መቼም ቢሆን እውነት እውነት ነው፡፡ እውነት እውነት ያዥውን ወደ ፈለገው አቅጣጫ ያሻግረዋል፤ ያለማዋል፤ ከክፉ ይታደገዋል፡፡ እውነት ያላት ሀገር የቱንም ያህል በውሸተኞች ብትፈተን የጊዜ ጉዳይ ነው እንጂ የሀገሪቱ እውነት ማሸነፉ አይቀርም፡፡
እውነት አለኝ ተብሎ ግን ተተኝቶ አይታደርም፡፡ እውነትን ቀብረው ሀሰትን ሊያነግሱ የሚፈልጉ ለእዚህም ተኝተው የማያድሩ አሉና እውነት መጠበቅ ይኖርበታል፡፡ እውነት የሚጠበቀው ደግሞ እውነትነቱን ማስገንዘብ ሲቻል ነው፡፡ እውነትነቱን ላላወቁ እንዲሁም ላልተረዱ ሁሉ ተከታታይነት ባለው መልኩ ማስገንዘብ ይገባል፤ ለእዚህም የተለያዩ መንገዶችን መጠቀም ያስፈልጋል፡፡ ይህ ሲሆን እውነት በሀሰተኞች ሳይሸፋፈን ሳይሸረሸር ህያው ሆኖ ይቆያል፡፡
ኢትዮጵያ በቅርቡ የትህነግ ቡድን በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በተላላኪዎቹ ዜጎችን የጨፈጨፈው አንሶት በመከላከያ ሰራዊት ሰሜን እዝ ላይ በጫረው እሳት በትግራይ ክልል በመሸገው በዚህ ቡድን ላይ የሕግ ማስከበር ዘመቻ አካሂዳለች፡፡ በዘመቻውም ቡድኑን በ15 ቀናት ውስጥ ድል በማድረግ አስወግዳዋለች፡፡ ሀገሪቱ ከዚያ በኋላ እየሰራች ያለችው ያልተያዙ የቡድኑን ወንጀለኞች ይዞ ለሕግ ማቅረብ፣ በሕግ ማስከበር ዘመቻው ድባቅ ሲመታ ጁንታው ያወደማቸውን መሠረተ ልማት ጠግኖ ወደ ሥራ ማስገባት፣ ሰብአዊ ድጋፍ ማቅረብ፣ አዲስ ጊዜያዊ አስተዳደር አዋቅሮ ነገሮች ወደ ቀድሞ ሁኔታቸው እንደሚለሱ ማድረግ ላይ ተጠምዳለች፡፡ ይህ ሁሉ ቁልጭ ያለ እውነታ ነው፡፡
ጁንታው በሕግ ማስከበሩ ላይመለስ ሲወገድ ‹‹በችሎት ሲረታ ሚስቱን ከቤት መታ›› እንደሚባለው ዓይነት ምንም በማይመለከታቸው የማይካድራ ንጹሃን ዜጎች ላይ ማንነትን መሠረት ያደረገ ጭፍጭፋ ፈጸመ፤ በእዚህ ጭፍጨፋ ከአንድ ሺ በላይ ንጹሃን ዜጎችን ሕይወት ቀማ፡፡ በጭፍጨፋው ክፉና ደግን ያልለዩ ሕፃናት፣ «ልጤ የተራሰ መቃብሬ የተማሰ» ብለው ሞታቸውን የሚጠብቁ አዛውንቶች፣ ሴት መግደል ነውር በሆነባት ሀገራችን እናቶችና ልጃገረዶች በአሰቃቂ ሁኔታ ተገድለዋል፡፡ ይህ ግልጥልጥ ያለ እውነት ነው፡፡ አንዳንድ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃንና ድርጅቶች ጭምር ይህን አረጋግጠዋል፡፡
የኢትዮጵያ መንግሥት በክልሉ ሰብአዊ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ወገኖች የምግብና የመድኃኒት ድጋፍ እያቀረበ ነው፡፡ ከድጋፉ 70 በመቶው እየቀረበ ያለው በኢትዮጵያ መንግሥት ነው፡፡ 30 በመቶውን ማቅረብ ያለባቸው የውጭ የእርዳታ ድርጅቶች ቢሆንም እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ያንን እያደረጉ አይደለም፡፡ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃንና የእርዳታ ድርጅቶች ባቀረቡት ጥያቄ መሠረት ትግራይ ውስጥ እንዲገቡ ተደርጓል፡፡ እነዚህ ለአብነት የተጠቀሱ እውነታዎች ናቸው፡፡
እነዚህን እውነታዎች ትንሽ ትልቁ መረጃ የሚደርሰው ዓለም አቀፉም ማህበረሰብና መገናኛ ብዙኃን፣ ምዕራባውያን ሀገሮች፣ የእርዳታ ድርጅቶች በሚገባ አያውቋቸውም ተብሎ አይገመትም፡፡ ጅብ በበላበት ይጮሃል እንዲሉ ከጁንታው ጋር በጥቅም ተሳስረው የነበሩት እነዚህ አካላት ግን ዓይናቸውን ጨፍነው ጆሯቸውን ጠቅጥቀው የኢትዮጵያን እውነት አላየሁም አልሰማሁም ብለው፣ የሚያውቁትም የማያውቁ መስለው ታይተዋል፡፡ የጁንታው ርዝራዦች መንግሥት በትግራይ እያደረገ ያለውን ሁሉ በመካድ የአዞ እንባ እያነቡ ባሰራጩት የሀሰት መረጃ ኢትዮጵያ የምዕራባውያኑ አጀንዳ እንድትሆን አድርገዋት እርምጃ ለመውሰድ እስከ ማቆብቆብ ተደርሶም ነበር፡፡
ይህ እንዲሆን የተደረገው ደግሞ በውጭ ሀገር በሚኖሩ የጁንታው ርዝራዦች ነው፡፡ እነዚህ የእናት ጡት ነካሾች የዲጂታል ቴክኖሎጂን በመጠቀም ባሰራጩት የሀሰት መረጃ ኢትዮጵያን ዋጋ ያስከፈለ የጥፋት ተልዕኮ አራምደዋል፡፡
በዚህ የተቆጡት በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን፣ ዲፕሎማቶች፣ በውጭ የሚገኙ ምሁራን፣ የኢትዮጵያ ወዳጆች ይህን ሀሰት ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ማስገንዘብ በመቻላቸው፣ ርዝራዦቹ የሚያሰራጯቸው መረጃዎች ሀሰተኛነት በተለያዩ መንገዶች እየተረጋገጡ መምጣታቸው እውነታችንን ይበልጥ ለማሳየት ዕድል ፈጥረውልናል፡፡
እነዚህ አቅጣጫዎች መቀየር አለባቸው፡፡ በእውነታችን ላይ ዘመቻ ሲከፈት እየተነሳን አጽፋ ለመስጠት የምናደርገው መሯሯጥ ባይከፋም፣ ወሳኙ መንገድ እውነታችንን ለጎረቤት ሀገሮች፣ ለምሥራቅ አፍሪካ ሀገሮች፣ ለአፍሪካ ህብረት፣ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብና ለተለያዩ ሌሎች ሀገሮች በየጊዜው ማስገንዘብ የሚያስችለንን ሥርዓት መዘርጋት ነው፡፡ ይህ ደግሞ በዘላቂነት መካሄድ ይኖርበታል፡፡ ለእዚህም ተቋም ማቋቋም ካስፈለገም መቋቋም ይኖርበታል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃንን፣ በየጉዳያችን በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚታወቁ ኢትዮጵያውያን እንዲሁም የውጭ ሀገር ምሁራንና ታዋቂ ሰዎችን፣ ወዘተ መጠቀም የሚያስችል ሁኔታ መፍጠር ይኖርበታል፡፡ አስፈላጊ ናቸው ተብለው የሚታመኑ በተለያዩ ዘርፎች ላይ የሚሰሩ ዓለም አቀፍ ድርጅቶችን መጠቀምም ይገባል፡፡
እውነታ አለን ብሎ መቀመጥ ብቻውን የምንፈልገውን ያህል እንድሄድ አያደርግም፡፡ ተቋም አቋቁሞ፣ በጀት መድቦ፣ በክፍያ የሚፈጸም ከሆነም እየከፈሉ፣ በትብብር የሚደረግ ከሆነ በትብብር እነዚህን አካላት በመጠቀም እውነታችንን ሁሌም ማስረጽ አለብን፡፡ ይህ ሲሆን እውነታችን ለአፍታም ቢሆን ጥርጣሬ ውስጥ አይገባም፡፡ ይህ ሲሆን በእውነታችን ላይ አንዳች ችግር ለመፍታት የምናደርገውን ሩጫ እናስቀራለን፤ ቢያንስ እንቀንሳለን፡፡
አዲስ ዘመን መጋቢት 13/2013 ዓ.ም