በአሁኑ ወቅት የተከሰተው ከፍተኛ የዋጋ ግሽበትና የኑሮ ውድነት የሁሉንም በር ያንኳኳ ጉዳይ ነው ማለት ይቻላል። በተለይ በከተሞች በመኖሪያ ቤት፣ በምግብና አልባሳት ላይ ብቻ ሳይሆን እንደ ትራንስፖርት፣ ትምህርትና ጤና ባሉ ማኅበራዊ አገልግሎቶችን በመሳሰሉት መስኮች ላይ እየተፈጠረ የመጣው ምጣኔ ሀብታዊ ጫና ከብዙኃኑ ሕዝብ የዕለት ገቢ ጋር ያልተመጣጠነ ሆኖ ይገኛል። የኑሮ ውድነት ባደጉትም ሆነ በማደግ ላይ ባሉት አገራት ሊወገድ የማይችል የኢኮኖሚው አንድ አካል ቢሆንም እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ቁጠባና ኢንቨስትመንት ደካማ በሆነባቸው አገራት ግን ጫናው የበረታ ነው፡፡
በኢትዮጵያ ከህዝብ ቁጥር መጨመርና ከዚሁ ጋር ተያይዞ በአቅርቦትና በፍላጎት መካከል ያለው ልዩነት እየሰፋ መምጣት ጋር ተያይዞ የሸቀጦችና የፍጆታ ዕቃዎች ዋጋ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየናረ መጥቷል። ከዚሁ በተጓዳኝ ግን አላስፈላጊ የሆነ ጥቅም ለማግኘት ሲባል በአንዳንድ ስግብግብ ነጋዴዎች ዕቃዎችን በመደበቅ የዋጋ ጭማሪ ለማድረግ የሚደረጉ ጥረቶችም ለኑሮ ውድነቱ መናር የራሱን የሆነ አሉታዊ አስተዋጽኦ በማበርከት ላይ ይገኛል፡፡
በመንግሥት በኩል በየጊዜ እያሻቀበ የመጣውንና ወደ ሁለት አሃዝ እያደገ የሄደውን የኑሮ ውድነት ለመግታትና ወደ አንድ አሃዝ ለማውረድ በርካታ ጥረቶች ሲደረጉ ቆይተዋል፡፡በተለይም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣውን የኑሮ ውድነት በዘላቂነት ለመፍታት በመሰረታዊ የንግድ ዕቃዎች ላይ የዋጋ ድጐማ በማድረግ ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ሲያደርግ መቆየቱ ይታወሳል። ሆኖም ግን ዘይት፤ ስኳር፤ የምግብ እህሎችና አትክልትና ፍራፍሬ ላይ ያለው የኑሮ ውድነት ከማይቀመስበት ደረጃ ላይ ደርሷል። በተለይም የዘይት ጉዳይ ለሸማቹ የክት ልብስ ሆኖበታል፡፡
በኢትዮጵያ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ከሚወጣባቸውና መሠረታዊ ከሚባሉ ምርቶች መካከል የምግብ ዘይት አንዱ ሲሆን በዓመት ከ620 ሚሊዮን ዶላር በላይ ማለትም ከ25 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ የሚደረግበትም ነው። በአጠቃለይ መንግሥት ኅብረተሰቡን የዘይት ፍላጎት ለማሟላት በየወሩ 52 ሚሊዮን ዶላር ወይም ከሁለት ቢሊዮን ብር በላይ ለምግብ ዘይት ፍጆታ ወጪ ቢያደርግም እጥረቱ ከመሻሻል ይልቅ ጭራሹን እየባሰበት ይገኛል። በሌላም በኩል የኑሮ ውድነቱን ለመቀልበስ መንግሥት 24 ሚሊዮን ብር መድቦ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ለህዝብ ከገለፀ ቆየ ቢሆንም አሁንም ብዙም የሚታይ ለውጥ አልመጣም፡፡
ስለዚህ መንግሥት እየወሰዳቸው ያሉ ጥረቶች ፍሬ አለማፍራታቸውና የኑሮ ውድነቱ በዚህ ደረጃ ተደግፎ ውጤት ካላመጣ ችግሩ ሰው ሠራሽ መሆኑን የሚያመላክት ነው። ከነዚህ ሰው ሠራሽ ምክንያቶች ውስጥ ደግሞ ዋነኛው ስግብግብ ነጋዴዎች ዋጋ ለመጨመር ሲሉ እጥረት እንዳለ በማስመሰል የሚያደርጉት የዕቃዎች ሥወራ ለዋጋ ንረቱ የራሱ የሆነ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው። መንግሥት በድጎማ የሚያቀርባቸውን የፍጆታ ዕቃዎች ጭምር በመሰወር ህብረተሰቡ እንደገና በውድ ዋጋ እንዲገዛቸው ይደረጋል። ይህ እንግዲህ በተለይ በመዲናዋ እንደአንድ አዋጭ የቢዝነስ ስልት ከተወሰደ ውሎ ያደረ ጉዳይ ሲሆን ችግሩ ከዚህ በላይ አይቶ እንዳላየ ከታለፈ ህዝቡንም ሆነ ሀገሪቱን ለውስብስብ ችግር መዳረጉ የሚቀር አይደለም፡፡
ሌላኛው ሰው ሠራሽ የዋጋ ግሽበት መንስኤ ደግሞ ርካሽ ፖለቲካዊ ጥቅማቸውን ለማሳካት የሚፈልጉ አካላት የሚፈጥሩት ደባ ነው። እነዚህ በህዝብ ጉሮሮ ላይ ቆመው ፖለቲካዊ ፍላጎታቸውን ማሰካት የሚፈልጉ አካላት ወደ ገበሬው በመሄድ ምርቱን ወደ ገበያ እንዳያወጣ የሚያደርጉት ቅስቀሳ ለጊዜውም ቢሆን እክል መፍጠሩ አይቀርም፡፡ ስለሆነም እነዚህ አካላት ከእኩይ ተግባራቸው እንዲቆጠቡ ማድረግ ከመንግሥትና ከሰፊው ህዝብ የሚጠበቅ ተግባር ነው፡፡
በሌላ መልኩ ደግሞ መንግሥት የኑሮ ውድነቱን ለማርገብ ያግዛሉ ብሎ ያሰባቸው በየቀበሌው የሚገኙ የሕብረት ሥራ ማህበራት ጭራሹኑ የኑሮ ውድነቱ አባባሾች ሆነው መገኘታቸው ሌላው እንቆቅልሽ ነው። እነዚህ ማህበራት ለህዝብ እንዲያዳርሱ የተሰጣቸውን ስኳር፤ጤፍ፤ዘይትና የመሳሰሉትን በጎን ለነጋዴ እንደሚያድሉ ብዙዎች ሲናገሩ ይደመጣሉ። ይህ ድርጊትም የነጋዴውን ኪስ አደልቦ ሸማቹን ማህበረሰብ ኑሮ እንደቋጥኝ እንዲከብደው እያደረገ ስለሚገኝ የሚመለከተው የመንግሥት አካል ጓዳውን ቢፈትሽ የተሻለ ነው።
በአጠቃላይ ዘንድሮ የሚታየውን የኑሮ ውድነት የተለየ ከሚያደርጉት ጉዳዮቸ ውስጥ ደግሞ የግብርና ምርቶች ዋጋ እያሻቀበ ባለበት ወቅት የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ አብሮ መከሰቱ ነው። ችግሩንም በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ አድርጎታል። የነዳጅ መጨመር በበኩሉ የትራንስፖርት መጨመርን በማስከተሉ አጠቃላይ ኢኮኖሚው እንዲነቃነቅና የሁሉም ምርቶችና አገልግሎቶች ዋጋ እንዲጨምር አድርጎታል። የቤት ኪራይ ጨምሯል። ልዩ ልዩ አገልግሎት ሰጪዎችም የበኩላቸውን ጭማሪ ለማድረግ ተገደዋል፡፡
ስለሆነም የችግሩን አሳሳቢነት ተረድቶ እንደአውሎ ንፋስ እየገሰገሰ የሚገኘውን የሸቀጦች ዋጋ ንረትና ይህንኑ ተከትሎ እየተስተዋለ ያለውን የኑሮ ውድነት እልባት ለማበጀት መንግሥትና ህዝቡ እጅ ለእጅ ተያይዘው ሊሠሩ ይገባል። በአቅርቦትና በፍላጎት መካከል የሚስተዋለውን ክፍተት ለማጠበብ የተጀመሩ ሥራዎችን ማጠናከር፤ የተጀመረውን ሥራ ዕድል ፈጠራ በማጠናከር የዜጎችን የመግዛት አቅም ማሳደግና ሰው ሠራሽ በሆነ መልኩ የዋጋ ጭምማሪ እንዲኖር ምክንያት የሆኑ ነጋዴዎች ላይ የማያዳግም እርምጃ በመውሰድ በኑሮ ውድነት እየተሰቃየ ያለውን ህብረተሰብ መታደግ ይገባል፡፡
አዲስ ዘመን መጋቢት 10 ቀን 2013 ዓ.ም