ዳንኤል ዘነበ
ተማሪ ደራርቱ አባ ራያ እውቀትን ፍለጋ ዘወትር አንድ ሰዓት ከግማሽ ትጓዛላች። በቅርበት ትምህርት ቤት ባለመኖሩ እርሷና መሰሎቿ እውቀትን ፍለጋ ለሰዓታት ይጓዛሉ። በጅማ ዞን ቀርሳን ወረዳ ቡልቡል ቀበሌ ገበሬ ማህበር ልዩ ስሙ ስንጉል አካባቢ ተወልዳ ያደገችው ደራርቱ፤ በትምህርት የላቀ ደረጃ ደርሳ የህክምና ባለሙያ መሆን የዘወትር ምኞቷ ነው።
ደራርቱ፤ ከመኖሪያ አካባቢዋ ስንጉል እስከ ቡልቡል ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ድረስ በምታደርገው ጉዞ ወቅት ድካም ሲሰማት ስለ ህልሟ በማሰብ 12 አድካሚ አመታትን መሻገር መቻሏን ስትናገር በጠይም ፊቷ ላይ ታላቅ በራስ መተማመን ይነበባል። «በአካባቢያችን ሴት ልጅ ተምራ ሥራ ትይዛለች ብለው አያስቡም። ሴቶች እንዲማሩ ከማድረግ ይልቅ፤ አግብታ ዛሬን ትተካልኝ የሚል ፍላጎትና አመለካከት መኖሩ ጫና አሳድሮብናል» ስትል ነበር እርሷና መሰሎቿ የሚደርስባቸውን ጫና ፊቷን ቅይም በማድረግ የገለጸችልን።
‹ሴት ልጅ ተምራ ሳይሆን አግብታ ነው ቤተሰቧን የምታኮራ› የሚል ባህላዊ አመለካከት መኖሩን ያጫወተችን ደራርቱ፤ ይህም እርሷም ሆነች የእርሷ የትምህርት ቤት ጓደኞቿ ትምህርታቸውን ጥለው ባል እንዲያገቡ ከፍተኛ የሆነ ጫና ይደረግባቸው ነበር። ‹ለሴት ልጅ ትምህርት ሳይሆን ባል ነው የሚያስፈልጋት› ከሚለው አመለካከት የተነሳ በቤተሰብ፣ በዘመድ አዝማድ፣ በአካባቢው ማኀበረሰብ እንድታገባ ጉትጎታዎች፣ ጫናዎች፤ ባስ ሲል ሀይም ጭምር ይገጥሟት እንደነበር ታስታውሳለች። ወጣቷ ደራርቱ እነዚህን ሁሉ ውጣ ውረዶችን በመጋፈጥ ከልጅነቷ የጨበጠችውን የተስፋ ዘንግ መከታ በማድረግ በድል አድራጊነት መወጣቷን በተደበላለቀ ስሜት እንዲህ አጫወተችን።
«በወቅቱ ጠያቂዋ ቢበዛም፤ የቤተሰቦቿ ጫና፣ ጉትጎታ መቋቋም ግድ ይለኝ ነበር። በዚህ መልኩ እስከ ዘጠነኛ ክፍል ዘለቅኩ። ወደ 9ኛ ክፍል ከተሸጋገርኩ በኋላ ጉትጎታው በእጅጉ እየቀነሰ መጣ። እድለኛ በመሆኔ ዛሬ የ12ኛ ክፍል ተማሪ ለመሆን በቅቻለሁ» ስትል በአሸናፊነት ድምጸት ነበር ያወጋችን።
እንደ ወጣቷ ደራርቱ ሁሉ የቡልቡል ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዋ ነጃት ረሺድ በተመሳሳይ የህይወት መርከብ ውስጥ የተጓዘች እንስት ናት። ሴት ልጅ እንድትማር ሳይሆን እንድታገባ የሚደረገው ግፊት፤ በተደጋጋሚ እንድታገባ ጥያቄ ይቀርብላት እንደነበር ትናገራለች። የማኀበረሰቡን ባህል ማክበር እንዳለባት በመግለጽ የሚደረጉ ግፊቶች ሳይቋረጡ ቢቀጥልም አሻፈረኝ በማለት 12ኛ ክፍል መድረስ ችላለች።
ተማሪ ነጃት ታግላ ማሸነፏ እንጂ፤ የእርሷ እድል ግን ጓደኞቿ አልገጠማቸውም። በትምህርት ትልቅ ደረጃ ደርሰው ራሳቸውን ሀገራቸውን የማገልገል ህልምን ሰንቀው ባለፉት አስራ ሁለት አመታት ሲያደርጉት ከነበረው ጉዟቸው በመቅረታቸው፤ እውን አልሆነም ስትል ልብን ሰርስሮ በሚገባ የሀዘን ድባብ ውስጥ ሆና ያጫወተችን።የማኀበረሰቡ ጎታች እሳቤ፣ የቤተሰብ ተጽዕኖ ተደምሮ የትምህርት ቤት አለማቸውን ጣጥለው ትዳር ወደተባለው ትልቁ ተቋም ሳይወዱ በግድ መቀላቀላቸውን በቁጭት ተሞልታ አወጋችን።
ሴቶችን ካለ ፍላጎታቸው የመዳሩ ባህል በተለይ በኮሮና ወቅት የጨመረ መሆኑን የገለጸችልን ተማሪ ነጃት ትዝብቷን እንደሚከተለው አጫውታናለች። «በኮሮና ምክንያት ትምህርት ቤት ለረጅም ወራት መቋረጡ ችግሩን የበለጠ አባብሶታል። በተለይ ደግሞ ስምንተኛና ሰባተኛ ክፍል የሚገኙ ተማሪዎች በውድም ይሁን በግድ አግብተው ትምህርታቸውን አቋርጠዋል።
የ12ኛ ክፍል የከፍተኛ ትምህርት መግቢያ ፈተና በተለያዩ ምክንያት መራዘሙ ደግሞ በተማሪዎቹ ላይ ተጨማሪ ጫና በመፍጠር ብዙዎቹ ሴት ተማሪዎች አግብተዋል» ስትል። ተማሪ ነጃት የእርሷ ጓደኛ የሆኑ አምስት ሴት ተማሪዎች የዚሁ ሰለባ መሆናቸውን በመግለጽ፤ «እቺ አለም በተለይ ኢትዮጵያ የወንዶች ሀገር ትመስለኛለች። ያውም ‹የሴቶችን አቅምና የመቻል ሚስጥር በቅጡ ያልተረዳች›»ስትል ንግግሯን በቁጭት የቋጨችው።
የቡልቡል አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መምህሯ መመህር በቀሉ ዴቢሳ በተመሳሳይ፤ የልጅነት ጊዜያቸውን ሳይጨርሱ የልጅ እናት የሆኑ ታዳጊዎች እየተዳሩ መሆኑን በቁጭት ተሞልታ ትናገራለች።የኮሮና ወረርሽኝን ተከትሎ ትምህርት ቤት በመዘጋቱ በመቶዎች የሚቆጠሩ ተማሪዎች እንደወጡ አልተመለሱም።ተማሪዎቹ ወደ ትምህርት ቤት ያልመጡበት ምክንያት በኃላ ቀር ባህል ጎታችነት ትዳር ወደ ተባለው ጥልቁ የህይወት ባህር በመግባታቸው መሆኑን መምህር በቀሉ አብራርታለች።
«በአካባቢው ከ15 ዓመት በታች የሆኑ ታዳጊ ሴቶች እንዲያገቡ የሚደረግ መሆኑን የምትገልጸው መምህር በቀሉ፤ታዳጊዎቹ በቤተሰብ ጫናም ይሁን በራሳቸው ፍላጎት ትምህርታቸውን አቋርጠው ባል እንዲያገቡ ይደረጋል ። በህብረተሰቡ ዘንድ ሴቶችን ከማስተማር ፍላጎት ይልቅ ባል እንዲያገቡ የመፈለግና ግፊት የማድረግ ዝንባሌን፤ማስቀረት ይገባል »ስትል አስገንዝባለች።
በጅማ ዞን የቀርሳን ወረዳ ሴቶች ፣ህጻናት እና ወጣቶች ቢሮ ኃላፊ ፤ራውዳ አወል በበኩላቸው፤ በወረዳው ላይ ሴት ልጆችን ያለ ፍላጎት የመዳር ፣ሴት ልጅን ወደ ትምህርት ቤት ከመላክ ይልቅ እንዲያገቡ የማድረግ ልማድ፣ያለ ዕድሜ ጋብቻ ችግር በከፍተኛ ሁኔታ መኖሩን ይገልጻሉ።
ከዚሁ ጋር ተያይዞ በኀብረተሰቡ ዘንድ ያለውን ልማድ ለማስቀረት፤ ግንዛቤ ለማስጨበጥ ከባድ ፈተና ቢሆንም፤ ጥረቶች እየተደረጉ መሆኑን ያመላክታሉ። በኮቪድ ምክንያት ትምህርት በመዘጋቱ ካለ ፍላጎታቸው ሊያገቡ የነበሩ አምስት ሴቶች ከአቃቢ ህግ፣ ከፖሊስ ጋር በመሆን ጋብቻው እንዲሰረዝ እስከማድረግ መደረሱን ያስታውሳሉ። በወላጆች፣ በሽማግሌዎቹም ሳይቀር እርምጃ በመውሰድ ህብረተሰቡ እንዲረዳ መደረጉ ችግሩ ከጊዜ ወደ ጊዜ መሻሻል ቢያሳይም፤ በአንዳንዶቹ አካባቢዎች ችግሩ ከትናንት ዛሬ አለመሻሻሉን በመጥቀስ ነበር የችግሩን አሳሳቢነት ያስረዱት።
ከጅማ ዞን ቀርሳን ወረዳ ቡልቡል ቀበሌ ገበሬ ማህበር በሚገኙ አካባቢዎች ላይ ተገኝተን ሴቶችን በተመለከተ በማኀበረሰቡ ዘንድ ያልተቀረፈውን ኋላ ቀር እሳቤ ለመታዘብ ችለናል። ‹ሴት ልጅን ማስተማር ሀገርን ማስተማር ነው› የሚል አባባል ተደጋግሞ ይነገራል። በገጠሩ የሀገራችን ክፍል ወረድ ብለን ስንመለከት የምናየው ልብን ይሰብራል።
በሌላ በኩል የሴቶች ክበብ በትምህርት ቤቶች ውስጥ ተማሪዎች የሚመካከሩበት፤ መረጃ ለሚመለከታቸው የሕግና የአስተዳደር ባለስልጣናት፣ እንዲሁም ለመምሕራኖቻቸው የሚያደርሱበት ነው። የሴቶች ክበብ በተለይ በገጠር አካባቢዎች ከትምህርት የቀሩ ልጃገረዶችን፤ ወይንም የጋብቻ ወሬዎችን በሙሉ ሰብስቦ፤ በሕግ የሚያስጠይቀውን ባህል ለማስቀረት ይረዳልና የትምህርት ቤት ክበቦች ላይ ትኩረት አድርጎ መስራት ያስፈልጋል። ለዚህ ደግሞ መንግስት ፣የሰፈር ሽማግሌዎች ፣የእምነት ተቋማት፣ የህግ ተቋማት፣ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ወዘተ በቅንጅት መስራት፤ በኮሮና ጦስ እና በኃላ ቀር ባህል ወደ ትዳር ባህር የተጣሉ ኮረዶች ዳግም እንዳይኖሩ ያደርጋል ባይ ነን።
አዲስ ዘመን መጋቢት 6/2013