ማህሌት አብዱል
የተወለዱት አዲስ አበባ ከተማ ቢሆንም እድገታቸው በጉራጌ ዞን እነሞርና ኤነር ወረዳ ነው። የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታውን የተማሩት በዚሁ ወረዳ በሚገኙ ሁለት ትምህርት ቤቶች ሲሆን እስከ ስድስተኛ ክፍል የተማሩበት ትምህርት ቤት ደግሞ ከመኖሪያ ቤታቸው አራት ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ፤7ኛ እና 8ኛ ክፍልን ደግሞ ስምንት ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኝ ትምህት ቤት በእግራቸው እየተጓዙ ነው የተከታተሉት።
በተለይም በአካበቢያቸው ትምህርት የሚማር ታዳጊ ባለመኖሩ ያን ሁሉ መንገድ ብቻቸውን የሚጓዙ መሆኑ የትምህርት ቤት ቆይታቸውን ፈታኝ አድርጎባቸው ነበር። ይሁንና የዛሬው የዘመን አንግዳችን የቦታው ርቀትም ሆነ ፈታኝ ሁኔታዎች ሳይገድባቸው የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን በአንደኝነት እየመሩ አጠናቀቁ። በ1987 ዓ.ም ስምንተኛ ክፍልን በከፍተኛ ውጤት ቢያጠናቅቁም በትውልድ ቀያቸው የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ባለመኖሩ አዲስ አበባ ድረስ በመምጣት ዘመድ ቤት በመጠጋት ዳግማዊ ምኒልክ ትምህርት ቤት ተከታተሉ። እስከ 12ኛ ክፍል ድረስ የአንደኝነት ደረጃቸውን ሳያስነጥቁ የቆዩት እኚሁ ብርቱ ተማሪ የሁለተኛ ደረጃ መልቀቂያ ፈተናቸውን በ1991 ዓ.ም 3 ነጥብ 8 አምጥተው አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መግባት ቻሉ።
ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በእንስሳት ህክምና የመጀመሪያ ዲግሪያውን እንዳገኙም በትምህርት ሚኒስቴር ተቀጠሩ። ብዙም ሳይቆዩ አዲስ አባባ ዩኒቨርሲቲ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን የመማር እድል ያጋጥማቸዋል። አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ዳግመኛ ገብተውም ትሮፒካል ቨተርነሪ ፒዲሞሎጂ በሚባል የእንስሳት በሽታ ስርጭት ዘርፍ ጥናት አድርገው የማስተርስ ዲግሪያቸውን ተቀበሉ። በመቀጠልም በየትኛውም የአገሪቱ አካባቢ ተዘዋውሮ ለማገልገል ከመንግስት ጋር በገቡት ውል መሰረት በእጣ ወሎ ዩኒቨርሲቲ ደረሳቸው። በዚያ መሰረት ወሎ ዩኒቨርስቲን ከማቋቋም ጀምሮ እስከ ምክትል ፕሬዚዳንትነት ድረስ ጉልበታቸውንና እውቀታቸውን ሳይሰስቱ አገለገሉ። በዚህም አልተወሰኑም ፤ እዛው ዩኒቨርስቲ እየሰሩ ሳለም በህንድ አገር ፒዲሞሎጂ ፕሪቨንቲቭ መዲስን በተባለ የበሽታ ሰርጭትና መከላከል ዘርፍ ላይ ሦስተኛ ዲግሪያቸውን ሰሩ። የመመረቂያ ጥናታቸውም ከእንስሳት ወደ ሰው የሚተላለፍ የሳንባ በሽታ ላይ ትኩረት ያደረገ ነበር። ትምህርታቸውን እንዳጠናቀቁም ወደ ወሎ ዩኒቨርሲቲ ተመልሰው በተለያዩ ኃላፊነቶች ላይ አገለገሉ።
ከ2009ዓ.ም ጀምሮ ደግሞ ወደ ሚዛን ቴፒ ዩኒቨርስቲ ተዛውረው በአካዳሚክ ምክትል ፕሬዚዳትነት እንዲሰሩ በሹመት ተመደቡ። ይሁንና ሁለት ሳምንት እንኳን ሳይቆዩ ፕሬዚዳንት ሆነው እንዲሰሩ ተመድበው ለሶስት ዓመታት አገለገሉ። ካለፈው አንድ ዓመት ወዲህ ደግሞ ወልቂጤ ዩኒቨርስቲ ለፕሬዚዳትነት ባወጣው የስራ ማስታወቂያ ተወዳድረው በማለፍ ተቋሙን በመምራት ላይ ይገኛሉ። የወልቂጤ ዩኒቨርስቲ ፕሬዚዳት ዶክተር ፋሪስ ደሊል የዛሬው የዘመን እንግዳችን ናቸው። ዩኒቨርሲቲው እያከናወነ በሚገኛቸው ስራዎች፣ በወቅታዊ አካባቢያዊና አገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ከእንግዳችን ጋር ያደረግነው ቃለምልልስ እንደሚከተለው ይቀርባል።
አዲስ ዘመን፡– የሙያና የምሁራን ማህበራት ለአገር እድገት ምንአይነት ፋይዳ እንዳለው ይግለፁልና ውይይታችንን እንጀምር?
ዶክተር ፋሪስ፡- እንዳልሽው ነው፤ ባለሙያዎችና ምሁራን በአንድ ላይ የሚሰሩበት ማህበር ወይም ህብረት መኖሩ ለአገር አጠቃላይ እድገት ወሳኝ ሚና አለው። ከዚህ አንፃር በኢትዮጵያ የተለያዩ የሙያ ማህራት አሉ። ለምሳሌ ካሉት የሙያ ማህበራት ውስጥ አንዱ የፊዚክስ ባለሙያዎች ማህበር ሲሆን ሰሞኑን ከወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር 15ኛ ጉባኤውን አካሂዷል። የዚህ ጉባኤ አላማም የፊዚክስ ሳይስን ለአገር እድገት ከፍታ አስተዋፅኦ ለማበርከት ያለመ ነው።
በዘርፍ ብዙ ምርምሮች ይሰራሉ። ለተለያዩ ግኝቶችና ፈጠራዎች መሰረቱ የፊዚክስ ሣይንስ እንደመሆኑ የዚህ ዘርፍ ባለሙያዎች ማለትም ከፍተኛ የምርምር ተቋማት፣ በዩቨርስቲዎች፣ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ባለሙያዎች ተገናኝተው እውቀታቸውንና ልምዳቸው የሚጋሩበት ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል። በአጠቃላይ የሳይንስ እድገት በሳይንቲስቶች መካከል ሃሳብ የሚለዋወጡበት መድረክ ነው። በመሆኑም እንደዚህ ያሉ ማህበራት ባለሙያዎች በጋራ ሆነው ሃሳብና ምርምር እንዲያፈልቁ፣ እርስበርስ እንዲተጋገዙና ለአገር እድገት ወሳኝ ሚና እንዲጫወቱ የላቀ አስተዋፅኦ አለው ብዬ አምናለሁ።
አዲስ ዘመን፡– ከዚህ አንፃር የፊዚክስ ሳይንስ ባለሙያዎች ለአገር እድገት ሚናቸውን እንዲወጡ ምንአይነት ምቹ ሁኔታዎች አሉ?
ዶክተር ፋሪስ፡- በአጠቃላይ ኢትዮጵያ ውስጥ በትምህርት ሴክተሩ ላይ አጠቃላይ ለውጥ እየተደረገ ነው። ይሄ ለውጥ ደግሞ ከፍኖተ ካርታው ይጀምራል። ሁሉንም ዘርፎች የሚያካትት የትምህርት ፍኖተ ካርታ ተዘጋጅቷል። በዚህ መሰረትም ዩኒቨርሲቲዎች በየመስኩ የመለየት ስራ እየሰሩና ራሳቸውን እየቀየሩ ነው ያሉት። በአምስት የተለያዩ ዘርፎች የተከፈሉ ሲሆን የእኛን ጨምሮ 15 የሚሆኑት ዩኒቨርስቲዎች ተግባር ተኮር ትምህርት እንዲሰጡ ነው የተለዩት። ፊዚክስ ራሱ ደግሞ ግኝቶቹ ወደ ትግበራ የሚቀየሩ ስለሆነ ይሄ የራሱ መሰረት ጥሎ ያልፋል ተብሎ ይታመናል። በጥናት ተለይቶ ይፋ ከተደረገና ዩኒቨርስቲዎች የትኛው ላይ እንዳረፉ ካወቁ በኋላ የራሳቸውን የአጭርና የረጅም ጊዜ እቅድ አቅደዋል። እኛም እንደዚሁ የአምስትና የአስር አመት እቅዳችንን አጽድቀንና አስተችተን ነው ወደ ትግበራ የገባነው።
ከእነዚህም እቅዶች መካከል የፊዚክስ ሳይንስ ለእድገት መሰረት እንዲጥል የማድረግ ነው። በአጠቃላይ ግን አሁን ላይ አለም የደረሰችበት የሳይንስ እድገት ላይ ለመድረስ የፊዚክስ ሳይንስ ሚና ትልቅ መሆኑ አጠያያቂ አይደለም። በዚህ መድረክ የቀረቡ ጥናታዊ ጽሁፎች በራሳቸው በቀጣይ ምን ላይ ለማተኮር እንዳለብን አመላካች ናቸው። ከእነዚህ ምርምሮች ባለሙያዎቻችን ብዙ ይማራሉ ብለን ተስፋ እናደርጋለን። ተማሪዎች ከአንድ ዩኒቨርስቲ ከሚያገኙት እውቀት በላይ ከሌሎችም ጋር ድምር እውቀት ያስጨብጣቸዋል።
በነገራችን ላይ የፊዚክስ ሳይንስ የማሳደግና የመደገፉ ጉዳይ ወቅታዊ አጀንዳም ጭምር ነው። በቅርቡ እንደምናስታውሰውም መንግስት የህግ ማስከበር ዘመቻ ሲወስድ ውጤታማ የሆነው በድሮን የተደገፈ ውጊያ በማካሄዱ ነው። የድሮን ሳይንስ ደግሞ እንደምናውቀው በፊዚክስ ውጤት ነው። ያደጉት አገራም እንደቀድሞው ሰራዊት አሰልፈው መዋጋት ከተው ሰነባብተዋል። አብዛኞቹ አገራት ወታደራዊ የሆኑ ሮቦቶችን ነው ይዘው የሚወጡት። እኛም ከዚያ መራቅ አንችልም። ምክንያቱም በተለይ በአሁኑ ወቅት የውስጥና የውጭ ችግሮች ያሉብን በመሆኑ መከላከያችንን በዘመናዊ ሳይንስ የተደገፈ ማድረግ ይገባናል። በሌላ በኩልም ታላቁ ህዳሴ ግድባችንን ግንባታ ከመጀመሩ በፊት የአካባቢ ጥናት ሲደረግ የነበረው በፊዚክስ ውጤት በሆነው ሳተላይት ነው። በአጠቃላይ አገራችን ያሰበችውን የተቀላጠፈና የተፋጠነ እድገት ለማስመዝገብ እንደዚህ አይነት ሳይንሳዊ የሆኑ መድረኮችን መፍጠር በጣም ያስፈልጋል።
አዲስ ዘመን፡– በዚህ ረገድ በተለይም አዳዲስ ዩኒቨርስቲዎች የግብዓት ችግር ትልቁ ፈተናቸው እንደሆነ ይታወቃል። ከዚህ አንፃር የወልቂጤ ዩኒቨርስቲ ያለበት ሁኔታ ምን ይመስላል?
ዶክተር ፋሪስ፡– በዚህ ረገድ የጎላ የሚባል ችግር አለበት ብዬ አላምንም። በዚህ አጋጣሚ ያለፉትንም አመራሮችንም ጭምር ማመስገነን እፈልጋለሁ። ዩኒቨርሲቲው ምንም እንኳን በእድሜው ለጋ ቢሆንም ለተግባር ትምህርት የሚያስፈልጉ ግብዓቶች ትኩረት ሰጥቶ ነው የሠራው። ለምሳሌ የፊዚክስ ትምህርት ክፍልን ብንወስድ ተማሪዎቻችን ለተግባር ተኮር ስራዎቻችው የሚያስፈልጋቸው ቤተ-ሙከራ የተደራጀ ነው። ቤተ-ሙከራቹ ምቾትን ከመጠበቅ አንፃር እንዲሁም ያሉትን የተግባር ትምህርቶችን በጣም በክህሎት የተሟላ የሰው ሃይል ከማቅረብ ረገድ ያሉ ውስንነቶች ቢኖርም የተሻለ ግብዓቶች አሉን። እንዳውም የፊዚክስ ስራቸውን የትም ሳይሄዱ እዚሁ የሚጨርሱት ምቹ ሁኔታ መፈጠሩ የተሻለ ያደርገናል ባይ ነኝ። ይህ ሲባል ደግሞ ፈፅሞ ችግሮቻችን ተፈተውልናል ማለቴ አለመሆኑ እንድትገነዘቢልኝ እፈልጋለሁ። ከጊዜው ጋር ተወዳዳሪ ለመሆን አዳዲስ ነገሮች የሚያፈልጉ በመሆኑ ለዚህ ትኩረት ሰጥተን በእቅዳችን አካተን እየሰራን እንገኛለን።
አዲስ ዘመን፡- ዩኒቨርሲቲው ከኮቪድ መምጣት ጋር ተያይዞ የመማር ማስተማሩ ሂደት በምን መልኩ እየተካሄደ ነው የሚገኘው?
ዶክተር ፋሪስ፡- እውነት ነው፤ ኮቪድ ያስተጓጎለው ኢትዮጵያን ብቻ ሳይሆን አለምን ነው። እንደምናስታውሰው ኢትዮጵያም የኮቪድን ተፅዕኖ ለመቋቋም የራስዋን ጥረት አድርጋለች። መግስትም ቁርጠኝነቱን በተግባር አሳይቷል። ዩኒቨርስቲዎቻችንም ደግሞ ለህዝባቸው ትልቅ አለኝታነታቸውን ያሳዩበት ጊዜ ነበር። ከዚህ አንፃር የእኛን ዩኒቨርሲቲ ተሞክሮ ብንወስድ በወቅቱ በአካባቢያችን ከፍተኛ የሆነ የግንዛቤ እጥረት ነበር። በመሆኑም በቫይረሱና ሊደረጉ በሚገባቸው ጥንቃቄዎች ዙሪያ የሰልጣኝ አሰልጣኞችን የማሰልጠን ስራዎችን ሰርቷል።
በተለይ በወቅቱ በበሽታው የሰለጠነ የጤና ባለሙያዎች ብርቅ በሆነበት ሰዓት ቀድመን ማሰልጠናችን በጣም ተጋላጭ በሆኑ አካባቢዎች ላይ ውጤታማ የሚባል ስራ ለመስራት አስችሎናል። በተያያዘም ለይቶ ማቆያ ማከሚያና ምርመራ ማዕከል አቋቁመን ነው ስንሰራ የነበረው። ምርመራ ማዕከሉ አሁንም ጭምር አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛል። በመሆኑም በኢትዮጵያ ደረጃ ሊሰሩ የሚችሉ ስራዎችን በሙሉ ዩኒቨርስቲያችን የአቅሙን ያህል እገዛ አድርጓል። ማስክ ማምረትና ለሃኪሞች አልባሳት ማዘጋጀት ስራ ሁሉ ላይ ተሳትፈናል።
በሽታውን እየተከላከልን ትምህርት እንዲጀመር መንግስት ሲዋጅም ሰፊ ዝግጅት አድርገን ነው ለተማሪዎቻችን ጥሪ ያደረግነው። ከፍተኛ ጥንቃቄ በተሞላበት ሁኔታ በመስራታችንም በተለይም ተመራቂ ተማሪዎቻችን ትምህርታቸውን አጠናቀው ጥር 8 ለመመረቅ ችለዋል። ከዚሁ ጎን ለጎን ለሌሎች ተማሪዎች ያለፈው የትምህርት ዘመን ያልጠተናቀቁ ትምህርቶችንም በማጠናቀቅ ላይ እንገኛለን። በዚህ ረገድ ኮቪድን እየተከላከልን ስራችንን እንድናከናውን የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ሰፊ ክትትል ነው እያደረገ ያለው። በወጣው መመሪያ መሰረት እየተገበርን ስለመሆኑ ቁጥጥር ያደርጋሉ። ይህም ማለት ከበር ጀምሮ የዩኒቨርስቲው ማህበረስብ ሙቀቱን እየተለካ፣ እየታጠበና ማስክ እያደረገ እንዲገባ ነው የሚደረገው። በመማሪያ ክፍሎች፣ ቤተ-መፅሃፍትና ቤተ-ሙከራዎች አቅራቢያ መታጠቢያ በማዘጋጀት ተማሪዎች ራሳቸውን እንዲጠብቁ ጥረት ይደረጋል።
ከዚሁ ጋር ተያይዞ መናገር የምፈልገው ነገር ከተሞች አካባቢ አሁን ላይ መዘናጋቶች ይታያሉ። ከተማም ሆነ በተለየዩ ተቋማት ውስጥ ህብረተሰባችን ማስክ የመጠቀሙ ዝንባሌ እየቀነሰ በመሆኑ አደራ ማለት ነው የምፈልገው። ቫይረሱ አሁን ላይ እንደሚታወቀው ራሱን ቀይሯል። አሁን የመጣው አደገኛ የቫይረስ አይነት ካልተጠነቀቅን ወደእኛ አገር የማይገባበት ምክንያት የለም። አሁን ላይ እየተፈጠሩ ያሉት የቫይረስ አይነቶች በባሕሪ በጣም የተለዩ ናቸው። የማጥቃት አቅማቸው ከፍ ያሉ ናቸው። በእድሜ ገደብም ቀደም ሲል መቋቋም የሚችሉት አሁን ላይ የተፈጠረውን ቫይረስ የሚቋቋሙ አይደሉም። በመሆኑም ህብረተሰባችን አሁን መዘናጋት የለበትም። ተማሪዎቻችንም ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ ይጠበቅባዋል።
አዲስ ዘመን፡– ወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ለጉራጌ ዞን ብቸኛው ከፍተኛ የመንግስት ትምህርት ተቋም እንደመሆኑ ማህበረሰቡን ያማከሉ ምን አይነት የምርምር ስራዎችን ሰርቷል? አበርክቶው እንዴት ይገለፃል?
ዶክተር ፋሪስ፡– እንደሚታወቀው ወልቂጤ ብቻ ሳይሆን አብዛኞቹ የኢትዮጵያ ዩኒቨርስቲዎች አበርክቷቸው ብዙ የሚቀረው ነው። የእኛ ዩኒቨርሲቲ ከተመሰረተ ገና ዘጠኝ ዓመቱ ነው። ነገር ግን ምርምር ማድረግ ሲቋቋም ጀምሮ የወሰደው ተልዕኮ ስለሆነ የተለያዩ ስራዎችን እየሰራ ይገኛል። ለምሳሌ ያህል ብጠቅስልሽ ወደዚህ አካባቢ ህብረተሰብና የደቡብ ቀጠና በቋሚነት የሚመገበው የእንሰትን ተክል ነው። ስለዚህ ዩኒቨርስቲያችን እንሰት ላይ ምርምር እያከናወነ ይገኛል። አንድ የእንሰት ምርምር ማዕከል አቋቁመን የምርምር ስራ እያከናወንን ነው ያለነው። በተለይም በሽታ የሚቋቋሙ የእንሰት ዝርያዎችን የመለየት ስራ ሰርተናል። በተመሳሳይ ቡና በተወሰኑ ወረዳዎች ይመረታል። ይህ ቡና በጥራቱ ታዋቂ ቢሆንም በሽታ የሚያጠቃው ነው። በመሆኑም በሽታ የሚቋቋሙ የቡና ዝርያዎች ላይ ምርምር እያደረግን እንገኛለን። እንዲሁም ለአርሶ አደሩን ችግኝ የምናፈላበት ማዕከል አለን። በተጨማሪም በዚህ ዞን የፍራፍሬ የማምረት አቅም አለ። ይህንን አቅም በምርምር በመደገፍ ለአርሶአደሩ ተጨማሪ የገቢ ምንጭ የመፍጠር ስራ ተቋማችን በመስራት ላይ ነው። በተለይም ምርታማ የሆኑ የአባካዶና ማንጎ ዝርያዎችን በማምረት ለአርሶአደሩ የማዳረስ ስራ እየተሰራ ነው። ከዚሁ ጎን ለጎን የአርሶ አደሮቻችንን ምርትና ምርታማነት በማሻሻል አንዱ ተግዳሮት ምርጥ ዘር የማቅረብ በመሆኑ ለአካባቢው ተስማሚ የሆኑ ምርጥ ዘሮች የማፍለቅ ስራ እየተሰራ ነው።
ሌላው ይህ ጉራጌ ማህበረሰብ እንደሚታወቀው ቱባ ባህል ካላቸው ብሄረሰቦች አንዱ ነው። ይህንን ባህል የመጠበቅ፣ የማሳደግ ስራ በዩኒቨርስቲያችን ይሰራል። ይህም ሲባል ቋንቋውንም ጭምር የማሳደግ ስራንም ያካትታል። በነገራችን ላይ በዚህ ዞን አሁንም ድረስ ተማሪዎች የአፍ መፍቻ ቋንቋቸው በሆነው በጉራጊኛ አይደለም እየተማሩ ያሉት። ይህንን ችግር ለመፍታት እየተሰራ ነው ያለው። በአፍ መፍቻ ቋንቋ እንዲማሩ መደረጉ ውጤታማ ተማሪ ለመፍጠር የሚያግዝ ከመሆኑም ባሻገር ቋንቋው በራሱ እንዳይጠፋ ያደርጋል። ይህ ብቻ ሳይሆን ነባር ባህልና ቅርሶችም እንዳይጠፋ ያደርጋል። በመሆኑም ቋንቋውን ከማበልፀግ አንጻር ከዞኑ መንግስት ጋር አብሮ እየተሰራ ይገኛል።
ከዚህም በተጨማሪ አገር በቀል እውቀቶች የመደገፍ ስራ በዩኒቨርስቲያችን እየተሰራ ይገኛል። ከባህላዊ ህክምና አዋቂዎች ጋር በመተባበር የባህላዊ ህክምና እፅዋቶች አቋቁመን እየሰራን እንገኛለን። ሌላው የጉራጌ ህብረተሰብ የራሱ የሆነ ባህላዊ የዳኝነትና የሽምግልና ስርዓቶች አሉት። እነዚህ ባህላዊ ሥርዓቶች በቀጣይ ትውልድም ተጠብቀው እንዲቆዬ ለማድረግ ዩኒቨርስቲያችን እየሰራ ይገኛል። ለዚህም የአቅም ግንባታ የመሰሳሉት ነገሮች በመስጠት ላይ ይገኛል።
አዲስ ዘመን፡– ዩኒቨርስቲው በሌሎችም የዞኑ አካባቢዎች ተጨማሪ ካምፓሶች ለመክፈት የጀመረው እንቅስቃሴ ምን ደረጃ ላይ ደረሰ?
ዶክተር ፋሪስ፡– ይሄ ጉዳይ ከተነሳ ትንሽ ቆየት ብሏል። ዩኒቨርስቲ ሲቋቋም ጀምሮ ጥያቄው ለመንግስት ቀርቦ ነበር። በተለይም ከወልቂጤ ያልተናነሰ ደረጃ ላይ በምትገኘው ቡታጀራ ከተማ ላይ ተጨማሪ ካምፓስ ለማቋቋም ታስቦ ነበር፤ በመግስትም ጭምር ቃል ተገብቶ እንደነበር ይታወቃል። በዋናነትም ዩኒቨርስቲያችን በቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ቡታጅራ ላይ ካምፓስ እንደሚገነባለት ቃል ቢገባለትም እስካሁን ተፈጸሚ አልሆነም። ዩኒቨርስቲው በተገባለት ቃል መሰረት በዚያ ቦታ ላይ የራሱን ካፒታል ኢንቨስት አድርጓል። ለምሳሌ መምህራን ትንንሽ ከተማ ላይ ሲኖሩ መኖሪያ ቤት ያሥፈልጋቸዋል። ስለዚህ ከቤቶች ልማት አስተዳደር 190 መምህራንን ሊያስተናግድ የሚችል ቤት ገዝቶ አጠናቋል። ነገር ግን መንግስት በይፋ ባለመፍቀዱ ዩኒቨርስቲው ወደ ግንባታ መሄድ አልቻለም። በዚህ የተነሳ ይሄኛው ካምፓስ ከሚገባው በላይ እንዲጨናነቅ አድርጎታል። ከሁሉም በላይ ግን ቡታጀራ አካባቢ ያለው ህብረተሰብ ፍትሃዊ የልማት ተጠቃሚ መሆን አለመቻሉ ለሁላችንም አሳዛኝ የሆነ ጉዳይ ነው። በተጨማሪም ለህብረተሰባችን ቅድም የጠቀስኳቸው የምርምር ስራዎች በዚህ ቦታ ላይ ተደራሽ መሆን አልቻሉም። በመሆኑም በዚህ ጉዳይ ላይ ማህበረሰቡ በአሁኑ ወቅት ሰፊ የሆነ የመልካም አስተዳደር ጥያቄ እያነሳ ነው ያለው። ይህንን ጥያቄ ደግሞ እኛም በተለያዩ መድረኮች ለመንግስት አሳውቀናል። መንግስት በቦርድ ደረጃ ጉዳዩ እንዲጤን ሃሳብ ሰጥቶበታል። እናም ይህ ጥያቄ በጣም መሰረታዊ ከመሆኑም ባሻገር በቀጥታ ወደ ተግባር ቢገባም አስቻይ ሁኔታዎች ያሉት ነው። በተለይም ህብረተሰቡ በጣም ተባባሪና ንቁ መሆኑ ትልቅ አስተዋፅኦ ያበረክታል ብዬ አምናለሁ።
ይሁንና በአሁኑ ወቅት የእዚህ አካባቢ ማህበረሰብ የከፍተኛ ትምህርት የማግኘት ፅኑ ፍላጎት ቢኖረውም በጠቀስኩት ችግር ምክንያት ተደራሽ ማድረግ አልተቻለም። በመሆኑም በመደበኛው ስላላገኙ የማታ መርሃግብር ተከፍቶ መምህራኖቻችን በየቀኑ ከወልቂጤ 90 ኪሎ ሜትር እየተመላለሱ እየሰሩ ነው የሚገኙት። በአንፃሩ ደግሞ ከእኛ እኩል የተከፈቱት የሶስተኛ ትውልድ ዩኒቨርስቲዎች ሶስትና ከዚያ በላይ ካምፓሶች አሏቸው። የመንግስት ዋነኛ ተልዕኮ የትምህርትን ተደራሽነት ማረጋገጥ እንደመሆኑ የሕብረተሰቡን ጥያቄ መመለስ አለበት የሚል እምነት አለኝ። ይህም ማለት ሰዎች በፈለጉበት ሰዓት በቀላሉ ሊማሩበት የሚችሉበትን ሁኔታ መፍጠርና ማመቻቸት ከአንድ መልካም አስተዳደር ከሰፈነበት መንግስት የሚጠበቅ ነው። በአጠቃላይ ግን የቡታጅራው ካምፓስ ጥያቄ ብዙ አመታትን የፈጀ ግን ደግሞ ያልተፈታ በመሆኑ ህብረተሰቡ ላይ ከፍተኛ ቅሬታ አሳድሯል። በመሆኑም በዚህ አጋጣሚ መንግስት ትኩረት እንዲሰጠውና እንዲደግፈን ጥሪ ማቅረብ እፈልጋለሁ።
አዲስ ዘመን፡– ዩኒቨርሲቲዎች ከመደበኛው ሥራቸው በተጨማሪ የአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎችን የመደገፍና የማንቃት ስራ ይሰራሉ። ከዚህ አንፃር የእናንተ ዩኒቨርስቲ ምንደረጃ ላይ ነው ያለው?
ዶክተር ፋሪስ፡– ትክክል ነው። ይህ ጅምር በእኛም ዩኒቨርስቲ አለ። በተለይም ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ላይ መምህራኖቻችን ባላቸው ትርፍ ጊዜ የቲቶሪያል ጊዜ አዘጋጅተው በዞኑ በሚገኙ ሁሉም ትምህርት ቤቶች እየተገኙ ያስተምራሉ። ያለውን ለውጥ በጥናት ባናረጋግጠውም ከተጠቃሚዎች የምናገኘው ግብረመልስ ግን ለውጥ እንደመጣ ያሳያል። በመሆኑም በተሻለ መንገድ አጠናክረን የምንቀጥልበት ነው የሚሆነው። እንዲሁም ‹‹ስቲም›› የሚባል ሳይንስ ማለትም ቴክኖሎጂ፣ ኢንጅነሪንግና የማቲማቲክስ ማዕከል እዚሁ አቋቁመናል። በቀጣይ ግን ራሱን የቻለ ማዕከል ለማዘጋጀት እየሰራን ነው የምንገኘው። እንደዚሁም ዞኑ የተሻለ ተሰጥኦ ያላቸውን ተማሪዎች የመደገፍ ስራ ይሰራል። በተለይም ከተለያዩ ወረዳዎች የተሻለ ውጤት ኖሮኣቸው ትምህርት የሚያቋርጡ ስላሉ ይህንን ለማስቀረት አዳሪ ትምህርት ቤት ለመክፈት አቅዶ እየሰራ ነው። ይህንን እየደገፍን እንገኛለን። ርቀት አያግደንም፣ በጣም አስቸጋሪ የሆኑ ቦታዎች ድረስ መምህራኖቻችን እየሄዱ የበኩላቸውን አስተዋፅኦ እያበረከቱ ይገኛሉ። እዚህ ጋር ግን ሳልጠቅስ ማለፍ የማልፈልገው ጉዳይ ዩኒቨርስቲው ካሉበት ተግዳሮቶች መካከል በዋናነት የተሽከርካሪ እጥረት ነው። በዩኒቨርስቲዎች ደረጃ ባላቸው ካፒታል የራሳቸውን ተሽከርካሪ መግዛት አይችሉም። በሌላ በኩል በመንግስትም እየቀረበልን ባለመሆኑ ከፍተኛ የሆነ የተሽከርካሪ እጥረት አለብን። ይህም ለህብረተሰቡ የምንሰጠውን አገልግሎት በአግባቡ ለማዳረስ እንዳንችል ተግዳሮት ሆኖብናል።
አዲስ ዘመን፡– ሴት ተማሪዎች ያለባቸውን ጫና ለመቀነስ ዩኒቨርስቲው ምን አይነት ድጋፎችን ያደርጋል?
ዶክተር ፋሪስ፡– ለሴት ተማሪዎቻችን ብቻ ሳይሆን ለሴት መምህራንም ጭምር ልዩ ድጋፍ እናደርጋለን። በተለይም አብዛኞቹ ተማሪዎቻችን ዝቅተኛ ኢኮኖሚ ካላቸው ቤተሰቦች የመጡ እንደመሆናቸው በኢኮኖሚ የመደገፍ ስራ ነው የምንሰራው። ተማሪዎቻችን በቆይታቸው ውጤታማ እንዳይሆኑ ተግዳሮት እንዳይሆንባቸው መለስተኛ የሆኑ ወጪዎቻቸውን መሸፈን የሚያስችላቸውን ድጋፍ ያደርጋል። ለምሳሌ ከኢትዮ- ቴሌኮም እንዲሁም በዩኒቨርስቲው የበጎአድራጎት ማህበር ከደመወዛችን በየወሩ እየተቆረጠ ድጋፍ እናደርጋለን። ሌላው ለሴቶች በተለየ ሁኔታ ቲቶሪያል ትምህርት ይሰጣል። በተጨማሪም ሴት ተማሪዎች እርስበርስ የሚማማሩበት ምቹ ሁኔታ ተፈጥሯል።
ከዚህ ባለፈ ውስጣቸው ተነቃቅቶ ተስፋ ሰንቀው እንዲማሩ ለማድረግ የተለያዩ ድጋፎች ይደረጉላቸዋል። ለምሳሌ ዘንድሮን ብንወስድ የሴት መምህራን ተሳትፎ ከወንዶች አንፃር በጣም አነስተኛ ነው። 12 በመቶ ብቻ ናቸው። ስለዚህ ዘንድሮ ካስመረቅናቸው 44 ፕሮግራሞች የተሻለ ውጤት ያመጣች ሴት ተመራቂ በምህርነት እንድትቀጠር አድርገናል። ይህም ከታች እየተማሩ ያሉትን ሴት ተማሪዎች ተስፋ ሰንቀው እንዲማሩ ያበረታታቸዋል። እንዲሁም ለሴት መምህራኖቻችንም የተለየ ድጋፍ እናደርጋለን። ለምሳሌ የቤት አቅርቦት በቂ አይደለም። ነገር ግን ካሉን ቤቶች ውስጥ ሴት መምህራን እርስ በርስ ተወዳድረው የሚያገኙበት ለእነሱ ብቻ የኮታ ስርዓት ጭምር በመመሪያ ለማካተት እየሰራን እንገኛለን። እንደዚሁም ከሌሎች ተቋማት ጋር በጋራ ፕሮጀክት ተቀርፆ የሚሰሩ ስራዎች አሉ። ለምሳሌ ከቢል ኤንድ ሜሊንዳ ጌትስ ፋውንዴሽን ጋር በመሆን በጋራ ለመስራት በቅርቡ የመግባቢያ ስምምነት እንፈራረማን። በዚህም ሴት ተማሪዎች የበለጠ ተጠቃሚ ይሆናሉ ተብሎ ይታመናል።
አዲስ ዘመን፡– ሴት ተማሪዎችን ከጥቃትና ከሱስ ከመከላከል አንጻር እየተሰራ ስላለው ስራ ቢያስረዱን?
ዶክተር ፋሪስ፡– ጥቃት በማንኛውም ሁኔታ ተቀባይነት የለውም። በአጋጣሚ ይህ ሁኔታ ከተከሰተ ተጣርቶ ዩኒቨርስቲው የማያዳግም እርምጃ ይወስዳል። ከዚያ ባላፈ ግን የግቢውን ሁኔታ ለጥቃት የማያጋልጥና ምቹ ከማድረግ አንፃር የምንሰራቸው ስራዎች አሉ። ለምሳሌ ተማሪዎች ትንኮሳ ሊደርስባቸው የሚችለው ማደርያቸው አካባቢ በመሆኑ አካባቢውን ለብቻው የመከለልና የመጠበቅ ስራ ይሰራል። በዋናነት ግን ግንዛቤ ላይ መስራት ላይ ትኩረት ይደረጋል። ጠንካራ የሆነ ህብረተሰብና ለመብቱ የቆመ ተማሪ መፍጠር ላይ ሰፊ ስራ እየሰራን ነው። በዚህ ረገድ የሰራነው ስራ ውጤታማ ነው ማለት ይቻላል። እንዳውም የዩኒቨርስቲው የማኔጅመንት አካል እስኪመስሉ ድረስ ለመብታቸው ይከራከራሉ።
ከዚህም ባሻገር በሴቶች ላይ ያለውን አመለካከት ለመቀየር ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር በቅንጅት የምንሰራበት መርሃ ግብር አለ። ለምሳሌ የዩኒቨርሲቲ አጠቃላይ ምክር ቤት በዞኑ አስተዳደር እና በዩኒቨርስቲ ምክትል የቦርድ ሰብሳቢ የሚመራ ሲሆን በዚያ መድረክ ላይ ስለመማር ማስተማሩ ከተቋም ውጭ ያሉ ተግዳሮቶች ጭምር ይነሱና በጋራ ገምግመን የተለያየ ስራ የምንሰራበት ነው። ከአደንዛዥ ዕፅ ጋር በተያያዘ በዋናነት ከተቋም ውጭ ባሉ የመንግስት አካላት የሚሰሩ ናቸው። እኛ ችግሮችን በመለየት መፈታት ያለባቸውን ችግሮች ለከተማውና ለዞኑ አስተዳደር እያቀረብን እንዲፈቱ እናደርጋለን። በቅርቡም የከተማ አስተዳደሩ ጥናት አድርጎ ከዩኒቨርስቲው አቅራቢያ በድብቅ ሽሻ ቤቶችና መሰል ቦታዎችን ለይተው ዘመቻ አካሄዷል። በመሆኑም እንደዚህ አይነት ችግሮች የሚፈቱት ከህብረተሰቡና ከአካባቢው አስተዳደር ጋር በቅንጅት ሲሰራ ነው።
አዲስ ዘመን፡– በእርሶ እምነት ባለፉት 27 ዓመታት የጉራጌ ዞን ህብረተሰብ ፍትሃዊ ተጠቃሚ ነበር ማለት ይቻላል?
ዶክተር ፋሪስ፡– በእኔ እምነት የጉራጌ ማህበረሰብ ፍትሃዊ ተጠቃሚ ነበር ለማለት አልደፍርም። አስቀድሜ እንዳልኩሽ ይህ ማህበረሰብ ለረጅም አመታት የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እንኳን አልነበረውም። እኔ የግሌ ጥረት ባላደርግና አዲስ አበባ የሚያስጠጋኝ ሰው ባይኖረኝ ኖሮ የዛሬ ህልሜ ይመክን ነበር። ይህንን እንደምሳሌ ነው ያነሳሁልሽ እንጂ በዞኖ በርካታ ችግሮችና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ናቸው ያሉት። ከ1987 ዓ.ም በኋላ ዩኒቨርስቲዎች ሲቋቋሙም ጉራጌ ዞን የመጀመሪያውን እድል ሊያገኝ ይገባ ነበር የሚል እምነት ነበረኝ። የሚገርመው ከአስር ዓመት በኋላ በሌሎች አካባቢዎች መሰረት ድንጋይ ተጥሎ ስራ የጀመሩት ዩኒቨርስቲዎች ጋርም እኩል የእድሉ ተቋዳሽ መሆን አልቻለም። ህብረተሰባችን ይገባኛል የሚል ሰፊ ትግል አድርጓል። በዚህም ከፍተኛ የሆነ የሕዝብ ትግልና ጥያቄ ነው በ 2004 ዓ.ም መሰረተ ድንጋይ ተጥሎ የተቋቋመው።
ዩኒቨርሲቲን እንደአንድ ምሳሌ አነሳሁልሽ እንጂ የጉራጌ ሕዝብ አሁንም በበርካታ ችግር ውስጥ እየዳከረ የሚገኝ ማህበረሰብ ነው። በተለይም የመሰረተ ልማት ጥያቄዎች ለአመታት ያደሩ ጥያቄዎች ከመሆናቸውም ባሻገር ዛሬም ጭምር ያልተፈቱና ህዝብ ቅሬታ የሚያነሳባቸው ናቸው። በነገራችን ላይ ያደኩበት ይህ አካባቢ ለልማት ተባባሪ፣ ቅርብና ቀና የሆነ አስተሳሰብ ያለው በመሆኑ የመንግስትን እጅ ሳይጠብቅ ልማቶችን በራሱ መንገድ ነው የሚሰራው። ለምሳሌ ብጠቅስልሽ ማህበረሰቡ በራሱ የሰራቸውን መንገዶች ነው ላለፉት 30 ዓመታት ሲጠቀምባቸው የነበረው። ከዚያ ባለፈ ግን በመንግስት ከመንገድ ተደራሽነት አንፃር እስካሁን እዚህ ግባ የሚባል ስራ አልተሰራለትም። ሌሎችም ህብረተሰቡን የሚመጥኑ የልማት ስራዎች እንዲሁም ፈጠራ ላይ የሚያግዙ ነገሮችም አልተሰሩለትም። እንደእውነቱ ከሆነ በዚያ አካባቢ ላይ ትላልቅ የኢንዱስትሪ ዞኖች መኖር ነበረባቸው። ይህ ባለመሆኑ የአካባቢው ወጣት ዛሬም ስራ ፍለጋ ወደማያውቃቸው አካባቢዎች ይሰደዳል።
በሌላ በኩል ደግሞ የእዚህ አካባቢ ተወላጅ ሌሎች አካባቢዎችን እየሄደ ያለማል። በጠንካራ ነጋዴነቱም ይታወቃል። ነገር ግን የራሱን አካባቢ አላሳደገም። ወልቂጤ ላይ ለምሳሌ ባነሳልሽ አንድ ስብሰባ ለማካሄድ ብታስቢ እንግዶችን የምታሳርፊበት ሆቴል አታገኚም። እርግጥ አንዳንድ ለአካባቢያቸው ተቆርቋሪ የሆኑ ግለሰቦች የሰሩት ሆቴልና ሎጅ አለ። ይሁንና ካለው በቂ አይደለም ። ያ ለምን ሆነ? የሚለው ነገር ለእኔ አሁንም እንቆቅልሽ ይሆንብኛል። በአጠቃላይ ጉራጌ ከስነልቦናው፣ ከታታሪነቱ፣ ከአቃፊነቱ ከስራ ወዳድነቱ አንፃር አካባቢውን አላለማም፤ አላሳደገም የሚል እምነት አለኝ። ዛሬ ላይ ያለው ትውልድ ግን ከተደጋገፈና በጋራ ከሰራ ማሳደግ ይችላል። አሁን ያለው የለውጥ መንግስትም ይህ ማህበረሰብ በብዙ ነገር የተጎዳ በመሆኑ የተለየ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ባይ ነኝ። ይህ ማህበረሰብ ደግሞ እንደሚታወቀው በጣም ሰራ ወዳድ ነው፤ ያሉትን የልማትም ሆነ የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች በጣም በሰለጠነና ዲሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ ነው የሚያነሳው። ከዚህ አንፃር አይቶ መንግስት ማገዝና መደገፍ አለበት ብዬ አምናለሁ።
አዲስ ዘመን፡– ከአገራዊ ለውጡ ጋር ተያይዞ ሊፈታ ይገባል የሚሉት ካለ ያንሱልንና ውይይታችንን በዚሁ እናብቃ?
ዶክተር ፋሪስ፡– አገራዊ ለውጡ የመጣበት መንገድ ሁላችንም የምናውቀው ነው። ምንአልባት በተለያየ አጋጣሚ ለመሪዎቻችንም አስተያየት ሰጥተናል። የፖለቲካ ምህዳሩ ላይ ከቆየንበት የአፈና ስርዓት አንፃር መሪዎቻችን በከፍተኛ ተስፋና ቀንአዊነት በዝቶ ነው የተከፈተው። ነገር ግን አሁን ላይ ለውጡ ሊቀለበስ በማይችልበት ሁኔታ ወደፊት ሄዷል የሚል እምነት አለኝ። ይህ ሲባል ደግሞ በቀጣይ ሂደት ላይ መንገራገጮች አያጋጥሙም ማለት አይደለም። ከዚህ በኋላ የሚያጋጥሙትን ተግዳሮቶች እንዴት ነው መወጣት ያለብን የሚለውን ማሰብ ያስፈልጋል። በተለይም በህዝባችን ዘንድ ያሉትን ብዥታዎች ማጥራት ይገባል። ምክንያቱም ለውጡን ሊያደናቅፍ የሚፈልገው አካል ያሉትን ሁሉንም አማራጮች ይጠቀማል። እነዚህን አማራጮች በሚጠቀምበት ጊዜ በተለያዩ መንገዶች የሚተረጎምበት ሁኔታ ስላለ እሱን በጋራ አይቶ በጋራ መከላከል፤ ማስከበርም ያስፈልጋል። ምክንያቱም እዚህም እዚያም የሚነሱ ግጭቶች በአብዛኛው ከህብረተሰቡ ጋር እንደሚያያዙ ይነገራል፡ ነገር ግን አንዳንድ ቦታዎች ላይ የሚነሱት ግጭቶች የፖለቲካ ሊሂቃኑ እንጂ የህብረተሰቡ አለመሆናቸውን አይተናል። ለስራ በተለያዩ አካባቢዎች የሚሄዱ ዜጎች የእዛ አካባቢ ማህበረሰብ ጥቃት አንደደረሰባቸው ተደርጎ ይጠቀሳል። ይህም በህዝብ መካከል ዘላቂ የሆነ ቅራኔ እንዲፈጥር ያደርገዋል። በመሆኑም የግጭቱ ምንጭ ህዝቡ አለመሆኑን ለማስረዳት ተግባራዊ ስራ መስራት በተለይም ከመንግስት ይጠበቃል። ህዝብ መቼም ሊጣላ አንደማይችል፣ የተሳሰረ አንደሆነ ማስገንዘብ ይገባል። ለዚህ ደግሞ የሁላችን ተሳትፎ ያስፈልጋል። ለምናደርጋቸው ነገሮች ሁሉ ምክንያታዊ መሆን ይገባል። በሚዲያ የምናገኛቸውን መረጃዎች በአግባቡ መመዘንና ከምንጩ ማጣራት ይገባናል። ከስሜታዊነት በፀዳና ከመንጋ ፍርድ መውጣት ይገባል። አሁን በተፈጠረው የፖለቲካ ስነምህዳር ምርጫ ለማድረግ በዝግጅት ላይ ነው ያለነው። ከፊት ለፊታችን ያለው ምርጫ ፍፁም ዲሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲካሄድና አገራችንን ወደፊት ሊያስኬድ የሚችል እንዲሆን ሁላችንም መስራት አለብን።
አዲስ ዘመን፡– ለነበረን ቆይታ በአንባቢዎቼና በዝግጅት ክፍሉ ስም ከልብ አመሰግናለሁ።
ዶክተር ፋሪስ፡– እኔም አመሰግናለሁ።
አዲስ ዘመን የካቲት 27/2013