በሀገራችን እየተሰሩ ያሉ ስራዎችና በቀጣይነት የተያዙ ዕቅዶች እንዲሁም የተገኙ ውጤቶችን አንድ ላይ ደምሮ አይኑን ገለጥ፤ ልቡን ከፈት አድርጎ ላያቸው ምንም አንኳን ተግዳሮቶች ቢኖሩም በኢትዮጵያ መፃኢው ጊዜ ተስፋ ሰጪ መሆኑ ቁልጭ ብሎ ይታያል። የተሻለች አገር ለመፍጠር የሚያስችሉ ጅምሮችና ቀጣይ ተስፋዎች ቦግ ብለው ይታያሉ። ባለፉት ሦስት የለውጥ ዓመታት በኢኮኖሚው ዘርፍ የተገኘው ውጤት ሲታይ የገንዘብ ስርጭት በ15 በመቶ ፤ ቁጠባ በ25 በመቶ ፤ የብድር አቅርቦት 38 ነጥብ 4 በመቶ ዕድገት አሳይቷል።
አሁን ላይ አገሪቱ ያለባትን የውጭ እዳ ጫና ባለፉት 3 ዓመታት ከነበረበት 37 ነጥብ 6 በመቶ ወደ 26 ነጥብ 8 በመቶ ዝቅ እንዲል ተደርጓል። እንዲሁም የብር ኖት በመቀየሩ ብቻ 6 ነጥብ 2 ሚሊዮን ዜጎች አካውንት በመክፈት 98 ቢሊዮን ብር መቆጠብ ችለዋል። ይሄ የኢኮኖሚው ምን ያህል ወደፊት እየሄደ መሆኑን አመላካች መስታወት ነው።
በ2010 ዓ.ም አጠቃላይ ባንኮች የሰበሰቡት 730 ቢሊዮን ብር ሲሆን በ2011 የተሰበሰበው 899 ቢሊዮን ብር ነው፤ በ2012 ለመጀመሪያ ጊዜ 1 ነጥብ 04 ትሪሊዮን ብር ተሰብስቧል። ዘንድሮ በስድስት ወራት ብቻ የተሰበሰበውም 1 ነጥብ 2 ትሪሊዮን ብር ደርሷል።
በሌላ በኩል በግብርናው እየታየ ያለው ውጤት ትልቅ ተስፋ ሰጪ የነበረ ነው። ክረምት ከበጋ ማምረት መቻል፤ መስኖ፣ ኩታ ገጠም እርሻ፣ ሜካናይዜሽን እና ሌሎችም በዘርፉ እየተሰሩ ያሉ ስራዎች በምግብ ራስን ለመቻል የታሰበውን ዕቅድ ከግቡ ለማድረስ የሚያስችል የተስፋ ብርሀን ፈንጥቀዋል። ከዚህም አለፍ ብሎ እስካሁን ያልተሞከሩትን ቴክኖሎጂዎች በመጠቀም ዳመናን ወደ ዝናብ ቀይሮ ኢኮኖሚውን ወደፊት ለማስፈንጠር ተስፋ ሰጪ ጅምር ተበስሯል። የግብርናውን ዘርፍ አሁን ካለው በእጥፍ በማዘመንና በማልማት እንደሀገር የሚታዩ የግብርና ምርት እጥረቶችን መቅረፍ ይቻላል። አሁን ኢትዮጵያ ይሄንን አቅም በመገንባት ላይ ናት።
ኢትዮጵያ ታላቅ ሀገር ነበረች። አሁንም ወደነበረ ክብሯ እና ስሟ የመመለስ ሥራ በተጠናከረ መልኩ እየተሰራ ነው። አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ፣ የሳተላይት ማምጠቅ የህዳሴ ግደብን ለፍጻሜ ማብቃት ታላቅነቷን ለመመለስ የተጀማመሩ እና ቀጣይነት ያላቸው ታላላቅ ክንውኖችና ውጤቶች ናቸው።
ይሄ ሁሉ ስኬት የተገኘው ግን አልጋ በአልጋ በሆነ መንገድ አይደለም። የኑሮ ውድነት፣ የኢኮኖሚ አሻጥር፤ የሰላም መደፍረስ እና ሌሎችም ኢኮኖሚውን የተገዳደሩት ችግሮች ባሉበት እንጂ። ችግሮችን እየተጋፈጡ ተስፋዎችን አርቆ በማሰብ በተሰራው ስራ ተስፋ አመላካች ውጤቶች ተገኝተዋል። በቀጣይ የሚተገበረው የአሥር ዓመቱ የፍኖተ ብልፅግና እቅድ ዓላማ ኢትዮጵያን የአፍሪካ የብልፅግና ተምሳሌት ማድረግ ነው። ኢኮኖሚውን ማሳደግ፣ የኢኮኖሚ ዘርፉንና ተዋናዮቹን እንዲሁም ተጠቃሚነትን ማሳደግና ድህነትን መቀነስ መቻልም ዓላማው ያደረገ ነው።
በቱሪዝም ዘርፍም ተመሳሳይ ጠንከራና የሚያኮሩ ስራዎች ተሰርተዋል። ሀገራችን ያላትን ሀብት በመጠቀም ቱሪስት ኢትዮጵያን መዳረሻ እንዲያደርግ ከዚህም ከፍተኛ ሀብት ለማግኘት ጎን ለጎንም የስራ ዕድሎችን ለማስፋት የሚያስችሉ ሰፋፊና አስገራሚ ጥረቶችና ውጤቶች ታይተዋል ። በአጭር ጊዜያት የተገኙት አመርቂ ውጤቶችም ሌት ተቀን በቁጭትና በጥንካሬ በመሰራቱ የተገኙ ሲሆን የክትትልና የቁጥጥር መንገዶቹም የአመራሩን ቁርጠኝነት ያሳዩ ናቸው። በቀጣይም በዚሁ ፍጥነት፣ በአንድነት፣ በሞራልና በቁጭት መስራት ከተቻለ ነገም የተሻለ ተስፋ በሀገራችን እንደሚኖር ያመላክታል። እስካሁን የተገኙ ውጤቶችም ዝም ብሎ ያለ ድካም የተገኙ አይደለም፤ በብዙ ተግዳሮት ውስጥ ታልፎ፣ ብዙ መሰዋዕትነት ተከፍሎና ብዙ አስቸጋሪ በሆኑ መንገዶች ታልፈው የተገኙ ናቸው።
በሀገሪቱ ውስጥ በነበረው የሰላም መደፍረስ፣ በዲሞክራሲያዊ ሂደት ባልዳበረ የፖለቲካ እንቅስቃሴ፣ ቅንነት በጎደለውና ለውጥን ለማደናቀፍ በሚሞክር ሴራና በሌሎችም ወደ ኋላ ጎታች የሆኑ ችግሮች ታልፈው ነው ውጤቶቹ የተመዘገቡት። ነገም ሀገራችን የተሻለ ደረጃ ላይ የምትደርሰው በተመሳሳይ አስቸጋሪ ሁኔታዎችን ታግላና አልፋ መሆኑ ግልጽ ነው። ከአፍሪካ በብልጽግና ማማ ላይ ተጠቃሽ ትሆናለች ሲባል እዚህ ደረጃ የሚደረሰው አልጋ በአልጋ በሆነ መንገድ በመጓዝና ቁጭ ብሎ ተስፋን በመሻት ብቻ አይደለም። በአንድነት ጠንክሮ በመስራት፣ በርካታ መሰናክሎች በመጋፈጥና እሾህ አሜካላዎችን ነቃቅሎ በማለፍ ብቻ አንጂ።
ለዚህ ደግሞ እያንዳንዱ ዜጋ የራሱን አስተዋጽኦ ማድረግ ይጠበቅበታል። የነገውን ብርሀን በተስፋ ማየትና ለብርሀኑ የራሱን አስተዋጽኦ ማድረግም ሁሉ ዜጋ ሊያደርገው የሚገባ አኩሪ ተግባር ነው። አሁን እንደሚታየው ከውስጥም ከውጪም የተደቀኑ፣ የማያልፉ የሚመስሉ ግን የምንወጣቸው በርካታ ተግዳሮቶች ተደቅነዋል። ይሁንና እነዚህን እንደተለመደው በጥበብና በእውቀት በመሻገር ተገዳሮቶችን አልፈን ወደ ብልጽግና ማማ መውጣታችን ግን አይቀሬ ነው!
አዲስ ዘመን መጋቢት 15 ቀን 2013 ዓ.ም