አስመረት ብስራት
ወላጆች እንዴት ሰነበታችሁ? መቼም ሰው ራሱን ከተካ በኋላ ልጁ በአግባቡ በአካልም በስነ ልቦናም ጎልብቶ አንዲያድግለት ይፈልጋል። ሁሉም ወላጅ የራሱን ጥረት ያደርጋል፤ ነገር ግን በእውቀትና በክህሎት የታገዘ የልጆች አስተዳደግ እንዲኖር ለማድረግ የባለሙያ እገዛ ያስፈልጋል። ይህን ጭንቀታችንን በእውቀት እንድንቀንስ ለዛሬም በልጆች አስተዳደግ ላይ ከተፃፉ ፅሁፎች ውስጥ መርጠን አቅርበንላችኋል።
ከልጆቻችን ጋር ስለስሜት/ቶች መወያየት ማውራት እጅግ ጠቃሚ ነው! መጀመሪያ ግን ወላጅ ወይም አሳዳጊ ስለ ስሜት ጠቅላላ እውቀት እና ስለእራሱ ስሜት ብቁ እውቀት ሊኖረው ይገባል። ስሜት ልጅም አዋቂም በግሉ የሚለማመደው ነው፤ በአእምሯችን ውስጥ የሚከናወን እንቅስቃሴ ሲሆን ከምናስበው ሀሳብ ጋር እና ከማህበራዊ ህይወት ጋር ትልቅ ቁርኝት አለው። ለምሳሌ የመራብ፣ የመጠማት፣ የመብረድና የማዘን ስሜት የግል ሲሆን ሌላ ሰው ሲወድቅ ወይም ሲያዝን የሚሰማን እና የምንጋራው ስሜት ነው።
አንድ ልጅ ሲያለቅስ “ዝም በል አታልቅስ፤ ይሄ ያስለቅሳል?” ማለት ትክክል አይደለም። ምክንያቱም የግል ስሜቱን አለማክበር ወይም አለመገንዘብ ነው። ቢቻል በጥልቅ ስሜቱን ለመረዳት መሞከር ጥሩ ነው። በልጆች ላይ የምናያቸው እና የማናያቸው ስሜቶች አሉ፤ ለምሳሌ ሲነጫነጩ የምናየው መነጫነጫቸውን ነው፤ ከዚያ ጀርባ ግን ምን ይኖራል? ናፍቆት፣ ረሀብ፣ ድካም እና የተለያዩ መንስኤዎች ሊኖሩ ይችላሉ። ልጆች ብዙ ጊዜ ሆዴን አመመኝ ሲሉ ብዙ ነገር ሊሆን እንደሚችል ተገንዝቦ ለስሜቱ ተገቢውን ትኩረት መስጠት አስፈላጊ ነው።
እንዴት እናውራ? የሚለው የአብዛኛው ወላጆች ጥያቄ ነው። ቀለል አድርገን እድሜን በሚመጥን የቋንቋ አጠቃቀም ማስረዳት፤ አንዳንዴም ምስሎችን ( ) በመጠቀም ከልጆች ጋር ስለተለያየ መሰረታዊ አይነት ስሜቶች ማውራት፤ ለምሳሌ ስናደድ ምን ይሰማኛል? ከዛስ ምን አደርጋለሁ? ምን ባደርግ ይሻላል ወይም የቱ ነው ትክክል? ወላጅም ልጅም ስሜታቸውን እንዲወያዩ መድረክ መፍጠር ስለስሜት ማውራት ጥቅሙ ሰፊ ነው።
የውይይት መድረክ ይፈጥርልናል፤ እራሳቸውን እንዲያዳምጡ ይረዳል። ልጆቻችንን በጥልቅ እንድናውቅ ይረዳናል፤ የተጎዱበት ወይም ያዘኑበት ነገር ካለ ቶሎ ችግሩን ማግኘት ያስችለናል። የተደበቀ ወይም ከጀርባ ያለ እና የፊት ለፊቱን ስሜት ስንረዳ ደግሞ ስሜታቸውን እንዲገዙ/ እንዲቆጣጠሩ ይረዳናል።
ይህም ሲሆን ሃሳቦችን ለያይተው የማየትን ብቃት ያዳብራሉ፤ የሌላ ሰውን ስሜት ያዳምጣሉ፣ ያከብራሉ፣ ያዝናሉ፤ ስለስሜት የሚኖራቸው ግንዛቤም ሰፊ ይሆናል። ስለዚህ ወላጆች ቁጭ ብለው የራሳቸውን ስሜት በመቆጣጠር ለልጆቻቸው ሰፊ ጊዜ ሰጥተው መወያየት ይኖርባቸዋል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 19 ቀን 2012 ዓ.ም