በላንዱዘር አሥራት (ጋዜጠኛና ከፍተኛ የኮሚዩኒኬሽን ባለሙያ)
የኢትዮጵያ ብሔር ፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች/ዜጎች በበርካታ የጭቆናና የአፈና ስርአት ውስጥ አልፈዋል ።ኢትዮጵያ በንጉሳዊ ስርዓት በምትተዳደርበትም በዚያን የጭቆና ጊዜ ነገስታቱና በእጅጉ በደም ትስስር ከነገስታቱ ጋር የተወዳጁ ታማኝ በመላ ሃገሪቱ ያሠማሩዋቸው ሹማምንት/ጌቶች ስዩመ እግዝአብሔር ነን በሚል የስነልቦና ጫና በሁሉም ላይ በማሳደር ያስገበሯቸው መሆናቸውን፣ ጭቆና፣ ብዝበዛና ዘረፋ በመላ ሃገሪቱ ተንሰራፍቶ እንደነበር ታሪክ ቁልጭ አድርጎ ያስረዳል፡፡
የኢትዮጵያ ብሔር ፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች/ዜጎችን ልክ እንደ ቅኝ ተገዥ መሬታቸው ተጠቃሎ ለገዥዎቻቸው ተሰጥቶ በገዛ ርስታቸው ገባርና ጭሰኛ ተደርገው ለዕለት ጉርሳቸው ብቻ ተገደው ገዥዎቻቸውን ያገለግሉ እንደ ነበር በውስጥም በውጭም የሚገኙ የታሪክ ምንጮችን አገናዝቦ መረዳት ይቻላል።
በዚህም ብቻ የጊዜው ጨቋኞች ሳይገቱ ለስልጣን በአምላክ የታጨን ነን በሚል የተሳሳተ የቡድን አቋም በሀሳብ የተሟገቷቸውን ሁሉ ሰብዓዊም ሆነ ዴሞክራሲዊ መብቶቻቸውን እየገረሰሱ ካለ ፍርድ የዜጎች ሕይወት በግፍ እንዲቀጠፍ በመደረጉ ሕዝቡ በዚያን የመከራና የጭቆና ወቅት በየፈርጁ ወደ ነጻነት ትግል ተገዶ እንዲገባ ሆኗል።
ዕልፍ እስከ ውጭ ሀገር ዘልቀው አገር ለማቅናት የተማሩ ምሁራን፣በሀገር ፍቅር ስሜት የነሆለሉ ወታደሮች፣ በወቅቱ ብዛት ያላቸው መብትና ግዴታቸውን ከመሠረቱ ጠንቅቀው የተረዱና ለሀገር ፍቅር የተሸነፉ የድፍን ኢትዮጵያ ጠያቂና ሞጋች የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ወጣቶች እንዲሁም በመላ ሀገሪቱ የሚገኙ ሕዝቦች የቡድን ጭቆናን አምርረው በመቃወም ልክ እንደ አንድ ሰው ሆነው ወደ ነጻነት ትግል ዘልቀዋል፡፡
ትግሉ በየአቅጣጫው ቀጥሎ አርሶ አደሮች፣የንግዱ ማሕበረሰብ ፣የታክሲ ባለንብረቶችና ለሕዝቡ የወገኑ ወታደሮች በጊዜው ሊሂቃንና በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች ፍታውራሪነት “መሬት ፣ትምርትና ነጻነት ለሰፊው ሕዝብ ከገዥዎች ተላልፎ ሊሰጥ ይገባል የሚልና ሌሎችንም አካታች የተጠቃለሉ የትግል መፈክሮችን አንግበው እጅግ የበዛ የሕይወት መስዋዕትነት ተከፍሎበት ለረጅም ጊዜ በተደረገ መራራ ትግል አጼያዊ ስርዓቱ በ1966 ጨርሶ እንዲወገድ ሆኗል”።
ድፍን የአገሪቱ ሕዝቦች አሁን አየሩን ሞልቶ ከሚፈሰው የልዩነት አስተምሕሮ ፤ጥምቀትና ኑ ፀበል ተቋደሱ በተቃራኒው ካለአንዳች ልዩነት በየወቅቱ ገዥ መደብ በነበሩ አካላት እኩል ተጨቁነው ታግለውም ውጤት በማምጣት የተባበረች ኢትዮጵያን ዕውን አድርገውና አጽንተው አልፈዋል።
ሆኖም ከነጻነት ፍላጎት ባለፈ ሕዝቦች በወቅቱ ሲያደርጉት የነበረውን የነጻነት ትግል የሚመራው የተደራጀ አካል ባለመኖሩና ዘውዳዊ ስርዓቱ እንደ ተወገደ ቦታውን ተረክቦ አገር ይመራ ዘንድ የተዘጋጀ ሀሳብ ያለው የተደራጀ ኃይል ባለመኖሩ ሕዝባዊ እምቢተኝነቱ ያመጣው አንፀባራቂ የመራራ ትግል ውጤት ተቀልብሶ ዳግም የሕዝቡ የዘመናት የለውጥ ፍላጎት በታጠቁ ወታደራዊ አምባገነኖች እጅ ባልተጠበቀ መልኩ ሊወድቅ ችሏል።
ሕዝባዊ እምቢተኝነቱን በቀላሉ በነፍጥ ቀልብሶ ስልጣን ተቆጣጥሮ የነበረው ወታደራዊ አምባገነናዊው ኃይልም የድርሻውን የአገርን ሕልውና ለማስቀጠል ከተስፋፊዎችና ከወራሪዎች ጋር እልህ አስጨራሽ ገድሎችን ፈጽሞ የሀገሪቱን ሉአላዊነት በጽኑ መሠረት ላይ እንዳትናወጥ አድርጎ ለምትከል እና አገሪቱን በእጅጉ በጠላትነት ለሚፈልጓት ኋይሎች ሁሉ የኢትዮጵያ ሕዝብ መቼም ቢሆን ከጥቃቅን የውስጥ ችግሮች በላቀ የሀገር ሉአላዊነትና አንድነት ላይ ከማንኛውም አይነት ምድራዊ ኃይል ጋር እንደማይደራደር ልክ እንደ አንድ ሰው ሆኖ መክቶ ድል በማድረግ የሀገሪቱን ሕልውና ማስቀጠል የቻለ ቢሆንም በሚከተላቸው አምባገነናዊ ተግባሮች ግን በህዝቡ ዘንድ ለመወገዝ ወራቶች አልፈጁበትም።
በጊዜው በሀገሪቱ ተዘርግቶ የነበረው የዕዝ (ኢኮኖሚ) በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ በመንግስት ጣልቃ ገብነት በሚመራ የገበያ ስርዓት ግለሰቦች (500,000) የኢትዮጵያ ብር በላይ ሀብት ማፍራት እንዳይችሉ አድርጎና ፕራይቨታይዜሽን እንዳያንሰራራ ገደብ ተጥሎበት የነበረ በመሆኑ የሀገሪቱ ኢኮኖሚ በሚፈለገው ልክ ውጤት እንዳያመጣ ኢኮኖሚውን በብርቱ መዶሻ ደቁሶትና ጠባሳን ጥሎ አልፏል።
ወታደራዊ እና አምባገነናዊው ኃይል በሀገር ውስጥ በየጊዜው ዜጎች የሚያነሱዋቸውን ልዩ ልዩ የለውጥ ፍላጎቶችንም ሆኑ ከጎሮቤት አገሮች ጋር የሚፈጠሩ አለመግባባቶችን በጥቅሉ በጠመንጃ ብቻ ለመፍታት በመሞከሩ ምክንያት አገር ውስጥ በልዩ ልዩ አካባቢዎች የማሕበረሰብ ነጻ አውጭዎች እንደ አሸን እንዲፈሉ ስርዓቱ ራሱ ገፊ ምክንያት ሆኖም ነበር።
በተጨማሪም በሀገሪቱ አማራጭ የፖለቲካ ሀሳቦች እንዳይኖሩ በአፈ ሙዝ ሀሳባውያንን ወታደራዊ አምባገነናዊው ስርዓት ሲያጨናግፍና የመኖር ሰብአዊ መብቶቻቸውን ጭምር ስርዓቱን በኃይል ለማቆየት ብቻ በማሰብ ካለ ፍርድ በመረሸን እንዲሁም በጅምላ መቃብር በመቅበር ስርዓቱን ለማቆየት ብርቱ ጥረት ሲደረግም ነበር።
ወታደራዊ ስርዓቱ ከመንግስታዊ ኃላፊነቱ አፈንግጦ በሐይማኖቶች መካከልም ዘልቆ በመግባት የሐይማኖት መሪዎችንና ተከታዮቻቸውን ሐይማኖታችሁን ወይንስ አብዮቱን ትመርጣላችሁ በሚል ጫና ውስጥ በመክተት ለዕንግልት ዳርጎ ያዋክባቸውም እንደነበር ስርዓቱን ወደ ኋላ ፈትሾ ከታሪክ መረዳት ይቻላል።
ዘወትር ሕዝብ አሸናፊ ነውና ስርዓቱ በዘላቂ ሕዝብዊ እምቢተኝነትና መራራ ትግል በ1983 እንዲወገድ ተደርጓል፡፡
በህወሓት አድራጊ ፈጣሪነት ተሰቅዞ/ፊታውራሪነት የተያዘው የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲ ግንባር (ኢህአዴግ) መንበረ ስልጣኑን እስከ ተቆጣጠረበት ጊዜ ድረስ ለእኩልነት፣ ለዴሞክራሲ ፣ ለፍትህ ፣ለፍትሃዊ የአገሪቱ ሀብት ተጠቃሚነትና የሀገር ባለቤትነት ዜጎች በጋራ እልህ አስጨራሽ ብርቱ ተጋድሎዎችን አድርገዋል።
ሆኖም በጊዜው ሲደረግ የነበረው ሕዝባዊ እምቢተኝነትና የመዋቅራዊ ለውጥ ትግል አስቀድሞ ሲደረግ በነበረው መልኩ በቅንጅታዊ አመራር እጦትና በአብዮት ቀልባሾች ሲደረግ የነበረው የሁለንተናዊ ለውጥና የብልጽግና ትግሉ እምብዛም በሚፈለገው ልክና ፍጥነት ግቡን ሳይመታ እንዲሁ መክኖ ቀርተዋል።
ኢትዮጵያ ውስጥ ከሀገረ መንግስት ምስረታ ማግስት አንስቶ የገዥው መደብ ጭቆና ነበር የሚሉ መደበኛና መደበኛ ያልሆኑ ሕዝባዊ አደረጃጀቶች የ1966ቱን የተማሪዎች አብዮትን አካቶ የሕዝቡን ለዘመናት ሊፈቱ ያልቻሉ ጥያቄዎችን አንግበው ሕዝባዊ እምቢተኝነታቸውን ከገዥዎች ጋር አድርገዋል።
በተመሳሳይ የብሔር ጭቆናም ነበር የሚሉ ኃይሎች ጫካ ወርደው ለዓመታት የትጥቅ ትግል ሲያደርጉ ከሰነበቱ ቦኋላ ዕድል ቀንቷቸው በስልጣን ላይ ለሩብ ምዕተ ዓመት ያክል መቆየታቸው የሚታወስ ቢሆንም እነሱም በተራቸው ከሰፊው ሕዝብ ፍላጎት ይልቅ በተቃራኒው ቡድናዊ ፍላጎቶቻቸውን ለማሳካት በመሽቀዳደም አገሪቱን ለከፋ የእርስ በርስ ጦርነት፤የብሔር ሽኩቻና አስከፊ ድህነት ዳርገዋት ሔደዋል።
በ1990ዓ.ም ከሻእቢያ ጋር በተደረገው ጦርነት ከሁለቱም ወገን ታላቅ ሰብአዊ ጉዳትና የኢኮኖሚ ድቀት ያጋጠመ ሲሆን ሁለቱም ተፋላሚ ወገኖች ከዚህ ዓላማ ከሌለው ግጭት ምንም በጎ ነገር ያላተረፉ መሆናቸው በብዙዎች ዘንድ ቁጭትን በቀላቀለ መልኩ ስሕተት መሆኑ ይነገራል።
በዚህ ዘላቂ ዓላማ በሌለው የወገን ጦርነት ሀገሪቱ የላይኛውን ሰሜናዊው ክፍሏን በባንዳዎችና የፖለቲካ አሻጥረኞች ካለ አንዳች ቅድመ ሁኔታ የህወሓት ቡድን አድራጊ ፈጣሪዎች መክፈላቸው በጊዜው አገሪቱ ያስተናገደችው አስከፊ እስካሁንም ድረስ ከወታደር እስከ ሲቪል ድረስ ዘወትር ክስተቱን ባስታወሱት ጊዜ እንደ እግር እሳት የሚፋጅና የሚያስቆጭ የጥቁር ታሪክ ገጽ ሆኖ ተመዝግቦ አልፏል።
ኢትዮጵያ ውስጥ የገዥው መደብ ጭቆና ሳይሆን የብሔር ጭቆና ነበር ሲሉ የነበሩ ኃይሎች ገና ትግላቸውን አንድ ብለው ከጀመሩበት ማግስት አንስቶ እነሱ ከተገኙበት ዘውግ ውጪ የሚገኙ ነገዶችን በተለያየ መልኩ ጨቋኝ ፤ጠላትና ፊውዳል በሚል ገዥ መደብንና ብሔሮችን ደባልቆ በመመልከት ከመነሻው በተሳሳተ የአመለካከት ቅኝት ታጥረው ጫካ መውረዳቸው በቀድሞ ታጋይ ጓዶቻቸውም ጭምር ይነገርላቸዋል፡፡
እርስ በርስ በትግል ወቅት የሚያጋጥማቸውን የሀሳብ ልዩነቶች በቅጡ በንግግር መፍታት ተስኖአቸው ከጫካ እስከ ቤተመንግስት እየተረሻሸኑ መዝለቃቸውን የኋላ ታሪካቸውን ተንተርሶ በቡድኑ ላይ የተጻፉ ጽሁፎች ያስረዳሉ፡፡
ሕዝቡ ጨቋኞችን አስወግዶ በመላ አገሪቱ እኩልነትንና ዴሞክራሲን ለማስፈን ለዘመናት ሲያደርገው ከነበረው ተጋድሎና መሻት የተነሳ ከስንቅ እስከ ሎጄስቲክስ ድጋፍ አድርጎላቸው ነፍጥ ስላነገቡ ብቻ በጊዜ ሂደት ይለወጡ ይሆናል በሚል ዕምነት በ1983 ስልጣን እንዲይዙ ረድቷቸዋል።
በነፍጣቸውና በሕዝብ ድጋፍ ወደ ስልጣን የመጡ ኃይሎች ኢትዮጵያ ውስጥ ከዚህ ቀደም በሕዝብ ላይ ከደረሱ አስተዳደራዊ በደሎች በእጅጉ በከፋ አኳኋን በመላ አገሪቱ የአንድ ቤተሰብ አድራጊ ፈጣሪነትን በማጎልበትና ከሀገር ውስጥ እስከ ውጭ የረቀቀ የሁለትዮሽ የጥቅም ሰንሰለትን በመዘርጋት ለሩብ ምዕተ ዓመት ያክል የሀገሪቱን ሀብት ወደ ባዕድ ሀገራት በማሸሽ ሥራ ተጠምደው መገኘታቸው እስከተወገዱበት ዕለት ድረስ በልዩ ልዩ ግለሰቦችና የሚዲያ አማራጮች በስፋት ይነገር ነበር፡፡
ይህንን ከፋፋይ እና መዝባሪ የፖለቲካ ስርዓት የሚቃወሙ የፖለቲካ ኃይሎችና ግለሰቦች ከሀገር በማሳደድ ፤ሰብዓዊ መብቶቻቸውን በመገርሰስ ከባድ አካላዊ ጉዳት ሞትን ጨምሮ በማድረስ፣ በጅምላ ሀሳባውያንንም ሆኑ ንጹሀንን ለፖለቲካ ትርፍ ገሎ በመሰወር ፤የተቃረኑዋቸውን ግለሰቦች ሀብት/ንብረት ካለሕግ በኃይል በመውረስና በማገድ፤ በተቃዋሚዎቻቸው ላይ ኢ ሰብአዊ ተግባራትን በመፈጸም ለከባድ የስነ ልቦና ጉዳት እንዲዳረጉ ማድረግን ጨምሮ ልዩ ልዩ የግፍ ድርጊቶችን በመፈጸም ሀገሪቱን ወደር ለማይገኝለት የኢኮኖሚ ስብራት፣ ማህበራዊ ቀውስና የሕዝብ ለሕዝብ ጥርጣሬ እንድትዳረግ አድርገዋል፡፡
ለበርካታ ዓመታት የትልቋን ኢትዮጵያ የጋራ አገራዊ ስዕል ለማደብዘዝ ልዩ ልዩ የአርት ስራዎችን ለሆዳቸው ያደሩ የአርት ሰዎችን በመጠቀም በጎሳ ተክቶ በማሰራጨት ፤አክራሪ ብሔርተኞችን ፈንድ በማድረግ የጋራ ታሪክ የለንም ዓይነት የጥላቻ አፍራሽ መልዕክቶች በማስነገር፣ የሀሴት ታሪኮችን እየፈበረኩ እገሌ እንዲህ አድርጎብህ ነበር በሚል ሕዝቦችን ለማቃረን በማሰብ ሀውልት በማቆም ፣ በብሔሮች መካከል ጥላቻን የሚሰብኩ አክራሪ የዲጅታል ሚዲያ የሽብር ቡድኖችን በማበራከት በሴራ አቃርኖ ለመግዛት ብዙ ተሞክሯል፡፡
ልክ እንደ ዶሮዋ ብቻዬን ጭሬ ካልበላሁ፤ ጭሬ ልበትነው፤ እንደ አህያዋም እኔ ከሞትኩኝ ሰርዶ አይብቀል በሚል የተበላሸ አመለካከት ሀገር የመናድ ድብቅ አጀንዳዎቻቸውንና የሴራ ፖለቲካቸውን እየከወኑ ከግብራቸው በተቃራኒ ሕዳር 29 የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን እንዲሁም ግንቦት 20 ሕዝቦች ከጭቆና ነጻ የወጡበት የነጻነት ቀን ወዘተረፈ እያሉን በተንኮል እያደናገሩን ኖረዋል።
ምንም እንኳ የሴራና የተቃርኖ ፖለቲካ ስልት በራስ ሀገር ላይ የማይሞከር ከ19ኛው ክፍለዘመን እስከ 20ኛው አጋማሽ ድረስ (separtion and segregation rule) በሐይማኖት ፣በዘርና በቋንቋ ከፋፍሎ እንዳይግባቡ አድርጎ የመግዛት ስልትና እሳቤ በአፍሪቃ የእንግሊዝ ቅኝ ግዛት በነበሩ አገራት ተተግብሮ አገራቱን ለከፋ የእርስ በርስ ግጭት ዳርጎ የማይረሳ የታሪክ ጠባሳን ጥሎ ያለፈ የነ ጆሴፍ እስታሊን ሀሳብ መሆኑን የፖለቲካና የታሪክ ሊህቃን አጽንኦት ሰጥተው ሲያወግዙት ኖረዋል።
ለአብነት ያክል ካለምንም ዓይነት ጥናትና ቅድመ ሁኔታ በ1983 የመሬት ባለቤትነትን ለጎሳ በመስጠት በቀጥታ” የሀገሪቱን የሀገረ መንግስት አወቃቀር ፌደሬሽን “በዘር በማካለል የጎሳ ሲያሜዎችን በመስጠት ለጥቂቶች ከለላ የማይሰጥ ሁለት ዓይነት ዜግነት የሚመስል አያያዝ በአገሪቱ እንዲፈጠር አድርገዋል።
ህወሓት ኢህአዴግ የአገሪቱን ፌደራላዊ አወቃቀር በዘር ያዋቀረበት የመጀመሪያ ምክንያት አወቃቀሩ በጊዜ ሒደት በዜጎች መካከል ከመሬት ባለቤትነት ጋር በተገናኘ መቃቃሮችን እንደሚፈጥርና ውሎ አድሮ የሀገር ሁለንተናዊ አንድነት ላይም የበኩሉን አሉታዊ ተጽዕኖ ማስከተሉ አይቀሬ መሆኑ ጠፍቶባቸው ሳይሆን በቀጥታ የአማራን ጥቂት ለም መሬቶች ለመንጠቅና ቢቻል አገር ገነጣጥሎ የራስን ሪፐብሊክ ለመመስረት ቀቢፀ ተስፋ በማድረግ ቡድኑ ሆን ብሎ ከሕዝብ አብልጦ ለራሱ ብቻ በማሰብ የፈጠረው ዘዴ መሆኑን በጥልቀት የሚያውቋቸው እውቅ ፖለቲከኞች አጽንኦት ሰጥተው እስከዛሬ ይሞግቷቸዋል።
ከነጻ አውጪ ግንባርነት ወደ አገራዊ አካታች ፓርቲነት ለመሸጋገር እንኳ ሩብ ምዕተ ዓመት ሙሉ ሲመራ ምንም ዓይነት ፍላጎት ያላሳየው ይህ የህወሓት የፖለቲካ ኃይል በእጅጉ በማያፈናፍን የፖለቲካ ሪዮተ ዓለምና አስተሳሰብ ታጥሮ አገሪቱን ለውስብስብና በቶሎ ለማይፈቱ ችግሮች ዳርጓት ላይመለስ አንድነትን አጥብቀው በሚሹ ኢትዮጵያውያን ጠንካራ ክንዶች ተቀብሯል፡፡
እዚያው( ኢህአዴግ) ውስጥ የነበሩ ለሀገር አጠቃላይ ለውጥና አንድነት ቀናኢ የሆኑ ግለሰቦች ከውስጥ ወደ ወጭ ከሕዝቡ ጋር በተናበበ አኳኋን ባደረጉት እንደ አገር የመለወጥ ትግል እነዚህም ተረኛ የጊዜው ጨቋኞች ከሕዝቡ ጫንቃ ላይ ተወግደው ላለፉት ሁለት ዓመታት ተኩል ለሚበልጡ ጊዜያት አዲሱ ውሕድ ፓርቲ ወደ ስልጣን መምጣት ችሏል፡፡
ከረጅም ጊዜ በኋላ በኢትዮጵያ ምድር የተገኘውን የሀገራዊ ለውጥ፤ የዴሞክራሲ ፣የእኩልነት፣ ፍትሃዊ የአገሪቱ ሀብት ተጠቃሚነት ዕድሎችንና ሌሎችንም ቁልፍ መሠረታዊ የህዝብ ፍላጎቶችን መንግስትን በመግራት እውን እንዲሆኑ መታገል የሁሉም አገር ወዳድ ዜጋ ቡድናዊ ተግባር ይሆን ዘንድ ጊዜው አሁን ነው፡፡
በሀገሪቱ እውነተኛ ዴሞክራሲ እንዲያብብ የራስን አዎንታዊ አሻራ በማሳረፍ እንደ ከዚህ ቀደም ሁሉ አሁን የተፈጠረው የለውጥ ዕድል ሳይጨናገፍ አካታች ብልጽግና እንዲረጋገጥ ብሎም ሀገሪቱን ወደ ሁለንተናዊ የለውጥና የብልጽግና ምዕራፍ ማሸጋገር የእያንዳንዱ ሀገር ወዳድ ዜጋ ቡድናዊና የነብስ ወከፍ ታላቅ ሀገራዊ ኃላፊነት ይሆን ዘንድ ይገባል እንላለን።
አዲስ ዘመን የካቲት 24/2013