የመካከለኛው አፍሪካ ሪፐብሊክ የእርስ በርስ ግጭትን ለማስቆም የአገሪቱ መንግሥትና አማፂያን ቡድኖች የሰላም ስምምነት መፈረማቸው ታውቋል። የሰላም ስምምነቱ በማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ ዋና ከተማ በሆነችው በባንጉኢ በመንግሥትና በ14 አማፅያን ቡድኖች መካከል የተፈረመ የሰላም ውል ነው፡፡ ከመፈራረማቸው በፊትም በሱዳን ርዕሰ ከተማ ካርቱም መምከራቸው ታውቋል፡፡
የAFP ጋዜጣ ወኪል እንደዘገበው ይህ የሰላም ስምምነት የተካሄደው በዓለም አቀፍ አደራዳሪዎች አማካኝነት መሆኑን ይገልጻል፡፡ የስምምነቱ ዓላማም እ.ኤ.አ ከ2012 ጀምሮ የነበረውን የእርስ በርስ ጦርነት ለማስቆም ታስቦ ነው፡፡
ስለ ጦርነት ሲነሳ የማይጨነቅ የለም፡፡ ለዚህ ደግሞ ዋነኛ ምክንያቱ ጦርነት ኪሳራ እንጂ ትርፍ አለማምጣቱ ነው። በጦርነት ወቅት የሚጎዱት ሕፃናት፣ አዛውንቶችና ነፍሰ-ጡሮች ናቸው፡፡ ብዙ ሕፃናት ያለዕድሜአቸው በግዳጅ ወደ ጦርነት ይሄዳሉ፡፡ ሕፃናት በዚህ ተግባር ተሰማሩ ማለት መማር ያለበት ተምሮ ወደፊት ሀገሩን በሚገባ ሁኔታ አያገለግልም ማለት ነው፡፡ ከዚህ ባለፈ ግን በጦር ሜዳ ያለ ዕድሜአቸው መቀጠፋቸው አሰቃቂ ነው። ዓለማችን በአሁኑ ወቅት በአራቱም አቅጣጫ ውጥረት ውስጥ ነች። ነገር ግን እንደ አፍሪካ የሚበዛበት አካባቢ አይኖርም፡፡
አፍሪካ ይህን ሁሉ የተፈጥሮ ሀብት ታድላ ነገር ግን ከዓለማችን ደሃው አህጉር ናት። አፍሪካዊያን በድንበር፣ በጎሳ፣ በሃይማትና በፖለቲካ እርስ በርሱ ጦርነት እየገጠሙ ከጊዜ ወደ ጊዜ ከችግር መውጣት ተስኗቸው ይታያል። በታደልነው የተፈጥሮ ፀጋ ልክ ብንሠራ የት ነበርን? ልክ እንደሌሎች አህጉሮች ሁሉ ከራሳችን አልፈን የሌላን ዜጋ መመገብ እንችል ነበር፡፡ የጦርነት አስከፊነትን ከሶሪያ፣ የመን፣ሊቢያ፤ ደቡብ ሱዳን፣ሶማሊያ፣ በማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ ወዘተ መማር ይቻላል፡፡ ሊቢያ ሰላም እያለች ዜጎቿ በቅንጦት የሚኖሩባት፣ የዜግነት የሚከፈላቸው፣ የከተሞቿ ሕንፃዎች የሚያስቀኑና መሰረተ ልማት በስርዓት የተሟላባት ሀገር ነበረች፡፡
አሁን ግን ያ ሁሉ የሀገር ሀብት የለም፤ እነዛ ቅንጦተኛ ህዝቦቿ ዛሬ የሞተው ሞቶ የቀረው ከሀገር ተሰዶና በወረርሽኝ በሽታ መከራውን እያየ ይገኛል፡፡ የማዕከላዊ አፍረካ ሪፐብሊክ ዕጣ ፈንታም ከዚህ የተለየ አይመስልም፡፡
በማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ ከ2013 ዓ.ም ጀምሮ ያለማቋረጥ በመንግሥትና በአማፅያን ቡድን መካከል የነበረው ግጭት ህዝቦቿን ክፉኛ ጎድቷል፡፡ ለእርስ በርስ ግጭቱም ዋነኛ ምክንያት የሙስሊም አማፅያን ቡድን በከፍተኛ ሁኔታ በመደራጀት የብዙ ክርስቲያን መኖሪያ በሆነችው ሀገራቸው ስልጣን መያዛቸውን ነበር፡፡
ይህን ተከትሎ ከፍተኛ ወደ ሆነ ብጥብጥ ውስጥ ገብታ የነበረችው ይች ሀገር በቀላሉ ከጦርነት መውጣት ተስኗት ይሄው እስከዛሬ ድረስ በጦርነት ውስጥ ትገኛለች፡፡ የሙስሊም አማፅያን ቡድን ስልጣን መያዛቸውን ተከትሎ ለመቃወም የሞከሩ የክርስቲያን ወታደሮች ኢ- ባላካ በመባል የሚታወቁ ሲሆን፤ አብዛኛዎቹ ለእስር ተዳርገዋል፡፡ ይህም ክስተት ለብዙ የሀገሪቱ ህዝቦች ለሞት ምክንያት ሆኖ አልፏል፡፡
በዚህ ቀውስ የተነሳ ዜጎች የዕለት ተዕለት ሥራቸውን በሚገባ ሁኔታ መሥራት ባለመቻላቸው ለከፋ እርሃብና በሽታ ተጋልጠዋል፡፡ እንዲሁም በእርስ በርስ ግጭቱ የተነሳ በሺዎች የሚቆጠሩ የሀገሪቱ ዜጎች ሲሞቱ ከአንድ ሚሊየን የሚበልጡት ደግሞ ሀብት ንብረት ካፈሩበት፣ ተወልደው አድገው ተፈጥሮን ከተላመዱበት አካባቢ ተፈናቅለዋል፡፡ ሀገራቸውን ሳይጠሉ ነገር ግን በአስገዳጅ ሁኔታ ወደ 570,000 የሚሆኑት ደግሞ ከሀገር ውጪ ተሰደዋል፡፡ ማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ በአሁኑ ወቅት ወደ 2ነጥብ9 ሚሊየን የሚጠጋ ህዝቧ አፋጣኝ የሆነ ዕርዳታ ይፍልጋል፡፡
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ግጭቱ ከተቀሰቀሰ ከአንድ ዓመት በኋላ 2014 የሰላም አስከባሪ ተልዕኮ በስፍራው አስፍሯል፡፡ እንዲሁም ወንጀል ሠርተዋል የተባሉ ሁለት ግለሰቦችን ለዓለም አቀፉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት አቅርቧል፡፡ ይህ እየታየ ያለው ግጭት ከንብረት ውድመት በዘለለ ከፍተኛ ወደ ሆነ የዘር መጠፋፋት ሊሄድ እንደሚችል አስጠንቅቆ ነበር፡፡ ጦርነቱን አስከትሎ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዘገባ እንደሚያሳየው በወባ ወረርሽኝ ምክንያት የሚታመም የሰው ቁጥር መጨመር፣ የሃይማኖት አባቶች መገደላቸው፣ ቤተ እምነቶች መቃጠላቸው፣ ሴቶች መደፈራቸውና የወረርሽኝ በሽታዎች በፍጥነት መስፋፋታቸው የግጭቱን አደገኝነትና ውስብስብነት የሚያሳይ ነው ይላል፡፡
እ.ኤ.አ በ2015 ፖፕ ፍራንሲስ ድፍረት በተሞላበት ሁኔታ ወደ ማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ በማቅናት ሀገሪቱን ለተወሰኑ ቀኖች ጎብኝተው ነበር፡፡ በውቅቱ ለመጎብኘት እንዲነሳሱ ያደረጋቸው ነገር በሀገሪቱ የነበረው የአረመኔ ተዋጊዎችና አድመኞች ሳይሆን በሃይማኖቶች መካከል ተፈጥሮ የነበረው አለመግባባት እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ በሀገሪቱ መዲና በሆነችው ባንጉኢ በሴንትራል መስጊድ በመገኘት ለሙስሊም ወገኖች እንዲህ በማለት መልዕክታቸውን በማስተላለፍ ከዚህ በኋላ ወደ ጥላቻ መግባት አስፈላጊ አለመሆኑን በአፅዕኖት ተናግረዋል፡፡ ፖፕ ፍራንሲስ በጊዜው የነበረውን ግጭት ለማስቆምና እንዳይባባስ የበኩላቸውን ሚና ተጫውተው አልፈዋል፡፡
ከአንፃራዊ ሰላም በኋላ ባለፈው ዓመት አገርሽቶ የነበረው የእርስ በርስ ብጥብጥ የሀገሪቱን ህዝብ ብቻ ሳይሆን ጎረቤት ሀገሮችንም ያስደነገጠ ነበር፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ ነገሩን አሳሳቢ እንዲሆን ያደረገው ከግጭቱ በኋላ ሰላም ያገኙ ቦታዎች ላይ ብቻ ሣይሆን ከጅምሩም ሰላም ወደነበሩ ቦታዎች መዛመቱ ነው፡፡ በሀገሪቱ አንፃራዊ ሰላም ከሰፈነ በኋላ ግጭቱ የተቀሰቀሰበት ምክንያት መሳሪያ የታጠቁ ቡድኖች በወርቅ፣ዳይመንድና ዩራኒየም የበለፀጉ የሀገሪቱን ቦታዎች በቁጥጥራቸው ሥራ በማድረጋቸው ነበር። በህዳር ወር በስደተኞች ጣቢያ ላይ አማፂ ቡድኑ ጥቃት በማድረስ ከ40 በላይ ሰዎችን ከገደለ በኋላ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰላም አስከባሪ ተልዕኮ ኃላፊና የሃገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር በጋራ በመሆን በአጭር ጊዜ ውስጥ አፀፋውን እንደሚመልሱ ያስታወቁ ቢሆንም ባሉት ልክ ግን በለስ ሳይቀናቸው ቀርቷል፡፡ በወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዲህ በማለት ተናግረው ነበር ‹‹አቃለው ህዝባችንን ከጥቃት ለመጠበቅ የሚያስችል አስፈላጊ ነገሮች በሙሉ የሉንም።››
እንደ AFP ዘገባ ባለፉት አምስት ዓመታት በማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሕፃናት ወኪል፤ እንደተናገረው ሁል ጊዜም ተዋጊዎች የሚንቀሳቀሱት ከማንኛውም በፊት ንፁሐንን፣ ትምህርት ቤቶችን፣ መስጊዶችን፣ ቤተክርስቲያኖችን፣ የስደተኛ መጠለያ ካምፖችን ነው ይላል፡፡ ይሄ ጉዳይ ደግሞ በጦርነት ውስጥ ያሉ ንፁሐን ዜጎችን ክፉኛ ይጎዳል፡፡ ዕርዳታም በቀላሉ እንዳይቀበሉና እንዳይደርሳቸው ያደርጋል፡፡
ከተፈናቀሉት ውስጥ ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ሕፃናት በመሆናቸው ስደተኞችን ሕይወት ፈተናውን አብዝቶበታል፡፡ ሕፃናት ተመጣጣኝ ምግብና የእናት ጡት ጠብተው በሚያድጉበት ጊዜያቸው ላልሆነ እንግልትና ስቃይ በመዳረጋቸው በየቀኑ የሚሞቱ ሕፃናት ቁጥር ከዕለት ወደ ዕለት እየጨመረ ነው፡፡ ታዲያ በርሀብ ምክንያትና በወረርሽ በሽታዎች ላለመሞት ሲሉ በሽዎች ሚቆጠሩ ስደተኞች ታጣቂ ቡድኑን ለመከላከል በሃሳብ ውስጥ መሆናቸውን ይጠቅሳል፡፡ ብዙ ጊዜ ግን በታጣቂ ቡድን አስገዳጅነት ወደ አማፂ ቡድኑ የሚቀላቀሉ የሰዎች ቁጥር ከቀን ወደ ቀን እየጨመረ መምጣቱ ለግጭቱ መባባስ አሉታዊ አስተዋዕኦ እንዲኖረው አድርጓ፡፡
ባለፈው ውር ተጅምሮ የነበረውን የሰላም ድርድር የኖርዌይ የስደተኞች ካዉንስል፤ በዚህ የሰላም ድርድር ስምምነት ላይ መድረስ ካልተቻለ ከፍተኛ የሆነ መቅሰፍት ሊደርስ እንደሚችልና በዓለማችን ላይ በድህነት ከሚቆጠሩት ሀገር መካከል የሆነችው ማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ መቆሚያ ወደ ሌለው የእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ እንደምትገባ አመልክቷል፡፡ ይህ ስምምነት ከብዙ የሰላም ስምምነቶች በኋላ በጭብጨባ ታጅቦ በመንግሥትና መሳሪያ በታጠቁ ቡድኖች መካከል የተደረገ ስምምነት ነው፡፡ ነገር ግን አሁንም ቢሆን ይህ ስምምነት ልክ እንደሌሎች ስምምነቶች ሊፈርስ የማይችልበት ምክንያት የለም የሚሉት ብዙዎች ናቸው፡፡ ምን አልባት የተለየ ነገር ካልተፈጠረ በስተቀር እንዲህ በቀላሉ በማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ በመንግሥትና መሳሪያ በታጠቁ ኃይሎች መካከል ሰላም አይመጣም የሚሉም በርካቶች ናቸው፡፡
አዲስ ዘመን የካቲት 2/2011
ሞገስ ፀጋዬ