ታምራት ተስፋዬ
ኢትዮጵያውያን አሉን ብለን ከምንኮራባቸው ባህላዊ የፋይናንስ ሥርዓቶቻችን መካከል ዕቁብ ቀዳሚውን ስፍራ ይይዛል። ዕቁብ የቆየ መሰረት ያለው ባህላዊ የገንዘብ ማሰባሰቢያ ዘዴ ነው። የእቁቡ አባላት በተወሰነ ጊዜ የሚከፈለውን ገንዘብ በመክፈል በእጣ ወይም በስምምነት በሚወጣው ቅደም ተከተል የተዋጣውን ገንዘብ የሚያገኙበት ነው።
በኢትዮጵያም ‹‹ሰውን ሰው ያደረገው ዕቁብ ነው›› እስከሚባል ድረስ ከምጣኔ-ሀብታዊና ማህበራዊ ህይወታችን ጋር በጥብቅ የተሳሰረው ዕቁብ ለብዙዎች የሥራ መጀመሪያ፣ ጎጆ መቀለሻና ወደ ዕድገት መወጣጫ እርካብ ሆኗል። ጥንታዊነት ካለው ከኢትዮጵያዊያን ባህልና ልማድ ጋር በተቆራኘ ሁኔታ ሲተገብር ረጅም ዕድሜ ያስቆጠረ መሆኑም ይታመናል።
ዘመናዊና የተደራጀ አሰራርን የማይከተል፤ በተቋማት የሚካሄድ ባለመሆኑ፤ ወለድ የማይታሰብበት፣ የሚመራበት ሕግ ወይም ተቆጣጣሪ አካል ወይም በህግ የታወቀ መብትና ግዴታዎችን መቀበል የሚያስችል ሕጋዊ ሰውነት የሌለው መሆኑም ከባንክ ወይም ከሌሎች የቁጠባ ማህበራት ይለየዋል።
ዕቁብ ለበርካታ ዓመታት ሚሊየኖችን ዘርፈ ብዙ ትሩፋቶቹን ሲያቋድስ መዝለቁ የማይካድ ቢሆንም በተለይም ዘመናዊና የተደራጀ አሰራርን የማይከተል መሆኑ እድገቱ አዝጋሚ፤ ተፅእኖው እና ጠቀሜታው በሚፈለገው ልክ እንዳይሆን አድርጎታል። ይሁንና በአሁን ወቅት የኢትዮጵያን ባህላዊ የቁጠባ ዘዴ ለማዘመን ወሳኝ የተባለ አንድ እርምጃ መራመድ ተችሏል። ባህላዊ የቁጠባ ስርዓቱን ዲጂታል በሆነ መልኩ እንዲከወን የሚያደርግ መተግበሪያ ይፋ ሆኗል። አዲስ ዘመን ጋዜጣም ስለ ዘመናዊው እና ዘመነኛው ዕቁብ ለቴክኖሎጂው መስራቾች ጥያቄን አቅርቧል።
የዕቁብ ፋይናንሻል ቴክኖሎጂስ መስራች እና ዋና የቴክኒክ ኃላፊ ዮሃና ኤርሚያስ እንደምትገልፀው በዕቁብ ፋይናንሻል ቴክኖሎጂስ ይፋ የሆነው ይህ መተግበሪያ ባህላዊው የቁጠባ ስርዓታችንን ማህበረሰባዊነቱን በጠበቀ መልኩ ወደ ዘመናዊ አሰራር የሚቀይር ነው። ዕቁብ ላይ የሚከናወኑ ተግባራትን አስመስሎና የበለጠ ተጠያቂነት፣ የአጠቃቀም ቅለት እንዲሁም እቁቦቹ በሌሎች ሰዎች ይበልጥ እንዲገኙ እንዲያስችል ተደርጎ የተሰራ ነው።
በኢትዮጵያ ለሚካሄደው የፋይናንስ ቴክኖሎጂ እና ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ትልቅ አስተዋፅዖ እንደሚያበረክት ስለሚታመነው መተግበሪያ ዮሃና እንደምትገልፀውም በመተግበሪያው እቁቦቹ ልክ እንደ ባህላዊ ስርዓቱ ሁሉ ከዕቁብተኞች የሚላከውን ገንዘብ የሚቆጣጠር የየራሳቸው ሰብሳቢ ሲኖራቸው የዕቁብ አወጣጡም እንዲሁ በእጣ የሚወሰን ይሆናል። ለአስተማማኝነቱ ሲባል መተግበሪያውን ለመጠቀምና ዕቁብተኛ ለመሆን ሥም፣ አድራሻ እና የመታወቂያ ካርድ ማቅረብ እንደ ግዴታ ተቀምጧል። መመዝገብ የሚፈልግ ማንኛውም ተገልጋይም፣ የትውልድ ቀን፣ የሚኖርበት ቦታ፣ መታወቂያ፣ ፎቶ፣ ጨምሮ የተለያዩ የግል መረጃዎቹን መስጠት አሟልቶ መቅረብ ግድ ይለዋል።
በመተግበሪያው መሰረት አንድ ዕቁብ አሊያም ዕቁብ ሰብሳቢ መሆን ፍላጎት ያለው ሰው በመተግበሪያው ላይ ዕቁብ መፍጠር ይችላል። የሚፈልጋቸውን በተለይ በቅርብ የሚያውቃቸውን ሰዎቹ መጥራት ይችላል። እያንዳንዱ ዕቁብም ፍላጎትን መሰረት ባደረገ መልኩ የሰፈር አሊያም የካምፓኒ ስም መለያ ሊሰጠው ብሎም ሊካተትበት ይችላል።
መተግበሪያው በበይነ መረብ አማካኝነት ሲሰራ ዕቁብተኞቹ ክፍያዎችን ከመከታተልም ባሻገር መረጃ እንዲለዋወጡ የሚያስችላቸው ይሆናል። እቁባቸውን በጊዜው ይጥሉ ዘንድ ማስታወሻ የሚልክላቸው መተግበሪያው በጊዜ የሚጥሉትንም ኋላ ላይ ማበረታቻ የሚሰጥ ይሆናል። በተጨማሪም ማን እቁቡን እንደጣለና እንዳልጣለ፤ ማን ዘግይቶ ገንዘቡን እየላከ እንደሆነ መረጃ እንዲሰጥና በአካባቢያቸው ያሉ ሌሎች እቁቦችንም መፈለግ እንዲችሉ ሆኖ የተሰራ ነው።
መተግበሪያው በዕቁብተኞቹ መካከል መተማመን እንዲኖር ለማድረግ ያስችሉኛል ያላቸውን ለየት ያሉ ገፅታዎችንም ይዟል። በቴክኖሎጂው በሚስጥር አጠባበቅ ረገድ ጠንካራ አሰራሮችን የተዘረጉለት ስለመሆኑ አፅንዖት የሚሰጡት መስራቿ፣ ‹‹ተጠቃሚዎቹ ሌሎች እቁቦችን በሚቃኙበት ሰዓት እቁቡ የስንት ብር እንደሆነ ከማስመልከትና ለመቀላቀል ጥያቄ እንዲያቀርቡ ከማመቻቸት በቀር ሌሎች የዕቁብ ቡድኑን መረጃዎች በሚስጥር ይጠብቃል። በመተግበሪያው አሰራር ማንኛውም ሰው እቁቡ ወርሃዊ ነው ሳምንታዊ ነው እንዲሁም ባለ ስንት ነው የሚለውን ከመመልከት ውጭ የሌሎችን የግል ሚስጢር መመልከት አይችልም›› ነው ያሉት።
መተግበሪያው በዚህ በሳምንት አሊያም ወር እቁቡን ያሸነፈው ማነው የሚለውን በቂ መረጃ ይሰጣል። እቁቡ ስለተጣለባቸው ዙሮች እንዲሁም እቁቡን ሳይጥሉ ያሳለፉ ዕቁብተኞች ስለመኖራቸው የሚያሳዩ መረጃዎችን የሚያቀርብ ስለሆነም ተጠቃሚዎቹ የተሻለ ተዓማኒነት ያላቸውን እቁቦች ለይተው እንዲቀላቀሉ ያስችላል ተብሎለታል።
ከአገር በተጓዳኝ ባህር በመሻገር በመላ ዓለም የሚገኙ ዲያስፖራዎችን ተደራሽ በመሆን ረገድ ሰፋፊ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ያስገነዘቡት መስራቿ በጥቂት ጊዜያት ውስጥ ከባለድርሻ አካላት በጋራ ለመስራት የሚያስችሉ የግንኙነት ስራዎች እንደተጠናቀቁም በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ዘመናዊውን ዕቁብ እንዲቀላቀል በሩ ይከፈትላቸዋል ተብሏል። በዚህ ረገድም የተለያዩ ማበረታቻዎች እየተዘጋጁ ስለመሆኑም ለማወቅ ተችሏል።
ዕቁብ ፋይናንሻል ቴክኖሎጂ መተግበሪያውን ከባንክ አገልግሎት ጋራ ለማስተሳሰር እና የገንዘብ ልውውጡንም ቀላል ለማድረግ ያስችል ዘንድ ከተለያዩ የባንክ ዘርፉ ባለድርሻዎች ጋራ እየተነጋገሩ መሆኑን ታውቋል። ዕቁብ ፔይ የተሰኘ ገፅታን በውስጡ ማካተቱንም ለማወቅ ተችሏል። መተግበሪያው ይፋ ከተደረገበት ዕለት አንስቶ ባሉት ቀጣይ ሦስት ወራት ውስጥ 30 ሺህ ተጠቃሚዎችን ለመሳብ አልሟል።
ከሳምንት በፊት በጉግል አፕ ስቶር ላይ እንዲቀመጥ የተደረገው መተግበሪያው በእስካሁኑ ቆይታው ከ500 ጊዜ በላይ ዳውንሎድ ለመደረግ በቅቷል። ድርጅቱ መተግበሪያውን የሚጠቀሙ ዕቁብተኞችን ታላሚ አድርገው ከሚሰሩ ማስታወቂያዎች ገቢ የሚያገኝ ይሆናል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 3/2013