አስመረት ብስራት
ልጆች እንዴት ናችሁ ሰላም ነው። ልጆች በኮሮና ቫይረስ የሚያዙ ሰዎች እየበዙ ስለመጡ እንደበፊቱ ትምህርት ቤት እንዳይዘጋ አድርጉ የተባላችሁትን ጥንቃቄ በሙሉ አድርጉ እሺ። ስለ ጥንቃቄያችሁ ያነጋገርኳቸው ልጆች ማስክ በትክክል እንዳማታደርጉ ነግረውኛል። ይሄ ትክክል አይደለም።
እዮሲያስ ስሜነህ ሰላም ትምህርት ቤት የአምስትኛ ክፍል ተማሪ ነው። እዮሲያሰ ኮሮና ቫይረስን ለመከላከል ሁልጊዜ የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛዎችን እንደሚያደርግ ይነግረናል። ሌሎች ልጆች ግን ማስክ ሳያደርጉ የሚጫወቱትን ነገር እንዲቀንሱ ይመክራል።
ጓደኞቹ መተቃቀፍና መላፋት እንደሚያስደስታቸው የሚነግረን እዮሲያስ ልጆች እባካችሁ እንዳንታመም ራሳችንን ከዚህ አስከፊ ቫይረስ መጠበቅ ይኖርብናል ይለናል።
ሌላዋ የሰላም ትምህርት ቤት የኬጂ3 ተማሪ የሆነችው ብሌን ይትባረክ በበኩሏ በእነሱ ትምህርት ቤት ህፃናት ማስክ በትክክል አለማድረጋቸውን ትናገራለች። ብሌን ማስክ ሳደርግ ስለሚያፍነኝ ሁልጊዜ እያወለኩኝ ነው የምጫወተው ትላልች።
እነዚህ ልጆች ራሳቸውን ለመጠበቅ የግድ ማስክ ማድረግ ቢኖርባቸውም በትክክል እያደረጉ አለመሆኑን ተመልክተናል። ለመሆኑ ልጆች የፊት ጭምብል መጠቀም አለባቸው? ስንል የኢትዮጵያ የህክምና ማህበር ፕሬዚዳንትና የኮቪድ 19 ሳይንሳዊ አማካሪ ምክር ቤት ሊቀ መንበር የሆኑትን ዶክተር ተግባር ግዛው ጠይቀናቸው ነበር።
በአንዳንድ ትምህርት ቤቶች እና በልጆች መዋእለ ሕጻናት ውስጥ በልጆች ላይ ጭምብልን ስለመጠቀም አንዳንድ የተሳሳቱ አመለካከቶች እንዳሉ እየሰማን ነው ይላሉ። ከ5 አመት በታች ላሉ ሕፃናት ሁሉ ጭምብልን አለመጠቀም መደበኛ እየሆነ መጥቷል፣ ምንም እንኳን አካላዊ ርቀቱ ዋስትና ባይሰጥም። ይህንን መልዕክት ማስተላለፍ ለሚመለከታቸው የትምህርት አካላት መልዕክት ያስተላልፋል እና ስርጭትን በስፋት ለመከላከል ይረዳል ብዬ አስባለሁ ይላሉ።
ዶክተር ተግባር የዓለም የጤና ድርጅትን እና የዩኒሴፍን ምክር ጠቅሰው እንደነገሩን ከ 5 ዓመት በታች የሆኑ ልጆች ጭምብል ማድረግ የለባቸውም። ምክንያቱም ጭምብሉን በደህና እና በተገቢው ሁኔታ መጠቀም ስለማይችሉ ብለዋል። በአንዳንድ አስገዳጅ ሁኔታዎች ግን የፊት ጭምብል መጠቀም ይኖርባቸዋል፣ ለምሳሌ ከሠዎች ቢያንስ የአንድ ሜትር ርቀት ዋስትና መስጠት በማይችሉበት ጊዜ በእነዚህ ሁኔታዎች ውስጥ ህፃኑ ጭምብል ከለበሰ ደህንነቱ የተጠበቀ ይሆናል። አጠቃቀምን ለመቆጣጠር ወላጅ ወይም ሌላ አሳዳጊ ክትትል ማድረግ አለበት።
በተጨማሪም ከ6 እስከ 11 አመት ለሆኑ ህጻናት ጭምብልን ለመጠቀም የተወሰነው በአንዳንድ ሁኔታዎች ላይ የተመሠረተ መሆን እንዳለበት የዓለም የጤና ድርጅት እና ዩኒሴፍ ይመክራሉ። ዕድሜያቸው 12 እና ከዚያ በላይ የሆኑ ልጆች ልክ እንደ አዋቂዎች በተመሳሳይ ሁኔታ ጭምብል ማድረግ አለባቸው ይላሉ።
ልጆች እናንተ የአገር ተረካቢ ትውልዶች ስለሆናችሁ ራሳችሁን በመጠበቅ ጤነኛ እንድትሆኑ እንደሚፈልጉም ዶክተር ተግባር ተናግረዋል። ስለዚህ በተቻላችሁ መጠን ራሳችሁን ከአስከፊው ኮሮና ቫይረስ ጠብቁ እሺ። መልካም ሳምንት።
አዲስ ዘመን መጋቢት 12/2013