የታላቁ የህዳሴ ግድብ ከተጀመረ 10 ዓመታትን እየደፈነ ነው። የግድቡ ግንባታ የኢትዮጵያ ህዳሴ ጅማሮ ተደርጎ የተወሰደ ነው። ግድቡ በመላው ሕዝባችን ውስጥ ታላቅ የይቻላል መነሳሳት የፈጠረ፤ ከዘመናት በኋላ የተገኘ አንድ የተስፋ ብስራት ድምጽም ነው። ከታላቅነቱ የተነሳም የብዙዎችን የልብ ምት የጨመረ ፣ የተስፈኞችን ተስፋም ከፍ ያደረገ ትልቅ ታሪካዊ ክስተት ነው።
በአንድ በኩል ለዘመናት የአዝማሪን ግጥም ከማድመቅ ባለፈ ለሀገሩ ባዳ የሆነውን ይህን ትልቅ የሀገር ሀብት በመግራት ለሀገር ባለውለታ ለማድረግ በዘመናት መካከል የተደረጉ ሙከራዎች በታላቅ ሀገራዊ ቁርጠኝነት ወደ አደባባይ የመጡበትም ነው።መላው ሕዝባችን ያለምንም ልዩነት አደባባይ ወጥቶ የዘመናት የአባት የአያቶቹ የቁጭት ማሰሪያ መሆኑን ያረጋገጠበትም ጭምር ነው።
በሌላ በኩል አንድ ሀገር ወደ ከፍታ ለመውጣት መነሻ የሚሆናት ያላትን ፣ በተፈጥሮ የታደለችውን ሀብት አውቃ ወደ ማልማት የመምጣቷ እውነታ በብዙ መልኩ የመጀመሪያው መጨረሻ ከመሆኑ አንጻር ዓባይን የማልማቱ ጉዳይ ከተራ የልማት አጀንዳነት ወደ የህልውና መሰረት ወደመሆን የተለወጠበት፣ ዜጎች ስለነጋቸው የተሻለ ተስፋ እንዲሰንቁ የተደረገበት ክስተት ነው።
የኢትዮጵያ መንግሥት ኃላፊነት እንደሚሰማው መንግስት የዜጎችን ዛሬዎች ከትናንቶች የተሻለ የማድረግ፣ ዜጎች ዛሬን አሸንፈው ለነገ የተሻለ ተስፋ ሰንቀው እንዲጓዙ ትልቅ ኃላፊነት አለበት። ይህ ኃላፊነት ሕገመንግስታዊ ብቻ ሳይሆን ሰብዓዊና ሞራላዊ መሰረት ያለው ነው። ይህን ኃላፊነት መወጣት ትውልዶችን በተስፋ ከማሻገር ባለፈ ሀገርን ሀገር የማድረግ የህልውና ጥያቄ ጭምር ነው፦
በዓለም አቀፍ ደረጃ ሀገራት አሁን የደረሱበት የስልጣን ሆነ የብልጽግና ከፍታ ላይ የደረሱት በአንድም ይሁን በሌላ ተፈጥሮ የለገሰቻቸውን አቅሞች በመጠቀም ነው። እነዚህ አቅሞች አንድም ሰብዓዊ አለበለዚያም ተፈጥሯዊ ጸጋዎችን ናቸው። እነዚህን ጸጋዎች በአግባቡ አውቆ መጠቀም የስልጣንና የብልጽግና አልፋና ኦሜጋ ናቸው።
ኢትዮጵያ እንደ ሀገር የብዙ ሰብዓዊና ተፈጥሯዊ ጸጋዎች ባለቤት ነች። ለዚህ ደግሞ በአንድም ይሁን በሌላ የሀገሪቱን ሕዝቦችና ሃገሪቱን ለማየት እድል ያገኘ የትኛውም ባለ ጤነኛ አእምሮ ባለቤት እውነታውን ሊመሰክር ይችላል። ከነዚህ ጸጋዎች አንዱ እና ዋነኛው ደግሞ የውሀ ሀብቷ ነው።
በ1960 መጨረሻ ላይ የተነሳው ለውጥ ፈላጊ ትውልድ ኢትዮጵያን የአፍሪካ የዳቦ ቅርጫት እናደርጋለን እያለ በየአደባባዮቹ ሲፎክር የነበረው ፤ ሀገሪቱ የአፍሪካ የውሃ ማማ ነች የሚለውን ተጨባጭ እውነታ መሰረት በማድረግና ውሃ ሀገሪቱ ካላት የተፈጥሮ ጸጋዎች አንዱና ዋነኛው ስለነበር ነው ።
ቀደም ባለው ዘመንም ሆነ በዘመኑም የነበሩ የሀገራቱ መሪዎች ይህን ሀብት ወደሚጨበጥ ተስፋ ለመቀየር የሚያስችሉ ሀሳቦችን ይዘው ለመነሳት የማሰቡ ችግር ባይኖርባቸውም ወቅቱ ግን ይህን ሀሳባቸውን ይዘው ወደ አደባባይ ለመውጣት አስቻይ ሁኔታዎች ያልነበሩበት እንደነበር ታሪክ ያወሳናል።
በአንድ በኩል በቅኝ ገዥዎች የቅኝ አገዛዝ አስተሳሰብ የጦዙ ቅኝ ገዥዎች ለሀገራቱ ሕዝቦች አስበው ሳይሆን ከሀገራቱ የተፈጥሮ ሀብት ያለተቀናቃኝ ተጠቃሚ ለመሆን ያስቀመጧቸውን የአንድ ወገን ኢ-ፍትሐዊ ስምምነቶች የሙጥኝ ብለው የሄዱበት የተሳሳተ መንገድ የሀገራቱ ሕዝቦች የተፈጥሮ ሀብቱ ፍትሐዊ ተጠቃሚ እንዳይሆኑ አድርጓቸዋል።
በሌላ በኩል ደግሞ የተፈጥሮ ሀብት ፍትሐዊ ተጠቃሚነት መርህን በሚጋጭ መልኩ የተፈጥሮ ሀብቶችን የውስጥ ፖለቲካ አቅም አድርጎ የመውሰድ፣የስልጣን መቆያ ስትራቴጂ አድርጎ የመጠቀሙ ሁኔታ የሀገራቱ ሕዝቦች ተፈጥሮ የለገሰቻቸውን ጸጋ በጋራ አልምተው፤ በጋራ ተጠቃሚ እንዳይሆኑ ዋነኛ ተግዳሮት ሆኗል።
ይህ እውነታ በ1960ዎቹ የአፍሪካ የነጻነት ትግል ወቅት ይቀነቀን የነበረው የፓን አፍሪካኒዝም መንፈስ በማሳነስ አፍሪካውያን የነጻነት ትግላቸውን ስኬት በጋራ ልማት ለማጽናት ያለሙትን ታላቅ ህልም ያጨናገፈ፤ በተፈጥሮ ጸጋቸው ተጠቅመው የጋራ ብልጽግናቸውን እውን እንዳያደርጉ ያደረገም ነው።
የአፍሪካውያን የተፈጥሮ ጸጋዎች ለሕዝቦቻቸው በረከት ከመሆን ይልቅ በሕዝቦች መካከል የስጋትና የጠላትነት መንፈስ ማጎልበቻ አቅሞች እንዲሆኑ ተደርገዋል። ይህ እውነታም በዓባይ ተፋሰስ ሀገሮች መካከል በተጨባጭ እየታየ ይገኛል። የዓባይ ውሀ የተፋሰሱ ሀገራት የትብብርና የልማት መሰረት መሆኑ ሲችል ግብጽ በምትፈጥረው ችግር የአለመተማመንና ስጋት ምንጭ እንዲሆን እየተደረገ ነው። ከዚህም አልፎ ለቀጠናው ሀገራት የጸጥታ ስጋት ሆኗል ።
ማንኛውም ሀገር በሉዓላዊ ግዛቱ የሚገኙ የተፈጥሮ ጸጋዎችን አልምቶ የመጠቀም ባለ ሙሉ መብት ነው። ሀብቱ በግዛቱ የተገኘውን ተጠቅሞ ዛሬዎችን አሸንፎ ለመውጣት ነገዎችን በተሻለ ተስፋ ለመጠበቅ ነው። እነዚህ ጸጋዎች የላንቲካ እቃ ሳይሆኑ ተጨባጭ የሀገራት ተስፋዎች ናቸው።
ሀገራት እነዚህን ሀብቶች አልምተው እንዳይጠቀሙ የመሞከሩ እውነታ የሀብቱን ባለቤት ሕዝብ ተስፋ የመንጠቅ ያህል ነው።ተስፋው የተነጠቀ ሕዝብ ደግሞ መጨረሻው ምን እንደሚመስል ፤ በተራ አሉባልታና በውሸት መረጃዎች ተስፋቸውን የተነጠቁ የዓለም ሕዝቦችን በማየት ማወቅ ይቻላል። እነዚህ ሕዝቦች በአንድ ወቅት ለብዙዎች የሚተርፉ መሆናቸው ቀርቶ ዛሬ ቀናትን ለማሸነፍ የሌሎችን ምጽዋት ጠባቂ ሆነዋል። ለራሳቸው ቀርቶ ለጎረቤቶቻቸው የስጋትና ያለመረጋጋት ምንጭ ሊሆኑም ችለዋል ።
ኢትዮጵያውያንም የህዳሴ ግድብ ጉዳይ ተራ የልማት አጀንዳ እንዳልሆነ ድምጻቸውን ከፍ አድርገው የሚያሰሙት ፣ ለግንባታው ስኬት ከሌላቸው ላይ አውጥተው የለገሱትና በይቻላል መንፈስ ለግንባታው ቁርጠኛ የሆኑት ከዚህ እውነታ በመነጨ ነው። ለኢትዮጵያውያን ውሃ የተፈጥሮ ትልቁ ጸጋቸው ነው።ነገዎቻቸው የሚመዘኑት ይህን ጸጋ አልምተው በሚፈጥሯቸው ነገዎች ነውና።
ይህን ተፈጥሯዊ ጸጋቸውን እንዳይጠቀሙ ተግዳሮት መፍጠር ምን ማለት እንደሆነ የሚታወቀው የተስፋ አልፋና ኦሜጋነት መረዳት ሲቻል ብቻ ነው። ለዚህ ነው ለእኛ ለኢትዮጵያውያን የታላቁ የህዳሴ ግድብ ጉዳይ የህልውና ጉዳይ የሚሆነው። የሚከፈለውን ከፍለን እንደጀመርነው እንጨርሰዋለን የምንለውም የነገ ተስፋችን በውሀ ሀብታችን ላይ የተመሰረተ ስለሆነ ነው። በዚህ ጉዳይ አንደራደርም የምንለው በተስፋ ላይ መደራደር ከራስ የሚያልፍ የትውልዶች እርግማን መሆኑን ከማንም በላይ መረዳት የሚያስችሉ እሴቶች ባለቤት ስለሆንንም ጭምር ነው!
አዲስ ዘመን መጋቢት 9 ቀን 2013 ዓ.ም