ለምለም መንግሥቱ
‹‹በዘንባባ የተዋበች፣ጣና የተሰኘ ሐይቅ ያላት፡፡ውሃው እንደ ህንድ ውቅያኖስ ጨው ያለው ሳይሆን፣ሰውም ከብቱም ሊጠጣው የሚችል፡፡በውስጡ ዓሳን ጨምሮ ብዝሓ ህይወት የሚኖርበት፡፡በጀልባ ለሁለትና ለሶስት ሰአታት የሚኬድበት፣ትንሽ ኩሬ ሳይሆን ሰፊና ትልቅ የውሃ ሀብት ያላት›› ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አህመድ ያወደሷት ባህርዳር ከተማ በአፍሪካ ውስጥ ምርጥ ከሚባሉ ከተሞች አንዷ ናት ፡፡ ለዚህ ሁሉ ውዳሴ ያበቃትም በውስጧ የያዘቻቸው እምቅ የተፈጥሮ፣የታሪክና ሰው ሰራሽ ሀብቷ መሆኑን ነው የገለጹት ፡፡
በንጉሱ ጊዜ ስፋት ባለው ተራራ ላይ ስለተሰራው ቤዛዊት ስለሚባለው ቤተመንግሥትም ጠቅላይ ሚኒስቴር ዶክተር ዐብይ አንስተዋል፡፡እርሳቸው እንዳሉት ቤተመንግሥቱ የሚገኝበት ቦታ የዓባይ ተፋሰስ የሚወርድበት፣አረንጓዴ ድንቅ ሥፍራ መሆኑ አስተውሎት ሳያገኝ፣ውበቱ ተደብቆና ጥቅም ሳይሰጥ ለሃምሳ አመታት ተዘግቶ ቆይቷል፡፡እንዲህ በአድናቆት የገለጹት ቤዛዊት ቤተመንግሥት አሁን ተመልካች አግኝቷል፡፡ከዚህ በኋላ እንደታሸገ አይቀመጥም፡፡በአረንጓዴ ስፍራነቱና በአቀማመጡ ታይቶ የማይጠገበውን ድንቅ ውበቱን ለመጠቀም፣ለጎብኝዎችም ሆነ ለሌሎችም ማረፊያ ሆኖ እንዲያገለግል፣ገቢም እንዲያስገኝ ባለአምስት ኮከብ ደረጃ ያለው ሆቴል ሆኖ አገልግሎት እንዲሰጥ መወሰኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አህመድ ሰሞኑን በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 11ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ ተገኝተው በቱሪዝም ላይ ሰፊ ማብራሪያ ሰጥተዋል ፡፡ እንዲህ ያሉ ታሪካዊ ቦታዎችን ጥቅም ላይ በማዋል መጠቀም በሌላው ዓለም የተለመደ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
ከቤዛዊት ቤተመንግሥት ዝቅ ብሎ በሚገኘው የዐባይ ተፋሰስ በሚወርድበት ላይ ከ380 ሜትር በላይ ከፍታ እና ከአራት ሜትር በላይ ስፋት ያለው ድልድይ እየተሰራ ነው፡፡ድልድዩ በውጭው ጎልደን ጌት፣ሳንፍራንሲስኮ ቤይ ተብሎ የሚጠራውና ሰዎች የማስታወሻ ፎቶግራፍ የሚነሱበት አይነት እንደማለት እንደሆነ በንጽጽር ለምክርቤቱ አባላት አብስረዋል ፡፡የአራት፣አምስትና ስድስት መቶ አመት ታሪኮች በውስጣቸው የያዙትን ከጣና እስከ ጎርጎራ ያሉትንም ገዳማት አስደማሚ ብለዋቸዋል፡፡
ይሄን እምቅ ሀብት ከፍተኛ የገንዘብ ወጭ ሳያስፈልግ ትንሽ ሀሳብ በማፍለቅና የእኔነት ኃላፊነት ወስዶ የሚሰራ አካል ካለ ለገበያ ቀርቦ የሚገኘው ገቢ ለሀገር ይተርፋል፡፡ይህን ለማድረግ ባህርዳር ትንሽ አይን መግለጥ ብቻ ነበር የሚያስፈልጋት ብለዋል፡፡በአሁኑ ጊዜም ጣናን ከጎንደር ከተማ ጋር ለማገናኘት ንድፍ (ዲዛይን) እየተሰራ ነው፡፡ እንዲህ ያሉ ሥራዎች የቱሪስት መስህብ እንዲሆኑ ብቻ ሳይሆን አማራጭ የጀልባ ትራንስፖርት ሆኖ እንዲያገለግልም ያግዛል፡፡በአካባቢው የሚገኘውን የተሳሰረ ሰፊ ታሪክና የተፈጥሮ ሀብት ለመጠቀም የሚባክን ጊዜ መኖር እንደሌለበት ነው ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ገለጻ መረዳት የሚቻለው፡፡
‹‹ቀኑን ሙሉ ብናገር የማልጠግበውና ተናግሬውም የማልጨርሰውን ታሪክ ማንሳት እችላለሁ››ያሉት ጠቅላይ ሚኒስቴር ዶክተር ዐብይ ለአብነትም ወንጪ፣ኮይሻ፣ገረአልታ፣አዋሽ፣አፋር፣ጋምቤላ፣ባሌ ጫካ አካባቢ ያሉትን የቱሪስት መስህቦችና ሀብቶች ጠቃቅሰዋል፡፡
በቱሪዝም ዘርፉ ላይ የተነሱትን ነጥቦች መሠረት አድርገን ያነጋገርናቸው ባለሙያዎች ሀሳባቸውን አካፍለውናል፡፡ የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተርና የታሪክ ተመራማሪ ረዳት ፕሮፌሰር አበባው አያሌው አንዱ ናቸው፡፡እርሳቸውም ስለቱሪዝም ሲወሳ ሶስት መሠረታዊ ነገሮች መነሳት እንዳለባቸው ያስታውሳሉ፡፡‹‹የመጀመሪያው መጎብኘትና መሸጥ የሚችል የተፈጥሮ ሀብት መኖሩን ወይም የሚገኝበትን ደረጃ ማየት ነው፡፡በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ እምቅ ሀብት አላት፡፡ ተፈጥሮ ዕምቅ ሀብት ከለገሰቻቸው መካከል ሰሜን ተራሮች ፓርክ ይጠቀሳል፡፡ፓርኩ በቱሪዝም ሁለተኛ መዳረሻ ነው፡፡በመሆኑም ተፈጥሮን ወደ ሀብትነት መቀየር ሊሰራ የሚገባ ሥራ ነው፡፡አውሮፓውያን ተፈጥሮ የለገሳቸውን በረዶ የቱሪዝም መስህብ አድርገው እየተጠቀሙበት ነው፡፡ዩናይትድ አረብ ኤምሬት ተፈጥሮ የሰጣቸውን በረሃውን አሸዋውን ተጠቅመውበታል። ስለቱሪዝም ስናስብ ተፈጥሮ ምን ለግሳናለች፡፡ያንን እንዴት ወደ ገንዘብ እንቀይረው ማለት ያስፈልጋል፡፡ በተፈጥሮው ሀብት ማፍራት ሲጀመር መንከባከቡ አብሮ ይከተላል፡፡ገንዘብ የማያስገኝ ነገር ላይ ሰው አይደክምም፡፡ስለዚህ ገንዘብ ሲያገኝ መንከባከብ ይጀምራል››ሲሉ ያስረዳሉ፡፡
ረዳት ፕሮፌሰር አበባው በሁለተኛ ደረጃ ያነሱት ደግሞ የታሪክ ቅርሶችን ነው፡፡የቅርስ ሀብቶችን የማስተዋወቅም ሆነ ለገበያ የማቅረቡ ሥራ ገና ነው በሚባል ደረጃ ላይ ነው የሚገኘው፡፡ረጅም ታሪክ ያላቸውን ከብዙ በጥቂቱ የሆኑትን የጣና ገዳማት፣አክሱም፣ላሊበላ ጢያ፣ጅማ ቅርሶች የቱሪስት መዳረሻ ሆነው ገቢ እንዲያስገኙ የተሰራው ሥራ እጅግ አናሳ ነው፡፡ የቱሪስቱን ቆይታ ሊያራዝም የሚችል ተግባር በማከናወን ላይም እንዲሁ አልተሰራም፡፡ አዲስ አበባ ከተማን ለአብነት እናንሳ ቢያንስ ቱሪስቱን ለሁለት ቀናት የምታቆይበት አቅም እንዲኖራት ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ እስካሁን ባለው እንቅስቃሴ አጥጋቢ አይደለም፡፡አሁን ግን አንድነት፣ወንድማማችነትና እንጦጦ ፓርኮች መሰራታቸው ተስፋ ሰጥቷል፡፡ይሄም በዚህ የሚያበቃ መሆን የለበትም፡፡ገና ብዙ ያልተነኩ የሸረሪት ድር ያደራባቸው ቅርሶችና የተፈጥሮ ሀብቶች ይገኛሉ፡፡እነዚህን ሀብቶች ተጠቅሞ ወደ ገንዘብ መለወጥ የመንግሥት ሥራ ብቻ ተደርጎ መወሰድ የለበትም፡፡እንደሌላው የኢኮኖሚ ዘርፍ ሁሉ ኢንቨስተሮችና ግለሰቦችን በማሳተፍ ተጠቃሚነትን ማሳደግ ይጠበቃል፡፡በቅርቡ በግለሰብ የተጀመረው ጣይቱን ማዕከል የማድረግ እንቅስቃሴ ለአብነት መጥቀስ ይቻላል፡፡መጽሐፍ የሚሰበስበው አብዲ የሚባል ሰው አለ፡፡ይህ ሰው አንቲኳሪያን ሊባል በሚችል ደረጃ መጽሐፍትን ይሰበስባል፡፡እንዲህ ያለውን ሰው ማበረታታትና በማሳተፍ የሚፈለገውን ማግኘት ይቻላል፡፡
በሶስተኛ ደረጃ ያነሱት ደግሞ ሥለ ባህል ቅርሶች ነው፡፡ለአብነትም እንደ ጥምቀት፣ፍቼ ጨምበላላ፣እሬቻ ያሉ የማይዳሰሱ ቅርሶች ባህላዊ ይዘታቸውን ጠብቀው እንዲቀጥሉና ቱሪስትም እንዲስቡ በማድረግ መሥራት ይቻላል፡፡በአጠቃላይ ወቅት ጠብቀው የማይመጡትንና ወቅት የማይጠብቁት የባህልና የታሪክ ቅርሶች ስንት ቱሪስት መሳብ ይችላሉ የሚለውን ቀመር በመሥራትና የቱሪስት ጊዜውን በማስፋት መጠቀም የሚቻልበት ዕድል መኖሩን ረዳት ፕሮፌሰሩ ያብራራሉ፡፡
እርሳቸው እንዳሉት አሁንም ኢትዮጵያ ብዙ ያልታዩና የገንዘብ ገቢ ያላስገኙ ሀብቶች አሏት፡፡በቅርብ ያለውን ዝዋይና ላንጋኖን እንኳን በአግባቡ ጥቅም ላይ ማዋል አልተቻለም፡፡በእግር ጉዞ ከተፈጥሮ ጋር መቆየት የሚቻልባቸው ለመዝናናት የሚውሉ ቦታዎችንም ምቹ ማድረግ ቱሪስቱን ከሚስቡ መዳረሻዎች መካከል አንዱ እንደሆነና አንኮበርንም በዚህ ረገድ መጠቀም እንደሚቻል አንስተዋል፡፡
‹‹ቱሪዝም ሲባል ሌላ ትርጉም የለውም ፡፡ሀብት መሰብሰቢያ ነው፡፡አንድም ባለሀብቱ ኢንቨስት እንዲያደርግ፣ሌላው ደግሞ ሀብታም ነህና መጥተህ ዘና በል ማለት ነው››የሚሉት ረዳት ፕሮፌሰር አበባው፤በዚህ መልኩ ቱሪስት እንዲመጣና ገንዘቡን እንዲያፈስ ከተፈለገ ለቱሪዝሙ ሰላም ወሳኝ እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡እንደ ኮቪድ 19 ቫይረስ ወረርሽኝ ያሉ ወቅታዊ ነገሮች በጊዜ ሂደት ያልፋሉ፡፡ቱሪስቱ ያለሥጋት አካሉንና አዕምሮውን አሳርፎ እንዲሄድ፣እንደ ሀገርም ከመስተንግዶው ገቢ ለማግኘት ሰላምን ማረጋገጥ ወሳኝ እንደሆነ አስምረውበታል፡፡
አሁን ኢትዮጵያ ላይ የሚስተዋለው የሰላም እጦት ከለውጥ ጋር የተያያዘ መሆኑ ይታወቃል፡፡ኮቪድም እንዲሁ ያልታሰበ ነው፡፡ይሄ ተደማምሮ አሁን ላይ ጭስ አልባውን የቱሪዝም ኢንዱስትሪ እየጎዳው ቢሆንም ቀደም ሲል እነዚህ ሁኔታዎች ባልተፈጠሩበትም ሀብቱ ጥቅም ላይ እንዳልዋለ በተደጋጋሚ የሚነሳ ጉዳይ እንደሆነ ረዳት ፕሮፌሰሩ ያብራራሉ። ዘርፉ ትኩረት አለማግኘቱን በቅድሚያ ያነሳሉ፡፡እንደ ሀገር ለመሠረተ ልማትና ለሌሎች ኢንዱስትሪዎች ትኩረት ሲሰጥ ቱሪዝም ዘርፉ ትልቅ ኢንቨስትመንት እንደሆነ ተዘንግቷል፡፡እዚህ ላይ ያልታየው መሠረተ ልማቱን ለመሥራት የሚውለውን ገንዘብ ከቱሪዝም ኢንዱስትሪው እንደሚገኝ አለመገንዘብ ነው፡፡
እንደርሳቸው ማብራሪያ ቱሪዝም ከሙያ ጋርም ይያያዛል፡፡ዘርፉን ከሚመራው ከላይኛው አካል ጀምሮ እስከታች ያለው በዘርፉ የሰለጠነና ክህሎት ያለው ባለሙያ መሆን ይኖርበታል፡፡የዘርፉ አደረጃጀትም እንዲሁ መስተካከል አለበት፡፡ቱሪዝም ኢንዱስትሪ መሆኑ ከታመነበት ከባህል ተላቆ ለብቻው መደራጀት ይኖርበታል፡፡ቱሪዝም እየተቀነቀነለት ግን በሁለት ቦታ ተከፍሎ ተቀምጧል፡፡
አንደኛው የኢትጵያ ቱሪዝም ድርጅት ነው፡፡በሌላ በኩል ባህልና ቱሪዝም ተብሎ በሚኒስቴር ደረጃ ተዋቅሯል።ነገር ግን ባህል አንድ ነገር ነው ቱሪዝም ሥራው ቅርስ መጠበቅ ወይንም ሌላ ተግባር ሳይሆን ኢንዱስትሪውን ማስፋፋት ነው፡፡ትልቅ ቦታ ሰጥቶ በራሱ እንዲሰራ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ባህል የሚዳስሰውንም፣የማይዳስሰውንም፣ስዕሉንም፣ሥነ-ጥበቡንም የሚያካትት በመሆኑ ባህል ሚኒስቴርን የባህልና ሥነጥበባት ብሎ ማዋቀር ነው የሚያስፈልገው፡፡የሌሎችም ሀገሮች ተሞክሮ ይህንኑ ነው የሚያሳየው፡፡በዚህ መንገድ ማየቱ የተሻለ ይሆናል፡፡
በዘርፉ የሚስተዋለው ክፍተት እንዲታረምም ሆነ የተሻለ ውጤት እንዲገኝ በጥናት በማመላከት ሥራው የጋራ እንዲሆን በማድረግ ረገድ እርሳቸውን ጨምሮ የዘርፉ ባለሙያዎች ስላበረከቱት አስተዋጽኦም ረዳት ፕሮፌሰሩን ጠይቄያቸው በሰጡት ምላሽ የቅርስና ጥበቃ ባለሥልጣንን በሁለት መንገድ በመፈተሽ ሥራዎች ተሰርተዋል፡፡የመጀመሪያው በ1992 ዓ.ም የወጣውን ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ መቋቋሙንና የተሰጠውን ሥልጣን የሚያመለክተውን አዋጅ እንዲሁም በ2006ዓ.ም የወጣውን ቅርስን በብሄራዊና በክልል ደረጃ የመመደብ፤ አዋጅ በአንድ የማድረግ ተግባር ነው፡፡ሁለቱን አዋጆች አንድ ከማድረግ በተጨማሪ ሌላው የተሰራው ቅርስ ላይ ትኩረት ያደረገ ነው፡፡ቅርስ እራሱን ችሎ ሰፊ ሥራ ይጠይቃል፡፡ሌላው በተለያየ አካባቢ የሚገኝ ቅርስን መፈለግ አንድ ሥራ ነው፡፡ የተገኘው ቅርስ ደግሞ ይመዘገባል፡፡ ይደራጃል፡፡ ጥናትና ምርምር ይካሄድበታል፡፡ እንደገና ቅርስ ይሰበሰባል፡፡ በመቀጠልም ይለማል፡፡ ሲለማ ደግሞ ሙዚየም ይቀመጣል በሌላ አነጋገር ለቱሪዝም ምቹ ሆኖ እንዲቀመጥ ይደረጋል፡፡ይሁን እንጂ ይህ ሁሉ ሥራ በአንድ ባለሥልጣን መሥሪያ ቤት አቅም ብቻ ይቻላል ወይ የሚል ሀሳብ ሲነሳ ደግሞ አይታሰብም፡፡ ባለሥልጣኑ በሀገሪቱ ላይ ያለውን ቅርስ መድረስ የሚያስችል አቅም የለውም፡፡ በመሆኑም ሁለተኛው ተግባር ሁሉም ድርሻውን እንዲወጣ ማድረግ ነው፡፡ ከመፈለግ እስከ ማልማት ያለውን ሂደት ድርሻው የተሰጠው አካል እንዲወጣ ማስቻል እንደሆነ ረዳት ፕሮፌሰሩ አብራርተዋል፡፡ ባለቤት ሲባል በክልልና በፌዴራል ደረጃ ሳይሆን ወደ ግለሰቦችም መውረድ ይኖርበታል ብለዋል፡፡የተሻሻለው አዋጅ በየደረጃው ካለው አካል ጋር ምክክር ተደርጎበት አዋጁን ለሚያፀድቀው አካል ተልኮ ሥራ ላይ እንደሚውል ይጠበቃል፡፡ አዋጁ ማሻሻል ያስፈለገው የቅርስ አስተዳደርን በደንብ መምራት የሚያስችልና ሁሉንም በየደረጃው ለማሳተፍ እንዲያስችል ታስቦ ሲሆን፣ጥሩ ሥራ ለተተኪው ማስተላለፍ ሌላው ተልዕኮ ነው፡፡
ቅርስን የማስተዳደርም ሆነ በቱሪዝም ኢንዱስትሪው የጋራ ተጠቃሚነት ከአንድነቱ ይልቅ መገፋፋቱና የሌላ አካል አድርጎ ማየት ስለመኖሩም ረዳት ፕሮፌሰሩ ‹‹የማስተዳደሩ ሥራ የሚሰጠው የእከሌ ነው ለማለት አይደለም፡፡ አንድ አልባስም ይሁን፣የፈረስ አለንጋ፣ጋሻም ቢሆን የክልል ወይንም የብሄር ሀብት ሳይሆን የሁሉም ሰው ሀብት ነው››በማለት ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የቱሪዝም ዘርፍ አማካሪ አቶ አህመድ መሐመድ፤ ኢትዮጵያ ለዓለም ህዝብ የሚሆን ሀብት እንዳላት ይገልጻሉ፡፡እርሳቸው እንዳሉት ተፈጥሮ የለገሰችው ሀብት በትወልድ ሲከፋፈልም ለሁሉም አይነት ይሆናል፡፡ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ ባህርዳር ላይ የጠቀሱት የባህርዳርም ሆነ የጎርጎራና ኮይሻ የቱሪዝም ልማት ሥራ በሁሉም ዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኝ የህብረተሰብ ክፍል ሊጠቀምባቸው የሚችሉ መስህብ በመሆኑ ሁሉንም ሊስብ የሚችል ሀብት ነው፡፡በአሁኑ ጊዜም ጎርጎራንና ኮይሻን የማልማቱ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ተጀምሯል፡፡ነገር ግን ልማቱ እንደሚታሰበው በአጭር ጊዜ ላይ ሊጠናቀቅ ይችላል፡፡እንዲህ ለሁሉም በሚመች መልኩ አልምቶ ማቅረብ ከተቻለ ግን ጠቀሜታው ሰፊ ነው፡፡
ሀገሪቱ እስካሁንም ከቱሪዝም ኢንዱስትሪው ለመጠቀም ያልቻለችው ከመሠረተ ልማት አለመሟላት፣ዘርፉን አልምቶና አደራጅቶ ለገበያ ካለማቅረብ፣ከተቋማዊ አደረጃጀት፣የአሰራር ሥርአት ካለመዘርጋት ጋር ይያያዛል፡፡መንግሥት ለዚህ ምላሽ የሚሰጥ የሀብት አሰባሰብ የዕቅድ ዝግጅት እየሰራ ይገኛል፡፡
ሀብቱን የጋራ አድርጎ ተቀብሎ በልማቱ ለመሳተፍም ሆነ ለመጠቀም የሚደረገው ጥረት ለምን አናሳ ሆነ ለሚለው ጥያቄ አቶ አህመድ በሰጡት ምላሽ ይሄ የሚመነጨው የኢኮኖሚ ሥርአትን መፍጠር የሚቻለው በቱሪዝም መሆኑን ካለመገንዘብ ነው፡፡እንዲህ ያሉ ክፍተቶችን ለማስተካከል ወደፊት ከቱሪዝም ጋር የተያያዘ መድረክ ለማካሄድ ታቅዷል፡፡መድረኩ ሁሉንም አሳታፊ ስለሚያደርግ ክፍተቶች ይታረማሉ የሚል እምነት ተይዟል፡፡
አሁን እየተከናወኑ ያሉት የቱሪዝም መዳረሻዎች ዘላቂነት እንዲኖራቸው ትኩረቱ ማልማት ላይ ብቻ መሆን የለበትም፡፡ የቱሪዝም ሥራው በተቋማዊ አደረጃጀት ሊመራ ይገባል፡፡ በአሰራርና በጠንካራ ፖሊሲም መደገፍ ይኖርበታል፡፡ ይሄ በአስር አመቱ የቱሪዝም መሪ ዕቅድ ውስጥ ተካቷል፡፡ ባለሙያዎቹ የጠቅላይ ሚኒስቴር ዶክተር ዐብይን ሀሳብ መነሻ አድርገው ሀሳባቸውን እንዳካፈሉት የቱሪዝም ኢንዱስትሪው ውጤት በሚያመጣ መልኩ መሰራት ይኖርበታል፡፡ሥራውም የአንድ አካል እንዳልሆነ ግንዛቤ ሊያዝ ይገባል፡፡
አዲስ ዘመን መጋቢት 19 ቀን 2012 ዓ.ም