መጋቢት አራት ቀን 2012 ዓ.ም ለሀገራችን ትልቅ የወረርሽኝ ስጋት የተደቀነበት ዕለት ነበር። ዕለቱ ኮቪድ 19 በሀገራችን የተከሰተበት ወቅት በመሆኑ መላ ኢትዮጵያውያን የተደናገጡበትና በብዙ ጭንቀት የተዋጡበት እንደነበር ሁላችንም የምናስታውሰው ነው። በዕለቱ በተለይ የአዲስ አበባ ጎዳናዎች ከወትሮው በተለየ ሁኔታ ጭር ያሉበትና የሰዎች እንቅስቃሴም በከፍተኛ ሁኔታ ቀንሶ ሰዎች በቤታቸው የተከተቱበት ሁኔታ ተፈጥሮ እንደነበር አይዘነጋም።
ይህ ግን በወቅቱ በዚያው አልቀጠለም ነበር። በተለይ በወቅቱ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር አንድ ወይም ሁለት እየሆነ ሲመጣና በዚያው ልክም አገግመው የሚወጡ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ ሲመጣ በርካታ ዜጎች በሽታውን ወደመናቅ የመጡበት ሁኔታ ተፈጠረ። ይሁን እንጂ መጋቢት 27 ቀን 2012 ዓ.ም አንድ የ60 ዓመት አዛውንት በኮቪድ 19 መሞታቸውን የጤና ሚኒስቴር ይፋ ማድረጉን ተከትሎ ዳግም መደናገጡ በረታ። በዚህ ዕለት በተለይ አዲስ አበባ ዳግም በ ዝምታ የተዋጠችበት ዕለት ነበር።
በእርግጥ ቫይረሱ በዚህ መልኩ መደናገጥን የፈጠረው በሀገራችን ብቻ አልነበረም። በርካታ አውሮፓውያንና አሜሪካውያን ጭምር በቫይረሱ የተነሳ ለከፍተኛ ጭንቀት የተዳረጉበት ወቅት እንደነበር ይታወሳል። በዚህ የተነሳ በአሜሪካ የሕክምና ዶክተር ራሷን እስከማጥፋት የደረሰችበት፣ የጀርመን የገንዘብ ሚኒስትር ከሥራቸው በገዛ ፈቃዳቸው የለቀቁበት እና በርካቶች ለከፍተኛ የአእምሮ ጭንቀትና ድንጋጤ የተጋለጡበትን ነባራዊ ሁኔታ ሰምተናል።
ይህ ሁኔታ ታዲያ በዚያው ደረጃ ሊቀጥል አልቻለም። በአንድ በኩል የበሽታው ስርጭት እየጨመረ ሲሄድ በሌላ በኩል ግን የኅብረተሰቡ ፍራቻ እየቀነሰ የሄደበት ሁኔታ ተፈጥሮ ቆይቷል። በተለይ አሁን አሁን ኅብረተሰቡ በሽታው ከሚያስከትለው አደጋ በተቃራኒው ስለበሽታው እየተረሳ መጨነቁም ቀርቶ በአግባቡ መጠንቀቁም የቆመበት ሁኔታ በስፋት ይስተዋላል። ይህ ደግሞ ትልቅ ዋጋ እስከፈለ ይገኛል።
ሰሞኑንም ኢትዮጵያ በሞትም ሆነ በቫይረሱ ስርጭት ከፍተኛ ቁጥር አስመዝግባለች። በአንድ ቀን ብቻ ከሁለት ሺህ በላይ ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸውን ስንሰማና የሟቾች ቁጥርም በአንድ ጀምበር ብቻ ከ30 ሲዘል አይተን ዛሬን ስለበሽታው የማንጨነቅና ተገቢውን ጥንቃቄ የማናደርግ ከሆነ ከማንወጣው አደጋ ውስጥ መግባታችን አይቀርም።
ከሕክምናውም ጋር በተያያዘ በአሁኑ ወቅት ለጽኑ ታማሚዎች የሚያገለግለው የአርተፊሻል መተንፈሻ ወይም የቬንቲለተር እጥረት መኖሩን የጤና ሚኒስቴር በተደጋጋሚ ሲገልፅ መቆየቱ ይታወቃል። ከዚህም አልፎ አሁን ደግሞ ማቆያም ለማግኘት አስቸጋሪ የሆነበት ደረጃ ላይ ደርሰናል። ይህ ደግሞ ምን ያህል ከፍተኛ ችግር ውስጥ እንዳለን የሚያመላክት ነው።
በአሁኑ ወቅት የበሽታው ክትባት መገኘቱ እውን ቢሆንም ይህ ግን ለእኛ አስተማማኝ መፍትሄ አይደለም። ምክንያቱም በአንድ በኩል ዋጋው በእኛ የኢኮኖሚ ሁኔታ ከምንችለው በላይ ነው፤ በሌላ በኩል ደግሞ ቫይረሱ በራሱ ተለዋዋጭ ባህርይ ያለው በመሆኑ ራስን ከዚህ በሽታ መከላከሉ ከሁሉም የተሻለው መፍትሄ ነውና።
በአገራችንም ኮቪድ 19 ያደረሰው ኪሳራ ከፍተኛ ነው። እስካሁን ድረስ የኢኮኖሚ ጉዳቱ መጠን በጥናት ባይረጋገጥም ከፍተኛ መሆኑ ግን አይካድም። ለዚህም የተቀዛቀዙት የንግድ እንቅስቃሴዎችና በማህበራዊ ዘርፉ ያጋጠመው ውጥንቅጥ አንድ ማሳያ ሊሆን ይችላል። በተለይ ቀድሞውንም በቋፍ ላይ የነበረው የአገራችን የትምህርት ዘርፍ ምን ያህል በከፍተኛ ቀውስ ውስጥ እንደገባ የብዙዎቻችን ቤት ምስክር ሊሆን ይችላል።
በአሁኑ ወቅት ደግሞ ከፍተኛ የዋጋ ግሽበትና የኑሮ ውድነት ባጋጠመበትና መንግሥት በዚህ ላይ በከፍተኛ ሁኔታ እየተረባረበ ባለበት ሁኔታ የኮቪድ 19 መስፋፋት ተጨማሪ የኢኮኖሚ ቀውስ ማስከተሉ አይቀርም። በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ በአሁኑ ወቅት ካለብን ዘርፈብዙ ችግር አንጻር በቀላሉ መከላከል የምንችለውን ኮቪድ 19 በራሳችን እንዝላልነት መከላከል ካቃተን ተጨማሪ አደጋ ማምጣት ነውና በጤና ባለሙያዎች ለሚሰጡ ምክሮች ጆሮ ልንሰጥ ይገባል።
ስለዚህ እያንዳንዱ ዜጋ እነዚህን ሁለት ተቃርኖዎች ከወዲሁ ማረም ይጠበቅበታል። በአንድ በኩል የቫይረሱ ስርጭት በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ መሄዱ እንደተጠበቀ ሆኖ ለዚህ የሚመጠን ቦታና ሕክምና ቦታ አለመኖሩ አንድ ጉዳይ ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ ኅብረተሰቡ ቫይረሱ የጠፋ እስኪመስል ድረስ ለጉዳዩ የሚሰጠው ትኩረት አነስተኛ መሆኑ ቆም ተብሎ ሊታሰበብት የሚገባው ነው!
አዲስ ዘመን መጋቢት 12 ቀን 2013 ዓ.ም