ወርቅነሽ ደምሰው
በውጭ ሀገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የሀገራቸውን መፃኢ ተስፋ እየናፈቁና በቅርብ ርቀት እየተከታተሉ ቆይተዋል ።ለዚህ ማሳያው የተለያየ ቢሆንም በተለያየ መልኩ በአገሪቱ ባሉ እንቅስቃሴዎች ላይ የሚያደርጉት ተሳትፎ ተጠቃሽ ነው ።ምንም እንኳ ቀደም ሲል የነበረውን የፖለቲካ እንቅስቃሴ በመቃወም የዲያስፖራ አባላት በሀገራቸው በሚካሄዱ የልማት ሥራዎች ላይ ያላቸው ተሳትፎ እምብዛም እንዳልነበረ መረጃዎች ያሳያሉ ።ነገር ግን ደግሞ ተቃውሟቸውን በመግለፅ በስፋት ቢታዩም፤ 10 ዓመታትን ያስቆጠረው የታላቁ ህዳሴ ግድብ ላይ ግን ድጋፋቸው የተለየ እንደነበር አይዘነጋም።
ቀጥሎም ኢትዮጵያ የጀመረችውን ሀገራዊ የለውጥ ጉዞን ተከትሎ ደግሞ ተስፋቸው ማበብ በመጀመሩ ተስፋ ሰንቀው ፊታቸው ወደ ሀገራቸው በማዞር ላይ ይገኛል ።በተለይ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የዲያስፖራው ተሳትፎ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱ ሲነገር፤ አሁን ላይ ለውጡን ተከትሎ ዲያስፖራው ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ከፍተኛ መነሳሳት በማሳየት በግል ሆነ በጋራ ያላቸው ተነሳሽነት ጨምሮ ኢንቨስት በማድረግ እንዲሁም ሀገራዊ ፕሮጀክቶችን በመደገፍ ከፍተኛ የሆነ ተሳትፎ እያደረጉ እንደሚገኙ እየተገለፀ ነው።
የዲያስፖራ አባላት በሀገራቸው ጉዳዮች ዙሪያ ወደ ኋላ ሳይሉ በተለያዩ ጊዜ እጃቸውን በመዘርጋት በሚያደርጉት ድጋፍና እርዳታ ከሀገራቸው ጎን በመቆም አለኝታነታቸውን እያስመሰከሩ ይገኛሉ። ለዚህ ምስክርነት ለማይሻው ተግባር ማሳያዎቹ በርካታ ናቸው። የዚህ ፅሁፍ ማጠንጠኛ ዲያስፖራው በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ላይ እያሳረፈ ያለው አሻራ የሚያስቃኝ ነው ።
የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የመሠረተ ድንጋይ ከተጣለበት ጊዜ ጀምሮ በሀገር ውስጥ ያሉ ሆነ በውጭ የሚኖሩ በርካታ ኢትዮጵያውያንና ትውልድ ኢትዮጵያውያን የራሳቸውን አሻራ ለመጣል ያላቸውን ሁሉ በመስጠት አስተዋጽኦ አድርገዋል፤ እያደረጉም ይገኛሉ ። ዲያስፖራው ለዘጠኝ ዓመታት ያህል በቦንድ ግዥና ስጦታ በመስጠት ተሳትፎ እያደረገ መቆየቱ የሚታወስ ቢሆንም፤ ከለውጡ በፊት የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ችግር ውስጥ ገብቶ በነበረበት ወቅት ዲያስፖራው ጥርጣሬ ውስጥ ገብቶ እንደነበር የሚታወስ ነው።በዚህ የተነሳ ዲያስፖራው ለግድቡ እያደረገ የነበረው የተሳትፎ መጠን ቀንሶ ነበር ።ሆኖ ግን ከለውጡ በኋላ በመንግሥት በተደረገው ርብርብ ደግሞ ግድቡ አንሰራርቶ የግድቡ የመጀመሪያ ዙር የውሃ ሙሌት መተግበሩ ሲታይ የቀድሞ ተፈጥሮ የነበረውን ችግር ወደ ጎን በመተው ዲያስፖራው ለሀገሩ ያለውን ፍቅር አገርሽቶበት እንደገና በመነሳሳት በማሳየት ገንዘብና ሀብቱን በመስጠት በተለያየ መልኩ ተሳትፎ እያደረገ ይገኛል።
የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ሰላማዊት ዳዊት እንደሚናገሩት፤ በተለይ ከውሃ ሙሌቱ በፊት ተቀዛቅዞ የቆየው የዲያስፖራው ተሳትፎ በተወሰነ መልኩ ቀንሶ ነበር ።ከግድቡ ውሃ ሙሌት በኋላ ግን በአጭር ጊዜ ውስጥ ብዙ ገንዘብ የተሰበሰበበት ሁኔታ አለ።
ኤጀንሲው በ2013 በጀት ዓመት 200 ሚሊዮን የሚጠጋ ብር ለመሰብሰብ ያቀደ መሆኑን የሚናገሩት ዋና ዳይሬክተሯ፤ በዘንድሮ ዓመት በመጀመሪያው በስድስት ወራት ውስጥ ለኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ 76 ሚሊዮን ብር የተሰበሰበ ሲሆን፤ ከአምና የበጀት ዓመቱ አፈጻጸም ጋር ሲነጻጸር የዘንድሮው የመጀመሪያው ስድስት ወራት የ43 ሚሊዮን ብር ልዩነት እንዳለው ይጠቁማሉ።ስለሆነም በዘንድሮ የመጀመሪያ ስድስት ወሩ ለመሰብሰብ ከታቀደው ብር በላይ መሰብሰቡን አብራርተዋል ፡፡
ኤጀንሲው በህዳሴ ግድብ ዙሪያ ዲያስፖራው የሚያደርገው ተሳትፎ አጠናክሮ ለማስቀጠል የግድቡን አሁናዊ ሁኔታ በተመለከተ ግንዛቤ ለማስፋት በርካታ ተግባራት እያከናወነ ይገኛል። በቅርቡም በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ ‘ግድባችን የዘመኑ አድዋችን’ በሚል ርዕስ በካናዳ በበይነ መረብ አማካይነት ውይይትና የሃብት ማሰባሰብ መርሃ ግብር መደረጉ የሚታወስ ነው።
ዋና ዳይሬክተሯ ወይዘሮ ሰላማዊት ዳዊትና የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ በክብር እንግድነት ተገኝተው መልዕክት አስተላልፈዋል። እንደዋና ዳይሬክተሯ ገለጻ፤ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን ጨምሮ ለልዩ ልዩ ሃገራዊ ፕሮጀክቶችና ጥሪዎች በገንዘብም ሆነ በፐብሊክ ዲፕሎማሲ ዘርፍ እያደረጉ ላለው ድጋፍ አመስግነው፣ ይኸው ድጋፋቸው ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አሳስበዋል ።
የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ክቡር አምባሳደር ዲና ሙፍቲም በበኩላቸው ባስተላለፉት መልዕክት ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብና አድዋ ኢትዮጵያውያን አንድነታቸውን ያስመሰከሩባቸው ክስተቶች መሆናቸውን አንስተው፣ ዲያስፖራውም በዘመናችን አድዋ ላይ አሻራውን ለማሳረፍ የጀመራቸውን አበረታች ስራዎች አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል ።
በወቅቱ በካናዳ በተደረገ የሃብት ማሰባሰብ መርሃ ግብር ከ128 ሺ በላይ ዶላር መሰብሰቡን ነው ከኤጀንሲው ድረ ገጽ ያገኘነው መረጃ የሚያሳየው ።ባለፈው ሳምንት የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት የቦንድ ሳምንት አስመልክቶ ለኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን እንዲሁም የኢትዮጵያ ወዳጆች ሁሉ ባቀረበው ጥሪ መሠረት የቦንድ ሳምንት በነቂስ በመሳተፍ ከ50 ብር እና 100ብር ጀምሮ አቅማችሁ በፈቀደ መጠን ለራሳቸው፣ ለልጆቻችው እንዲሁም ለወዳጆቻቸው ሰዎች ጭምር የቦንድ ግዥ በመፈፀምና በስጦታ ማበርከት የሚችሉ መሆኑ ገልጿል ።
አሁን ላይ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የመሠረተ ድንጋይ ከተጣለበት መጋቢት 24 ቀን 2003 ጀምሮ ዘንድሮ አሥረኛ ዓመቱን ለማክበር በዝግጅት ላይ ይገኛል ።ግድቡ በኢትዮጵያውያን የሚሰራ እንደመሆኑ መጠን ግንባታው እስከሚጠናቀቅ ድረስ ያለውን አስተዋፅኦ አጠናክሮ ለማስቀጠል በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ለግድቡ የሚያደርጉት ተሳትፎ በማበረታታት ያላቸውን ተነሳሽነት አጠናክሮ እንዲቀጥሉ ለማድረግ ብርቱ ሥራ መስራት ይጠበቃል ።
አዲስ ዘመን መጋቢት 22/2013