ጆሴ ኦርቴጋ የሚባል ፖርቹጋላዊ ፀሐፊ ሀገር የሚመሰረተው ምን ላይ ነው? ሲል ይጠይቅና በጋራ አብሮነት (common future) ነው ሲል ይመልሳል፡፡ ከዚህ ብያኔ አንፃር ሰንቃኘው ኢትዮጵያዊነት የጋራ አብሮነት ውጤት መሆኑን በቀላሉ እንረዳለን፡፡ እኛ ኢትዮጵያውያን የጋራ መሠረትና የጋራ ጉዳይ ያለን፣ ለወደፊትም የጋራ ዕድል የሚኖረን ሕዝቦች ስለሆንን ነው በኢትዮጵያዊነት ጥላ ሥር የተሰባሰብነው፡፡
ኢትዮጵያዊነት በመጀመሪያ ኢትዮጵያዊ መሆን ማለት ነው፡፡ የአንዲት ኢትዮጵያ የምትባል ሀገር፣ ሕዝብና መንግሥት ማንነትም ነው፡፡ በሌላም በኩል ኢትዮጵያዊነት ማለት በኢትዮጵያ ማንነት ላይ የተመሰረተ ሀገራዊ ብሔርተኝነት ነው፡፡ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ቅርፅ፣ ይዘትና አቅጣጫ የሚነድፍና የሚመራ ፍልስፍናም ነው፡፡ ኢትዮጵያዊነት የህዝቧን አንድነት፣ የመንግሥቷን ቀጣይነት፣ የግዛቷን ሉአላዊነት፣ የዜጎቿን እኩልነት የሚያቀነቅን የአብሮነት አስተሳሰብም ነው፡፡ ኢትዮጵያዊነት በርዕዮታዊ፣ ባህላዊና ታሪካዊ አንድነት ላይ የቆመ ጠንካራ አስተሳሰብም ነው፡፡
ኢትዮጵያዊነት ማለት በልዩ ልዩ ቋንቋ ባህልና እምነት ደምቆ በአብሮነት የመኖርና፣ የወደፊት ራዕይን ሰንቆ ነፃነትን በማስከበር በጋራ ለማደግና ለመኖር የመስማማት ውጤት ነው፡፡ በዚህ መንፈስ ነው ነፃነታችንን አስከብረን ዛሬ ላይ የደረስነው፡፡ ሌሎች አገሮች ቅኝ ግዛት ውስጥ የወደቁበት ሚስጥርም ይሄን አብሮነት ማጣታቸው ነው፡ ፡ ስለዚህ ኢትዮጵያዊነት ማለት የጋራ ውብ ታሪክን እያደሱ በመኖር በወደፊት አብሮነት ላይ የተመሰረተ አንድነት ነው ማለት ነው፡፡
ኢትዮጵያ በነፃነት ታፍራና ተከብራ የኖረችውና አንድነቷ ተጠብቆ እዚህ የደረሰችው ጠላት አጥታና መንገዱ ሁሉ ፈተና አልባ ሆኖላት አልነበረም፤ ይልቁኑ ለዚህ ክብር ማንነት ብዙና ውድ ዋጋ ተከፍሎ እንጂ፡፡ በረጅም ዘመን ታሪኳ ኢትዮጵያ ለአንድም ጊዜ የሌላውን ድንበር ገፍታና የማንንም አገር ነፃነትን ተፃርራ አታወቅም። ይልቁኑ ደቡብ አፍሪካና ዚምባቡዌን የመሳሰሉ አገራት ነፃነታቸው በወራሪዎች በተጣሰ ጊዜ እውነተኛ አጋር ሆና ነፃነታቸውን እንዲቀዳጁ ግንባር ቀደም ሚና ተጫውታለች።
ኢትዮጵያዊነት በትዕግስት የታሸ ጀግንነት ነው። የሌላውን ነፃነትና ደንብር አለማጋፋቱ፣ አገር ወዳድነቱ፣ ለነፃነት ያለው ፍቅርና ክብር፣ በደማቁ የተጻፈለት የጀግንነት ገድሉ፣ ነፃነት አልባነትን መፀየፉና ታሪክ ሠሪነቱ ለዚህ ጥሩ ምስክሮች ናቸው። በሌላም በኩል ኢትዮጵያዊነት ከግላዊነት የራቀ ማህበራዊ ፍቅር እንዲሁም ከግለኝነትና ከራስ ወዳድነት የፀዳ የወገን ተቆርቋሪነት ውጤት ነው። አንድ እውቅ ደራሲ በአንድ ወቅት እንዳሉት፣ የኢትዮጵያ ሕዝቦችና ማህበረሰቦች በአንድ መደብ የበቀሉ መልከ ብዙ ውብ አበቦች ናቸው፡፡ አበቦቹ ብዙ ዓይነት ቀለማት ቢኖራቸውም መጠሪያቸው አበባ እንደመሆኑ ኢትዮጵያውያንም የተለያየ ቋንቋ ቢናገሩ ልዩ ልዩ ዓይነት ባህልና ትውፊት ቢኖራቸውም ዓለም የሚያውቃቸውና የሚኮሩበት የጋራ ማንነት ኢትዮጵያዊነት የሚል ነው።
ብዙዎች ወድ ህይወታቸውን የከፈሉለትን ይህን አኩሪ ማንነት ለማላላትና ቢቻልም ለማፍረስ ከውስጥም ከውጭም ብዙዎች የሚችሉትን ሁሉ አድርገዋል። የኢትዮጵያውያንን የባህል፣ የእምነትና የቋንቋ ልዩነት ተጠቅመው በመከፋፈል የተዳከመች ኢትዮጵያን ለመፍጠርም በየዘመናቱ ብዙ ጥረት ተደርጓል። አንዳንዶች የህዝቧን የሥነልቦናና የመንፈስ ጥንካሬን ሳይረዱም የአገሪቱን ሉዓላዊነት ለመዳፈር ሞክረውም ዓለም የተማረበትን ሽንፈት ተከናንበዋል።
በታሪክ አጋጣሚ እጃቸው ላይ የገባውን አገርን የማስተዳደር ዕድልን ተጠቅመው ልዩነታችንን በመስበክ አንድነትን ለማላላት ትልቅ ሴራ ሲሰሩ የነበሩ የአገር ጠንቆችንም መላ ኢትዮጵያውያን ከዳር ዳር ተንቀሳቅሰው አደብ በማስገዛት የጥፋት ዓላማቸውን ህልም አድርገው አስቀርተዋል። በዚህም ከየትኛውም አቅጣጫ የሚነሳ ኢትዮጵያዊነትን የመናድ ሙከራ ከንቱ ልፋት መሆኑ ተመስክሯል።
አሁንም መላ ኢትዮጵያውያን በአንድነት በመቆም የጥፋትና የዘረፋ ዕቅዳቸው መና የሆነባቸውና በአገራችን የመከላከያ ሠራዊት ላይ ጥቃት ፈጽመው እጅግ አሳፋሪ ሽንፈትን የተከናነቡ የጁንታው ርዝራዦች የአገሪቱን ስም ለማጠልሸት ሲያደርጉ የነበረውን የሀሰት ዘመቻ በተባበረ ክንድ በመቀልበስ በታሪክ የሚወደስ አኩሪ ጀብዱ ፈፅመዋል። ከዚህ የምንረዳው ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን ለመናድ የሚደረግ ሙከራ ከንቱ ልፋት መሆኑንና ኢትዮጵያዊነት ማለት ሁሌም እውነትና አሸናፊነት መሆኑን ነው!
አዲስ ዘመን መጋቢት 8 ቀን 2013 ዓ.ም