
- ስፖርታዊ ውድድሮችን በክረምት ወራት ማካሄድ አዳጋች በመሆኑ ስፖርታዊ ፉክክሮች እምብዛም ናቸው። በዚህም ምክንያት የክረምት ወራት በተለይ ከቤት ውጪ ለሚከወኑ ስፖርቶች የእረፍት ጊዜ ነው።
በዝናብና ከፍተኛ ቅዝቃዜ ምክንያት የተለያዩ ውድድሮች ብቻም ሳይሆኑ ለወትሮ የሚከወኑ ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎችም ሲቋረጡ ማየት የተለመደ ነው። የበጋው የአየር ሁኔታ አመቺነት ብዙዎችን አካላዊ እንቅስቃሴ እንዲያደርጉ የሚያነሳሳ እንደመሆኑ የክረምትን መግባት ተከትሎ ግን መሰል እንቅስቃሴዎች በቤት ውስጥ ይገደባሉ።
በየትኛውም ሁኔታ ውስጥ አካላዊ ጤናን በስፖርት መጠበቅ አስፈላጊ ቢሆንም በክረምት ወቅት ከቤት ይልቅ ውጪ ላይ ማከናወኑ የተሻለ እንደሚሆን ባለሙያዎች ይመክራሉ። ነገር ግን በቅዝቃዜ ምክንያት ከሚመጣውና በሳይንሳዊ አጠራሩ ‹‹ሃይፖተርሚያ›› ከሚባለውና ሌሎች መሰል ሕመሞች እንዳይጋለጡ አስቀድሞ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚያሻም ያሳስባሉ። ጊዜውንና ሁኔታውን አስቀድሞ በመለየት እንዲሁም አስፈላጊውን ቅድመ ጥንቃቄ በማድረግ ከቤት ውጪ ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎችን መከወን በበጋ ወቅት ከሚገኘው የጤና ጥቅም በላይ እንደሚያስገኝም የሃርቫርድ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎች ይጠቁማሉ።
ከወቅቱ የአየር ሁኔታ አንጻር ስፖርተኞች የተለያዩ ጥቅሞችን ለማግኘት እንደሚመርጡት መረጃዎች ይጠቁማሉ። አትሌቶችና እግር ኳስ ተጫዋቾች በተለይ የሚመርጡት የማገገሚያ መንገድ የሆነው በበረዶ የመዘፍዘፍ ሂደት በዚህ ወቅት የተመቸ ይሆናል። በልምምድ የደከመ ሰውነትን ለማነቃቃት፣ የሰውነት መቆጣትን ለመቀነስ እንዲሁም እብጠትን ለማጥፋት ተመራጭ የሆነው ይህ ተፈጥሯዊ ሂደት በጣም ታዋቂ ነው።
በክረምት ወቅት አካላዊ ጥንካሬ የሚጨምር ሲሆን፤ የልብ ምትም በቅዝቃዜው ምክንያት ይቀንሳል፣ ተጨማሪ ጉልበት የማይጠይቅ በመሆኑም የሰውነት ላብም ከወትሮው ይቀንሳል። የምግብ መፈጨት ሂደትን ለማፋጠን እንዲሁም ሰውነት ስብን በማቃጠል ወደ አስፈላጊ ኃይል የሚቀይር በመሆኑ ክብደትን ለመቀነስ የተሻለ ወቅትም ነው። ስፖርታዊ እንቅስቃሴ ከሚያስገኘው አካላዊ ጤና በዘለለ ከወቅቱ ጋር ተያይዞ ብዙዎች ላይ ሊከሰት የሚችለውን የድባቴ ስሜት ሊያስወግድ እንደሚችልም ነው በሃርቫርድ ዩኒቨርሲቲ የስፖርት ሕክምና ረዳት ፕሮፌሰር የሆኑት ዶክተር አዳም ቴንፎርድ የሚያመላክቱት። በእንቅስቃሴ ወቅት በአዕምሮ ውስጥ የተለያዩ ኬሚካሎች የሚፈጠሩ በመሆኑ ድብርትን የሚያጠፉ ሲሆን፤ በሽታን የመከላከል አቅምንም ይጨምራል።
የክረምት ወቅት በተነጻጻሪነት ለጉዳትና አደጋ ሊያጋልጥ እንደሚችል ባለሙያዎች ይጠቁማሉ። በመሆኑም አስቀድሞ አካልን ማሟሟቅና ማሳሳብ የግድ ነው። ይህንንም ወደ ውጪ ከመውጣት አስቀድሞ ለ10 ደቂቃ ያህል በመከወን ሰውነት ሙቀት እንዲያገኝ በማድረግ ውጪ ላይ ወደሚደረገው ቀጣዩ እንቅስቃሴ ማለፍ ይገባል። በዚህም ወቅት ሰውነትን በተለይም በተገቢ ሁኔታ መሸፈንና ለእንቅስቃሴው አመቺ የሚሆን አልባሳትን መለየት ያስፈልጋል። በተለይ ጭንቅላትን፣ እጅንና እግርን መሸፈን እንዲሁም የማያዳልጥ ጫማ መጠቀምም ያስፈልጋል። የትኛውም ስፖርታዊ እንቅስቃሴ በሚከወንበት ወቅት ራስን ከድርቀት መጠበቅ መሠረታዊ ጉዳይ በመሆኑ የመጠማት ስሜት ባይኖርም ፈሳሽ ነገሮችን መጠቀም የግድ መሆኑን የምታሳስበው ደግሞ በኮሎምቢያ ዩኒቨርሲቲ መምህር ዶክተር ሞርጋን ቡስኮ ናት።
ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎቸው ካላቸው ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎች አንጻር በበጋ ብቻ የተገደቡ ከማድረግ ይልቅ በክረምትም በመደበኛነት ማከናወን አስፈላጊ መሆኑን ባለሙያዎች ይስማማሉ። ይሁን እንጂ አካላዊ እንቅስቃሴ የሚደረግበትን ጊዜ፣ ሁኔታና ቆይታውን መገደብ የግድ ነው። ሰውነትን ማዳመጥ፣ እንደ አስምና የልብ ሕመም ካሉም አስቀድሞ ያሉበትን የጤና ሁኔታ ማረጋገጥም ይገባል። በክረምት ወራት በተለይ እንደ ሩጫ እና ርምጃ ያሉ እንቅስቃሴዎች የሚመከሩ ሲሆን እንደ ብስክሌት መጋለብ ያሉት ደግሞ ከፍተኛ ጥንቃቄና ቦታ መምረጥ የሚያስፈልጋቸው ናቸው።
በብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን እሁድ ሐምሌ 6 ቀን 2017 ዓ.ም