ታምራት ተስፋዬ
ግዙፉ የማህበራዊ ሚዲያ አውታር ፌስቡክ፣ሰዎች ጓደኛ የሚያፈሩበት፤ስሜት፤ሃሳብና እውቀታቸው የሚለዋወጡበት፤ የሚያሰራጩበትና የሚስተላልፉበት ነው።መድረኩ መልካምና ገንቢ እሳቤዎችን የሚንሸራሸሩበትን ያህል እኩይ ተግባራትም ይስተዋሉበታል።
ከሰላም ይልቅ ጦርነት፣ ከፍቅር ይልቅ ጠብ፣ከልማት ይልቅ ጥፋትን የሚሹ የተለያየ ፍላጎትና ተልእኮ ያላቸው ግለሰቦች፣ቡድኖችና ፓርቲዎችም ዓላማቸው ለማስፋፋት ብሎም ለማሳካት ማህበራዊ ሚዲያውን ተመራጭ ያደርጉታል ። ግለሰብን፣ሕዝብንና አገርን የሚዘልፉና የሚያፈርሱ መልእከቶችን ያስተላልፉበታል።
ፌስቡክ በአንፃሩ ደህንነቱ የተጠበቀና ከስህተት የፀዳ አገልግሎት ለማቅረብ እንደሚተጋ በተደጋጋሚ ከማሳወቅ ባሻገር ሕገ ደንቦችን በማውጣት የተለያዩ የቁጥጥር እና ክልከላ ተግባራትን እያደረገ መሆኑን ሲገልጽ ቆይታል።፡ይሑንና አንዳንድ ግለሰቦች እና ተቋማት በጥላቻ የተሞሉ ፅሁፎችና አሳሳች መረጃዎች በፌስ ቡክ ገፁ ላይ በስፋት ስለመሰራጨታቸው ቅሬታ ሲያቀርቡ ይሰማል።
ባሳለፍነው ሳምንትም መቀመጫውን በፈረንሳይ ፓሪስ ያደረው ሪፖርተርስ ዊዛውት ቦርደርስ የተባለ ተቋም ማህበራዊ ሚዲያው በገፁ ላይ ከፍተኛ የጥላቻ ንግግር እና የተሳሳተ መረጃ በስፋት እንዲተላለፍበት ፈቅዷል ሲልም ወንጅሎታል ። የሲ ኤን ኤኑ ፀሐፊ ቻርልስ ሪሊ እንዳተተውም፣ ተቋሙ ፌስቡክ ተጠቃሚዎችን ከጥላቻ ንግግር መጠበቅ አልቻለም በሚል ክስ መስርቷል።
ተቋሙ ለፍርድ በሚያቀርበው የቅሬታ መዝገብ ክስ የባለሙያዎች ትንታኔ፣የግለሰቦችን ምስክርነት መግለጫ እንዲሁም ቀደም ሲል በማህበራዊ ሚዲያው ይሰሩ ከነበሩ የነበሩ ግለሰቦችን በማስረጃነት እንደሚያቀርብም አሳውቋል።
ክሱ ፈረንሳይ ውስጥ ያለውን ስራ የሚያከናውንባቸው ቅርንጫፎቹ የሆኑት ፌስቡክ ፈረንሳይ እና ፌስቡክ አየርላንድ ላይ ያነጣጠረ ነው ። ክሱ በተለይም በገጹ በጋዜጠኞች ላይ የተቃጣው የጥላቻ መልእክት እና የግድያ ዛቻ እንዲሁም በኮሮና ቫይረስ ላይ አተኩሮ በተሰራ ሀሰተኛ መረጃን ላይ ያተኮረ መሆኑም ተመላክቷል።
ፌስቡክ በፈረንሳይ ከ38 ሚሊዮን ተጠቃሚ ያለው ሲሆን 24 ሚሊየን የሚሆኑት ደግሞ እለት ተእለት የማህበራዊ ተጠቃሚዎች ናቸው ። በፈረንሳይ ሕግ መሰረት አሳሳች የሆኑ የንግድ ተግባራትን ያከናወኑ ድርጅቶች 10 በመቶ የሚሆነው ዓመታዊ ገቢያቸውን በቅጣት መልክ እንዲከፍሉ ይገደዳሉ።
ፌስቡክ በመላው ዓለም የሚገለገልበት የአጠቃቀም ደንቦቹ ተመሳሳይ እንደመሆናቸው መጠንም የፈረንሳይ ፍርድ ቤት ውሳኔ ዓለም አቀፍ ተፅእኖ ሊኖረው እንደሚችልና ሌሎች ሀገራትም ይህን በአርዓያነት ወስደው ተመሳሳይ ክሶችን ሊመሰርቱ እንደሚችሉ ተጠቁማል።
አንዳንድ መገናኛ ብዙኃን ማህበራዊ ሚዲያው በጥላቻ የተሞሉ ፅሁፎችና አሳሳች መረጃዎች እንዲሳለጡ መደላድልን ፈጥራል፣ በተለይ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝም የተመለከቱ የተሳሳቱ እና አደገኛ መረጃዎች ዋነኛ ምንጭ ሲሆን ታይቷል የሚል ዘገባን አስነብበዋል።
በሪፖርተርስ ዊዛውት ቦርደርስ ለቀረበበት ቅሬታ እና ክስ በቃል አቀባዩ በኩል መልስ የሰጠው ፌስቡክ፣ በገፁ ላይ ማናቸውም አደገኛ እና በጥላቻ የተሞሉ ፅሁፎችና አሳሳች መረጃዎች መለጠፍ በምንም አይነት መልኩ ተቀባይነት ብሎም ምህረት የሌለው ስለመሆኑ አፅእኖት ሰጥቶታል።
መረጃዎቹ በገፁ ላይ እንዳይንሸራሸሩ ለመገደብም ከፍተኛ ገንዘብ በመመደብ የተለያዩ ተግባራት ማከናወኑን በተለይም የደህንነት ተቆጣጣሪ ባለሙያዎቹን ቁጥር በሶስት እጥፍ በመጨመር 35 ሺ ማድረሱን አሳውቃል።
ከኮሮና ቫይረስ ጋር በተገናኘም ከ 12 ሚሊየን በላይ የሚሆኑ አደገኛ እና ተሳሳቱ መረጃዎች ከገፁ ላይ ማጥፋቱን አሳውቃል። በቀጣይም በጥላቻ የተሞሉ ፅሁፎችና አሳሳች መረጃዎች የመለጠፍ ወንጀሎችን ውጤታማ በሆነ መልኩ ሙሉ በሙሉ ለማስቆም ጥናቶችን መሰረት በማድረግ ባለሙያዎችን በመመደብ እና የተለያዩ ቴክኖሎጂዎችን እንደሚጠቀምም አረጋግጧል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 21/2013