አንድ ጥበብ አሳሽ ጥበብን ፍለጋ በየሀገሩ የሚዞር ሰው ነበር። አንድ ቀን ወደ አንድ መንደር ሲደርስ ሰዎች ድንጋይ ሲፈልጡ ተመለከተ። ቀና ብሎ ቢያይ በአካባቢው ምንም የሚገነባ ነገር የለም። ወደ አንዱ ድንጋይ ፈላጭ ተጠግቶ «እባክህ ወዳጄ እኔ ለአካባቢው አዲስ በመሆኔ አንድ ነገር ልጠይቅህ ፈለግኩ፣ ለመሆኑ ምን እያደረጋችሁ ነው?» አለው። ያም ድንጋይ ፈላጭ «ወንድሜ የማደርገው ነገርኮ ግልጽ ነው፤ አንተም ታየዋለህ፤ ድንጋይ እየፈለጥኩ ነዋ» ሲል መለሰለት።
እልፍ ብሎም ሁለተኛ ሰው አገኘና «ወዳጄ ለሀገሩ እንግዳ ለሰው ባዳ ነኝ እባከህ ምን እየሠራችሁ እንደሆነ ንገረኝ?» አለው። ያም ድንጋይ ፈላጭ «ወዳጄ እኔ የዕለት እንጀራዬን ለማግኘት እየደከምኩ ነው» ሲል መለሰለት። ጥበብ አሳሹ አንገቱን ነቅንቆ ወደ ሦስተኛው ፈላጭ ጋር ተጠጋና ተመሳሳይ ጥያቄ አቀረበለት። ድንጋይ ፈላጩ ቀና አለና መፍለጫውንም ተደግፎ ከቆመ በኋላ «ይኸውልህ ወዳጄ እኔ ድንጋዩን በመጠቀም ካቴድራል እየሠራሁ ነው» አለው። ያን ጊዜም «አሁን መልሱን አገኘሁት» ብሎ ሄደ ይባላል። ይህ ታሪክ ከዳንኤል እይታዎች ድረገጽ ላይ የተወሰደ ሲሆን፤ ብዙ ቁምነገሮችን ያስጨብጣል።
ዓለምን የሚለውጡት፣ ችግርን የሚያሸንፉት፣ ሀገርን የሚያሳድጉት ድንጋይ ሲፈልጡ ካቴድራል እየገነቡ የሚያስቡት እንደሆነ ማንም ይረዳል። ሦስቱ ሰዎች ድካማቸው ተመጣጣኝ ነው፤ የሚከፈላቸውም አንድ ዓይነት ነው፤ የያዙት መፍለጫም እንዲሁ ይመሳሰላል። ዋናው ልዩነታቸው ግን ስለ ስራቸው ያላቸው አመለካከት ነው። ግባቸውና ራዕያቸውም ይለያያቸዋል። አንዱ እጆቹ የሚሠሩትን እንጂ ሥራው የሚያመጣውን ውጤት አያውቅም። አንዱ ሥራው የሚያስገኝለትን ዕለታዊ ገቢ እንጂ ሥራው የሚፈጥረውን ትልቁን ሥዕል አይረዳም። አንዱ ግን የሚያመጣውን ለውጥ እያሰበ ነው የሚሰራው።
ይህ ደግሞ ለውጥ የሚመጣው በዘመናዊ መሣሪያ በመሥራት፣ በቂ በጀት በመመደብ፣ የሠለጠነ የሰው ኃይል በመቅጠር፣ የቢሮ እቃዎችን በማሟላት ብቻ እንዳልሆነ ያስገነዝባል። እነዚህ ሁሉ አጋዦች እንጂ አንቀሳቃሾች እንዳይደሉ ያስረዳል። በመሆኑም ለውጥ የሚመጣው ለምንድን ነው የምሠራው? ለሚለው ጥያቄ ምላሽ ሲሰጥ መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል። ትልቁን ሥዕል እያሰቡ መስራት ግድ ነው። ለዕለት እንጀራ የሚሆን ምን ያህል ድንጋይ ፈለጥን ሳይሆን ካቴድራሉን በምን ያህል ፍጥነትና ጥራት መስራት እችላለሁ ብሎ መትጋትን ይጠይቃል።
በየመሥሪያ ቤቱ እነዚህ ሦስቱ ሰዎች እንዳሉ እሙን ነው። ሥራዎችን ለደመወዝ የሚሰሩ፣ የሥራ ዝርዝራቸውን ቅጣት እና ሽልማታቸውን ብቻ አስበው የሚሰሩት ብዙዎች ሲሆኑ፤ ሥራው ለሀገር እና ለወገን ይጠቅማል ብለው አስበው የሚሰሩት ደግሞ ጥቂቶች ናቸው። ልክ ካቴድራል እንደሚገነባው ሁሉ። እናም ለአገር እድገት ካቴድራል እገነባለሁ እንዳለው ሰው ራዕይ የሰነቀ ዜጋ ያስፈልጋል። ድንጋይ ፈላጮች ብቻ ሳይሆን አገር ቀያሪ፣ ለውጥ የሚያመጣ ሰው ይጠበቃል።
በየቢሮው ድንጋይ ፈላጭ እንደሆኑ ብቻ የሚያስቡ ሰራተኞች አገሪቱ አያስፈልጋትም። እነርሱ የተሰጠቻቸውን ሥራ ከመሥራት ያለፈ ምንም ራዕይ የላቸውም። ስለሆነም አገር እያሳደጉ መሆኑን፣ ለውጥ እያመጡ መሆኑን፣ ታሪክ እየሠሩ መሆኑን እንዲረዱ ማድረግ ላይ መሰራት አለበት። ሀገሪቱ ስላላደገችበት ምክንያት ተጠያቂ ነን ብሎ የሚያስብ ትውልድ መፍጠር ይገባል።
የስነምግባር እሴቶችን በየግድግዳው ላይ ማዋል ብቻ ሳይሆን በአዕምሮ ውስጥ አስቀምጦ ለአገር ለውጥ የሚሰራ አርቆ አሳቢ ትውልድ መፍጠርም ተገቢ ነው። ድንጋይ ፈላጮች በካቴድራል ገንቢዎች መተካት አለባቸው። ለለውጥ በቆረጡ፣ መለወጥ እንችላለን ብለውም በሚያስቡ፣ ከዕለት ጉዳይ አልፈው ታላቁን ካቴድራል ለመገንባት የሚሹ ሰዎች አገሪቱ ዛሬ ላይ ያስፈልጋታልና ካቴድራል ገንቢዎችን ለማጉላት መስራት ይኖርበታል።
ሁሉም በተመሳሳይ ደረጃ፣ ፍጥነት፣ አቅም፣ ችሎታ፣ ዕውቀት እና ሥልጣን አንድ ዓይነት ተግባር ሲከውን ለውጥ ይመጣል። የተለያየ ፍላጎት፣ የተለያየ መንገድ፣ የተለያየ ርዕዮት፣ የተለያየ ስትራቴጂ፣ የተለያየ ደረጃ ሊኖር ይችላል። ሆኖም አንድ ነገር ላይ ግን መግባባት ያስፈልጋል። የሁሉም ጥረት ካቴድራሉን ለመገንባት መሆን አለበት። ያ ደግሞ የአገር ለውጥ ነው። ካቴድራሉን ለመሥራት የብዙ ድንጋይ ፈላጮች ላብ፣ ችሎታ እና ጊዜ እንደሚያስፈልግ ሁሉ ትውልዱን በአገር ግንባታና ለውጥ ላይ እንዲሳተፍ ማድረግም ይገባል።
በእርግጥ አንዳንዶች የካቴድራሉ ገንቢዎች ሥራቸውን ሳያዩት ሊያልፉ ይችላሉ። ልክ መልካም ስራ ሰርተው እንዳለፉት እንደቀደሙት አባቶቻችን። ይሁንና ትውልድ አስቀምጠዋል፤ አገር አቆይተዋል፤ በአለት ላይ አሻራቸውን አሳርፈዋል። ስለዚህም የማይፈርስ ግንብ ስለገነቡ ለትውልዱ ስንቅ ናቸው። እናም ለአገር ለውጥ እሰራለሁ የሚል ሰው የግድ ሥልጠና እስኪሰጥህ፣ መመሪያ እስኪወጣ መጠበቅ የለበትም። ይልቁንም «ልታየው የምትፈልገውን ለውጥ መጀመሪያ አንተው ራስህ ሁነው» እንዲል ማኅተመ ጋንዲ ይህንን በማድረግ ለአገር ለውጥ መስራት ይገባል።
አዲስ ዘመን የካቲት 3/2011