አዲሱ ገረመው
ጎንደር ከተማ ፒያሳ አካባቢ የሞባይል ካርድ ልገዛ ወደ አንዲት ሱቅ እያመራሁ ነው። ሁለት አባቶች ከሱቁ አጠገብ ቆመው ይነጋገራሉ። ቋንቋቸው አማርኛ መስሎኝ ጆሮዬን ወደ እነሱ ጣል ባደርግም አማርኛ ሊሆንልኝ አልቻለም። ይሄ ሙከራዬ ሲከሽፍ በምን ቋንቋ እየተነጋገሩ እንደሆነ ጠየቅኳቸው። በግእዝ መሆኑን ነገሩኝ።
እኔ ከድክመቴ ብዛት ከአማርኛ ውጪ ሌላውን ቋንቋ እጾማለሁ። በእርግጥ ከአምስት በላይ ቋንቋዎችን መስማት እችላለሁ፤ ግን መናገር አልችልም። ቋንቋ ብቻ ሳይሆን ባህላዊ ጭፈራም ነው የሚታክተኝ። አንድ ቀን ግን ኤሌክትሪክ ይዞኝ የ80ውንም ብሄረሰብ ጭፈራ እንዳስጨፈረኝ መቼም አልረሳውም። ይገርማችኋል ቋንቋ መናገር ባልችልም የማወቅ ፍላጎቴ ከፍተኛ ነው።
ለዚህም ነው ግእዝ ቋንቋ ይህን ያህል በአደባባይ መነጋገሪያ መሆኑ ቢደንቀኝ እንዴት ሊሆን ቻለ የሚለውን ጥያቄ አከታትዬ ለአንድ ግእዝ ተናጋሪ አባት አቀርብኩላቸው። እዚህ አካባቢ ሰው ቋንቋውን ባይማረውም እንኳን መስማት እንደሚችል ነገሩኝ። መቼስ ግእዝ ከተነሳ ቅኔው የሚረሳ ስላልሆነ ጥቂት ስለእርሱ ያጫውቱኝ ዘንድ ጠየቅኳቸውና ማለፊያ ቆይታ አደረግን።
ሊቀ ኅሩያን ነቃጥበብ እሸቴ ይባላሉ። በጎንደር ደብረ ምህረት አቡነ ቤት ቅዱስ ገብረኤል ገዳም የቅኔ መምህር ምስክርና የብሉያትና ሀዲሳት ሊቃውንት መምህር ናቸው። በአሁኑ ወቅት ወደ 600 የሚደርሱ ደቀማዘሙርት በማስተማር ላይ ይገኛሉ።
“ቅኔ መገዛት፣ ግዛት፣ ተገዢነትን የሚያሳይ ማለት ነው አንድ ሰው ቅኔ ሲያደርግ ለፈጣሪ መገዛቱን ለማስረዳት ፈጣሪውን ያመሰግንበታል። አሊያም በቤተ ክህነትም ሆነ በቤተ መንግሥት በስልጣን ከፍ ላሉ ሰዎች ቅኔ ሊቀርብ ይችላል። ተገዢ መሆኑንም የሚያሳይበት ነው” ሲሉ የቅኔን መነሻ ሃሳብ ይናገራሉ።
እርሳቸው እንደሚሉት፤ ቅኔ መዳሰስ፣ መፈለግ፣ መመራመር፣ ማወቅ ማርቀቅ፣ የተሰወረውንና የተሸሸገውን ምስጢር መፈለግ የሚለውን እሳቤ የያዘ ነው። ቅኔ ሁሌም አዲስና አንድ ጊዜ ከተባለ በኋላ የማይደገም ነው። ታሪክ ተተርኮ ሰምና ወርቁ ተራቅቆ የሚቀርብ ነው። የራሱ የቃል ርዝማኔና ያለውና ዜማም ያለው ነው። ጮክ ተብሎም ነው የሚባለው። ስልቱ ከተበላሸ ደግሞ ለመጮህ ያስቸግራል።
ቅኔ ለመቀኘት በተለይ የግእዝ ቋንቋ እውቀት ያስፈልጋል። በዚህ ውስጥ ግስ የሚባል አለ። ግሱ በደንብ ይጠናል። በየወሩ ባሉት 30 ቀናት የሚውሉ ቅዱሳን ታሪክ ለቅኔ ተማሪው ይተረክለታል። ያጠናውን ግእዝ ከበዓላት ጋር እያያዘ ቅኔ ይቀኛል። በሰሙ ደግሞ በዘመኑ የሚደረገውን፤ ለምሳሌ በአዝመራ ጊዜ ገብሬው ሲያጭድ፣ ሲሰበስብና ሲወቃ፤ በክረምት ደግሞ ከዝሪቱ፣ ከአረሙ፣ ከደመናው፣ ከዝናቡ፤ በጸደይና በመጸውም ያሉትና በወቅቱ የሚከናወኑትን ሁነቶች ከቅዱሳን ታሪክ ጋር አያይዞ ግእዝ ቋንቋን ተጠቅሞ ይቀኛል ይላሉ ሊቀ ኅሩያን ነቃጥበብ።
በእርግጥም ቅኔ ራሱን የቻለ ጥበብ ነው። በውስጡ ሥነ ምግባርንና ብልሀትን ያስተምራል። አዲስ ግኝትን ያሳያል። በቅኔ ቤት ከማይረሱ ጉዳዮች አንዱ የሆነውና “ነጠቃ” ተብሎ የሚጠራው ይህንን ያሳያል። ለመሆኑ ነጠቃ ምንድነው?
ሊቀ ኅሩያን እንደሚሉት፤ በነጠቃ አንድ ሰው ቅኔ ሲቆጥር በልቡ ያስባል፤ ከዚያም ቅኔውን ሲጀምር ጎበዝ የሆነና በደንብ የተመራመረ ሌላ መምህር ወይም ደቀ መዝሙር የተቀኚውን ምስጢር ይወስድበታል።
ሃሳቡን ቀድሞ ይወስድበታል። (ይነጥቀዋል) የሰውዬውን ሃሳብ ሲቀማ ነጠቀው ይባላል። ይህም የተለየ ተሰጥኦ ይጠይቃል። በተለይ የተሰጠ የመትርጎም ሀብት፣ የማንበብ ሀብት፣ የማመስጠር ሀብት ያስፈልጋል። ስጦታው እንዳለ ሆኖ መማር፣ ማጥናት፣ መጠየቅ የመሳሰሉ ትጋቶች ያስፍልጋሉ። እነዚህ ነገሮች ካሉ ምናልባት ስጦታው ሊለያይ ይችላል እንጂ የበለጠ ተመራማሪ መሆን ይቻላል።
ምስጢር የገባው ሰው ቅኔውን ያውቀዋል። ይህን ሊል ይችላል ብሎ ስለሚያስብ ይነጥቃል። በሙከራው መሠረት ሊያገኝም ላያገኝም ይችላል። ነጠቃ የተባለው ተቀኚው ያለውን ሳይጨርሰው ቀድሞ በመቀማት ስለሚጨርሰው ነው።
እዚህ ላይ ልብ ሊባል የሚገባው፤ ነጠቃ ሲኖር የተቀኚውን ቅኔ ድክመት አያመላክትም ወይ? የሚለው ጥያቄ ነው። እንደ ሊቁ ገለጻ፤ በነጠቃ ጊዜ የሚነጠቀው ሰው ደካማ ቅኔ ተቀኘ አይባልም። እንዲያውም አዋቂነቱን ነው የሚያስረዳው። ምክንያቱም ቅኔው ጥሩ ከሆነ ነው ሊነጠቅ የሚችለው። የሚሰማ፣ ምስጢር ያለው ነው የሚነጠቀው።
አንዳንዶች በተለምዶ እንደ ድክመት ወይም እንዳለማወቅ አድርገው ሊቆጥሩት ይችላሉ። ነገር ግን የሚነጠቀው ሰው የተሻለ ቅኔ ሲያቀርብ ነው የሚነጠቀው። ይህም ችሎታውን ነው የሚያሳየው። ታዲያ ለመንጠቅ ሰምና ወርቅም ያስፈልጋል።
ሊቀ ኅሩያን ትምህርታቸውን የተከታተሉት ጎጃም ውስጥ ነው። ቅኔውን የተማሩትም እዚያው ነው። በትምህርት ቆይታቸው ቅኔ ይነጣጠቁ እንደነበር ይናገራሉ። ቅኔ በመቀማትም ይታወቃሉ። እንዲያውም አንዳንድ ጊዜ ቅኔ የሚያቀርብ ሰው “እስኪ ያን ሰውዬ እዩት” ብሎ ነው አለመኖራቸውን አረጋግጦ የሚቀኘው ይላሉ። ቅኔ አቅራቢው ቅኔውን እነጠቃለሁ ብሎ በማሰቡ ነው ይህን ያለው። ያው ነጠቃ ሲደረግ የአቅራቢው ይሁንታ አይጠየቅምና ነው።
ይህ የሚያሳየው አንዳንድ ጊዜ ባላወቁ ሰዎች ዘንድ ጠብ ሊፈጠር እንደሚችል ነው። እንዲያውም እስከ ዱላ ሊያዳርስም ይችላል። ነጠቀኝ ብሎ የሚማር አይጠፋምና። ነገር ግን ላወቀው ሰው ብልህነት ነው። ምስጢር ለምስጢር መገናኘት እንጂ ችግር የሚፈጥር አይደለም።
አንዳንድ ጊዜ በዕድሜ ተለቅ ያሉና በስልጣንም ከፍ ያሉ ትላልቅ ሰዎች ቅኔ ሲያቀርቡ መንጠቅ እየተቻለ ዝም ይባላሉ። ምክንያቱም በሰው እይታ “እገሌን” እኮ ነጠቃቸው ይባላል። በተለይ ሕፃናት ሆነው የትልቅን ሰው ቅኔ ከነጠቁ አላዋቂዎች እንደ ንቀት ሊያዩት ይችላሉ። በሰው መካከል እንዳቃለለውም ይቆጥሩታል። በዚህም ምክንያት ቅኔው ቢታወቅም ሳይነጠቅ ይታለፋል።
አንዳንዱ ቅኔ አቅራቢ ሲነጠቅ ደስ ብሎት ሲመርቅ አንዳንዱ ደግሞ ወደ እርግማንም ሊገባ ይችላል። ከዚህ አንጻር ብዙ ጊዜ ነጠቃ በሚቀራረቡ ሰዎች መካከል የሚካሄድ እየሆነ መጥቷል።
እንግዲህ ከላይ እንደተመለከትነው ነጠቃ በቅኔ ቤት ሲሆን፤ እውቀት መቀማት ነው። በሌላ በኩል ደግሞ ንብረትን መቀማት የሚል አሉታዊ ትርጓሜም አለው። ታዲያ ይህን መሰል የነጠቃ ትውፊት እያለን ስለምን ንብረት መንጠቅ ለመደብን? ከንብረት ይልቅ ቅኔ መዝረፍና መቀማት እውቀትን ያሰጣል። እና ንጠቁ፤ ዝረፉ። የእውቀት ነጠቃ የማወቅ አድማሳትን ያሻግራል። ምስጢርም ይገልጣል።
ቅኔውን ለመዝረፍም ለመንጠቅም ያብቃን፤ ከዚህ ውጪ ግን “ዝርፊያን በጋራ እንከላከል” የሚል ቲሸርት ለብሰው ከሚዘርፉም ይሰውረን። ሰላም!
አዲስ ዘመን መጋቢት 16/2013