አዲስ አበባ፡- መጻኢውን የአፍሪካ ተስፋ ወደ ተሻለ ደረጃ ለማሸጋገር በአህጉሪቱ የተጀመሩ የማሻሻያ ሥራዎች በተሻለ አፈጻጸም እንደሚቀጥሉ የወቅቱ የአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበር የግብጽ ፕሬዚዳንት አብዱልፈታህ አል ሲሲ ገለጹ፡፡
ፕሬዚዳንት አብዱልፈታህ አል ሲሲ 32ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባዔ ትናንት ምሽት ሲጠናቀቅ እንደገለጹት፤ መሪዎቹ የሠላምና የጸጥታ ጉዳዮችን ጨምሮ እየተሠሩ ባሉ የህብረቱ ማሻሻያ ሥራዎች ላይ ተወያይተው ውሳኔዎችን አሳልፈዋል፡፡
የአፍሪካን ችግሮች በሚመለከት በዋናነት በቀጣይ ዓመታት እንዲሠሩ የተለያዩ ውሳኔዎች መተላለፋቸውን ጠቅሰው፣ በዚህም በአፍሪካ የተጀመሩ የማሻሻያ ሥራዎች በተሻለ አፈጻጸም ተግባራዊ እንደሚደረጉ ገልጸዋል፡፡
ህብረቱን ከመከረባቸው ዋና ዋና ጉዳዮች የሰላምና ደህንነት ጉዳይ አንዱ መሆኑን ጠቅሰው፣ በዚህም በቀጣይ ዓመታት አፍሪካን ሠላማዊ ለማድረግና አፍሪካውያንን ከውስጣዊም ሆነ አካባቢያዊ ግጭት ለመከላከል የተጀመሩ ሥራዎች በተጠናከረ መልኩ እንደሚፈጸሙ አስታውቀዋል፡፡
የአፍሪካ ህብረትን ለአፍሪካውያን በሚመጥን መልኩማደራጀት የሚለው ሌላው የጉባዔው ጉዳይ እንደነበር ጠቅሰው፣ ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮችን በማጠናከር አፍሪካን ትልቅ የማድረግ ሥራው በዘላቂነት እንደሚተገበር ጠቁመዋል፡፡ በተለይም የአፍሪካ የልማት ተቋማት በአህጉሪቱ ጉዳይ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ የማስቀጠሉ ሥራ እንደሚከናወን ተናግረዋል፡፡
ሊቀመንበሩ እንዳሉት፤ ሁሉም የአፍሪካ አገራት በጋራ ሊያድጉ የሚችሉባቸው አቅጣጫዎች በጉባኤው ላይ ተነስተዋል፡፡ የዘንድሮ መሪ ሀሳብ ሆኖ ለተመረጠው የስደተኞችና የተፈናቃዮች ጉዳይ መፍትሄ ለመስጠትም በትኩረት ይሠራል፡፡ በአፍሪካ ያሉና የተጀመሩ ኢኮኖሚያዊ ውህደቶች በፖቲካዊ ውህደት ጭምርም ያድጋሉ፡፡ ለዚህም 32ኛው የአፍሪካ ህብረት ጉባዔ ያሳለፋቸው ውሳኔዎች በሙሉ ተግባራዊ ለማድረግ በቁርጠኝነት ይሰራል፡፡
‹‹የአፍሪካ አገራት በመሰረተ ልማት ትስስራቸው የላቀ ደረጃ ላይ እንዲደርሱ ይሰራል፡፡ በዚህም የተጀመረውን የባቡር ትራንስፖርት ትስስር ቀጣይነት ባለው መልኩ በማሳደግ ረገድም ትኩረት ተሰጥቷል፡፡ በአፍሪካ የሚደረገውን አጠቃላይ የለውጥ ሥራ ለማሳካት የአፍሪካ የልማት ተቋማትን ማጠናከር ይገባል›› ብለዋል፡፡
በጉባኤው ማጠናቀቂያ ላይ በሳይንሳዊ ፈጠራዎች ላይ ውጤታማ ለሆኑ አፍሪካውያን ሽልማት ተበርክቷል፡፡
በጉባኤው ላይ የህብረቱ አባል ሀገሮችን መሪዎችን ጨምሮ፣ የሀገሮች ተወካዮች፣ የዓለም አቀፍና አህገራዊ ተቋማት ኃላፊዎችና ተወካዮች እና ተዋቂ ሰዎች ተገኝተዋል፡፡
ለመሪዎቹ እና ለተሳታፊዎቹ በጉባዔው ዋዜማ ምሽት በአዲሱ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ስካይ ላይት ሆቴል የእራት ግብዣ ተደርጓል፡፡ በሥነ ሥርዓቱ ላይም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ንግግር አድርገዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከጉባዔው ጎን ለጎን ከግብፁ ፕሬዚዳንት አብዱልፈታ አል ሲሲ እና ከሱዳኑ ፕሬዚዳንት ዑመር አልበሽር ጋር በጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት ተወያይተዋል፡፡ በተመሳሳይ ከሌሎች ሀገሮች መሪዎችና የዓለም አቀፍ እና አህጉር አቀፍ ተቋማት ኃላፊዎች ጋር መክረዋል፡፡
አዲስ ዘመን የካቲት 5/2011
በአዲሱ ገረመው