(ጌታቸው በለጠ – ዳግላስ ጴጥሮስ)
gechoseni@gmail.com
ከቀደምት የሀገራችን ድምጻውያን መካከል ነፍሰ ሄር ጥላሁን ገሠሠ እና ከዘመነኞቹ መካከል ደግሞ እጅጋየሁ ሽባባው (ጂጂ) ስለ ፍቅር ርሃብ ያዜሟቸው የጥበብ ሥራዎች በዘመን ተሻጋሪነት ሲታወሱ ከሚኖሩትና ብጤ ጭብጥ ካላቸው ተወዳጅ ዜማዎች መካከል በቀዳሚነት ቢጠቀሱ ይገባቸዋል ባይ ነኝ።
“ፍቅር እማ ሞልቷል ሆዴ መች ጎደለ፣
ፍቅራችን ብቻ ነው ያልተደላደለ።”
በማለት ጥላሁን የተጫወተው ዜማ በፍቅረኛነት ለሚያሞካሻት ለምናባዊ የእንስት ጾታ ብቻ ሳይሆን የገለጻው ክብደት ከውሱን መልእክት አድራሽነቱ ከፍ ብሎ ቢተረጎም ተገቢነት ይኖረዋል። ነፍስን ለማቆየት ወይንም ደካማ ሥጋን ለማበርታት የእህል ድርሻ ተስተካካይ እንደሌለው ሁሉ በሰዎች መካከል ሊኖር ለሚገባው የእርስ በእርስ መቀባበልና አብሮነትም ፍቅር ወሳኝ ብቻም ሳይሆን የግድ ይሉት ዓይነት ተፈጥሯዊ የስብእናችን መገለጫ ነው።
የሰው ልጅ ያለምግብ፣ ያለውሃና ያለ አየር ምን ያህል ቀናትና ሰዓታት ሊቆይ እንደሚችል የሚወስነው አቅሙና የብርታቱ ልክ ነው። ያለ ፍቅር ከሰው ተለይቼና ራሴን ሸሽጌ ልኑር ማለት ግን “ዓለማዊነትንና እኔነትን ገሎ” ለመንፈሳዊ የጽድቅ ትሩፋት “በፈጣሪ ፍቅር ተማርኮ” ካልጨከኑ በስተቀር በእለት ተእለት ኑሮ የሚሞከር አይደለም።
“ያለ ፍቅርም እኮ መኖር ይቻላል” የሚለውን ሃሳብ እንከራከርበት ቢባል እንኳን ሙግቱ የሚያመራው ወደ ሰብዓዊነት ሳይሆን ምናልባትም ወደ እንስሳነት ባህርይ ሊሆን ስለሚችል ረቺና ተረቺ ይኖረዋል ተብሎ አይገመትም። የጥላሁን ገሠሠ “በእህል ብቻ አልኖርም” የሚለው ሀረግ የሚያስታውሰውም ይሄንንው ተፈጥሯዊ እውነታ ነው።
ጀርመንን ከ1196-1250 ዓ.ም የመራው ዳግማዊ ፍሬዲሪክ በአስተዳደርና በጦር አመራር ችሎታው የላቀ አድናቆት ካተረፉት የዓለማችን መሪዎች አንዱ እንደነበር ይጠቀሳል። ይህ ንጉሥ የሚታወቀው በበሳል የአመራር ብቃቱና የጦረኝነት ብርታቱ ብቻም ሳይሆን በምርምር ወዳድነቱም ጭምር አንቱታን ያተረፈ እንደነበር ታሪኩ ይነግረናል። ምርምር ካደረገባቸው መስኮች አንዱ ይሄው የማፍቀር፣ የመፈቀርና የእርስ በእርስ ሰብዓዊ ግንኙነት ጉዳይ ነበር።
ጥንታዊያን ከሚሰኙት ከዕብራይስጥ፣ ከላቲን፣ ከግሪክኛ ከዐረብኛ ከሮማይስጥ እና ከመሳሰሉት ቋንቋዎች መካከል ሕጻናት በየትኛው ቋንቋ ቀድመው አፍ እንደሚፈቱ ለማወቅ ንጉሥ ፍሬዴሪክ ከፍተኛ ጉጉት አደረበት ይባላል። በመሆኑም ሕጻናቱ በእነዚህ ጥንታዊ ቋንቋዎች አፍ መፍታት ባይችሉ እንኳን የእናታቸውን ቋንቋ ቀድመው ሊናገሩ ይችሉ ይሆናል ብሎ በመገመት ገና ከተወለዱ የሳምንት ዕድሜ ያልሞላቸውን ጨቅላዎች ከመላ ሀገሪቱ ወደ ቤተ መንግሥቱ እንዲሰበሰቡ አደረገ።
ጡት የሚያጠቧቸውንና አስፈላጊውን እንክብካቤ የሚያደርጉላቸውን ሞግዚቶችንም በአግባቡ መደበላቸው። ሞግዚቶቹ ለሕጻናቱ አስፈላጊ ነገሮችን ከማቅረብ ውጭ በምንም ሁኔታ በንግግር፣ በቃል አልባ አካላዊ እንቅስቃሴም ሆነ በተግባር ጭምር ፍቅር እንዳያሳዩአቸው ከፍ ያለ ማስጠንቀቂያ ተሰጣቸው። የታዘዙትንም ፈጸሙ። ከተወሰኑ ጊዜያት በኋላ ግን ምርምሩ መክሸፉ ተረጋገጠ። ለምን ቢሉ የተሰበሰቡት ሕጻናት በሙሉ ሕይወታቸው ማለፉ ስለተረጋገጠ።
ጨቅላዎቹ ለምን ሊሞቱ ቻሉ? ይህንን ታሪክ ያስነበቡት መረጃዎች የሰጡት ምክንያት እንዲህ የሚል ነበር። “ሕጻናቱ ሞቱ። ምክንያቱም የሰው ልጅ ያለ ተግባራዊ ፍቅር፣ ያለ አፍቃሪና ተፈቃሪ መኖር ስለማይችል ብቻ ነው። (አለኝታ መጽሔት 1998 ፖፑሌሽን ሚዲያ ሴንተር)።
በዘርፈ ብዙ የፍቅር ርዕሰ ጉዳይ ዙሪያ ከጥላሁን ገሠሠ የበለጠ ያዜመ የሙዚቃ ሰው ስለመኖሩ እርግጠኛ አይደለሁም። ድምጻዊው የተጫወታቸው የፍቅር ግጥሞች የተቃራኒ ጾታዎችን ግንኙት የሚመለከቱ ብቻም ሳይሆኑ የእውነተኛ ፍቅርን ምንነት የሚያጠይቁ ዓይነት የፍልስፍና ሃሳቦች የታጨቁባቸው ጭምር ናቸው። ያውም በበርካታ ቁጥር። ስለ ፍቅር ምንነት ከሞገተባቸው ጥያቄዎች መካከል አንዱ እንዲህ የሚል ይዘት አለው፤
ጥያቄ እስቲ ላቅርብ እንዲያው ለነገሩ፣
በየት በኩል ይሆን የፍቅር ሀገሩ?
በይፋ ያየው ሰው ምናልባት እንዳለ፣
ፍቅር ምን እንደሆን ቢያስረዳኝ ምን አለ።
ባይገባኝ ነውና እኔ የጠየቅኋችሁ፣
ፍቅር ምን እንደሆን አስረዱኝ እባካችሁ።
የጥላሁን ገሠሠን መሠረታዊ “የፍቅር ድንጋጌን አፋልጉኝ” ጭንቀት ለጊዜው በእንጥልጥል እንለፈውና ወደ እጅጋዬ ሽባባው ጥልቅ ምልከታ እናቅና።
እጅጋየሁ (ጂጂም) እንዲሁ በተስረቅራቂ ድምጽዋ “እኔን የራበኝ ፍቅር ነው!” እያለች እህህታን በማከል አድማጮቿን እየሞገተች የምታንጎራጉረው ዜማ ስሜትንና ውስጥን ሰርስሮ የመግባት ብርታቱ ይህ ቀረህ የሚባል አይደለም። የጎጃም ገበሬ ወደ ወለጋ ተሻግሮ ምርቱን ካልሸጠ፣ የምሥራቁ ወደ ሰሜን አቅንቶ በመተሳሰብ ካልተገበያየ፣ የወዲያኛው ከወዲህኛው የማዶ ወገኑ ጋር በጋብቻ እየተጣመረ ካልተዋሃደ “ፍቅር ወዴት ወዴት አለ!?” እያለች ትሞግታለች። ለጥላሁንም ሆነ ለጂጂ ሞጋች ጥያቄዎች “ትክክለኛውን መልስ እነሆ!” ብሎ ለመገላገል አቅምንም ሆነ እውቀትን መፈታተኑ አይቀሬ ስለሚሆን የማይሞከረውን ለመሞከር አይሞከርም።
የድፍረትና የጅምላ ድንጋጌ እንስጥ ከተባለ ግን ፍቅር ለአብሮነት የሚቀርብ የዕለት እንጀራ መሆኑን አስረግጦ በመናገር “መገላገል” ይቻላል። የሐዋርያውን የጳውሎስ ገለጻ እንጠቀም ካልንም “እምነት፣ ተስፋ፣ ፍቅር እነዚህ ሦስቱ ጸንተው ይኖራሉ፤ ከእነዚህም የሚበልጠው ፍቅር ነው።” 1ኛ ቆሮንቶስ ምዕራፍ 13 ሙሉው ክፍል ይነበብ።
እውነት ነው ፍቅር እንደ እህል ውሃ ይርባል፤ ይጠማልም። ፍቅርና ርህራሄን ከጓዳው የሚያስወጣ ቤተሰብ፤ መደማመጥ፣ መቀባበልና መከባበርን ከግዛቱ የሚያባርር ሕዝብና መንግሥት ውጤቱ ምን ሊሆን እንደሚችል ከእኛ ወዲያ የሚመሰክር ያለ አይመስለኝም። “እርቅ ደም ያድርቅ”፣ “ለእርቅ የከፋ ምግባሩ የጠፋ” ወዘተ. የሚሉት የሥነ ቃል ውርሶቻችን የተመሠረቱት ይሄንን እውነታ ለመግለጽ በማሰብ ይመስላል።
የፍቅር ማዕዳችን ተሟጦ ማኅበራዊ “አወያችን” ክው ብሎ እየደነገጠ እንዳለ በብዙ ማስረጃዎች ማመላከት ይቻላል። ፍቅር በስፋት “የሚሰበከው” ከማለት ይልቅ የሚጎርፈው ከቤተ እምነቶች ምስባክ ላይ መሆኑ ይታወቃል። ሰዎች እንደየእምነታቸው ወደ ቤተ ጸሎታቸው የሚተሙት የፈጣሪን ፍቅርና ርህራሄ ለመማጠን ብቻም አይደለም።
ለቤተሰብ አባላት፣ ለወዳጅ፣ ለሕዝብና ለሀገር ለመጸለይ ጭምር ነው። ምንም ስም ይሰጠው ምን የእያንዳንዱ እምነት ተከታይ ምእመን “በፈጣሪ ደጆች” እየተጋፋ በመንፈሱ የሚቃትተው ለራሱ ብቻም ሳይሆን ከራሱ ያለፈ በፍቅር የሚዘረጋውን የአምላኩን እጅና ልብ ለመሻት ነው። በአጭሩ መልከ ብዙ የፍቅር ርሃቡን ለማስታገስ ነው ብንልም ያስማማናል።
መሠረታዊው እውነታ ይህን ይምሰል እንጂ የየቤተ እምነቶቹ ዐውደ ምህረት የፍቅር መፍለቂያ ከመሆን ይልቅ ለጠብና ለሙግት መመከቻ ሲሆኑ ማስተዋል እየተለመደ ብቻም ሳይሆን ባህል ወደ መሆን ደረጃ ተሸጋግሮ መእመናን ግራ በመጋባት ሥጋት ላይ ከወደቁ ውሎ አድሯል። የተከበሩ የሃይማኖት አባቶች ምክር አብዛኛውን ጊዜ “በጆሮ ዳባ ልበስ” ንቀት ሲገፈተር እያስተዋልን ነው። የሀገር ሽማግሌዎችን ክብር “እርቃኑን ለማስቀረት” የደፋሮች ሙከራ አስደንጋጭ እየሆነብን አንገት የደፋንባቸውን አጋጣሚዎችም እንዲሁ በአለፍ አገደም ውሏችን እየተመለከትን ነው። የአገልጋዩና ተገልጋዩ መነቃቀፍ ዳርቻው ሰፍቶ ሁሉንም አካቷል። ስለዚህ እንደ ሀገር የፍቅር ርሃብተኛ ሆነን ብንገረጣ እንደምን ግድ አይሆንም!?
የሕዝብ ለሕዝብ የፍቅር መቋደሻ ማዕዳችንን ጦም አስውለው ጦም የሚያሳድሩት የፖለቲካው ሠፈርተኞች “ምንዱባን” ጉዳይም ቸል የሚባል አይደለም። ተፋቅሮና ተስማምቶ፣ ተዋዶና ተከባብሮ በኖረ “ምስኪን ሕዝብ መሃል” በእንክርዳድ የተጠመቀ የሴራ ጉሽ የዋሁን ወገን እየጋቱ የሚያጋድሉትና የሚያፈናቅሉት እነዚሁ “የፖለቲካ ቫይረስ” የተጠናወታቸው የዘመናችን ጉዶች ናቸው። የሃሳብ ልዕልና ከፍታ ላይ በደረሰበት በዚህ በ21ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ላይ የዝቅዝቅ ቆመው ለድንክዬ ሃሳባቸው ምርኮኛ በመሆን የእርስ በእርስ መጠፋፋት ሲሰብኩ ማስተዋል እንግዳችን አይደለም።
ሰብዓዊ ፍጡር እንዴት በወገኑ ሞት ይሳለቃል? እንደምንስ እንደ ወራሪ ሠራዊት ከነፍስ እስከ ሃብት እያወደመ ያቅራራል። ፍቅር ርቦናል የምንለው እነዚህን መሰል “የዘመን ጉዶች” የአብሮነት ማዕዳችንን እየደፉ ሲሳለቁብን ስለምናስተውል ነው። ፖለቲከኞችን ጫን ብሎ የሚያስታግስ ምድራዊ ሕግም ሆነ ሰማያዊ ኃይል ለጊዜው መንበሩ ላይ ማግኘት የተሳነን ለምን ይሆን? መልስም መላሽም ለማግኘት አዳጋች እንደሚሆን አልጠፋኝም። ስለዚህ የፍቅር ርሃባችን ጠንቶብን በጠኔ ልንሰቃይ ግድ ሆኖብናል።
ዘመን ተሻጋሪ ካልኩት ከጥላሁን የፍቅር ዜማ ውስጥ “እህልማ ሞልቷል ሆዴ መች ጎደለ” የሚለው ስንኝ ዘመናችንን የማይመጥን አገላለጽ መሆኑን በእግረ-ብዕር ጠቁሞ ማለፉ ግድ ይላል። እርግጥ ነው እህል ከሀገራችን ማሳ አልጠፋም። ምድሪቱም በረከቷን አልነፈገችንም። ችግሩ ስግብግብነት እንደ ባህል ተጣብቶን የንግድ ሲስተሙ በአልጠግብ ባዮች ቁጥጥር ሥር ውሎ ከመንበርከኩ የተነሳ የዕለት እንጀራ ለማግኘት ብርቅም፣ ድንቅም፣ ቅንጦትም ሆኖብናል። እህል ሞልቶ ተርበናል። ሸቀጥ ተትረፍርፎ ጦም እያደርን ነው። ምክንያቱም ቀድሞ ፍቅር ሞቶ፤ መተሳሰብ ጠውልጎ እኩያን የርሃባችን ምክንያት ስለሆኑ።
የሀገሪቱ የንግድ ፍሰት በየደረጃው “በጨካኝ ባለድርሻ” አካላት እየታነቀ መተንፈሻ ስላጣ የሕዝቡ ኑሮ “ከእጅ ወደ አፍ” ከምንለው ቅንጡ አባባል ወደ “ጦም አደርነት” ከተሸጋገረ ውሎ አድሯል። የመንግሥት የአስፈጻሚነት ጉልበት በአወቅሁሽ ናቅሁሽ ቱሻ ስለተተበተበም ቢጮኹ ሰሚ፤ ቢያለቀሱም እንባ የሚያብስ ርሁሩህ ማግኘት እንደ ሰማይ እርቆናል። ስለዚህም የፍቅር ርሃብ አመንምኖ ስብእናችንን ወደ አልፈለግነው አቅጣጫ እየመራ ወደማንወጣው የገደል አፋፍ አቃርቦናል። ሕግ እየተጣሰ ጉልበተኛ መበርከቱ፣ ፍትሕ ጠፍቶ ተበዳይ ማልቀሱ፣ ሙስና ተስፋፍቶ እውነት መደፍጠጡ ፍቅርና መተሳሰብ እየሞተብን ስላለ ነው።
“ፍቅር፣ መቀባበል፣ መከባበር፣ መደጋገፍ፣ መተጋገዝ” የሚሉት ማኅበራዊ ነባር እሴቶቻችን ከመሃል ተገፍትረው ወደ ዳር የተጣሉ ይመስላል። ፍቅር ፍርሃትን አውጥቶ ይጥላል የሚለው እውነት ተሸርሽሮና የተገላቢጦሽ አግድም ሄዶ ፍርሃት ፍቅርን አውጥቶ ያሽቀነጠረ እስኪመስል ድረስ ተራቁተናል። መዳረሻችን የትና እንዴት ሊሆን እንደሚችል ሁሉ ግራ ተጋብተን በቁዘማ ውስጥ ለመኖር ተገደናል። ፍቅር እርቦናል፣ ፍቅር ጠምቶናል። በጥላሁን ዜማ የከፈትነውን በር በራሱ ዜማ መልሰን ገርበብ ካላደረግን በስተቀር እህህታችንን እንቀጥልበት ካልን ማቆሚያ የለንም።
“ፍቅር ከእኛ እንዳይለየን፣ እንዲቃናልን ኑሯችን፣
መጨቃጨቅ ይወገድና ሰላም ይሁን ለሁላችን።
ኑሮ ለሰው ልጆች በእውነት ቀላል ስላልሆነ ዋዛ፣
በሆነ ባልሆነው ይቅር ንዝንዛችን አይብዛ።
በየተሰማራበት የሰው ልጅ እንደ ሙያው፣
ነጋዴውም ወደ ንግዱ ገበሬውም ወደ እርሻው።”
ለራበን ፍቅር ማስታገሻውና መፈወሻው መከባበር ነው፤ መደማመጥ። ጠቢቡ እንዳሉት “እንደ ዘላለማዊ ነዋሪ ተግቶ መስራት፤ ሞት ከፊታችን እንዳለም አዘውትሮ ማሰብ” ይኼው ነው። ሰላም ይሁን!
አዲስ ዘመን የካቲት 27/2013