መርድ ክፍሉ
በኢትዮጵያውያን ዘንድ መረዳዳት ትልቅ ባህል ተደርጎ ይወሰዳል። በተለይ ወላጅ የሌላቸውን ህፃናት ወስዶ ማሳደግ ባህል ብቻ ሳይሆን እንደ መገለጫም የሚታይባቸው ብሄሮች አሉን። ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ግን እንደዚህ አይነት ባህሎች እየተቀዛቀዙ መጥተዋል። በዚህም ጎዳና ላይ የሚወድቁ ህፃናት ቁጥር በየጊዜው እየጨመረ ይገኛል። በተመሳሳይም በቁም የመረዳዳት ባህሎችም እየተሸረሸሩ መጠያየቅ፣ የታመመን ማስታመም እንደ ነውር እየተቆጠረ መጥቷል።
ቱባ ባህሎች አሉን ብለን የምናወራውን ያክል በተግባር የሚታዩ ነገሮች በመጥፋታቸው ረጂ ያጡ ዜጎች የሰው ያለህ እያሉ ወደ ማይቀርላቸው ሞት እያዘገሙ ይገኛሉ። በተወሰነ መልኩም ቢሆን የበጎ አድራጎት ማህበራት በተቻላቸው አቅም ድጋፍ ለማድረግ ቢሞክሩም በህብረተሰቡ ውስጥ የመረዳዳት ሁኔታው እያደገ ባለመሆኑ ችግር እያጋጠማቸው ይገኛል። ከዚህም ባለፈ በመንግስት ደረጃ የሚሰሩ የድጋፍ ስራዎች በጣም አነስተኛ በመሆናቸው ድጋፍ የሚያገኙት ውስን ሰዎች ብቻ እንዲሆኑ አድርጓል።
ባህል ይሁን ህግ ግልፅ ባይሆንም ቤተ እምነት ውስጥ የሟች ሬሳ በሸክም ሲያልፍ በአቅራቢያ የሚገኙ ሰዎች ቆመው ያሳልፉታል። ምናልባት ሟችን ከሶስት ቀን በፊት በባቡር ስትሄድ አንተ ቁጭ ብለክ ሟችም ከመሞቱ በፊት ድንገት ባቡር ውስጥ አጠገብክ ቆሞ አይተከው ላለመነሳት ባላየ ስልክህን እየነካካክ ‘ላሽ’ ብለኸው ነበር። አሁን ግን ባንዲራ እንደሚሰቅል ወታደር እስኪያልፍ እንደ ጅብራ ቀጥ ብለህ ቆምክ። አቤት ለሬሳ ያለን አክብሮት
ለታመመ ሰው ማሳከሚያ ገንዘብ ለማዋጣት ፊቱን ያጠቆረው የስራ ባልደረባክ ምናልባት ታማሚው ሲሞት ለመቃብር ማስቆፈሪያና ለሳጥን መግዣ በሀዘኔታ ከንፈሩን እየመጠጠ ግማሽ ወጪውን ይችላል ምን እሱ ብቻ አበባም በስሙ ያበረክታል። በህመምና በተጎሳቆለ አኗኗር ሲማቅቅ ዞር ብሎ ያላየውን ሰው አሟሟቱን አነጋጋሪ በሆነ ድምቀት ‘ያሳምርለታል’።
ማደግና ለትውልድ መሻገር ያለባቸው መልካም እሴቶቻችንን መንከባከብ የሚገባ ቢሆንም የሰዎችን አሟሟት ከማሳመር ይልቅ ባለን አቅም አኗኗራቸውን ማሳመር ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል። ምንም ያልሰራን ሰው ሲሞት የምናሞግሰው ነገር ደግሞ ያስቃል። ለራሱ ለሟች እንኳን የሚገርመውን ሀውልት ትሰራለታለክ.. መንገድ በስሙ ትሰይማለክ….ቲሸርትህ ላይ ፎቶውን ታሳትማለክ…. በእርግጠኛነት ለሟች ይሄንን ሁሉ ፍቅርና ገንዘብ ሰጥተኸው ቢሆን ኖሮ አይሞትም ነበር።
አንተም ከአሟሟትህ ይልቅ አኗኗርህ እንዲያምር አድምተህ ስራ። ሰው ካንተ ሊማር ይችል ይሆናል እንጂ ከሞትክ በኋላ አንድ ሺህ ትውልድ ቢረግምህም ቢመርቅህም ላንተ ምንህም አይደለም። አሟሟትህን ለማሳመር ከአኗኗርህ ላይ አትቀንስ። የህፃናትን አኗኗር ማሳመር ከቻልክ ያንተም የኢትዮጵያም አኗኗር ያምራል። የአኗኗር እንጂ የአሟሟት ውበት ከሴሪሞኒ አይዘልም። ይህን ፅሁፍ ያገኘሁት ከአስካል በጎ አድራጎት ማህበር ማህበራዊ ትስስር ገፅ ላይ ነው።
የአስካል የበጎ አድራጎት ማህበር የተመሰረተው መስከረም ወር 2011 ዓ.ም ላይ ሲሆን ሰዎችን ባለ አቅም ለመርዳት ታስቦ የተቋቋመ ነው። ምድር ላይ ሲኖር ስም ሊያስጠራ የሚችልና ለሌላው የሚጠቅም ስራ ለመስራት በተነሳሽነት የተከናወነ መሆኑን መስራቾቹ ይናገራሉ። የአስካል በጎ አድራጎት ማህበር መስራችና ስራ አስኪያጅ አቶ በላይ ንጉሴ ጋር ቆይታ አድርገናል ተከታተሉት።
ማህበሩ ያከናወናቸው ተግባራት
አስካል በጎ አድራጎት ማህበር በዋናነት የሚሰራው በህፃናት ላይ ነው። የተመሰረተው ከ2011 ዓ.ም ላይ እንደመሆኑ ህፃናት ሁሉን አቀፍ ድጋፍ እንዲያገኙና ጠቅላላ እርዳታ እንዲደረግላቸው በማድረግ በቀጣይ ትውልድ አገር የሚረከብ ዜጋ መፍጠር አላማ ያደረገ ነው። ከምስረታው ጀምሮ ድጋፍ የሚያገኘው ማህበሩ በጎ ከሚያደርጉ ሰዎች በሚገኝ ድጋፍ ለልጆቹ እርዳታ ይደረግ ነበር። ይህ አካሄድ አዋጪ ስላልነበረ ማህበሩ በራሱ መንቀሳቀስ የሚችልባቸውን መንገዶች መፍጠር ጀመረ።
በዚህም የኪነጥበብ ምሽቶችን በማዘጋጀት ከሚገኘው ገቢ ድጋፎች ይደረጉ ነበር። ማህበሩ ከምስረታው ጀምሮ 417 ሰዎች ላይ ተደራሽ መሆን ተችሏል። በአገሪቱ የኮቪድ 19 ወረርሽኝ እስከገባበት ጊዜ ድረስ በርካታ ስራዎች ተከናውነዋል። ለተቸገሩ ሰዎች አስቤዛ መስጠት፣ በዓላት ሲደርሱ የበዓል መዋያ አንዳንድ ነገሮች ማድረግ፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለተማሪዎች ጫማ ከመስጠቱ በፊት ማህበሩ ጫማ ለተማሪዎች ሰጥቷል፣ ለተማሪዎች የማጠናከሪያ ትምህርት ተሰጥቷል፣ ህፃናት ስለ አገራቸው ያልተበረዘ ነገር ይዘው እንዲድጉ ታሪካዊ ቦታዎችን እንዲጎበኙ በማድረግ እንዲሁም ከወላጆች ጋር ውይይት በማድረግ የበጎ አድራጎት ማህበሩን ስም የመገንባት ስራ ተከናውኗል።
ማህበሩ የተመሰረተበትን ዓላማ ከማሳካት አንፃር ብዙ ስራዎች ሲከናወኑ ቆይተዋል።በአገሪቱ የነበሩ አገራዊ ጥሪዎች በተለይ ከኮሮና ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ፣ ከኩፍኝ ክትባት ጋር በተያያዘ፣ ከአረንጓዴ አሻራ ጋር በተያያዘ እንዲሁም በሌሎች ላይ ተሳትፎ በማድረግ ማህበሩ አስተዋፅኦ አበርክቷል። የማህበሩ ስም አስካል የሚለው ትርጉም ፍሬ ማለት ሲሆን ፍሬ የሚለውን በሁለት መልኩ መመልከት ይቻላል። የመጀመሪያው ዘር ማለት ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ የአንድ ምርት ውጤት ማለት ነው።
በኢትዮጵያ የሚገኙ ህፃናት ትልቅ ደረጃ ደርሰው የሚጣፍጥ ፍሬ እንዲያፈሩ ለማድረግ ማህበሩ አቅዶ እየሰራ ይገኛል። ማህበሩ በህፃናት ላይ አተኩሮ የሚሰራ ቢሆንም በህፃናቱ ወላጆች ላይም ትኩረት ይደረጋል። የህፃናት ወላጆች፣ ጡረታ የወጡ ሰዎችን፣ በቤተሰብ ውስጥ የሚኖሩ ታማሚዎችን እንዲሁም በህፃናቱ ዙሪያ ያሉትን ማህበሩ ይደግፋል። በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ወቅት የማዕድ ማጋራት ስራዎች በህፃናቱ ዙሪያ ተከናውኗል። በዚህም ሁሉን የቤተሰብ አባላት የሚያካትት ነው።
የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ከገባ በኋላ ማህበሩ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ የተንቀሳቀሰበት ሁኔታ ነበር። የመጀመሪያው የነበረው የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎችን ማከናወን ነበር። ወረርሽኙ በተነሳበት ወቅት ህብረተሰቡን የማረጋጋትና ጥንቃቄ እንዲደርግ ትምህርቶች ተሰጥተዋል። ከዚህ ባሻገር በወረርሽኙ ምክንያት ኑሮ የጎዳቸውን ሰዎች ከሶስት ወረዳዎች ለተወጣጡ መቶ ሀምሳ ሰዎች ማጋራት ስራ ተከናውኗል። በተጨማሪም የንፅህና መጠበቂያ እቃዎች ተሰጥተዋል።
የህዝቡ አቀባበል
ማህበሩ እንደተመሰረተ የመጀመሪያ ስራው የነበረው የህብረተሰቡ አቀባበል ምን ሊሆን ይችላል የሚለው ነበር። ወደ ህብረተሰቡ እንዴት ተደርጎ ተደራሽ መሆን ይቻላል የሚለውን አስቀድሞ ታስቦ ነበር። ማህበሩ የተመሰረተው በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለከተማ ውስጥ እንደመሆኑ ከሶስት ወረዳዎች ድጋፍ የሚፈልጉ ህፃናት በመመልመል ነበር ስራው የተጀመረው። በመቀጠል ከአቃቂ ቃሊቲ ክፍለከተማ ውስጥ የሚገኙ ወረዳዎች በመሄድ ወደ ሶስት መቶ ህፃናትን ማግኘት ተቻለ። ይህንን ወደ ተግባር ለማስገባት ዘጠና ወላጆች ተጠሩ። በዚህም ስለ ማህበሩ ግንዛቤ ማስጨበጥ ተቻለ።
በሌላ በኩል ማህበሩ የሚያዘጋጃቸው የጥበብ ምሽቶች ከሰዎች ጋር የመገናኘት፣ የመገናኛ ብዙሃን ሽፋኖችን ማግኘት፣ እንዲሁም በሌሎች ጉዳዮች የህብረተሰቡ አቀባበል ከመጀመሪያው እየተሻሻለ መጣ። ከተቀባይነት አንፃር የማህበሩ ስም በአንዳንድ ቦታዎች ላይ መታወቅ ጀመረ። የማህበሩን ስም ለማሳወቅ የጫማ መጥረግ ዘመቻ ተከናውኖም ነበር። በማንኛውም ዘመቻ ማህበሩ ሲሳተፍ እራሱን ለማስተዋወቅ ረድቶታል። በአረንጓዴ ዘመቻ በተሳፈበት ወቅት ብዙም እውቅና ያልነበረው ሲሆን በጊዜ ሂደት የተለያዩ አካባቢዎች ላይ እውቅና አገኘ።
ማህበሩን ያጋጠሙ ችግሮች
ማህበሩ ስራዎችን ከጀመረ በኋላ የተለያዩ ችግሮች አጋጥመውታል። በተለይ የኮሮና ወረርሽኝ ከተከሰተ በኋላ ከባድ ሁኔታዎች ተፈጥረው ነበር። በዋናነት ማህበሩን ገጥሞት የነበረው ተግዳሮት ማህበሩ የሚሰራቸው ስራዎች አጥንቶ ሳያጠናቅቅ የኮቪድ ወረርሽን መከሰት ነው። አንድን ነገር እንደ አዲስ መጀመር በራሱ ስራዎችን ለመስራት ከማነሳሳት በተጨማሪ ለማስተዋወቅ ስራዎችን ይጠይቃል። የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ሲከሰት ስራዎችን አስተጓጉሏል።
ሌላው ችግር የነበረው የሀብት ማነስ ነበር። ማህበሩ ሲመሰረት መቶ ሀምሳ ህፃናትን ለመደገፍ አስቦ ቢሆንም በመጀመሪያው ዓመት 228 ህፃናትን መደገፍ ተችሏል። ማህበሩ የነበረው አቅም መቶ ሀምሳ ህፃናትን መደገፍ ቢሆንም ድጋፍ የተደረገላቸው ብዙ ነበሩ። ማህበሩ ያለው ሀብትና እገዛ የሚፈልጉ ሰዎች ቁጥር የሚመጣጠን አልነበረም። ከዚህ ባሻገር ቋሚ ገቢ ከሌለ ቋሚ ነገር ማድረግ አይቻልም። በዚህም ቀጣይነት ያለው ስራ ከመስራት አስቸጋሪ ነገር ፈጥሯል። የቤት ኪራይ እየተወደደ በመምጣቱ የማህበሩ አባላት በየቤታቸው እየሰሩ ይገኛሉ። በአሁን ማህበሩ ቋሚ ገቢ ስለሌለው የቤት ኪራይ መክፈል አይችልም።
መገናኛ ብዙሃን ይሁኑ ባለሀብቱ አዲስ ለተመሰረተ በጎ አድራጎት ድርጅቶች ትኩረት አይሰጡም። ሁሉም ትኩረት የሚያደርጉት ቀደም ብለው የተመሰረቱት ላይ ሲሆን ሁሉም አንድ ቦታ ላይ ግር ብሎ የመሄድ ነገር አለ። አዳዲሶቹን የማብቃትና የመደገፍ ሁኔታው አነስተኛ ነው። ሁሉም አላማው አንድ እስከሆነ ድረስ መደጋገፍ የግድ ያስፈልጋል። ሁሉም ወደ አንድ ቦታ መሄድ የለባቸውም።
የማህበሩ ቀጣይ እቅድ
ማህበሩ የአጭር ጊዜና የረጅም ጊዜ እቅድ አዘጋጅቶ እየሰራ ነው። ማህበሩ ድጋፍ የሚያደርግላቸው ህፃናት አድገው አገሪቱን ከድህነት ሲያወጡና እራሳቸውን ሲችሉ ማየት ትልቅ ህልሙ ነው። ለዚህ እንዲረዳ አስካል መንደር የተባለ ለመመስረት እቅድ አለ። ሙሉ የመሰረተ ልማት የተሟላበት ለምሳሌ ወላጆች የቤት ኪራይ ለመክፈል አቅም ላይኖራቸው ይችላል። በሚመሰረተው መንደር ሁሉም ቤተሰብ እንዲኖሩ ይደረጋል። ድጋፍ የሚደረግላቸው ህፃናት በማዕከሉ አስፈላጊውን ትምህርት አግኝተው አድገው እራሳቸውን ሲችሉ በራሳቸው እንዲኖሩ ሁኔታዎች ይመቻቹላቸዋል።
ማህበሩ ልጅና ወላጅን ማለያየት ፍላጎት የሌለው ሲሆን ልጆች ከገጠማቸው ድህነት በተጨማሪ ቤተሰቦቻቸውን ማጣት ስለሌለባቸው አንድ ላይ እንዲኖሩ ይደረጋል። የወላጅና የልጅ ፍቅር ባለበት ሆኖ ሁለቱ የሚደገፉበት ሁኔታ ይመቻቻል። ማዕከሉ ትምህርት ቤትና ሌሎች መሰረተ ልማት የሚባሉ ነገሮች ይኖሩበታል። በሌላ በኩል ቢሮዎችን መስራት እቅድ ያለ ሲሆን ለዚህ ቋሚ የሆነ ገቢ ያስፈልጋል። ለዚህ ቆመው የነበሩ የኪነጥበብ ምሽቶች ይዘጋጃሉ። ከነዚህ ውጪ ማህበሩ ያሰባቸው ስራዎች ያሉ ሲሆን በረጅምም በአጭርም ስራዎች ለማከናወን ታስቧል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 3/2013