እፀገነት አክሊሉ
የጁንታውን ሴራ ተከትሎ በተፈጠረው የሕግ ማስከበር ዘመቻ በትግራይ ከልል በርካታ ጉዳቶች ደርሰዋል። ህብረተሰቡም ለከፍተኛ ችግርን እንግልት መዳረጉም እየተገለጸ ሲሆን ከዚህ ጉዳቱ ያገግም ዘንድም በመንግሥትና በሕዝቡ እንዲሁም በሌሎች አካላት ከፍተኛ የሆነ እገዛም እየተደረገ ነው። እኛም በተለይም የሰሜን ምዕራብ ዞን ያለውን ሁኔታ አስመልክተን በትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር የሰሜን ምዕራብ ዞን የሽሬ እንዳስላሴ ምክትል አስተዳዳሪ ከሆኑት ከአቶ ሙሉብርሃን ሀይለ ጋር ቆይታ አድርገናል፤ መልካም ንባብ።
አዲስ ዘመን ፦ በመጀመሪያ አቶ ሙሉብርሃን ማናቸው ለሚሉ አንባቢዎቻችን የትውልድ ቦታዎን እንዲሁም ወደ ፖለቲካው መቼ እንደተቀላቀሉ ቢነግሩን ?
አቶ ሙሉብርሃን ፦ የተወለድኩት በትግራይ ክልል ሽሬ ከተማ ዞን በሚባል አካባቢ ሲሆን ወደ ፖለቲካው የተቀላቀልኩትም በ1997 ዓም ነው። በወቅቱ ከቅንጅት ለአንድነት ፓርቲ መፈጠር ጋር ተያይዞ የአገሪቱ የፖለቲካ ሁኔታ ደስ የሚል ነበር።
እኔም አማራ ክልል ላይ የነበርኩ ሲሆን ይካሄዱ የነበሩ የፖለቲካ ክርክሮችም እጅግ ሳቢ በመሆናቸው በዛው ፓርቲ በመቀላቀል ወደ ፖለቲካው ሂደት ገብቻለሁ። በወቅቱ ተካሂዶ የነበረው ምርጫ ገና ከጅምሩ ጥሩ ድባብ የታየበት ቢሆን አጨራረሱ ግን ሳያምር ገዢው ፓርቲም በማጭበርበሩ ምክንያት ያላስፈላጊ ችግሮች ውስጥ ገብተን እንደነበርም የሚታወስ ነው። በወቅቱ ታፍሰው እስር ቤት የገቡ የተገደሉ ብቻ ብዙ ስቃይና መከራን ያስተናገዱ ብዙ ወጣቶች ነበሩ። እኔም ከዛን ጊዜ ጀምሮ ፖለቲካውን ተቀላቀልኩ።
በ 2001 ዓም የኢትዮጵያ ራዕይ ፓርቲን በመመስረት ስንቀሳቀስ ከቆየሁ በኋላ ለውጡን ተከትሎም የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ሲመሰረት እኔም ወደ ፓርቲው በመግባት ስራ አስፈጻሚና የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ በመሆን አገልግያለሁ።
አሁን ደግሞ የጁንታው ቡድን የሰነዘረውን ጥቃት ተከትሎ ከተካሄደው የሕግ ማስከበር ዘመቻ በኋላ በትግራይ ክልል በተቋቋመው ጊዜያዊ አስተዳደር ውስጥ የሰሜን ምዕራብ ዞን የሽሬ እንዳስላሴ ከተማ ምክትል አስተዳዳሪ በመሆን እያገለገልኩ እገኛለሁ።
አዲስ ዘመን ፦ እርስዎ አሁን እየመሩት ባለው አካባቢ ላይ የተካሄደው የሕግ ማስከበር ዘመቻ ምን ይመስላል ምናልባት በሰውና በንብረት ላይ የደረሰው ጉዳት እንዴት ይገለጻል?
አቶ ሙሉብርሃን ፦ የሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል በግጭት ውስጥ የቆየ ነው፤ በተለይም አሁን ላይ የተካሄደው ጦርነት አስፈላጊም አልነበረም፤ የኢትዮጵያ መንግሥትም ይሁን ሕዝቡ ይህንን ሁኔታ በፍጹም አይፈልጉትም ነበር፤ ይህንንም ግጭት የምንሸከምበት ትከሻም አልነበረንም፤ ለነገሩ እኛ እንኳን እንደ ፓርቲ ህወሓት በዚህ ሁኔታ ወደ ጦርነት ሊያስገባን እንደሚችል ግምቶች ስለነበሩን ስጋቶቻችንንም በተለያዩ መንገዶች ስንገልጽ ፀረ ጦርነት መግለጫዎችንም ስናወጣ ነበር ። በመሆኑም ህወሓት ሕዝቡን ወደ ግጭት ሊያስገባው እንደሆነ ነገር ግን ግጭቱ ለአገር በተለይም ደግም ለክልሉ አስፈላጊ ያልሆነ ብሎም ጎጂ መሆኑን እንነጋገር ነበር።
ህወሓት በተለይም ፖለቲካዊ ኪሳራ አጋጥሞት ከመሐል አገር ወጥቶ መቀሌ ከመሸገ በኋላ የተለያዩ ሴራዎችን በመሸረብ እንዲሁም የማያቋርጡ የፕሮፓጋንዳ ሥራዎችን ሲሰራ ነበር። ይህንንም ተከትሎ ግጭቱ አስፈላጊ እንዳልሆነና ችግሮችን በመነጋገር በድርድር መፍታት ተገቢ እንደሆነ ገልጸናል ነገር ግን አልተሳካም።
ህወሓት በተፈጥሮው በድርድር በሽምግልና የማያምን ነው። ለዚህ ማሳያው ደግሞ እስከ አሁን የገጠሙትን ችግሮች በሙሉ በጉልበት እየፈታ የመጣ ፓርቲ መሆኑ ነው። በመሆኑም አሁንም ይህ አመሉ መጥቶበት የገጠመውን የመሸነፍ ስሜት በጉልበት ለመፍታት ብሎ በሰሜን እዝ ላይ ያንን ጥቃት ፈጸመ ።
አዲስ ዘመን ፦ እንደ ፖለቲከኛ እንደ ሰውም በሰሜን እዝ ላይ የተቃጣውን ጥቃት እንዴት ይገልጹታል?
አቶ ሙሉብርሃን ፦ ከ20 ዓመት በላይ በትግራይ ክልል ተቀምጦ ዳር ድንበር ሲጠብቅ ከደሞዙ ቀንሶ ትምህርት ቤት ክሊኒክ ሲሰራ የተራቡትን ሲመግብ የኖረ ከሕዝቡ ጋር የተጋባ የተዋለደ በእለቱም እህል ሲያጭድና አንበጣ ሲያባርር በዋለ ሠራዊት ላይ በተኛበት ማረድ ከባድ ወንጀል ህሊናም ሊቀበለው የማይችል ግፍ ነው። ይህንን እኩይ ተግባራቸውንም የትግራይ ሕዝብ አያውቅም አላማከሩትም።
በመሰረቱ ይህንን ያደረጉትም ለትግራይ ሕዝብ አስበውም አይደለም ፤ ለራሳቸው ምኞትና ለስልጣን ጥማታቸው ነው ። ይህንን ካደረጉ በኋላም የሰሜን እዝ ከጎናችን ነው በማለት የትግራይን መላው የአገሪቱ ሕዝብ እንዲሁም ዓለምንም ዋሽተዋል ።
ማዕከላዊ መንግሥቱም ሕገ ወጥ በሕዝብ ያልተመረጠ እንደሆነም ሲያወሩ ቆይተዋል። ከዚህ ጎን ለጎንም እነሱ ያካሄዱትን ሕገ ወጥ ምርጫ ህጋዊ በማስመሰል ዓላማቸውን ለማሳካት ከፍተኛ ጥረትም አድርገዋል።
ይህንን የሥልጣን ጥማቸውን ለማስታገስ አይነተኛ ምርጫ ያደረጉት ማዕከላዊ መንግሥቱን በማዳከም እንደሆነ በመገንዘብም ይህንን ዓይነት አረመኔያዊ ድርጊት ፈጸሙ።
ለጦርነት መጀመሪያ እንዲሆነውም መከላከያው የአገር ድንበርን ሲጠብቅበት የነበረውን አጥር አፈረሱ። በዚህ ምክንያት ደግሞ የውስጥም የውጪም ጠላት እንደፈለገ ወደ አገሪቱ ገባ ። ከዚህ ጋርም ተያይዞ የተከሰተው ጦርነት እጅግ አስከፊና ከባድም ነበር ።
አዲስ ዘመን ፦ ጦርነቱ በትግራይ ክልል ላይ ያስከተለውን ውድመት እንዴት ይገልጹታል ?
አቶ ሙሉብርሃን ፦ ጦርነቱ በሮኬት በቢኤም በመድፍና በታንክ የታገዘ ዘመናዊ ወታደሮች ያሉበት ነው፤ ይህንንም በትግራይ ክልል ላይ ከፍተኛ የሆነ ውድመት አስከትሏል ። ሥርዓት አልበኝነትም ተፈጥሯል።
በነገራችን ላይ ይህ የጁንታ ቡድን ሕዝቡን በተለያየ ጫፍ ላይ ወስዶት ስለነበር እውነታውን ማስረዳትም ከባድ ነበር ። እነሱ የሥልጣን እድሜያቸውን ለማራዘም እያደረጉ ያሉት ጦርነት ሆኖ ሳለ ሕዝባዊ እንደሆነ የማስመሰል እንዲሁም ትግራይን ለማንበርከክና በማንነቱ ለማጥፋት እንደሆነ አድርጎ በመናገር ሕዝቡን ለጦርነት የመቀስቀስ ሥራም ተሰርቷል። ከዚህ ጋር ተያይዞም በርካታ ሕዝብ ወደጫካ ገብቶ ነበር ፤ ከዚህም ሌላ በክልል በርካታ ንብረቶች ቤቶች ወድመዋል፣ ተሰርቀዋል፣ የመንግሥት ተቋማት እንዳልነበሩ ሆነዋል ፤ በዚህ መካከልም ነው እንግዲህ እኔ ወደሽሬ ከተማ የሄድኩት።
አዲስ ዘመን ፦ በተለይም እርስዎ ከሁለት ወራት በፊት ጀምሮ ወደ አካባቢው በመሄድ በከፍተኛ ኃላፊነት ላይ ነዎትና በክልሉ በንብረት በሰው በመሰረተ ልማት ላይ የደረሰው ጉዳት እንዴት ይገልጹታል? በወሬ ከሚሰማው አንጻርስ ጉዳቱ ምን ያህል ነው?
አቶ ሙሉብርሃን ፦ አንደኛ ወቅቱ የመኸር ጊዜ ነበር፤ የክልሉ ሕዝብ 85 በመቶ የሚሆነው በግብርና ስራ የሚተዳደር እንደመሆኑ የዘራውን እህል አልሰበሰበም ። በዚህ ምክንያት ደግሞ በጦርነቱ ሰብሎች ተቃጥለዋል ። ይህም ብቻ ሳይሆን ወደ ጦርነቱ ከገባ በኋላም ጥቃቱን
መቋቋም ሲያቅተውና እንደሚወድቅ ሲያውቅ ሕዝቡን ለአደጋ ነው አጋልጦ የሰጠው።
አንደኛ የታሰሩ ሌቦችን ፈትቶ ሕዝቡን እንዲዘረፍ አድርጓል፤ ይህም ብቻ አይደለም እድሜያቸው ትንሽ የሆኑና ወደ ሥራ ያልገቡ በየአካባቢው ያሉ ወጣቶችን በየስታዲየሙ በመጥራት በሰሜን እዝ ውስጥ የነበረውን ትጥቅ ለወጣቱ ነው ያስታጠቁት።
በዚህ መልኩ ምንም እንኳን ጦርነቱ ጥቂት በሆኑና ሕገ መንግስትዊ ስርዓቱን በናዱ አካላት መካከል የሚደረግ ቢሆንም የሕዝብ ለማስመሰል በከፍተኛ ሁኔታ ስራዎችን ሰርተዋል። ከዚህ ጋር ተያይዞም በርካታ ውድመቶች ደርሰዋል፤ የሰው ሕይወትም ጠፍቷል። ለዚህ ሁሉ ኪሳራ ግን ተጠያቂው የጁንታው ኃይል ነው። ሕዝቡም አሁን ላይ በዚህ መልኩ እየተረዳው ነው።
በጠቅላላው ግን ጦርነቱ መፍትሔ ካለመሆኑም በላይ አስፈላጊም አልነበረም ፤ ነገር ግን በሕዝቡ ውስጥ ከፍተኛ የሆነ ብዥታ ነበር፣ አሁን እርሱንም የማጥራት ስራ እየተሰራ በመሆኑ ሚዛኑንም ማስተካከል ችለናል።
አዲስ ዘመን ፦ በዞኑ ምን ያህል ወረዳዎች አሉ? አሁን በሁሉም ወረዳዎች ጊዜያዊ አስተዳደር ተቋቁሟል ማለት ይቻላል?
አቶ ሙሉብርሃን ፦ የገጠር ወረዳዎችና የከተማ አስተዳደር አሉ ። የገጠሮቹ ጽሕፈት ቤታቸው በከተማው ነው፤ ለምሳሌ ሽሬ ከተማን ብንወስድ አንድ ከተማ አለ፤ ታህታይ ቆራሮ የሚባል ደግሞ ዙሪያው ላይ አለ፤ በተመሳሳይ ሌሎችም አሉ፣ አሁን ላይ ግን በሁሉም ጊዜያዊ አስተዳደሩ ተደራጅቷል።
በነገራችን ላይ ውጊያው ሲጀመር ሕዝቡ በጣም ተደናግሮ ነበር። በዚህም የሚመለከተውም የማይመለከተውም የሆቴል ጥበቃ ሳይቀር መሳሪያ ስለታጠቀ ብቻ እገደላለሁ በሚል ስጋት ዘሎ ጫካ ነው የገባው ። በዚህም ምክንያት አብዛኛው አደረጃጀት የመንግስት ተቋማት ዳኛ አቃቤ ሕግ የፖሊስ ሠራዊት ሳይቀር በጠቅላላው ሁሉም ነገር ፈርሶ ነበር ።
ይህንን ሁኔታ የፈጠረው ደግሞ ለዘመናት ሲወራ የነበረው የትግራይ ሕዝብና ህወሓት አንድ ነው የሚለው የተዛባ አገላለጽ አንዱ ሲሆን ሌላው ደግሞ መንግሥትና ፓርቲም የተለያዩ አለመሆናቸው ነው። ፓርቲው ሲጠፋ እነዚህ ተቋማት ሁሉ አብረው ነው የጠፉት፤ በመሆኑም እነዚህን አስተካክሎና እንደገና አዋቅሮ ለሕዝቡ አገልግሎት መስጠት በጣም ፈታኝ ነው የነበረው።
ነገር ግን እኛ ወደአካባቢው እንደደረስን ያደረግነው የሃይማኖት አባቶችና የአገር ሽማግሌዎች በመሰብሰብና በማወያየት ምን እናድርግ የሚል ጥያቄያችንን ነው የሰነዘርነው፤ በነገራችን ላይ በዚህ ስብሰባ የተረዳነው ሕዝቡ በጣም የነቃ የሚሰማው ካገኘም ብዙ ሃሳብ ያለው መሆኑን ነው ። ከዚህ አንጻርም ለእኛ አቅጣጫን ነው ያሳዩን፣ አመራሩንም እራሳቸው እንዲመርጡ ነው ያደረግነው ። በቶሎም ወረዳዎችን በማደራጀት ከዛም እነሱ ቀበሌዎችን እንዲያደራጁ በማድረግ ለሕዝቡ እርዳታም ሌሎች አገልግሎቶችንም እንዲያገኝ አስችለናል።
አንዳንድ የመንገድ የእህል አቅርቦት እጥረቶች የነበሩ ቢሆንም እነዚህን ችግሮች ከስር ከስር ለመፍታት ከፍተኛ ጥረት ከመደረጉም በላይ በዞኑ ላሉ የመንግስት ሰራተኞችም የሁለት ወር ደመወዝ ለመክፈል ተችሏል ።
በሌላ በኩልም በሚሰሙት ነገር ተደናግረው ጫካ የገቡትንም በአገር ሽማግሌዎችና በሃይማኖት አባቶች አማካይነት እንዲመለሱ ለማድረግ ተችሏል። ሚሊሻዎችንም ትጥቃቸውን ለመንግሥት እንዲያስረክቡና አስፈላጊ ከሆነ በኋላ መንግሥት እንደሚያስታጥቃቸው በመንገር ወደ ቤተሰቦቻቸው እንዲመለሱ፤ አይ ውጊያው አስፈላጊና ፍትሐዊ ነው ያሉ ግን አካባቢውን ለቅቀው እንዲወጡ በሽማግሌዎች ተገልጾላቸዋል ። በዚህም የሚገቡ ገቡ አንገባም ያሉም በዛው ሄዱ።
አዲስ ዘመን ፦ በዞንና በወረዳ ደረጃ ጊዜያዊ አስተዳደሮቹን ከመሰየም ባሻገር በእነዚህ መዋቅሮች አማካይነት ለሕዝቡ እርዳታዎች እንዲደርሱ በማድረግ በኩል የተሄደበት ርቀት ምን ያህል ነው?
አቶ ሙሉብርሃን ፦ አሁን በሕዝቡ ላይ የደረሰው ጉዳት ከፍተኛ ነው ። መንግስት ደግሞ ህይወት የማዳን ስራን እየሰራ ነው ። በአካባቢው በጣም ብዙ የተራበ ሕዝብ ነበር፤ ሀብታሙም ደሃውም የመንግስት ሰራተኛውም ሥራ የሌለውም ሁሉም ተረጂ ነው የሆነው፤ ከዚህ ቀደምም ቢሆን በክልሉ በርካታ በምጽዋት የሚኖሩ ሰዎች የነበሩበት ነው፤ ብዙዎች በቀን ስራ የሚተዳደሩ ሴት እህቶቻችን የጀበና ቡና እያፈሉ ኑሯቸውን የሚገፉ ከመሆናቸው ጋር በተያያዘ አንድ ቀን ካልሰሩ በሁለተኛው ቀን ለመመገብ የሚከብዳቸው ናቸው ። ገንዘብ ያላቸውም ቢሆኑ የባንክ አገልግሎት በመቋረጡ ምክንያት ገንዘባቸውን አውጥተው ባለመዘጋጀታቸው ሁሉም ችግር ውስጥ ነው የገባው።
ከዚህ አንጻር በዞናችን የተራበው ሕዝብ ቁጥር በጣም ከፍተኛ ነበር፤ በሌላ በኩል ደግሞ ምዕራብ ከሚባለው ወልቃይትና ራያ አካባቢዎች በርካታ ዜጎች ሸሽተው ወደ ወረዳው መጥተውም ስለነበር ለዚህ ሕዝብ የመጡትን እህሎች በተቻለ መጠን ለማከፋፈልና በረሃብ ሕይወቱ የሚያልፍ ሰው እንዳይኖር ማድረግ ችለናል ፤ የተሟላ ባይሆንም በረሃብ የሚሞት አልነበረም።
ከዚህ በኋላ ገበያዎች ፣ወረዳን ከወረዳ የሚያገናኙ መንገዶች እንዲከፈቱ በማድረግ ገበያው እንዲረጋጋም የተቻለንን ጥረት በማድረግና መንግሥትም ተቋርጦ የነበረውን የኤሌክትሪክ ኃይል እንዲያገናኝልን በማድረግ ባንኮችም ተመልሰው ተዘጉ እንጂ በተለይም ዞኑ ወደቀድሞ ሁኔታው ተመልሶ ነበር ለማለት ይቻላል።
አዲስ ዘመን፦ አሁን ላይ በተጨባጭ በዞኑ ያሉ የንግድ የአገልግሎት መስጫ ተቋማት የትራንስፖርት የፍትሕ ተቋማት እንዲሁም የጤና ኬላዎች አገልግሎት ምን ይመስላል ? ወደ ስራ ገብተዋል ወይስ ገና ናቸው?
አቶ ሙሉብርሃን ፦ እዚህ ላይ ለሁለት ነገሮች ትኩረት ሰጥተን ነው የሰራነው። አንዱ ሕዝቡ በረሃብ እንዳይሞት ማድረግ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ በዞኑ የተንሰራፋውን ሥርዓት አልበኝነት በቁጥጥር ስር ማዋል ነው። በዚህም ከኮማንድ ፖስቱ በተጨማሪ ሕዝባዊ ፖሊስና ከህብረተሰቡ የተውጣጡ የጸጥታ አካላት መኖር አለባቸው በሚል ከዞኑ መቶ የሚሆኑ ወጣቶችን በመመልመል ዩኒፎርም አስለብሰንና ባጅ እንዲያንጠለጥሉ አድርገን ከመከላከያ ጎን በመሆን ሌሊት ሌሊት ከተማዋን እንዲጠብቁ አድርገናል ። ይህም ውጤታማ ነበር ።
አሁን ላይ ግን ፖሊሶችም ዳኞችና አቃቤያነ ሕግም ደመወዝ የተከፈላቸው በመሆኑ ከዚህ በኋላ ሕዝባዊ አገልግሎታቸውን እንዲሰጡ ተነግሯቸዋል። በአጭር ጊዜ ውስጥም ወንጀል የሰሩ ሰዎች የሚያዙበትና ለፍርድ የሚቀርቡበት ሁኔታም ይመቻቻል።
አዲስ ዘመን፦ በተለይም እርስዎ በሚያስተ ዳድሩት ዞን ሕግ ማስከበር ዘመቻውን ተከትሎ በመሰረተ ልማቶች ላይ የደረሰው ጉዳት ምን ይመስላል? አሁንም ምን ያህሉ ተጠግነው ለአገልግሎት በቅተዋል?
አቶ ሙሉብርሃን ፦ በእኛ ዞን አየር ማረፊያውም የተለያዩ ድልድዮችም ጉዳት አልደረሰባቸውም ፤ከዚህ የተነሳም አገልግሎት እየሰጡ ነው። እንደ ኤሌክትሪክ ኃይል ቴሌኮምና መሰል አገልግሎቶችም ምንም እንኳን ለጉዳት ተዳርገው የነበረ ቢሆንም አሁን ላይ አስፈላጊው ጥገና ተደርጎላቸው ወደ ሥራ ገብተዋል።
ነገር ግን በዞኑ የነበሩ ተቋማት ከፍተኛ የሆነ ውድመት አስተናግደዋል። ለምሳሌ ትምህርት ቤቶች ከፍተኛ ጉዳት ደርሶባቸዋል። አሁን ላይ መቀመጫ ወንበሮች እንኳን የሏቸውም፤ ቤቶቹም ተጎድተዋል የትምህርት መርጃ መሳሪያዎችም ቀላል የማይባል ጉዳትን አስተናግደዋል። ፍርድ ቤቶች ማዘጋጃ ቤት የዞኑ አስተዳደርም የጉዳቱ ሰለባዎች ናቸው። በተለይም በዞኑ የነበሩ ስራ አጥ ወጣቶችና ከወህኒ ቤት የተለቀቁ ወንጀለኞች ከፍተኛ የሆነ ዘረፋን ፈጽመዋል። አሁን ላይ በተቻለ መጠን ሕዝቡን በማስተባበር አንዳንድ ንብረቶች እንዲመለሱ ተደርጓል።
ጤና ጣቢያዎችና ሆስፒታሎች ጉዳት ደርሶባቸዋል፤ አንቡላንሶች አልነበሩም፤ ይህ የሆነው ደግሞ ጁንታው ከአካባቢው ሸሽቶ ሲሄድ አምቡላንሱንም፣ መድሃኒቱንም ጭኖ በመሄዱ ነው። ይህ ምናልባትም ከሕይወት ጋር የሚያያዝ ስለሆነ ከባድም ነበር። ነገር ግን ጁንታው ሲጠፋ በመከላከያ እጅ የገቡ አምቡላንሶች ነበሩና እነሱ ተመልሰው ለህብረተሰቡ አገልግሎት እንዲሰጡ ተደርጓል። አሁንም በየጫካው ወድቀው ያሉ አሉ። በቀጣይም እነሱን በማምጣት አገልግሎቱን እንዲሰጡ እናደርጋለን።
አዲስ ዘመን ፦ እንደ ፖለቲከኛም እንደ ሰውም በሰሜን እዝ ላይ ከተቃጣው ጥቃት ኋላም ወደሕግ ማስከበር ዘመቻው ተሄዶ የተከናወኑ ተግባር ለእርስዎ ምን ስሜት አላቸው?
አቶ ሙሉብርሃን ፦ የትግራይ ሕዝብ አንደኛ ጠላት ህወሓት ነው። አሁን ይህ ጠላት ተወግዷል። በዚህ ደግሞ በግሌ ደስታ ይሰማኛል። የትግራይ ሕዝብም ተጠቅሟል ነው የምለው። ከዚህ ጋር ተያይዞ ግን ሕዝቡ ያለምንም ኃጥያቱ የእነሱን አበሳ በመክፈሉ በጣም አዝናለሁ።
የትግራይን ሕዝብ ላለፉት በርካታ አመታት አፍነውታል፤ በኑሮውም ከሌሎች የአገሪቱ አካባቢዎች በባሰ ሁኔታ በድህነት የተሰቃየ ነው፤ ለሳምንት የሚያቆየው ቀለብ መያዝ የማይችል ሕዝብ አድርገውታል። ይባስ ብሎ በዚህ ጦርነት እንዲህ መጎዳቱ ከፍተኛ የሆነ ህመም ይፈጥራል።
ይህም ቢሆን ግን አሁንም መላው የአገሪቱ ህዝብ የትግራይ እህት ወንድሞቹ ስቃይ የእኔም ነው ብሎ ከገባበት ችግር ሊያወጣው ይገባል።
አዲስ ዘመን ፦ አሁን ላይ እሩቅ ሆነን እኛም ሌላውም ህብረተሰብ ስለ ትግራይ የምንሰማው ነገር በጣም ብዙ ነውና እንደው እርስዎ የሚያስተዳድሩት የሰሜን ምዕራብ ዞን የሽሬ እንደስላሴ አካባቢ አሁናዊ ሁኔታ ምን ይመስላል?
አቶ ሙሉብርሃን ፦ ሽሬ ማለት ደደቢት ማለት ነው። ህወሓት ትግል የጀመረበትና 17 ዓመት የትግራይ ሕዝብም ለፍትህ ለነጻነት ብዙ መስዋዕትነትን የከፈለበት ቦታ ነው። ከዚህ ጋር ተያይዞም ብዙ ጀግኖችን ያፈራም አካባቢ ነው። ይህም ቢሆን ግን ባለፉት ዓመታት አካባቢውን ሊያሳድግ የሚችል ሥራ አልተሰራም። በተቃራኒው ከወርቅ ጀምሮ ሌሎች አካባቢው ላይ የሚገኙ የከበሩ ማዕድኖችን በህወሓት ሲዘረፍ ነው የኖረ። ይህ ደግሞ በሕዝቡ ላይ ቁስል ፈጥሮ ቆይቷል። ጀግኖቹን ቢገብርም እንደ ሕዝብ ተገፍቶ ሌቦች መካከል ገብተው ትግሉን ጠልፈው ለራሳቸው ጥቅም እንዳዋሉት በደንብ ይረዳል። በመሆኑም እኛ አካባቢው ላይ እንደደረስን በቶሎ ተቀብሎን የሚመሩትን አካላት እራሱ መርጦ ነው ወደ ለውጥ የገባው።
በዚህም በቶሎ ተደራጅቶ ንግድ ቤቶችን በመክፈት ፣ ትራንስፖርትና የሆቴል አገልግሎቶች ወደ ሥራ እንዲገቡ በማድረግ አሁን ላይ አካባቢው ጦርነት የተካሄደበትም አይመስልም። መሀል አገርም ሆነ ሌላው ዓለም ላይ ያለው ሕዝብ ግን ይህንን ሀቅ አያውቅም።
አዲስ ዘመን ፦ በዘላቂነት ግን መላውን ትግራይ ወደ ቀድሞ ሰላምና መረጋጋቱ ለመመለስ ከማን ምን ይጠበቃል ይላሉ?
አቶ ሙሉብርሃን ፦ መጀመሪያ በክልሉ ያለውን ተጨባጭ ሁኔታ በቅጡ መረዳት ያስፈልጋል። በሌላ በኩል ደግሞ አሁንም ህወሓት ጉድጓድ ከገባ በኋላ ተመልሼ እመጣለሁ ይላል፤ ግን ይህ እንደማይሆን መታወቅ አለበት። ይህ ከሆነ በኋላ የራስን እድል በራስ ለመወሰን መንቃትና መደራጀት ያስፈልጋል ። እያንዳንዱ የሚደረጉ ነገሮችን በእውቀትና በጥንቃቄ ከዘላቂ ሰላም አንጻር ማየት ተገቢ ነው ። ከውሸት ፕሮፖጋንዳ መራቅ ያስፈልጋል።
ከትላንት ተምረን ነጋአችንን ለማሳመር መደራጀት፣ መደማመጥና መስራት አለብን፤ ከመላው ሕዝብም ይሁን ከጎረቤት አገሮች የሚያጋጨንን አካል ማስወገዳችንን በማመን በአዲስ ምዕራፍ ወደፊት መገስገስ አስፈላጊ ነው። በተለይም ወጣቱ የራሱን ታሪካዊ ኃላፊነት መወጣት መቻል አለበት ።
አዲስ ዘመን ፦ በመላው አገሪቱ ያሉ ብሔር ብሔረሰቦች የትግራይ እህት ወንድሞቻቸውን ለማገዝ የተለያዩ ድጋፎችን በማድረግ ላይ ናቸውና ይህንን ከቆየው የመረዳዳት ባህላችን አንጻር እንዴት ያዩታል?
አቶ ሙሉብርሃን፦ ሕዝቡ ገና አለም ሳይሰለጥን ጀምሮ አብሮ የኖረ ነው፤ ይህንን በሰፊው መቀጠል መቻል አለበት። በሌላ በኩልም ህወሓት በትግራይ ሕዝብ ላይ የረጨው መርዝ ሕዝቡ በሌሎች እህት ወንድሞቹ ላይ ልቡ እንዲሸፍት አደርጎታል። በመሆኑም መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ይህንን የሸፈተ ልብ የመመለስ ስራ ቢሰራ ፤ በሌላ በኩልም ጁንታውና የትግራይ ሕዝብ የተለያዩ መሆናቸውን በደንብ መረዳት አለበት።
በትግራይ ክልል የወደመው ንብረት የኢትዮጵያ ነው፤ የረገፈው ሕይወት የእኛው ነው፤ በመሆኑም ባለመደማመጣችንና ባለመግባባታችን የፈጠርነው ኪሳራ እንደሆነ በመረዳት አሁንም በመልሶ ግንባታው ላይ የዳር ተመልካች ከመሆን ተላቀን መተባበር ያስፈልጋል ።
ሕዝቡ ከዚህ በፊትም በተለያዩ አውዶች በአንድ ጉድጓድ ሲቀበር አብሮ ሲኖር የቆየ ነው፤ አሁንም እያሳየ ያለው ድጋፍ እጅግ ደስ የሚል ነው፤ ይህንን አጠናክሮ መቀጠል ያስፈልጋል።
አዲስ ዘመን ፦ ለነበረን ቆይታ በጣም አመሰግናለሁ።
አቶ ሙሉብርሃን፦ እኔም አመሰግናለሁ
አዲስ ዘመን የካቲት 26/2013