ጌቴሴማኔ ዘ-ማርያም
የትኞቹም ታሪክ ፀሐፊዎችም ሆኑ የከተቧቸው መዛግብቶች ኢትዮጵያውያን ፀብ አጫሪዎች እንዳልሆኑ ይመሰክራሉ ። ጨዋና ኩሩ ሕዝቦች፣ ጀግኖችም እንደሆኑ ሲፅፉላቸው ይታዩና ሲተርኩላቸው ይደመጣሉ ። ሀገሪቱ ኦርቶዶክሱም፣ሙስሊሙና ፕሮቴስታንቱ እንዲሁም ሌላ ሌላው ዕምነት ተከታይ በሙሉ እርስ በእርስ ተቻችሎ የሚኖርባት ሕዝቡም ፈራሂ እግዚአብሄር ያለው እንደሆነ ደጋግመው ይገልጹታል ።
ኢትዮጵያውያን የሰው ሀገር ሰው ሲበደል ፤የየትኛውም ሀገር ዜጋ ሲንገላቱ ማየት እንደማይሹ ደጋግመው ሲናገሩ ይደመጣሉ ። እነዚሁ የውጭ ጸሐፍት እንደሚሉት እነዚህ ሀገራት ሲወረሩ በጠላት እጅ ወድቀው የድረሱልኝ ጩኸት ሲያሰሙ ፈጥነው ይደርሳሉ።ሰምቶ እንዳልሰማ አይቶ እንዳላየ መሆን ኢትዮጵያውያንን አይገልፃቸውም።
ማስመሰል ፣ ደግሞም በምን አገባኝ ስሜት ተሸብቦ ማለፍና ከዳር ቁጭ ብሎ መመልከት አይሆንላቸውም ። አንድም በግልግል ፤ ሁለትም ራሳቸውን አሳልፈው እስከ መስጠት በመድረስ ችግር በመፍታት ፣ግጭት በማስወገድና ፀብ በማብረድ ይታወቃሉ።
ኢትዮጵያውያኖች በዚህ መልክ አጋርነታቸውን ካሳዩባቸው ሀገራት ኮንጎን፣ሶማሊያን፤ኮርያን፤ሱዳንን፤ ላይቤሪያ፤ብሩንዲን ለማሳያነት መጥቀስ ይቻላል ። ፀሐፍቱ ኢትዮጵያውያን አንድ ፀባይ እንዳለቸውም አይክዱም ። አትንኩኝ ባይ ናቸው ይላሉ ። ከነኳቸው እንደማይለቁም ያሰምሩበታል ። እራሳቸውንም ብቻ ሳይሆን ሌላው ሲነካ ዝም ብለው የመመልከት ባህሪም፤ታሪክ እንደሌላቸው አበክረው ጽፈዋል ፡፡
ቀፎው እንደ ተነካ ንብ ዳር እስከ ዳር ይነሳሉ ። በሀገራቸው ለመጣባቸው ወራሪ ጠላት አይተኙም ይሏቸዋል። ፍፁም ለቅኝ ግዛት የማይንበረከኩና የማይመቹ እንደሆኑ ብዙዎች ይመሰክራሉ። የኢትዮጵ ያውያንን ጀግንነት ሲያወድሱም ‹‹ለአውሮፓውያኑና ለምዕራባውያኑ ትምህርት ሰጥተው ያለፉ ፤ለድፍን አፍሪካ አርአያ፤ ለነጻነቱ ደግሞ አርማ የሆኑ አያሌ ገድል ያላቸው አይበገሬ ሕዝቦች ናቸው ›› ሲሉ ይገልጽዋቸዋል ።ለዚህ ውዳሴ ያበቃን ደግሞ ዓለም አቀፍ ፀሐፍቱና መዛግብቱ እንደሚሉት አንዱና ዋነኛው ዛሬ 125ኛ ዓመቱን የያዘው ታላቁ የዓድዋ ድል በዓል ነው።
እውነት ነው። የዓድዋ ድል የጥቁር ሕዝቦች የነፃነት ተጋድሎ ቀንዲል ! በእርግጥም የኢትዮጵያውያኖች አትንኩኝ ባይነት የታየበት ብቻም ሳይሆን በትክክልም ቀፎው የተነካ ንብነታቸው የተረጋገጠበትም ድንቅ የተጋድሎ ውጤት ነው።ዕውነት ለመናገር ኢትዮጵያውያኖች ለእዚህም ድል ምክንያት ለሆነው የፋሽሽት ኢጣሊያ ወረራ ፈፅሞ ፀብ አጫሪ አልነበሩም።
ራሳቸው ኢጣሊያኑ ፀሐፍት (ኢትዮጵያ ውስጥ በምርኮ ቆይቶ ወደ ሀገሩ የተመለሰው ጄኔራል አልቤርቶኒ ከተመለሰ በኋላ በፃፈው መጽሐፍ እንደከተበው የዓድዋ ጦርነት መነሻ በኢጣሊያኖች የረቀቀው የውጫሌው ውል አንቀጽ 17 ነበር ። የዚህ ከመዲናችን አዲስ አበባ በስተሰሜን 468 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኛው የዛሬዋ ደቡብ ወሎ ዞን ‹‹ንጉስ ይስማ›› በሚሰኝ ስፍራ በተደረገው ውል ችግር ፈጣሪዎች እራሳቸው ኢጣሊያኖች ነበሩ ። የዚህ አንቀጽ 17 ውል የጣሊያንኛውን ትርጉም መመልከት በራሱ ኢትዮጵያኖችን በቀላሉ ማደናገርና እንደሌላው የቅኝ ግዛት ሰለባ ሀገር በማጭበርበር ኢትዮጵያውያንን መግዛት እንደማይቻል ያሳየ ነበር ።ኢትዮጵያውያን ንቁዎች ናቸው ፡፡
ይህ ውል ‹‹ኢትዮጵያ ከአውሮፓ መንግስታት ጋር ማድረግ የምትፈልገውን ግንኙነት በኢጣሊያ መንግስት በኩል ማድረግ አለባት›› የሚል ነበር ። ዳግማዊ አፄ ምኒሊክና በዘመኑ በብልህነታቸው፣ በአስተዳደርና አመራር አዋቂነታቸው ‹የሴት ወንድ› የሚል ቅጽል መጠሪያ ያተረፉት ባለቤታቸው እቴጌ ጣይቱ ብጡል ታድያ ይሄ የኢጣሊያኖች ብልጣብልጥነት ፍፁም አልተዋጠላቸውም ነበር።በጣሊያኖች ሴራም የሚሞኙ አልነበሩም ።
ይሄ ሀገራቸው ከአውሮፓ መንግስት ጋር ማድረግ የምትፈልገውን ግንኙነት በኢጣሊያ መንግስት በኩል ማድረግ እንዳለባት የሚያስገድደው የኢጣሊያን ብልጣብልጥ ፍላጎት የያዘ የሞግዚት ውል ትርጓሜ የሀገራቸውን ህልውና የሚዳፈር፣ የሕዝባቸውን ልዕልና የሚያጓድል እንዲሁም ብሔራዊ ክብርና ጥቅሟን የሚነካ መሆኑንም ተገንዝበው፤ ተቃውሟቸውንም ገልጸዋል።
በቆራጥነትም እንዲህ ዓይነቱን ድርጊት እንኳን ወድደው ተገድደው እንደማይቀበሉትም ደጋግመው አስታውቀዋል። ትዕግስትም ልክ አለው ። ልኩም ቢያልፍ ትዕግስት ፍራቻ አይደለምና ከፋሽሽት ኢጣሊያ ጋር አይቀሬው ጦርነት ውስጥ ተገባ።
ኢትዮጵያውያኖች ቁጣቸው፣ መነካትና መደፈ ራቸው በዚህ ጦርነት በተገባበት ዘመን ፋሽሽት ኢጣሊያ የሰለጠነና የጦር መሣሪያ እስከ አፍንጫው የታጠቀ መሆኑ ቁብም አልሰጣቸውም። በትንሹ 56 መድፎች፣ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ከባድና ቀላል መትረየሶች፣በመቶ ሺ የሚቆጠሩ ጥይቶች፣ ቀላል የማይባል ቁጥር የነበራቸው የተለያዩ ዓይነት የነፍስ ወከፍ መሣሪያዎች ኢጣሊያኖች በ1888 ሀገራችንን ኢትዮጵያን ከገጠሙበት ዘመናዊ የጦር መሳሪያ ጥቂቶቹ ነበሩ ።
በዚህ ላይ ደግሞ የፋሽሽት ኢጣሊያ ወታደሮች የዘመናዊ ወታደራዊ ስልጠና የወሰዱም ነበሩ። ዕውነት ለመናገር በኢጣሊያኖች በኩል የነበረው ከጦር መሣሪያ ዝግጅት አቅም አንፃር በኢትዮጵያ ከነበረው ጋር ሲነፃፀር ፍፁም የማይመጣጠን ነበር። ሆኖም በአትንኩኝ ባዮቹ ኢትዮጵያውያን የጣሊያን ሰራዊት ድባቅ ተመትቷል።
ዓድዋ የኢትዮጵያውያን ህብር የታየበበት፤ አብረው ለሃገራቸው ተዋድቀው፤አብረው የተነሰቡት የጋራ ድል ነው፡፡ ከደጀንነት ያለፈና ጥበብ የተሞላበት የሴቶች የጦርነት ተሳትፎና ምጡቅ የአመራር ሰጪነት በጎላበት በዚህ በዓድዋ ጦርነት በመቶ ሺ የሚቆጠሩ ዜጎች፣ አርሶ አደሮች፣ ወጣቶች፣ ታዳጊዎች፣ አዛውንቶችና ህፃናት ሳይቀሩ ‹ኢትዮጵያን አትንኳት› በማለት በዱር በገደሉ ደማቸውን አፍስሰዋል፤አጥንታቸውን ከስክሰዋል ፡፡
እንደ ዕድል ሆኖ ዛሬም ሀገራችን ኢትዮጵያ ሳትነካቸው በነገር በመተንኮስ የሚነኳት ጠላቶች አላጣችም። በተለይ ትላንት ከመበታተን በማዳን ህልውናዋ እንዲቀጥል ያደረገቻት ሱዳን ዛሬ ውለታዋን እረስታ የኢትዮጵያን ድንበር በድፍረት ወራለች ።በሌላ ወገን የምትገፋው ሱዳን ወዲያ ወዲህ እያለ ሲዋዥቅ የኖረ አቋሟ ዘንድሮ ለይቶለት ኢትዮጵያን እስከ መውረር ደርሳለች። ኢትዮጵያ መልካም ጉርብትናዋን አክብራ ስታስታምመው የኖረው የወዳጅ ጠላትነቷም በይፋ ተረጋግጧል።
የሆኖ ሆኖ ኢትዮጵያውያን ጎረቤት አክባሪዎች፤ እንግዳ ተቀባዮች፤ ለክፉ ቀን ደራሾች የመሆናቸውን ያህል ሉዓላዊነታቸውን ተዳፍሮ ለመጣ አካል የማይመለሱ አንበሶች መሆናቸውን ለማንም የሚጠፋው አይመስለንም። ምናልባትም በውስጥ ባለው ፖለቲካ ኢትዮጵያውያን የተከፋፈሉ የመሰላቸውና በዚህም ኢትዮጵያውያንን እናንበረክካለን ብለው የቋመጡ አካላት ካሉ የዓድዋን የነጻነትና የሉዓላዊነት ተጋድሎን መለስ ብለው ቢመለከቱ ብዙ ትምህርት ያገኛሉ ብለን እናስባለን፡፡
አዲስ ዘመን የካቲት 24/2013