አዲሱ ገረመው
ዛሬ በዓለማችን በርካታ አሳሳቢ ጉዳዮች እየተከሰቱ ነው።ከሀብት ጎን ድህነት፤ ከእውቀት ጎን ማይምነት፤ ከሳይንስና ቴክኖሎጂ እምርታ ጎን ርሀብ፣ እርዛትና መጠለያ ማጣት በተለያዩ በሽታዎች አሰቃቂ የሕይወት ህልፈት የዘመናችን መገለጫዎች ናቸው።የሰው ልጅ ለራሱ ችግር ፈች የመሆኑን ያህልም ራሱ በፈጠራቸው ችግሮች እየተጠለፈ የሚወድቅ ራሱ መሆኑ ጎልቶ እየታየ ነው።በአጭሩ አሁን በዓለም ላይ የሚኖረው የሰው ልጅ እንቆቅልሽ ሕይወት እየመራ ይገኛል።
በዚህ ምክንያት አሁን በዓለም ላይ ያለው ችግር እጅግ የተወሳሰበ ሆኗል።በተለይ ደግሞ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ታዳጊ ሀገራት ይህ ችግር ጉልበቷል። ለዚህ ችግርም አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ድርጅቶች፤ ማኅበራትና ተቋማት በየጊዜው መፍትሔ ያሉትን ይደረድራሉ።ሴሚናሮች፣ አውደ ጥናቶች፣ሲፖዜሞች፣ የፓናል ውይይቶች በችግሮቹ ዙሪያ ይካሄዳሉ።ችግሮቹን ለማስወገድም ውሳኔዎች ይተላለፋሉ፤ስልቶች ይቀየሳሉ፤ ፖሊሲዎች ይነደፋሉ ፤ፕሮግራሞች ይዘጋጃሉ፤ ስምምነቶች ይፈረማሉ፤ ይሁን እንጂ ችግሮቹ የበለጠ ሲበራከቱና ሲወሳሰቡ እንጂ በሚፈለገው ፍጥነት ሲወገዱ አይስተዋልም።
ለምን? በዘመናችን ከሰው ፍቅር የቁሳቁስ ፍቅር አይሏል፣ለጥቅም ሲባል መጠላለፍና መዋደቅ ተበራክቷል።ከመከባበበር ይልቅ መጨካከንና መናናቅ፣ከመተማመን ይልቅ መጠራጠርና መካካድ ከአብሮነት ይልቅ ግለኝነት አይሏል።አባት ለአቅመ ሄዋን ያልደረሰች ሴት ልጁን ይደፍራል ፣ወንድም ወንድሙን ይገድላል፣ ባልና ሚስት ይገዳደላሉ።ራስ ወዳድነት፣ክፋትና ተንኮል፣ስርቆትና ውሸት፣ ዋልጌነትና ስንፍና፣ ቂምና በቀል፣ ሙስናና አባካኝነት፣ ግድየለሽነትና ምንቸገረኝነት በዓለማችን በእጅጉ ተንሰራፍተዋል።
እነዚህን መሰል ኢ-ግብረ ገባዊ (Immoral) ድርጊቶች መበራከታቸው የአዳባባይ ምስጢር ነው።ዋናው ጥያቄ የሚሆነው ሰው ምንሆኖ ነው የሚፈልገውን ሕይወት አጥቶ በማይፈልገው የችግር ማዕበል ውስጥ የሚደፍቀው፤ የሚጠቅመው እየራቀው የሚጎዳው የሚቀርበው፤ የሚጣፍጠው ሰላም ርቆት ጦርነት የሚለበልበው ሲሉ ምሁራን ይጠይቃሉ።
በርግጥም ዓለም የጎደላት ትልቅ ነገር አለ ግብረ ገብነት።ህንጻ ሳይሆን ሰው መገንባት፤ መሬት ሳይሆ ሰው ማልማት ይጎድላታል።ለዚህ ደግሞ መጻሕፍት ቢመረመሩ ግብረ ገብነትን ለማስተማር ጥሩ መፍትሄ ሊሆኑ እንደሚችሉ ይነገራል።
በቅርቡ በጎንደር ከተማ የተካሄደው ስድስተኛው አገር አቀፍ የግእዝ ጉባዔ በዚህ ላይ ያተኮሩ የጥናት ምክረ ሀሳቦች ተነስተውበታል።ከጥናት አቅራቢዎቹ በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የግዕዝ ቋንቋ መምህርት የሆኑት ወይዘሮ አዲሴ ያለው ሀተታ ዘዘርአ ያዕቆብና አንጋረ ምሳሌ ዘግዕዝለግብረ ገብነት ያላቸውን ፋይዳ ዳስሰዋል።
ግበረ ገብነት ላይ ከተከተቡት መጻሕፍት ሀተታ ዘዘርአ ያዕቆብና አንጋረ ምሳሌ ዘግዕዝን ተጠቃሽ የሆኑት እነዚህ መጻሕፍት ስለ ሥነ አመክንዮ፣ ሥነ ምግባርና ግብረ ገብነት በእጅጉ የሚያብራሩና ለአፍሪካ የጽሑፍ ፍልስፍና ፈር ቀዳጅ የሆኑ መጻሕፍት መሆናቸውን አንስተዋል።
ግብረ ገብ ትክክል ወይም ስህተት ሠናይ ወይም እኩይ ነገሮችን የሚገልጽ፣ ሰው ሊኖረው ስለሚገባና ስለማይገባ ጠባይ የሚደነግግ ነው።የግብረ ገብ ህግጋትም አትዋሽ፣ ቃል ኪዳን ጠብቅ አትግደል፣ የሌሎችን ነጻነት አክብር፣ አትስረቅ፣ አታጨበርብርና የመሳሰሉት ናቸው፡ ከዚህ አንጻር ሀተታ ዘዘርአ ያዕቆብና አንጋረ ምሳሌ ዘግዕዝን ሲፈተሹ የግብረ ገብ ህግጋትን በየፈርጁ ያሳያሉ።
በተለይ መደረግ ያለበትንና የሌለበትን የሚገልጹ የአድርግ አታድርግ ግበረ ገባዊ ህግጋትን ለማጽናት “አስርቱ ቃላተ ኦሪት እና ስድስቱ ቃላተ ወንጌልን” ዘርአያዕቆብ ያስቀምጣል።በዚህም በአድርግ ግብረ ገባዊ ህግጋት ላይ ሁለንተናዊ ይዘት ያላቸውና የሰው ልጅ ማድረግ ስለሚገባው ጉዳይ በመጻሕፍቱ ገጾች ላይ ሰፍሯል።የነገሮች ቅደም ተከተልን በጠበቀ መንገድ ለመረዳት ያመቸን ዘንድ በሰው ልጅ እድገት እነዚህን ጽሑፎች እንፈትሻቸው፡-
እንደ መምህርቷ ማብራሪያ፤ ማኅበረሰብ የሚመሰረትበት የመጀመሪያው ተቋም ከቤተሰብ ይጀምራል።በዚህ ቤተሰብ ውስጥ ልጆች ይኖራሉ። የግብረ ገብ ህግም “አክብር አባከ ወእመከ “ ይላል።ይህም እናትህንና አባትህን አክብር የሚል ነው።በዚህ ቤተሰብ ያሉ ልጆች ሰውን (ወላጆቻቸውን ማክበር ገና በህፃንነታቸው ይለማመዳሉ።ቤተሰብ ማክበር ልማዱ የሆነውን ልጅ (ያወቀውን ልጅ) “አፍቅር ቢጸከ ከመ ነፍስከ” በማለት ማክበሩ ወይም ፍቅሩ በአካባቢው ወደሚገኘው ወይም ትምህርት ቤት አብሮት ወደሚያሳልፈው ጓደኛው እንዲያድግ ይረዳዋል።
በእነዚህ ግብረ ገብ ህግጋት የታነጸውን ልጅ አረጋዊ ህጻን ወጣት ጎልማሳ፣ ወንድ ሴት፣ ብሔር ሀገር ሳይለይ ማንኛውንም የሰው ልጅ በሰውነቱ ብቻ ያከብርና ይወድ ዘንድ “ሰብእሰ ክቡር ውእቱ (ወሰብእ ይከብር እምኩሉ ፍጥረት) በማለት የሰው ልጅ ሁሉ ክቡር እንደሆነና ከሁሉ ፍጥረታት በላይ ሊከበር እንደሚገባው ያስተምረዋል።ሆኖም ሰው በሰው ላይ በክፋት ቢነሳበትስ (ክፉ ቢሆንበትስ)የሚል ጥያቄ ይነሳ ሆናል።
ለዚህም አንጋረ ምሳሌዎቹ መልስ አላቸው በመጀመሪያ ስለ ሰው ክፋት ከማንሳታችን በፊት ራሳችንን እንድንፈትሽ ይመክሩናል።ምክንያቱም ጥሩ ስናደርግ ሰዎችንም ጥሩ ማድረግ ስለምንችል ነው።“ኩኑ ከመ ይእዜ እለ ተወለዱ ህፃናት፣ ኩኑ ጠቢባነ ከመ አርዌ ምድር ወየዋሃነ ከመ ርግብ፣ ቅድመ አውጽእ ሠርዌ እም ዐይንከ” ይሉናል።እነዚህ እምቅ አባባሎች ፍፁም ደግ እንድንሆን ከሰው ጋር ለመኖር ጠቢባን እንድንሆን ሰው ስለሰራው ክፉ ነገር ከመኮነናችን በፊት እኛ ማን ነን ብለን እንድንፈትሽና ራሳችንን በመልካም ሥነ ምግባር አንጸን ሌሎች እንድናስተምር ይመክሩናል።
አሁንም ራሳችንን በግብረ ገብነት ብናንጽ ሌሎች ክፉ ከሆኑስ ተብሎ ሊጠየቅ ይችላል።መልሱ ይቀጥላል።በእነዚህ አባባሎች መልካም ሰውን በማመስገን በበጎ ስራው እንዲቀጥልበት እና ለሌሎችም አርአያ እንዲሆን “ወድሶ ለሰብእ በዘይደሉ” በሚለው ህግ አርያነቱን እንዲያስቀጥል እናደርጋለን።
ሌላም አስተዋይ የሆነ ግን ኢ ግብረ ገባዊ ጉዳዮችን ሲፈጽም የተመለከተ ሰው ቢኖር “ ዝልፎ ለጠቢብ ከመ ይዌስክ ጥበበ “ በማለት አስተዋይን ሰው ብንመክረው ብንገስጸው ማስተካከል እንደምንችል ያስረዳናል።ከዚህ ሁሉ የተለየ ክፉ ሰው ቢገጥመን ወይም ቢኖር ደግሞ ክፋቱ ፣ደግነታችን ወይም ሕይወት ራሱ ያስተምረው ዘንድ እንድንተወው ወይም እንዲሁም ያለ ዋጋ እንድንወደው “ጸላእተክሙ አፍቅሩ፣ ኅድጉ አበሳ ለቢጽክሙ” ይሉናል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 19 ቀን 2012 ዓ.ም