አንተነህ ቸሬ
የዋጋ ንረት በየጊዜው ማሻቀብ እንጂ ዝቅ ማለት አልሆነለትም። ይህም የኅብረተሰቡን፣ በተለይም ዝቅተኛ ገቢ ያለውን የኅብረተሰብ ክፍል፣ ኑሮ እጅግ የከበደ እንዲሆን አድርጎታል። ለዋጋ ንረቱ የተለያዩ ምክንያቶች ሲጠቀሱ ቆይተዋል። የዶላር የምንዛሬ ዋጋና የነዳጅ ዋጋ መጨመር እንዲሁም የምርት ግብዓቶችና የውጭ ምንዛሬ አቅርቦት እጥረት ተደጋግመው ሲነገሩ የኖሩ የዋጋ ንረቱ ምክንያቶች ናቸው።
እነዚህ ምክንያቶች ተደጋግመው ይገለፁ እንጂ ኑሮ ናላውን ላዞረው ኅብረተሰብ በሚፈለገው ደረጃ መፍትሄ አላስገኙም። ‹‹ኑሮውን አልቻልነውም … የዋጋ ንረቱ መፍትሄ ሊበጅለት ይገባል …›› የሚሉና ከተለያዩ አቅጣጫዎች ሲደመጡ የቆዩ የኅብረተሰብ ድምፆች ዛሬም እየተስተጋቡ ነው። አንዳንድ ግለሰቦች የዘንድሮው የዋጋ ንረት ከዚህ ቀደም ከነበረው ሁሉ የተለየ ስለመሆኑ ተናግረዋል። በአንዳንዶቹ ምርቶች ላይ ደግሞ በገበያ የሚታየው የዋጋ ንረት ጠዋትና እና ከሰዓት በኋላ የዋጋ ልዩነት እስከማሳየት የደረሰ ነው። የማዕከላዊ ስታስቲክስ ባለስልጣንም የዋጋ ንረቱ ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር ጭማሪ ማሳየቱን ይፋ አድርጓል።
እጅግ የሚያስገርመው ነገር አገሪቱ ከበቂ በላይ የምታመርታቸው ምርቶች ሳይቀሩ ዋጋቸው ሰማይ መድረሱ ነው። ለአብነት ያህል የአትክልትና ፍራፍሬ ምርቶች ከበቂ በላይ ተመርተው ከማሳ የሚያነሳቸው አጥተው ለብክነት እንደሚዳረጉ የምርቶቹ ባለቤቶች ይናገራሉ። በከተሞች ያለው የእነዚህ ምርቶች ዋጋ ግን ‹‹ጆሮ አይስማ›› የሚያሰኝ ነው።
‹‹ … አንዳንድ ጊዜ የአትክልትና ፍራፍሬ ገዢ ስለማይኖር ማሳ ላይ ይቀርና ከብት ይበላዋል …›› ይህ አትክልትና ፍራፍሬ አምራች ከሆነ አርሶ አደር የተነገረ ነው። አርሶ አደሮቹ እንደሚሉት ሽንኩርትና ቲማቲም ከማሳቸው ላይ የሚሸጡት ከአራት እስከ ስድስት ብር ነው። ምርቱ አዲስ አበባን ጨምሮ ወደ ሌሎች ከተሞች ከገባ በኋላ ግን ገበሬው ከሸጠበት ከእጥፍ በላይ በሆነ ዋጋ ይሸጣል። አትክልትና ፍራፍሬን ለማሳያነት ያህል ጠቀስኩ እንጂ በሌሎቹም ምርቶች ላይ ያለው የዋጋ ንረት የሚቀመስ አይደለም።
ከዓመት ዓመት መጨመር እንጂ መቀነስ ለማያሳየው ከፍተኛ የዋጋ ግሽበት መንስዔዎቹ መሠረታዊ የሆኑ የምጣኔ ኃብት መዋቅሮች አለመስተካከል፣ የምርት አቅርቦት እየቀነሰ መምጣት እንዲሁም የሰላምና የፀጥታ መደፍረስ እንደሆኑ የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች ያስረዳሉ። የውጪ ምንዛሬ እጥረት እና የገንዘብ የመግዛት አቅም መዳከም ተደራርበው የኑሮ ውድነትን ማክበዳቸውንም ይገልጻሉ።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ሰማይ ለነካው የምርቶች ዋጋ በምክንያትነት ከሚጠቀሱ ነገሮች አንዱ የነዳጅ ዋጋ መጨመር ነው። በዚህም ምክንያት የትራንስፖርት ታሪፍ ላይ ማስተካከያ ተደርጓል። መቼም ‹‹ነዳጅ ጨመረ›› ሲባል የማይጨምር ዋጋ የለም። በዚህም ምክንያት የነዳጅ ዋጋን ሰበብ በማድረግ በእያንዳንዱ እቃ ላይ የሚጨመረው እያንዳንዱ ዋጋ ተጠራቅሞ ኅብረተሰቡ ትከሻ ላይ ያርፋል።
ታዲያ በዚህ ሁሉ ምስቅልቅል መሐል ደግሞ በንግድ ሰንሰለት የሚፈጠርና በኅብረተሰቡ በተለይም ደግሞ በሸማቹ ላይ የተጋረጠ እጅግ አደገኛ ነቀርሳ አለ። ይህ ውስብስብ የንግድ መንገድ የደላሎች ጫና የበረታበት ሰንሰለት ነው። በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ በደላሎች ተፅዕኖ ስር ያልወደቀ የኢኮኖሚ ዘርፍ የለም። ‹‹ደላላ በመሐል ሲገባ ገበሬ እና ነጋዴ አይገናኙም። ደላላና ነጋዴ ይነጋገራሉ። ደላሎች ከገበሬው እንደፈለጉ ገዝተው ነው ለነጋዴው የሚሸጡት …›› ይላሉ አርሶ አደሮቹ። ይህ ሁኔታ ደግሞ ገበሬውንም ሆነ ሸማቹን ተጠቃሚ እንዳይሆኑ ከማድረጉም ባሻገር የኅብረት ስራ ዩኒየኖች ምርቶችን በሙሉ አቅማቸው ተረክበው ለተጠቃሚው ማድረስ እንዳይችሉ አድርጓቸዋል። ይህ ቅጥ ያጣው የደላሎች ተግባር ለአገሪቱ ምጣኔ ሀብትም ትልቅ መሰናክል ሆኗል።
መንግሥት በበኩሉ የዋጋ ንረቱን ለመቆጣጠር ይረዳሉ ያላቸውን ተግባር እያከናወነ እንደሚገኝ ይገልጻል። የአዲስ አበባ ከተማ ንግድ ቢሮ ከሦስት ሳምንታት በፊት በሰጠው መግለጫ ምክንያታዊ ባልሆነ የዋጋ ጭማሪ እና መሰል በሆኑ ህግ ወጥ የንግድ ተግባራት ላይ በሚሳተፉ ነጋዴዎች ላይ የጀመረውን እርምጃ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቋል። አቅርቦትና ፍላጎትን ለማጣጣምና ዋጋን ለማረጋጋት የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑና መሰረታዊ የፍጆታ ምርቶችን ተደራሽነት ለማረጋገጥ ጥብቅ ቁጥጥር እየተደረገ እንደሆነ ገልጿል። በሕገ ወጥ መልኩ ተከማችቶ የተገኘ ዘይትና ስኳር በቁጥጥር ስር እንዲውል ተደርጎ በህብረት ስራ ማህበራት በኩል እንዲሰራጭ ስለመደረጉም አስታውቋል።
ሕገ ወጥ የዋጋ ጭማሪ ያደረጉ ሱቆችን ማሸግም ሌላው እርምጃ ነው። ይህ እርምጃ ከዚህ ቀደምም እንደመፍትሄ አማራጭ ሲተገበር የቆየ ተግባር ነው። ሱቆችን ማሸግ/መዝጋት ምን ያህል አዋጭ የመፍትሄ አማራጭ እንደሆነም ሊታሰብበት ይገባል። ሱቆች ሲታሸጉ የሚታሸገው ምርት/ሸቀጥ በአቅርቦት ላይ የሚፈጥረው የራሱ ጫና ይኖራል። ይህ እርምጃ የአቅርቦት ሰንሰለቱን እንደሚጎዳው ልብ ሊባል ይገባል። እንዲያውም የዋጋ ንረትን ሊያባብስ የሚችልበት እድል አለ። በተጨማሪም ሱቆችን ማሸግ የመጨረሻ አማራጭ ሆነው ከሚጠቀሱ እርምጃዎች መካከል አንዱ በመሆኑ የመጨረሻ አማራጮችን ከመተግባር አስቀድሞ ሌሎች እርምጃዎችን መውሰድ ያስፈልጋል።
በሌላ በኩል የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለሸገር ዳቦ ፋብሪካ በየወሩ 100 ሺህ ኩንታል ስንዴ አቀርባለሁ ብሏል። ይህም ፋብሪካው በቀን የሚያመርተውን የዳቦ መጠን ከ900ሺ ወደ አንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን እንደሚያደርሰው ተነግሯል። ለኑሮ ውድነት ጊዜያዊ መፍትሄ ለማምጣት በጎ እርምጃ ነው ተብሎም ተስፋ ተጥሎበታል።
የምርት መሸሸግ ለዋጋ ንረቱ ዋነኛ ምክንያት እንደሆነ በሹማምንቱ ዘንድ ተደጋግሞ ሲነገር ይሰማል። ነገር ግን ለምርት መሸሸግ ምክንያት ስለሆነው ጉዳይም ማወቅና ማብራሪያ መስጠት ተገቢ ነው። ‹‹የአቅርቦት አሻጥር እንዲከሰት ያደረጉት ምክንያቶች ምንድን ናቸው?›› ለሚለው መሰረታዊ ጥያቄ በቂ ምላሽ መስጠት ያስፈልጋል።
የሆነው ሆኖ በነዳጅም ሆነ በሌላ ምክንያት የናረው የሸቀጦችና የምርቶች ዋጋ ጠንካራ የሆነ መንግሥታዊ ቁርጠኝነትን የሚፈልግ አንገብጋቢ ጉዳይ ነው። የኑሮ ውድነትን ጨምሮ ለበርካታ የአገሪቱ ችግሮች መነሻ የሆነው የሰላምና መረጋጋት መደፍረስ ዋነኛ ትኩረት ሊያገኝ ይገባል። በተለይ ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የተከሰተው የፀጥታ መደፍረስ የምጣኔ ሀብት እንቅስቃሴውን ክፉኛ ጎድቶታል። የአገሪቱ የሰላምና ፀጥታ ሁኔታ ከመሻሻል ይልቅ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየባሰበት ሄዷል። ሰላም ካልሰፈነ ማረስ፣ መነገድ፣ አምርቶ ወደ ውጭ መላክ፣ ኢንቨስትመንት … ፈፅሞ የማይታሰቡ ናቸው። ሰላምን ለማስፈን ዜጎችም አስተዋፆኦ እንዳላቸው ባይካድም ዋነኛው ኃላፊነት የመንግሥት ነው። የማንኛውም መንግሥት መሰረታዊው (የመጀመሪያውና ትንሹ) ኃላፊነቱ ሰላምና ፀጥታን ማስፈንና የዜጎችን ደህንነት ማስጠበቅ ነው።
የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች እንደሚሉት፤ በአገሪቱ እየታየ ያለው የኑሮ ውድነት ዘላቂ መፍትሄ ሳያገኝ ከቀጠለ አገሪቷን ውስብስብ ወደ ሆነ ችግር ሊመራት ይችላል። ስለሆነም መንግሥት ሰላምን በማስፈን ለኑሮ ውድነቱ የአጭር፣ የመካከለኛና የረጅም ጊዜ መፍትሄዎችን ማበጀት ይጠበቅበታል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 13/2013 ዓ.ም