ባለፈው ሳምንት ዕትም ስለልጆች መልካም ስነምግባር አቀራረፅ እና ወላጆች ከልጆቻቸው ጋር ማድረግ ስለሚኖርባቸው ግንኙነት አስመልክቶ ማቅረባችን ይታወሳል። በዛሬው ዕትም ደግሞ ስለ በጎ ወላጅነት መሰረታዊ መርሆዎች በተመለከተ ይዘን ቀርበናል። መልካም ንባብ።
በጎ ወላጅነት የልጆችን ሁለንተናዊ አካላዊ፣ የስነልቦናዊ ጤናና ደህንነትን ያስጠብቃል። በዋናነትም በስነ-ምግባር የታነፁ ብቁና ፍሬያማ ዜጎችን የምናፈራበት መንገድ ነው፡፡ በመሆኑም በጎ የሆነ ውጤትን ለማስመዝገብ የሚያስችሉ የበጎ ወላጅነት መሰረታዊ መርሆች ምንድን ናቸው? የሚለውን እንቃኛለን።
ልጆች መልካም ነገርን በሚያደርጉበት ጊዜ ማድነቅና ማመስገን፣ መልካም ባይሰሩም ጥረታቸውን ማበረታታት፣ ልጆችን በእርጋታና በጥሞና ማዳመጥ፣ በአግባቡ ውይይቶችን ማድረግ፣ ልጆችን በስነ ምግባር ማነፅ (Discipline) እና ማስተማር እንጂ ቅጣትን ማስወገድ ይገባል፡፡ ልጆችን በስነምግባር ስናንፅና ስንመክር ደግሞ ለነገው ህይወታቸው ሀላፊነትን ይማሩበታል። ከቅጣት ግን አሉታዊ ነገርን እንጂ መልካም ነገርን አያገኙም፡፡
ልጆችን ሀላፊነትን ማለማመድና ለሀላፊነት ብቁ እንዲሆኑ ማስቻል የወላጆች በጎ ሃላፊነት ነው። ለምሳሌ ቤቱን ዝብርቅርቅ እንዲል ያደረገ ልጅ “ለምን እንዲህ አደረግህ” ብለን ከመቆጣት ይልቅ “ይህን ነገር እዚህ ጋር ይሄን እንዲህ አድርገን ብናስተካክለው ቤታችን ያምራል” ብለን መምከርና ማሳየት ተገቢ ነው።
የልጃችንን ባህሪ ለይቶ ማጥናት ያስፈልጋል። ለምሳሌ “አንተ እንደዚህ ስላደረግህ መጥፎ ልጅ ነህ” ከማለት ይልቅ “እነዚህን መጥፎ ባህሪያት ብታስወግድ እኮ በጣም ጥሩ ልጅ ነህ” ብሎ መምከር፡ ፡ ምንም ቢያደርግ ለልጃችን ያልተገደበ ፍቅር እንዳለን ሁልጊዜም ማሳየት ያስፈልጋል፡፡
ድርጊቶች ከቃላት በላይ ኃይል ስለሚኖራቸው የልጃችን ድርጊት ምን እንዳስከተለ ማሳየትና መምከር አለብን። ለምሳሌ ዩኒፎርሙን ከትምህርት ቤት መልስ በአግባቡ መቀየርና ማስቀመጥ እንዳለበት ስንነግረው ችላ ያለን ልጅ በነጋታው ቆሻሻ ዩኒፎርሙን ለብሶ እንዲሄድ በማድረግ ለድርጊቱ በመጠኑም ቢሆን ዋጋ ማስከፈል አስፈላጊ ነው፡፡
ወላጆች ከልጆች ጋር በቂ የሆኑና ጥራት ያላቸውን ጊዜያት በማሳለፍ ግንኙነታቸውን ማጠናከር ይኖርባቸዋል። ብዙ ጊዜ ወላጆች በስራ ተጠምደው ውለው ቤት ከመጡም በኋላ ስለስራቸው መብሰልሰልና ማውራት ይቀናቸዋል፡፡ ይህ አግባብ ባለመሆኑ የስራ ጣጣቸውን ቤታቸው ይዘው ባለማምጣት ለቤተሰባቸውና ለልጆቻቸው ሙሉ ትኩረት መስጠት ይገባቸዋል፡፡
ልጆችን በቤት ውስጥ በሚደረጉ ነገሮች ውሳኔ ላይ ተሳታፊ ማድረግ የነሱን ሀሳብ መቀበልና ያሉት ተገቢ ከሆነ መተግበር፣ ካልሆነም የማይሆንበትን ምክንያት ማብራራት ተገቢ ነው፡፡ ይህም ልጆቻችን አቅም እንዳላቸውና ብዙ ነገሮችን ማሳካት እንደሚችሉና የነሱም ሀሳብ ዋጋ እንዳለው ያሳያቸዋል፡፡ ለምሳሌ ቤተሰብ የሚገናኝበት መጠነኛ ስብሰባን በሳምንት ወይም በሁለት ሳምንት ጊዜ ውስጥ በመደበኛነት መተግበር የበጎ ወላጅነት ተሞክሮ ነው።
ለልጆቻችን ሩህሩህና ደግ መሆን ነገር ግን ሁልጊዜ ቀጥተኛ አቋም እንዳለን ማሳወቅ አለብን፡፡ ልጆቻችን ያልናቸውን ነገሮች ካላደረጉ ሁል ጊዜ ተመሳሳይ እርምጃዎችን መውሰድም አስፈላጊ ነው።
ለምሳሌ የጨዋታ ጊዜ ከአንድ ሰዓት በላይ መሆን የለበትም ብለን ከነገርናቸው ሰዓት ዝንፍ ሳናደርግ ጨዋታቸውን እንዲያቆሙ ማድረግ አለብን። መለመንና ማባበል አያስፈልግም። ወላጆች ለልጆቻው ላስቀመጡላቸው ገደቦች ተገዢ እንዲሆኑ ሁል ጊዜ ቁርጠኛና ቀጥተኛ መሆን አለባቸው። ሁል ጊዜ ቁርጠኛ ሆነን ያልነውን ካደረግን ልጆቻችን አክብረውንና የኃይል ሚዛኑንም በኛ በኩል አስጠብቀን መቀጠል እንችላለን።
እነዚህ ሁሉ የልጆች እንክብካቤ እና ክትትል ማድረጋችን አደግ ሲሉ በወጣትነታቸውም ሆነ በጎልማሳነታቸው ጊዜ ብቁ እና ለሀገር የሚተርፉ ዜጎች እንዲሆኑ ለማስቻል ነው።
እኔም የበጎ ወላጅነትን ጠቃሚ ምክሮች እና ሳይንሳዊ ሃሳቦችን “ልጅ በእድሉ አይደግ” በተሰኘው መፅሀፌ ውስጥ በስፋት አስፍሬዋለሁ። ለዚህ ዋነኛ ምክንያቴ የማህበረሰብም ሆነ የሀገር ልማትና ለውጥ የሚገኘው ከህጻናት እንክብካቤ እና በወላጆች ቀና አስተዳደግ የሚመጣ መሆኑን ለማህበረሰባችን የእለት ተዕለት እርምጃ ውስጥ ለማስረጽ በመፈለጌ ነው።
የጤና ሚኒስቴርም ሆነ በርካታ ተቋማት ስለሀጻናት አስተዳደግ እና በጎ ወላጅነት ተግባራዊ ስራ ቢያከናውኑም እኛ የህክምና ሙያተኞች ደግሞ በዘርፋችን ማበርከት ያለብን ጉዳይ አለና ስለ በጎ ወላጅነት ዛሬም ነገም ቢሆን ሊነገርና ህብረተሰቡ ሊሰበክ ይገባል የሚል እምነት ማሳደር ያስፈልጋል። ምክንያቱም በውጤቱ የእትብታችን መቀበሪያ የሆነችውን ሀገር ብልጽግና የማምጣት እድሉ ሰፊ ስለሆነ ነው።
ሀገር መሰረቷ ህጻናት ናቸው ሲባል ትውልዱ እየተገነባ ካልመጣ በአንድ ጊዜ ሊለወጥ እንደማይችል በማሰብ ጭምር ነው። ለነገው የቤተሰብ እና የሀገር ግንባታ ማማር ደግሞ የህጻናት አስተዳደግ ላይ ትኩረት ማድረግ ያስፈልጋልና በጎ ወላጅነትን እናበረታታ እናጎልብት የሚለውን መልዕክት ማስተላለፍ ያስፈልጋል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 5 ቀን 2013 ዓ.ም