አንተነህ ቸሬ
ኢትዮጵያ ረጅም ዘመናት ያስቆጠሩ የስዕል ጥበብ ያላት አገር ናት። ነባሩ ሀገርኛ የአሳሳል ጥበብ ከቤተ-ክርስቲያን ትምህርት ጋር በጥብቅ የተቆራኘ ነው። በአገሪቱ ዘመናዊ የአሳሳል ጥበብ የተጀመረው ዝንባሌው ያላቸው ኢትዮጵያውያን ወደ ውጭ አገራት ሄደው ዘመናዊ የስዕል ጥበብን በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ተከታትለው ከተመለሱ በኋላ ነው። ከእነዚህ በኢትዮጵያ ዘመናዊ የስዕል ጥበብ ታሪክ ቀደምት ከሆኑና ግንባር ቀደም ስም ካላቸው ሰዓሊያን መካከል አንዱ ሰዓሊ አገኘሁ እንግዳ ናቸው።
አገኘሁ የተወለደው በ1895 ዓ.ም በጎንደር ከተማ ነው። በታላቁ የማኅደረ ማርያም ገዳም የአብነት ትምህርት ተምሯል። ይህ ትምህርቱ ከሐይማኖታዊ እውቀት ባሻገር የግዕዝ ቋንቋን በሚገባ እንዲያውቅ አስችሎታል። በልጅነቱ የአብነት ትምህርት የተማረበት የጎንደሩ ማኅደረ ማርያም ገዳም ለስዕል ጥበብ እጅግ ቅርብ መሆኑ አገኘሁ ወደ ስዕል እንዲያዘነብል ሳያደርገው አልቀረም።
በ1919 ዓ.ም አገኘሁ በአልጋ ወራሽ ተፈሪ መኮንን (የኋላው ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ) አበረታችነትና ድጋፍ አማካኝነት ወደ ውጭ አገራት ሄደው የስዕል ትምህርት የመማር እድል ካገኙ ኢትዮጵያውያን መካከል አንዱ መሆን ቻለ። የሄደውም ወደ ፈረንሳይ ነበር።
ሰዓሊ እሸቱ ጥሩነህ ‹‹አገር ወዳዱ ሰዓሊ አገኘሁ እንግዳ›› በሚለው ጽሑፋቸው ላይ እንዳብራሩት፣ አገኘሁ ለስዕል ትምህርት ወደ ውጭ አገር የተላከበት ወቅት በኢትዮጵያ ሁለተኛው የዘመናዊ ስነ-ጥበብና ትምህርት ፍላጎት የታየበት ጊዜ ነበር። የመጀመሪያው ወቅት በዳግማዊ አፄ ምኒልክ ዘመነ መንግሥት ሰዓሊ አፈወርቅ ገብረኢየሱስ በ1897 ዓ.ም ወደ ቱሪን፣ ኢጣሊያ የሄደበትና በአልበርቲና የስነ-ጥበብ አካዳሚ (አካዴሚያ አልቤርቲና ዲ ቤሌ አርቲ – Accademia Albertina di Belle Arti di Torino) ገብቶ የስዕል ትምህርት የተማረበት ጊዜ ነው ማለት ይቻላል።
ሰዓሊ እሸቱ በዚሁ ጽሑፋቸው እንዳስረዱት፣ አገኘሁ ፓሪስ በሚገኘው የስነ-ጥበብ ትምህርት ቤት (École des Beaux-Arts) የዘመናዊ ስዕል ትምህርቱን ሳያገባድድ በ1922 ዓ.ም የመጀመሪያ ወራት ላይ ወደ ኢትዮጵያ ተጠራ። አገኘሁ በውዴታ ግዴታ ለአልጋ ወራሽ ተፈሪ መኮንን የንግሥ ዋዜማ አዲስ የተሰራውን ፓርላማ ለማስጌጥና በውስጡ የሚሰቀሉ የኪነ-ቅብ ስዕላትን እንዲያዘጋጅ ታዘዘ።
ጥበባዊ የስዕል ስራውን ወዲያውኑ በአስቸኳይ ሲጀምርና ሲያከናውን እግረ መንገዱን ወጣትና አንጋፋ ትውፊታዊ ሰዓሊያንን በአጋዥነት አሰባስቦ እየሰራና እያሰራ እያስተማረና እያሰለጠነ ነበር። ኪነ-ስዕላቱ ፋሺስት ኢጣሊያ አዲስ አበባ እስከገባበት ጊዜ ድረስ በፓርላማው ግድግዳዎች ላይ በግራና በቀኝ በኩል ተንጠልጥለው እንደነበሩ ይታወቃል። ፋሺስት ኢጣሊያ አዲስ አበባን ከተቆጣጠረ በኋላ ግን ስዕሎቹን አንስቶ በስርዓት ያስቀምጣቸው ወይንም ያውድማቸው በዛሬው ትውልድ የታወቀ ነገር የለም።
ሰዓሊ አገኘሁ እንግዳ ኢጣሊያ ነፃነቷን አስከብራ ለዘመናት የኖረችውን ኢትዮጵያን ቅኝ ግዛቷ ለማድረግ አቅዳ ለወረራ እንደተዘጋጀችና ጦሯን ወደ ኢትዮጵያ ማስጠጋቷን የሰማው እንደሌላው ኢትዮጵያዊ ሁሉ በታላቅ የአገራዊ ክብር መደፈር ቁጭትና እምቢታ ነበር። ወረራውን በመቃወም የዘመኑ አገር ወዳድ ምሁራን ተሰባስበው የሐገር ፍቅር ማኅበርን ሲመሰርቱ ሰዓሊ አገኘሁ ከማኅበሩ መስራቾች መካከል አንዱ ሆነ። በተወለደበት ጎንደር በልጅነቱ በአብነት ትምህርት ቤት የግዕዝ ቋንቋን በሚገባ የተማረው አገኘሁ በሕይወቱ ያካበተውን ሁለገብ ህሊናዊ እውቀቱን፣ ተግባራዊ ክህሎቱንና ልምዱን በመጠቀም ፀረ-ፋሺስት ቅስቀሳ ላይ ተሰማራ።
ከዘመን ጓዶቹ ከነደራሲ ተመስገን ገብሬ ጋር በግልና በጋራ በመሆን በተለያዩ የአዲስ አበባ አድባራትና አደባባዮች ላይ በመገኘት ለዛ ባለው አንደበተ ርቱዕ ንግግሩ ስለኢትዮጵያ ታሪክና ጀግንነት ለፈፈ። የኢትዮጵያ ሕዝብን የነፃነት ታሪክን የማንነት ክብርና የእምቢ አልገዛም ባይነት መንፈስን ወደኋላ በማጣቀስና በማመላከት ስለአንድነት ኃይልና ጠቀሜታ ሰበከ።
ሰዓሊ አገኘሁ እንግዳ በስዕል ሙያው በኢትዮጵያ የመጀመሪያ የሆነውን ልዩ ልዩ ስዕሎችን በመሳል በራሪ ወረቀቶችን የማዘጋጀት ተግባር ከውኖ ስዕሎቹን በተነ። በ1927 ዓ.ም በቃለ ነቢብ ጽሑፍ ግጥሞችን በመጻፍና በ1928 ዓ.ም በመግለጫ ስዕላት የታጀበ ‹‹ስለኢትዮጵያ የተገጠመ›› የሚል ርዕስ ያለው መጽሐፍ በቤተ ሳይዳ ማተሚያ ቤት አሳትሞ ለሕዝብ አሰራጨ። በዚህም ሰዓሊ አገኘሁ እንግዳ ከዚህ በፊት ባልታዬና ባልተለመደ ሁኔታ ከዘመን ጓዶቹ ጋር ፀረ-ፋሺስት እንቅስቃሴውን በማጧጧፍ ብሔራዊ የአርበኝነት ግዴታውን ተወጥቷል።
የፋሺስት ኢጣሊያ ጦር በተለያዩ ግንባሮች በወኔ የገጠመውን የኢትዮጵያን ጦር በአውሮፕላን የቦምብ ድብደባና በመርዝ ጢስ ፈጅቶ ሚያዝያ 27 ቀን 1928 ዓ.ም አዲስ አበባ ገባ። የአዲስ አበባ ሕዝብ በዘራፊዎችና በጉልበተኞች ተመዘበረ። የቻለ ቆየ፤ ያልቻለም ከተማዋን ለቆ ወጣ። ምሁራን፣ ሀገር ወዳድና ፀረ-ፋሺስት ቅስቀሳ ያደርጉ የነበሩ ኢትዮጵያውያን ከያሉበት ሲታደኑ ሰዓሊ አገኘሁ እንግዳ የት እንደተሰወረ በጊዜው አልታወቀም ነበር።
ግን በወረራው ዘመን አገኘሁ ራሱን ቀይሮ በሸዋ ደብረ ብርሃን ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ከአለቃ መዝሙር ዘዳዊት ጋር ተራ ረዳት ሰዓሊ መስሎ ስዕሎችን አብሮ ሲሰራ እንዳሳለፈ ትውፊታው ሰዓሊ አለቃ መዝሙር ዘዳዊት ከነፃነት በኋላ በ‹‹አዲስ ዘመን›› ጋዜጣ ላይ ታትሞ በወጣው ቃለ ምልልሳቸው ውስጥ ጠቅሰዋል።
ፋሺስት ኢጣሊያ ከኢትዮጵያ በተባረረ ማግሥት፣ ከ1934 ዓ.ም ጀምሮ የሰዓሊ አገኘሁ እንግዳ ፍላጎትና ሕልም ዘመናዊ የስዕል ትምህርት ቤት መመስረትና ማስተማር በመሆኑ በመጀመሪያ በግል የስዕል ማደራጃቸው፤ ቀጥሎም በአራት ኪሎ አካባቢ በከፈቱት ማስተማሪያ ቦታ ወጣት ሰዓሊያንን ማስተማርና ማሰልጠን ጀምረው ነበር።
የሰዓሊ አገኘሁ እንግዳ የስዕል ስራዎች የት እንደሚገኙ በደንብ አልተጠኑም። ከስራዎቻቸው መካከል በመንበረ ፀባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል፣ በበዓለ እግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያን፣ በቅድስተ ቅዱሳን መግቢያ በሮች፣ በደብረ ብርሃን ከተማ በደብረ ብርሃን ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን እና በቀድሞ የፓርላማ አዳራሽ ግድግዳዎች ላይ የሚገኙ ስዕሎች፣ የራስ በራስ መልክዓ ምስል እና የአስቴር መንገሻ (በጊዜው በአዲስ አበባ ታዋቂና ዝነኛ የነበረችው የአፄ ዮሐንስ ፬ኛ የልጅ ልጅ እና የልጅ ኢያሱ ሚካኤል የመጀመሪያ ሚስት) መልክዓ ምስል እንዲሁም በታሪክና ምሳሌ መጽሐፍ ውስጥ የተረት ስዕል መግለጫዎች … ይጠቀሳሉ።
አገኘሁ እንግዳ ከሰዓሊነታቸው ባሻገር ገጣሚም ነበሩ። በግጥሞቻቸውም ስለኢትዮጵያውያን ጀግንነት ታሪክና አበርክቶ አውስተዋል። አገኘሁ በግጥማቸው ውስጥ በእናት ኢትዮጵያ አንደበት የተነገረ በማስመሰል ‹‹እስኪ ስማቸውን በተራ ላንሳው›› ወደኋላ ታሪክ ጠቅሰው የነባሩን ትውልድ የጀግንነት መንፈስና የነፃነት ክብርን ዋጋ ለራሳቸው ዘመን እንዲያወርሱ ይማፀናሉ። ስማቸውን እያነሱ ከገጠሙላቸው የኢትዮጵያ ቆራጥ ጀግኖች መካከል በጥቂቱ ስንመለከት፡-
ለዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስ
አሁንም ሙትልኝ ታጠቅ እንደገና፣
መቼም ሞት አይገድልህ ሞት በእጅህ ነውና።
የቴዎድሮስን ልጅ ማንም አይደፍርህ፣
አንተ ካልሞትክ በቀር ራስ በራስህ።
ለአፄ ዮሐንስ ፬ኛ
እስኪ ካሳን ጥሩን በል አንተ ያዘኝ፣
ቴዎድሮስን ወስዶ ካሣ አንተን ሰጠኝ።
እጅግ ደስ ይለኛል ያንተ ስም ሲነሳ፣
የቁና አፈር ንፉግ አንተ ነህ ወይ ካሣ።
ለራስ አሉላ አባነጋ
ይኸው ነጋ አሉላ ምጥዋ ገስግስ፣
አልወድም ባዕድ ሰው ከባሕር መለስ።
ክፉ አረም በቀለ በምጥዋ ቆላ፣
አሁን ሳይበረክት አርመው አሉላ።
ለራስ መንገሻ ዮሐንስ
አሉላ አባነጋ መንገሻን ጥራው፣
ያባቱ ነውና ጋሻዬን ስጠው።
አይከፈት በሩ መውጫ መግቢያችን፣
በል ተነስ መንገሻ ግጠም በር በሩን።
ለዳግማዊ አፄ ምኒልክ
ምኒልክ ዝም አልክወይ ተኩሎች ከበውኝ፣
አባርልኝ ወዲያ እንዳይጮሁብኝ።
ዓድዋ ላይ ጣለን የዘፈነለ’ት፣
ምኒልክ ጎራዴ ወረደ በአንገት።
ለእቴጌ ጣይቱ
ፎክራ ፎክራ ምንም አልቀረች፣
አልፋ ከሴቶቹ ወንድ አሰለፈች።
መድፉ መትረየሱ ምንም አልጎዳቸው፣
እንደጎመን ዝልቦ ጣይ አዛለቻቸው።
ለራስ መኮንን ወልደሚካኤል
ይህ ራስ መኮንን ውብ ገበሬ ነው፣
አላጌ ላይ ዘርቶ መቀሌ አጨደው፣
ዓድዋ ላይ ከምሮ መረብ ላይ ወቃው።
በተጨማሪም የራስ ዳርጌን፣ የራስ ጎበናን፣ የራስ ወልደጊዮርጊስን፣ የራስ አባተን፣ የራስ ወሌንና የሌሎችን ሹማምንት ነባሩን የነፃነት ብሔራዊ መንፈስና ገድል፣ ስሜትና አስተሳሰብ እንዲሁም ዝና በማንሳት በዘመኑ ትውልድ ውስጥ ለማስረጽና ለማውረስ በብርቱ ሞክረዋል።
ሰዓሊ አገኘሁ የጀመሩት ተተኪ ሰዓሊያንን የማፍራት ጥረቱ ባሰቡት ልክ ሳይሰምርላቸው ሞት ቀደማቸው። ስለአገኘሁ ሞት መንስዔዎች የሚነገሩትና የተፃፉት ማስረጃዎች የተለያዩ ናቸው። አንዳንዶቹ ምጸትና ሽሙጥ ያዘሉት ስዕሎቻቸው ለመሞታቸው ምክንያት እንደሆኑ ይገልፃሉ። በተለይም ባለስልጣናትን በአህዮች መስለው የሳሉት ስዕላቸው የሕይወት ዋጋ አስከፍሏቸዋል ይላሉ።
ሰዓሊ እሸቱ በጽሑፋቸው ላይ የጠቀሱት ደግሞ ከዚህ የተለየ ነው። ሰዓሊ እሸቱ ‹‹ስለሰዓሊ አገኘሁ አሟሟት ሰዓሊ አለ ፈለገሰላም ከአጎታቸው የሰሙትን ነገሩኝ›› ብለው በፃፉት ጽሑፋቸው ላይ እንዲህ ብለዋል…
‹‹ …የሞቱ ምክንያት በጊዜው በአዲስ አበባ የተነሳው ወሬ ነበር። ይኸውም በዘመኑ ሰዎች እጅግ በጣም የሚፈሯቸውና የንጉሰ ነገሥቱ ቀኝ እጅ የነበሩ ባለስልጣን የንጉሰ ነገሥቱን የመጀመሪያ ሴት ልጅ ለማግባት አማላጅ ይልካሉ። ንጉሡም ጉዳዩን ለዙፋን ጠባቂዎች ምክር ቤት ይልካሉ። ምክር ቤቱም በዘመኑ የጋብቻ መስፈርት መሰረት ገምግሞ ጥያቄውን ውድቅ ያደርገዋል።
ሰዓሊ አገኘሁ እንግዳ በጣም ግልጽና ደፋር ሰው ነበር። ውስጥ ውስጡን ይወራ የነበረውን ይህን የጋብቻ ጥያቄ ውድቅ መደረግና የውድቀቱን መነሻ ምክንያት እያነሳ በይፋ በተለይም በየመጠጥ ቤቱ በነፃ ስሜት የቀልድና የነገር መሳለቂያ አልፎም የፖለቲካ መተረቢያ አድርጎት ነበር። ሰዎች እጅግ በጣም ይፈሯቸው የነበሩት ባለስልጣንም በሁኔታው በመናደዳቸው ራሳቸው ወይንም ታማኞቻቸው ሳይሆኑ አይቀሩም ሰዓሊ አገኘሁን በመኪና ገጭተው የገደሉት። አገኘሁ እንደልማዱ አራት ኪሎ አካባቢ አምሽቶ ወደቀበና የቤቱ አቅጣጫ በእግሩ ሲሄድ ሺ ሰማንያ አካባቢ ሲደርስ በመኪና ተገጨ … ››
ሰዓሊ እሸቱ ጨምረውም ‹‹ በእርግጥም ሰዓሊ አገኘሁ እንግዳ የካቲት 30 ቀን 1939 ዓ.ም ወደ ማታ ያልታወቁ ሰዎች በሚነዱት መኪና ተገጭቶ መጋቢት 3 ቀን 1939 ዓ.ም ከዚህ ዓለም መለየቱን ‹አዲስ ዘመን› ጋዜጣ በመጋቢት 6 ቀን 1939 ዓ.ም ዕትሙ ሲገልጽ ‹የኤርትራ ድምጽ› ጋዜጣ ደግሞ በመጋቢት 12 ቀን 1939 ዓ.ም እትሙ ‹ … የአቶ አገኘሁ እጅ በሙያዋ ለኢትዮጵያውያን ሁሉ የመጀመሪያው መኩሪያና መመኪያ ትታይ ነበር።
ይህን ሁሉ ባለሙያነትን ይዛ የነበረችውን እጅ ልብም እንጂ አንዲት መኪና ጨከነችና ለማጥፋት መብቃቷን ሰማን። መኪናዋ አንድ ገደልኩ ብላ ይሆናል፤ አይደለም፤ ብዙዎችን መግደሏንና አገርንም መበደሏን አውቀንላታል። እሷ ግን ይህን ሁሉ አልተረዳቸውም። አገኘሁ ረቂቁን ነገር በስዕል አጉልቶ በመግለጽ እጅግ በጣም የበለጠ ስጦታ ነበራቸው … › በማለት መኪናዋን በሰውኛ ነፍስና ሃሳብ አካልና ተግባር እንዳላት አስመስሎ ‹ሆድ ሲያውቅ ዶሮ ማታ እንዲሉ› የጋዜጣው ጸሐፊ መኮንን ወርቃኘሁ መኪናዋን ይጠይቃታል። በሾርኔ ደግሞ ሾፌሩን ወይንም ባለስልጣኑን መጠየቁ ሳይታለም የተፈታ ነው›› ብለዋል።
ሰዓሊ እሸቱ ጥሩነህ ስለሰዓሊ አገኘሁ እንግዳ አበርክቶዎችና ልዩ ተሰጥዖዎች ሲገልፁ እንዲህ በማለት ነው …
‹‹ … ሰዓሊ አገኘሁ እንግዳ በኢትዮጵያ የመጀመሪያው ዘመናዊ ሰዓሊ የሚያሰኘውን ጥበባዊ ፈጠራ የፈፀመ አገር ወዳድ፣ አንደበተ ርቱዕ፣ ባለቅኔ፣ ፋና ወጊ ሰዓሊና መምህር ነበር/ነውም ሲባል እስካሁን የተገኘውን መረጃ በማጣቀስ ነው። እንዴት ቢሉ በዘመናዊ የኢትዮጵያ ሰዓሊያን ዓለም ውስጥ የመጀመሪያ የሆነውን የመልክዓ ምስላትና የገፀለታት ኪነ-ጥበቦችን አስቀምጦና አስመስሎ የመሳል ጥበባዊ ስርዓትን ያስተዋወቀ ሰዓሊ ነው።
የኢትዮጵያውያን ሴቶችን መልክዓ ምስላት በባሕል አለባበስ፣ በዕለት ስራ ላይ እንዳሉ፣ የዘመኑን ታዋቂ ሰዎች በማዕረግ አለባበሳቸው … በመሳል የተለየ ዘመናዊ ሰዓሊነቱን አስመስክሯል። ሰዓሊ አገኘሁ እንግዳ የራስ ምስል በሚለው ኪነ-ቅብ የራሱን መልክ እጅግ በጣም አስመስሎና የቀባ የመጀመሪያው ሰዓሊ ነው … ››
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአለ የስነ ጥበብና ዲዛይን ትምህርት ቤት ዳይሬክተርና የስነ-ጥበብ መምህር አቶ አገኘሁ አዳነ በበኩላቸው ስለሰዓሊ አገኘሁ አዳነ ቀደምትነትና አበርክቶ ለ‹‹አዲስ ዘመን›› ጋዜጣ ሲናገሩ እንዲህ ብለዋል።
‹‹ … አገኘሁ እንግዳ በዳግማዊ አፄ ምኒልክ ዘመነ መንግሥት ማብቂያ እና በንግሥት ዘውዲቱ ዘመነ መንግሥት መጀመሪያ ዘመናዊ የስዕል ትምህርት እንዲያጠኑ ወደ ውጭ አገራት ከተላኩ ኢትዮጵያውያን መካከል አንዱ ነበር። በወቅቱ ወደ ውጭ አገራት የተላኩት የስዕል ተማሪዎች አፈወርቅ ገብረኢየሱስ፣ አገኘሁ እንግዳ፣ አበበ ወልደጊዮርጊስ፣ ጌታቸው ዳፈርሳ እና ዘሪሁን ዶምኒክ ነበሩ። ነባሩ የኢትዮጵያ አሳሳል የሚባለው ከቤተ ክርስቲያን የአሳሳልና የአተራረክ ፈሊጥ ጋር የተገናኘ ነው። እነዚህ ሰዓሊያን ይህን ነባር አሳሳል ከምዕራቡ ዓለም ከተገኘ እውቀት ጋር ቀላቅለው አዲስ ስነ-ጥበባዊ ጣዕም አስተዋውቀዋል።
አገኘሁ እንግዳ ለቤተ ክህነት ቅርብ ሰው ነበሩ። ተወልደው ያደጉበትና የተማሩበት የጎንደሩ ማኅደረ ማርያም ገዳም ለሥዕል ጥበብ እጅግ ቅርብ ነው። አገኘሁ በልጅነታቸው በዚያ የተማሩት ነባር እውቀት ነበራቸው፤ በዚያ ነባር እውቀት ላይ ዘመናዊን እውቀት ጨመሩበትና የሁለቱ መቀላቀል አዲስ ስነ ጥበባዊ ቃና እንዲያስገኝ አድርገዋል። ስራዎቻቸው በተለያዩ አድባራትና አብያተ ክርስቲያናት፣ በኢዮቤልዩ ቤተ መንግሥት፣ በፓርላማና በብሔራዊ ሙዚየም ውስጥ ይገኛሉ።
ሌላው አስተዋጽኦዋቸው ተተኪ ሰዓሊያንን ለማፍራት ያደረጉት ጥረት ነው። ከፓሪስ ከተመለሱ በኋላ ከሰዓሊ አበበ ወልደጊዮርጊስ ጋር ሆነው ፈቃደኛ የሆኑ ባለተሰጥዖ ልጆችን የስዕል ትምህርት ያስተምሩ ነበር። ከአለ የስነ ጥበብና ዲዛይን ትምህርት ቤት በፊት የቀደመው ሙከራ የአገኘሁ የማስተማር ጥረትና ተነሳሽነት ነው። በአጠቃላይ አቶ አገኘሁ እንግዳ ቀደምት ከሚባሉት ዘመናዊ የኢትዮጵያ ሰዓሊያን መካከል አንዱና ዋነኛው ነበሩ።
አዲስ ዘመን መጋቢት 15/2013