚህ ችግር በመጠኑም ቢሆን እፎይ እንድትል አድርጓል። በገንዘብም ቢሆን ከ500 ሚሊዮን ብር በላይ አበርክተዋል፡፡
የበጎ አድራጎት ሥራውም እንዲሁ ወደ 100 ሚሊዮን የሚገመት ቁሳቁሶችን ድጎማ በማድረግ የታገዘበት ነው። ዊልቸር፣ የሆስፒታል አልጋዎች፣ መነጽርና ከዚያም የተለዩ የሕክምና ቁሳቁሶችን አስፈላጊ ከሆነ ሕክምና ጋር ድጋፍ ሲደረግ ነበርም።ለዚህ ሁሉ ቅንጅት ደግሞ የተቋሙ መመስረትና የአላማው ሁኔታ በአግባቡ ተግባብተው መስራት መጀመራቸው ነው።አንድ ዲያስፖራን የሚመለከት ኤጀንሲ ተቋቁሞ ወደ ሥራ መግባቱም ነገሮች በተሳካ ሁኔታ በአንድ መስመር እንዲጓዙ አግዟል።
አገር ዞሮ መግቢያና መጠለያ ነች።ሆኖም የሚያስተባብር ሳይኖርና በየሜዳው እየተበተነ የሚፈለገው ላይ መድረስ ካልቻለ የዲያስፖራው ልፋት ከንቱ መሆኑ አይቀርም።ስለዚህም አብዛኛው ዲያስፖራ አላደርግም የሚለው አገሩን ጠልቶ ሳይሆን የሚያደርገው ነገር በውጤት ተደግፎ አለማየቱ ስለሆነ የኤጀንሲው መቋቋም ተጠያቂነትም ስላለበት ይህንን መሸሹን እንዲቀርለትና አገር ኑ አግዙኝ ስትል ወደኋላ እንዳይል አድርጎታል።ዲያስፖራውም ይህንን አውቆ እየሰራም ይገኛል።በቀጣይም ቢሆን በተጠሩበት ብቻ ሳይሆን በአገር ጉዳይ በሚመጣው ሁሉ ለማገልገል ዝግጁ መሆናቸውን ከአሁኑ ሥራቸው መረዳት ይቻላል።
አዲስ ዘመን፡- በውጭ አገራት የሚደረገውን ጫና እርስዎ እንዴት ያዩታል፤ ምክንያቱስ ምንድነው ይላሉ?
ወይዘሮ ሰላማዊት፡– ኢትዮጵያ ያልተገዛች፤ ክብሯን ጠብቃ የቆየችና ለረጅም ጊዜ መንግሥት የነበራት አገር ነች።ብዙ ነገሮችም በራሷ ስታደርግ የኖረችም ነች።ይህ ደግሞ ብዙዎች ያማቸዋል።በዚህም የተለያዩ ወከባዎችን እየፈጠሩ ይገኛሉ።በተለይ በሚዲያው አካባቢ እየተከፈላቸው የሚደረጉት ውንጀላዎች ተገቢነት ያላቸው አይደሉም።አላስፈላጊ ጫና ውስጥ ለመክተትና ያለፍላጎቷ ነገሮችን እንድታደርግ የሚሞከሩበት ግፊቶችም ናቸው።
በተመሳሳይ ሌላው ችግር እኛ እራሳችን ነን።ምክንያቱም ውሻ በቀደደው ዓይነት ነው ነገሩ።ብዙ ሳይለፉ ተቃዋሚ መኮነን የሚቻልበት መድረክን እየተጠቀሙበት ነው። እናም ቅድሚያ ውስጣችንን ማጥራት አለመቻላችን ጫናውን አባብሶታል።ስለዚህም ይህንን የሚያደርጉ ግለሰቦችም ሆኑ አገራት ሥራቸው እንደማያዋጣቸው ሊያውቁ ይገባል።ምክንያቱም ኢትዮጵያን በመጫን፣ በማስፈራራት፣ በውሸትና በማዋ ከብ የተለየ ውሳኔ ውስጥ አትገባም።
አገራችን እስከዛሬ በነበራት ልምድ ከዚህ የባሰ ችግር አሳልፋለች። ማንም ረትቷትም እንደማያውቅ ያውቃሉ። እናም አሁንም ያንን ተገንዝበው ችግር ከመፍጠር መቆጠብና በመስማማትና በመተባበር መስራት ላይ ቢያተኩሩ ይበጃቸዋል ባይ ነኝ። ኢትዮጵያዊነት ትሁትነት ነው።የሚመለስ፣ ለሰዎች የሚያዝንና በጎ ነገሮችን በስፋት መመልከት ባህሪው የሆነ የሃይማኖት ሰው ነው።አልፈው ከመጡበትም የማይታገስ ነው።ስለዚህም የዓለምአቀፉ ማህበረሰብ ይህንን ተረድቶ በጋራ መስራት ቢችል ይጠቀማል እንጂ አይጎዳም።የመቶ ሚሊዮን ሕዝብም ገበያ አጋር መሆን ይችላልና።የፖለቲከኛው አድርባይነትና አገር ውስጥ ያለው አለመረጋጋት ነገሩን አባብሶታልና ሰከን ብሎ ባለን መጠቀም ላይ ማሰብም ያስፈልጋል።
ያለን ጸጋ አይደለም ለኢትዮጵያዊ ለዓለም ይበቃል። ሆኖም የታየው ላይ ብቻ ስለምንረባረብ ነው ዓይናችንን ስስት የያዘው።እናም ባለን ትንሽ ነገር ላይ ከመነጣጠቅ ይልቅ ያለንን ብዙ ሀብት ወደማየቱ እንግባ።ይህ የሚሆነው ደግሞ ተግባብቶና ተደማምጦ መስራት ሲኖር ነውና ይህንን ልምዳችን ልናደርገው ይገባል።የውጭ ጫናውም እኛ አንድ በመሆናችን ይመለሳል።
አዲስ ዘመን፡- የዲያስፖራውን እንቅስቃሴን ከዚህ አንጻር እንዴት ተመለከቱት?
ወይዘሮ ሰላማዊት፡- እጅግ የሚያስመሰግን ነበር። እንደ ኤጀንሲ ብቻ ሳይሆን በተለያየ የመንግሥት አካላትም ምስጋና የተቸረው ነው።ምክንያቱም ዲያስፖራው ከኤጀንሲው በሚያገኘው መረጃ በራሱ ተነሳሽነት ብዙ ሥራዎችን ሰርቷል።በተደራጀ መልኩ እውነቱ ሲያወጣም ነበር። እውነት ላይ መነሻ ተደርጎ የሚነገረውን ማንኛውንም ነገር ችግር እንዳይሆን ያደረገውም ይህ እንቅስቃሴያቸው ነው።ውሸቱን የማጋለጥ ሥራ ሲሰራ ወደ እውነታው የሚመጣው ብዙ ስለሚሆን ብዙዎች እንዲገለጥላቸውና የኢትዮጵያ መንግሥት እየሰራ ያለው ሥራ ተገቢነት ያለው እንደሆነ እንዲረዱም አድርጓል።
መረጃው ትክክል ያልሆነው በመናገርና በመቃወም ትክክለኛውን መረጃ መስጠት ላይ ብዙ ለፍተዋል። ገጽታዋን በሚጎዳ መልኩ የሚነገሩ ነገሮችን በመቃወም ትክክለኛዋ ኢትዮጵያ የቷ እንደሆነች አስረድተዋልም። ይህንን በማስተባበሩ በኩል ደግሞ ኤጀንሲው ብዙ ተግባራትን ከውኗል።
አገራት ስለ አገራቸው ለሚዲያ የሚናገሩበት ሁኔታ ምንም ዓይነት ጥፋት ቢኖር የተለየ ነው።በጣምም ይጠነቀቃሉ።ምክንያቱም ሰው አዕምሮ ላይ በሚዲያ በኩል የሚገባ ነገር ለማጥፋት ብዙ ዘመናትን ይፈጃል። ስለዚህም በሚሰጠው መረጃ መሠረት መልካም ገጽታን በመገንባቱ ዙሪያ ብዙ ተግባራትን ከውነዋል።ወደፊትም ይህንኑ እንደሚያደርጉ እሙን ነው።ለምሳሌ በአባይ ጉዳይ ላይ ሲተረኩ የቆዩት የተሳሳቱ ትርክቶችን ከማጥፋት አንጻርም የማይተካ ሚናቸውን ተጫውተዋል።ከታሪካዊው ጀምሮ እስከ አዳዲስ ውሸት ፍብረካው ድረስ የማጥራት ሥራም ሲሰራ ቆይቷል።
አዲስ ዘመን፡– ተሰሚነት ያላቸው ብዙ የአገራችን ዲያስፖራዎች በውጭው ዓለም እንዳሉ ይታወቃል።ያሉበትም ቦታ ሚዲያውን ለመያዝ ትልቅ አቅም ይሰጣቸዋል። ከዚህ አንጻር የሚጠበቀውን ያህል ሰርተዋል የሚል እምነት አልዎት ?
ወይዘሮ ሰላማዊት፡– የለኝም። ምክንያቱም በውጭ አገር የሚኖሩ ዲያስፖራዎች ከሦስት ሚሊዮን በላይ ናቸው።በአፍሪካ ከናይጄሪያ ቀጥላ ሁለተኛዋ ሰፊ ቁጥር ያላት አገርም ናት።ሆኖም ካላቸው ቦታና እውቅት አንጻር በብዛታቸው ልክ አልተጠቀመችም።ለዚህ ደግሞ መንስኤው ተደራጅተው የሚያገለግሉበት ሁኔታ አለመመቻቸቱ ነው። የነበሩ የተሳሳቱ አስተሳሰቦችም እንዲሁ ዲያስፖራውን ለአገሩ እንዳይሆን አድርገውታል። አሁን ግን ይህ ነገር ኤጀንሲው በመቋቋሙ ተፈቷል የሚል እምነት አለኝ።ብዙ ነገሮችም እየተቀየሩ ናቸው። በተቻላቸው ፍጥነት በብዙ ነገሮች ለማገዝም እየሞከሩ ይገኛሉ።
አዲስ ዘመን፡– እንደ ዲያስፖራ አገርን ከውጭ ኃይሎች ጫናና መሰል ችግሮች ከመታደግ አንጻር የሚያጋጥሙ ችግሮች ምን ምን ናቸው፤ ችግሮቹንስ ለመፍታት ምን መደረግ አለበት?
ወይዘሮ ሰላማዊት፡– የአንድ አገር ዜጎች ሆነው ሳሉ በአንድ እውነታ የያዘ መረጃ መለያየታቸውና ኢትዮጵያን ዝቅ አድርገው የሚያዩ እንዲሁም ለሌሎች እንቅፋት መሆናቸው መታየቱ አንዱ ፈተና ነው።ሌላው በባህላችን እውነት ራሷ ትወጣለች በሚል ሳንናገርና እውነታውን ማስረዳት አለመቻላችንም እንዲሁ ፈተና ነው። ምክንያቱም ቀድመን ተናግረን እውነታውን የዓለሙ ማህበረሰብ ቢያውቀው ችግሮች አይፈጠሩም ነበር።ጫናዎችም እንዲሁ በየጊዜው መልክ እየቀያየሩ አይመጡም ነበር።በተመሳሳይ የሀሳብ ልዩነቶችም ቢሆኑ እንዲህ አይሰፉም ነበር። አገርን በመልካም ገጽታ ቶሎ የመሸጥ ባህሪንም ይዳብር ነበር።አሁንም ቢሆን አልረፈደም፡፡
ብዙ ነገሮች በመናገር ይቀየራሉ።ነገር ግን ስንናገር እውነቱን መሆን አለበት።ያለመረጃና ማስረጃም ምንም ነገር መተንፈስ የለብንም። የአገራችን ደህንነት ላይ ጥላ የሚያጠሉ ነገሮችን መቃወምና ስለ አገር መቆምን ልምዳችን ማድረግም ይገባል።ዛሬ ዲያስፖራው ብዙ መፍትሄዎች ማምጣት የሚችልበት ጊዜ ነው።ምክንያቱም ብዙ ጫናዎች ከውጭው ዓለም ባለመረዳት እየመጡ ይገኛሉ።ይህንን ለማስተካከል ደግሞ ከእነርሱ ውጪ ማንም አይኖርም።እናም የመፍትሄ አማራጮችን በማየት መስራት አለባቸው።
አዲስ ዘመን፡– አገሪቷ ህዳሴ ግድቡን ብቻ ሳይሆን በቀጣይ በርካታ መሰል ተግባራትን ለማከናወን ታስባለች።እድገቷን የማይፈልጉ አካላት ደግሞ በዚያው ልክ ፈተና ይሆኗታል።ይህንን ከማገዝና ከመፍታት አኳያ እንደ ዲያስፖራ ምን መሰራት አለበት ይላሉ?
ወይዘሮ ሰላማዊት፡– በአሰራር ደረጃ ይህ ድጋፍ እንዲኖር እየተሰራ ነው። በመዋቅር ደረጃም ብዙ ነገሮች ተሰርተዋል። አሁን እንደ ድሮው የተቋም ችግር የለም። ስለዚህም በተፈጠረለት መድረክ ጊዜውን የዋጀ ሥራ መስራት ይችላል።ስለዚህም ዲያስፖራው የምኖርበት አገር አገር ሲኖረኝና ሳይኖረኝ እንዴት ያየኛል የሚለውንም ከግምት የሚያስገባበት ጊዜው አሁን ነው። ስለዚህም ለአገር ህልውና መቆምም አሁን ያስፈልገዋል።ምክንያቱም ይህ ጊዜ እንደድሮው ዝም ብሎ የሚኖርበትም የቅንጦት ጊዜ አይደለም። ስለዚህም ትውልደ ኢትዮጵያዊው የትኛውም ጫፍ ላይ ቢኖር ዕድሜ ለቴክኖሎጂ አቀራርቦታልና በአገሩ ጉዳይ መገናኘቱንና መነጋገሩን መተው የለበትም።ለአገሩ የሚበጀውን ሁሉ ማድረግ አለበት።
በሚጽፈው፣ በሚያደርገውና በሚናገረው ሁሉም ኢትዮጵያን ከፍ የሚያደርግ መሆኑን ማረጋገጥ የውዴታው ግዴታው እንደሆነ ማመን ይገባዋል።በተለይም ጫና እየፈጠሩ ባሉ እንደ አባይ ጉዳይ ላይ ድምጻቸውን ከፍ አድርገው መናገር መጀመር ይገባቸዋል።እኛ እንደ ባለቤትነታችን ሁሉም ይገባን ነበር።ሆኖም በእኩልነት ስለምናምን እኩል እንጠቀም እንጂ ሁሉም የእኛ ይሁን አላልንም።ስለዚህም ዲያስፖራው ይህንን በማስገንዘብ ሥራዎችን በጀመረው ልክ ማስቀጠልም አለበት።ከዚያ ባሻገር ገንዘብ ያለው በገንዘቡ፣ ጉልበት ያለው በጉልበቱ አለያም በእውቀቱ ማገዝ ይኖርበታል።
ጥሩ የመናገር አቅሙ ያለውም ሆነ አጋጣሚው ዕድል የሰጠው ሁሉም በተሰጠው መድረክ ሁሉ ትክክለኛውን መረጃ መንገርና ማሳወቅ አለበትም።ጊዜው ሁሉም የራሱን ድንበሩን የሚያስጠብቅበት፣ አገራዊ ጥቅሙን ከፍ የሚያደርግበት በመሆኑም ትውልደ ኢትዮጵያውያንም ይህንን አውቀው ሊሰሩ ይገባል። ዜጎች እየኖሩበት ያለው አገርም ቢሆን የተወለዱበትን አገራቸውን ሲነካባቸው እንደማይታገሱት ሁሉ ዲያስፖራውም ይህንን ማድረግ ላይ መታተር ይጠበቅበታል።ምክንያቱም አገራቸው ነገ ለልጆቻቸው ታሪክ የሚያስቀምጡባት፣ ማንነትና ታሪካቸውን የሚነግሩባትና የሚያስረክቡባት ነች።
ችግሮቿ የተቀረፉላት፣ የበለጸገች አገርን ለትውልድ ማሻገር የማይፈልግ ዜጋ አይኖርም።እናም ይህንን ማድረግ ላይም መረባረብ አለባቸው። አገር ውስጥም ይሁን በውጪ የሚኖሩ ዜጐች የሚያዝኑበትንና የሚያፍሩበትን አገር መፍጠር የለባቸውምና በችግሮች ዙሪያ መፍትሄ ሰጪ መሆን ይጠበቅባቸዋል።አሁን እያደረጉ ባለው ተግባርም በኤጀንሲው ስምም ሆነ በግሌ ከልቤ ማመስገን እፈልጋለሁ።ይህ ተግባራቸው የማይቋረጥም መሆን አለበት። ወቅቱ የዲጅታል ጊዜ በመሆኑ በተለይ በዲጅታል ዲፕሎማሲው ላይ በሚዲያው በኩል በስፋት ሊሰሩበትም ይገባል፡፡
ትንሽ ቁጥር ያላቸው ዲፕሎማቶች ሚዲያው ላይ ወጥተው ጫናው መልኩን እንዲቀይር እንዳደረጉ ታይቷል።አሁንም መደረግ ያለበት ይህ ነው።ብዙ ቁጥር ያለን በመሆኑም በተለያዩ ድረገጾቻችን ላይ የኢትዮጵያን ገጽታ በመገንባቱ ዙሪያ ከመናገር እስከ መጻፍና ትክክለኛውን መረጃ በአካል እስከማሳወቅ ድረስ የደረሰ ተግባር መከወን ያስፈልጋል። ይህ ደግሞ የማንደራደርበት መሆን ይኖርበታል።ምክንያቱም ጥቅምንና ታሪክን ማስከበሪያው ጊዜ ዛሬ ነው።
አዲስ ዘመን፡– አንዳንድ ዲያስፖራዎች አሁንም ለአገራቸው ያላቸው ምልከታ የተጣመመ እንደሆነ በተለያዩ መድረኮች ላይ ሲሳተፉ ይታያል።ከጫና አሳራፊው ወገን የመሰለፍ አዝማሚያም ይታይባቸዋል። ይህ ነገር ምንጩ ምን ይሆን፤ ለምንስ እንዲህ ያደርጋሉ፤ መፍትሄው ምን ሊሆን ይችላል?
ወይዘሮ ሰላማዊት፡– ምንጩ የተለያየ ነው።አንድም የፖለቲካ አስተሳሰብ፣ አንድም ጥቅም ፍለጋ ሊሆን ይችላል።የጠራ መረጃ አለማግኘትም የሚሆንበት አጋጣሚ አለ።በዚህ ዙሪያም የተለያዩ ሥራዎች በኤጀንሲው በኩል እየተሰራ ነው። ለአብነት ዓለምአቀፉ ማኅበረሰብ ስለ ኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ ትክክለኛውን ግንዛቤ እንዲይዝ ዲያስፖራውን የማስተባበር ሥራ እየሰራ ነው።በተጨማሪም የሚዲያ ባለቤቶችና ለሚዲያ ቅርብ የሆኑ ሰዎች፣ የዲያስፖራ ሚዲያዎችና ጉዳዩ የሚመለከታቸው ኢትዮጵያውያን እንዲንቀሳቀሱም ተደርጓል።
የዲያስፖራው ማኅበረሰብ ሠልፍ ከማድረግ ባለፈ ጉዳዩ ለሚመለከታቸው ዓለምአቀፍ ተቋማትና ለመንግሥታት እውነታውን እንዲረዱ ፊርማ አሰባስበው ልከዋልም።አሁንም የውጭ ጫናው እውነቱን በማስረዳት ካልሆነ በሌላ መንገድ ሊፈታ አይችልምና ይህንን ማድረጉ ላይ በርካታ ሥራዎች እየተከናወኑ ናቸው።ወደፊትም ይከናወናሉ።
አዲስ ዘመን፡– የሌሎች አገራት ዲያስፖራዎች ያላቸው ተሞክሮ የፖለቲካውን ወሰን ትተው በአገር ላይ መስራት ነው።ከዚህ አንጻር የእኛ አገር ተሞክሮ ምን ዓይነት ነው ይላሉ?
ወይዘሮ ሰላማዊት፡– ፖለቲካ መሻገሪያ ነው።ብዙ ነገሮችን ለዓለም አገራት ያበረከተችን አገር አኮስሶ መንደር ለማድረግ መሞከር የትኛውም ፖለቲካ የሚደግፈው አይደለም።ፖለቲካ ከአለንበት ከፍ የሚያደርገንና ቢያንስ አለንበት ላይ የሚያቆየን ቢሆንም በደንብ ያልገባቸው ግን ይህንን ሊያደርጉ እንደሚችሉ መታሰብ አለበት።ምክንያቱም በራሳቸው ምህዋር ውስጥ የሚዘወሩ ብዙዎች ናቸው። በዚያ ላይ ቀደም ሲል የነበረው ተሞክሮ ፖለቲካን ከአገር ያለየ ነበር።አንዳንድ ዲያስፖራዎችም በዚህ አስተሳሰብ ብዙ ዓመታትን ዘልቀዋል።ዛሬ በውጭው ዓለም ተቃራኒ ሀሳብ የሚያንጸባርቁትም እነርሱ ናቸው።ነገር ግን ዛሬ ይህ ነገር አለ ብዬ አላምንም።ምክንያቱም ኤጀንሲው ከፖለቲካም ሆነ ከመንግሥት ነፃ ሆኖ ዲያስፖራው ለአገሩ በሚያበረክትበት መልኩ እንዲሰራ እያገዘ ነው።ፖለቲካና አገር ለየቅል የሚጓዙ መሆናቸውንም አውቆ እየተንቀሳቀሰ ነው።
ዲያስፖራውም እንዲያስበው የምንፈልገው ይህንኑ ነው። ምክንያቱም በቀደመ ታሪክ ፖለቲካን እያጧጧፍን አገራችንን ገደል አፋፍ ላይ ጥለናታል።ይህ ደግሞ ከዚሁ መያዝ ካልቻለና መፍትሄ ካልተበጀለት መመለሻው ቀላል አይሆንም።ስለዚህም በተቻለ መጠን ሁሉም ሰው የራሱ የፖለቲካ አስተሳሰብና የሃይማኖት አዲዮሎጂ ይኖረዋል፤ ብሔርም እንዲሁ።ነገር ግን ይህንን ከአገር ሉአላዊነት ጋር ማቀላቀል የለበትም።አገር ከብሔርም ከፖለቲካም በላይ ነውና።
አገርን በፖለቲካ እቅፍ ውስጥ አድርገው የሚመዝኑ ዜጎች ኢትዮጵያዊ ናቸው ለማለት ያስቸግራል።ምክንያቱም አገሩን የሚከዳ፣ ለሌላ ያደረ ስሜት ያንጸባርቃሉ።በራሳቸው መድረክ ብቻ የሚዘወሩም ናቸው።የእነርሱ የፖለቲካ አመለካከት ከአገር ይበልጥባቸዋልም።በዚህም ይሸወዱና አገርን በሚያፈርስ ተግባር ላይ ሊሳተፉ ይችላሉ።እናም ይህን አስተሳሰብ የያዘ ሰው አገርንም ሆነ ዲያስፖራውን አይወክልም።
በውጭ አገር ያሉ አንዳንድ በእነዚህ ዓይነት ሱሶች የተጠመዱ ዲያስፖራዎች በተጠናው ጥናትና በሰው አገር ጥፋት አጥፍቶ መሰወር ስለማይቻል ሲመረምሯቸው በቁጥር አነስተኛ እንደሆኑ ታውቋል።በጣም ዕድሜ ጠገብም ናቸው።ቤተሰብና አድራሻ የሌላቸው ስማቸው እንኳን በቅጡ የማይታወቁም ናቸው።ከአንዱ አገር አንዱ አገር እየተሰደዱ የሚመጡም እንደሆኑ ተደርሶበታል።በጣም በጣት የሚቆጠሩት ደግሞ በፖለቲካው ዓለም የሚታወቁና የገቢ ምንጫቸው ከአገር ጠል አካላት የሆነላቸውም አሉ።እናም በምንም ተአምር አገሩን የሚወድ ሰው አገርን ዳውን ዳውን እንደማይል በዚህ መልኩ ይታያልና ሁለት መልክ ያለው ዲያስፖራ መኖሩ አይቀርም።በአገራችን ሁኔታም ሲታይ ይህ ነው ያለው።
አዲስ ዘመን፡– ዲያስፖራው መንግሥት ሲቀያየር አብሮ የሚቀያየር እንደሆነ በተለያየ መልኩ ይታያል።እዚህ ላይ የእናንተ ኤጀንሲ ሚናው ምንድነው ይላሉ?
ወይዘሮ ሰላማዊት፡– ኤጀንሲው ሲቋቋም በመሠረታዊነት ይህንን ችግር ለመፍታት ነው።ምክንያ ቱም የመንግሥት ወገንተኝነት ሳይሆን የአገር ወገንተኝነት እንደሚቀድም ማንም ይረዳል።እናም ቀደም ሲል የነበረው አስተሳሰብ የእኔን ፖለቲካ አትከተልምና ሂድልኝ፤ እኔን ደጋፊ ነህና ናልኝ ነበር። አንዱን የሚገፋ ሌላውን የሚቀበልም ነው። ስለዚህም ይህ አስተሳሰብ ኢንስቲትዩቱ ላይ መኖር ስለሌለበት የመጀመሪያው ጉዳይ ተደርጎ ተሰርቶበታል።እንዲያውም ሕግም ተደርጎ እየተወሰደ ነው።ማንም የፈለገውን የፖለቲካ አመለካከት ሊይዝ ይችላል።ወደ ኤጀንሲው ሲመጣ ግን ኢትዮጵያዊና ዲያስፖራ መሆን ብቻ ነው የሚጠበቅበት።በዚህም መርህ ብቻ ነው እያስተናገድን ያለነው።
ኤምባሲዎች ውስጥ ሲሄዱም ማንንም በፖለቲካ አስተሳሰቡ እንዲያገሉት መደረግ የለበትም በሚል ነው እየሰራን የምንገኘው።ሁሉም ዜሮ ፖለቲካ በሆነ መንገድ እንዲሰራም እያበረታን ነው።መሆንም ያለበት ይህ ብቻ ነው።ምክንያቱም አገር ከፖለቲካ በላይ ነች።አገር ከመንግሥትም በላይ ነች።ዛሬ መንግሥት የነበረ ነገ ላይኖር ይችላል።አገር ግን መቼም የማትቀየርና ዘላለማዊት ነች።ሁሉም የሚጫወትበት ኳስ የሚኖረው ሜዳው ሲኖር ነውና አገርን ማስቀደም ለሁሉም ነገር ይበጃል።ስለዚህም የኤጀንሲው ዋና ሥራ ሜዳውን እንጠብቅ፣ ለሜዳው እንጠንቀቅለት ነው።በዚህም በተቻለ መጠን አገራዊ አስተሳሰቦችን በመፍጠርና አገራዊ መግባባቶችን በማምጣት ይሰራል።
በሰሜኑ አካባቢ የተፈጠረውን ችግር ብቻ እንኳን ብናነሳ ብዙ የፖለቲካ አጀንዳ የታየበት ነው።ሆኖም ኢትዮጵያን የሚያጠለሽ ተግባር የሚከውነውን ዝም ብሎ የሚታገስ አይደለም። ምክንያቱም ፖለቲካ ሳይሆን አገር ነው እየተሰደበ ያለው። በዚህም ዲያስፖራው በነቂስ ወጥቶ ተቃውሞውን እያሰማ ይገኛል።ስለሁኔታውም እያስረዳ ነው።በተለይ ስለአገሩ ትክክለኛ ምንነት በሚገባ ተናግሯል።ስለዚህም አገርን በመገንባት፣ አገርን በመደገፍ፣ አገርን በማስተዋወቅና በአገር ላይ የመጡ ችግሮችን በመቃወም መስመራቸውን እንዲያስተካክሉ በማድረግ ይሰራል።
የህዳሴ ግድቡ የማንም ፖለቲካ አቀንቃኝ አይደለም። የኢትዮጵያውያን ነው።እናም ከእያንዳንዷ እናት መቀነት ወጥቶ እየተገነባ ያለን ህዳሴ ማንም ሲዘልፈውና አይቻልም፣ አይገነባም ወዘተ እያለ ሲቃወመው ዲያስፖራው ፖለቲከኛ አይደለሁም ብሎ ዝም ሊለው አይችልም።ምክንያቱም ጉዳዩ የአገር ነው።
አዲስ ዘመን፡– በቀጣይ አገርን በውጭው ዓለም ታዋቂና ተሰሚነት ያላት ከማድረግ አኳያ ምን ለመስራት ታስቧል ?
ወይዘሮ ሰላማዊት፡– ኤጀንሲው ከተጀመረ ሁለት ዓመት የሞላው ቢሆንም በርካታ እቅዶች ግን ይዟል።ከእነዚህ መካከልም አገራዊ ጥሪና ፕሮጀክቶች ላይ በስፋት መሳተፍ የመጀመሪያው ነው።ኤጀንሲው የብድር አማራጭ ከሚያመቻቹ ባንኮችና የቢዝነስ ሀሳብ ካላቸው የመንግሥት አነስተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪ ዘርፍ ተቋማት ጋር በመሆን አነስተኛና መካከለኛ ገቢ ያላቸውና በመካከለኛው ምሥራቅና በአፍሪካ የሚገኙ ዲያስፖራዎች በአነስተኛና መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ እንዲሰማሩ ለማስቻል ያለመ ሥራ ይሰራል።ለዚህ ደግሞ ፓኬጅ አዘጋጅቷል።
ይህ ፓኬጅ ዲያስፖራዎቹ ያካበቱትን ገንዘብና ልምድ ለአገራቸው እድገት እንዲያውሉትና ሀብታቸውም እንዳይባክን ይረዳቸዋል።በአገራዊ የልማት ሥራዎች በመካከለኛው ምሥራቅና በአፍሪካ የሚገኙ ዲያስፖራዎች ተሳትፎ ከፍተኛ እንዲሆንም ያደርጋል። ምክንያቱም ለአብነት ገቢያቸው አነስተኛ ቢሆንም በኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ በከፍተኛ ሁኔታ ተሳትፈዋል።ይህ የሚያሳየው ከብዛታቸው አንጻር ብዙ ሀብት መኖሩንና በአንድ ላይ በማሰባሰብ በፓኬጅ ቢደራጁ ለአገር ኢኮኖሚ ዕድገት ውጤት እንደሚያመጡ ነው።ስለዚህም በአገር የኢኮኖሚ ዕድገት የድርሻቸውን እንዲወጡ የኢንቨስትመንት አማራጮች እንዲቀርብላቸው እየተሰራ ነው።
ሌላው ሊሰራበት የታሰበው የዳስ ትምህርት ቤቶችን የመቀየር ተግባር ላይ መሰማራት ሲሆን፤ ፕሮጀክቶችን ከየአካባቢው እያሰባሰብን እንገኛለን።ከሚመለከተው አካል ጋር ምክክር ተደርጎም የማስተዋወቅ ሥራ ብቻ ቀርቷል።በተመሳሳይ ሥራው ምንም እንኳን የሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሆንም በውጭ ያለውን የሥራ ዕድል የማወቁ ጉዳይ የእኛ በመሆኑ ያለውን ዕድልና የሥራ አማራጩን በማየትና በማጥናት እናሳውቃለን።ስምምነት እስከመፈራረም የሚያደርሱ ሥራዎችን እንሰራለን።
የተፈራረምነው ስምምነት ላይ ችግር ካለም በምክክር እንዲፈታ የማድረግ ሥራን ከውጭ ጉዳይ ጋር በመሆን እንሰራለን።ከዚህ በፊት የኢትዮጵያን ባለሙያዎች የማያውቁ አገራትን ጭምር በመዳሰስ በርካታ ባለሙያ ስላለን እዚያ ሄደው የሚሰሩበትን አማራጭ ለመጠቆምም ይሰራል።
አዲስ ዘመን፡– የሚያስተላልፉት መልዕክት ካልዎት?
ወይዘሮ ሰላማዊት፡– መልዕክቴ የሚሆነው ለሁለት አካላት ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ ላሉና ውጭ ለሚኖሩ ነው።ኢትዮጵያውያን ብዙ ጸጋ ያለን፤ ትልቅና ታሪክ ያለንም ነን።ስለዚህም በአገር ውስጥ ያለነው ሰዎች ከመለያየት ይልቅ አንድ መሆንን፣ መግባባትን፣ መዋደድን፣ መደማመጥን ማምጣት መቻል አለብን።ይህ ካለን ከዚህ የተሻለ መስራት እንችላለን።ዛሬ በጣም ከፍተኛ ችግር የሆነብን ነገር ብንነጋገር የምንፈታው ነው። እናም ለመነጋገር ቅድሚያ እንስጥ።
በውጭ የምንኖር ኢትዮጵያውያን ደግሞ ዛሬ ላይ ያለችን ይህቺ አገር አገር አለችን ብለን ደረታችንን ነፍተን እንድንጓዝ ያደረገችን ነች።ይህ የሆነው ደግሞ በቀደሙ አባቶች መሰዋዕትነት ነው።እናም አንዲት አገራችንን ለማቆየት ደግሞ አንድ ሆነን መነሳት ለነገ የምንለው አይደለም።ምክንያቱም ዞሮ መግቢያችን ናት።ነገ ለልጆቻችን የምናሳያት ናት።ስለዚህም በምንችለው ሁሉ መደገፍ መቻል አለብን።
ለኢትዮጵያ ዘብ መቆምም የሁልጊዜ ሥራችሁ መሆን ይኖርበታል እላለሁ።ምክንያቱም ትናንት በጣም ከፍ ያለ አገር ያላቸው ፤ በጣም የሚኮሩባት አገር ያለቻቸው ዛሬ በየመንገዱ ወድቀው አይተናል።እነዚህ ሰዎች በሰው አገር እንዴት ተጥለው እንዳሉም እናውቃለን።አገር ያለውና የሌለው እኩል ክብር የለውምና ለተሻለች ኢትዮጵያ የመስራት ጊዜው አሁን ነው።
አዲስ ዘመን፡– ስለሰጡን ማብራሪያ እናመሰ ግናለን።
ወይዘሮ ሰላማዊት፡- እኔም አመሰግናለሁ።
አዲስ ዘመን መጋቢት 24/2013