በአሸናፊ ወሰኔ- ከገላን
በታዋቂው ኮሜዲያን ተስፋዬ ካሳ ቀልድ ጽሑፌን ብጀምር ሃሳቤን ያሳምርልኛል ብዬ አምናለሁ።አፈሩ ይቅለለውና ኮሜዲያን ተስፋዬ ካሳ በሕይወት ዘመኑ በርካታ አዝናኝና አስተማሪ ቀልዶችን ትቶልን አልፏል።
ቀልዶቹ ለየት የሚያደርጋቸው ከአስቂነታቸው ባለፈ ከሁኔታዎች ጋር የተዛመዱ መሆናቸው ነው።ይህም ቀልድ ከአድዋ ድልና ከአርበኞቻችን ገድል ጋር ይተሳሰራል።ለጽሑፍ እንዲመች አሳጥሬዋለሁ።እንዲህ ነው ቀልዱ፦
ጋዜጠኛ፦ በጣሊያን ወረራ ጊዜ በአንድ የጣሊያን ወታደር ላይ የሰሩት ነገር አለ ይባላል።ምን ነበር፤ እሱ? በአንዳንድ መጽሐፍቶችም ተዘግቧል።በአንዳንድ ጓደኞችዎም ይነገራል።እስኪ ከእርሶ አንደበት እንስማው።ሲል አባት አርበኛውን ይጠይቃል።
አባት አርበኛው፦ አዋ! ምንድነው . . . ጣሊያን ሀገራችንን እንደወረረ . . . ጭራሽ አልፎ ተርፎ ካምቦ አቋቁሞ. . . ስንቁንም እዚያው መሣሪያውንም እዚያው አድርጎ አንድ የጣሊያን ወታደር ዘብ ተብሎ ይንጎራደዳል. . . በኋላ ደሜ ፈላ።ይህንን ሶላቶ እከነብለዋለሁ! አልዃቸው ጓደኞቼን፡፡. . . ተው ግድየለህም. . . እኛ የመጣነው የጠላት አቀማመጥ እንዴት እንደሆነና የካምፑ ይዘት ምን እንደሚመስል ለመሰለልና ለቀሪው ጦራችን ለመናገር ነው . . . ነገር ታበላሻለህ አሉኝ።. . . የለም እደፋዋለሁ . . . ተጠግቼ ነው ግንባሩን የምለው፤ አልዃቸው፡፡. . . እንዴት አድርገህ? ሲሉኝ . . . ጠጋ ብዬ . . . እንዴት በምን ትጠጋለህ? ሲሉኝ . . .በራሱ ቋንቋ እጠጋዋለሁ፤ አልዃቸው ።ኧረ በስመአብ በል አንተ ሰውዬ. . . የነሱን ቋንቋ ከየት ትችለዋለህ! ሲሉኝ . . . ያው የነሱ ቋንቋ ቶቶ. . .ቶቶ ነው የሚበዛበት።እና በሱ እገባበታለሁ አልኩ. . . ኋላ ጠጋ አልኩና ረፋድ ላይ ነው. . . አሎራቶ!. . .እንዴት አደሩቶ. . .እችን ለደረቶ . . . አልኩና ገደልኩታ. . . አሉ።ቦምቡን እንዴት የጠላት ወታደር ላይ እንደወረወሩበት በስሜት ለጋዜጠኛው እያሳዩት።
ይህን የመሰሉና ከዚህም የደመቁ የአርበኝነት ገድልና ጀግንነት የተንፀባረቀበት ነው- የአድዋ ድል።ከቀልዱ የሚተላለፈው ጭብጥ ለዚህ ትውልድ የሚሻገር አንዱ ስንቅ ተደርጎ ይወሰዳል።በወቅቱ የጣሊያን ጦር በሀገራችን ላይ የእብሪት ወረራ መፈፀሙን በንጉሱ መታወጁንና የክተት ጥሪውን ተከትሎ፤ አርበኞች ከሺህ ኪሎ ሜትሮችን የዘለለ ርቀት ያላቸውን የሀገራችንን ተራሮች፣ ገደሎች፣ ወንዞችና ሰበርባራ መሬቶችን ሉአላዊነታቸውን ለማስከበር አቆራርጠዋል።
ስንቅና ቀለቡ በያለፉበት እና በየአረፉበት መንደር ኅብረተሰብ እየተደገፉ ከክተት እስከ ድል አድርጎ መመለስ ድረስ ያለውን ጊዜ ተሻግረዋል።ባልዘመነ የጦር መሣሪያ ቤት ያፈራው እንዲሉ ከየእልፍኛቸው የተሰቀሉ ጦርና ጋሻ አውርደውና ወልውለው ለክተቱ ፈጣን ምላሽ ሰጥተዋል።
አንድ ምሁር በቅርቡ በሚዲያ ሲናገሩ የሰማሁት በሰውና በእንስሳ መካከል ያለ ሌላ ፍጡር ተደርጎ ነበር ጥቁር ሕዝብ የሚታየው የሚል ነው።ከዚህ ሃሳብ እንደምንገነዘበው ጥቁር ሕዝብ በቅኝ ገዥዎች እንደሰው አለመታየቱን ነው።ኢትዮጵያውያን በአድዋ የተቀዳጁት ድል ይህን አመለካከት የሰበረና የዓለም ጥቁር ሕዝቦችን ታላቅነት ያበሰረ መሆኑንም ምሁሩ በአስተያየታቸው አፅንኦት ሰጥተውታል።
የዛሬ 125 ዓመት የተከሰተው ይህ ገድል ከላይ ያነሳነውን ቁርጠኝነትና ከዚህም ያለፈ ጀግንነት ተስተውሎበታል።እናም የአድዋ ድል የዓለም ጥቁሮችን ዓይን ገልጧል።ዘረኛ አመለካከት ያላቸው ነጮችን የትምክህት አስተሳሰብን ሰብሯል።
በተግባርም ንቀት የተሞላበት የጥቁሮች ምድርን ወረራና መቀራመትን ዳግመኛ እንዳይከጅሉት አድርጓል።ድሉ ለበርካታ የአፍሪካ ሀገራት ከቅኝ ተገዥነት መላቀቅም መሠረት ሆኗል።የአድዋ ድል ለትውልዱ በርካታ ልምድና ተመክሮን ያስተላልፋል።
ይሁን እንጂ የትናንቱን የአባቶቻችንን ገድል ወደ ትውልዱ የማሽጋገሪያ መንገዱ ውስንነት ይስተዋልበታል።በሚፈለገው ደረጃ ትውልድ እየተቀረፀበት አይደለም።ወቅት እየጠበቁ የሚተላለፉ መልዕክቶች ከአንጀት አይደርሱም ወይም ከአዕምሮ ጠብ አይሉም።ከዛሬ 30 ዓመት በፊት እንዲህ ዓይነት የድልና የአብዮቱ በአላት እንዲሁም የተመረጡ ዓለም አቀፍ በዓላት በትውልዱ ዘንድ ሀገራዊ አንድነትን ለማስረፅ የነበረው ሥርዓት በሰፊው ተጠቅሞበታል።
ለምሳሌ የዓለም ወጣቶች፣ ሴቶችና ሕፃናት ቀን ይነሳሉ።በዓላቱን አስመልክቶም ስፖርታዊና ኪነታዊ ፌስቲቫሎች ይካሄዱ ነበር።የጥያቄና መልስ እንዲሁም የተለያዩ ኪነ-ጥበባዊ ውድድሮችም ይካሄዱ ነበር።ሥርዓቱ የተለያዩ ችግሮች የነበሩበት ቢሆንም ኢትዮጵያዊ አንድነትን አስተሳሰብን በዘመኑ ትውልድ አዕምሮ ውስጥ በማኖር ዘንድ ጉልህ ሚና ተጫውቷል።
በትምህርት ደረጃም አንደኛ ደረጃ በአማርኛ፤ ሁለተኛ ደረጃ ደግሞ በእንግሊዝኛ በታሪክ፣ በአካባቢ ሳይንስ (ጂኦግራፊ) እና ባህልን በተለያየ መንገድ ይሰጥ ነበር።ይህ ደግሞ ወጣቱን አካባቢውን፣ ሀገሩንና ከዚያም ያለፈ የታሪክ፣ የባህልና የተፈጥሮ ገፅታን እንዲያውቅ አድርጎታል።ከዚህ ውስጥ የአድዋ ድል ታሪክ አንዱ ሆኖ ይጠቀሳል።
ከሥርዓቱ ለውጥ ጋር ኢትዮጵያዊ አንድነት እየተሽረሽረ መጣ።በተለይም ከዛሬ 3 ዓመታት በፊት የነበሩት የሃያ ሰባት ዓመታት ሰበካዎች ሁሉ ኢትዮጵያነት ስሜትን እንደጉም እያተነኑት መጥተዋል።
በአድዋ ድል ላይ የነበረው ትርክትም ከኢትዮጵያዊነት ግንባታ ይልቅ ወደታሪክ ሽርሸራና የኔነት ፍላጎት ማንፀባረቅ አደላ።የትውልድ ቀረፃው ወደ ማንነትና መንደር ታሪክ ጠበበ።የማንነታችን መገለጫና እልፍ ተሞክሮ የሚሰነቅበት የአድዋ ድል እየተድበሰበሰ ዓመታትን ዘለቀ።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለይም በያዝነው 2013 ዓ.ም የካቲት ወር የአድዋ ድል ወር በሚል ድሉ በበርካታ ኩነቶች መከበሩ በትውልዱ ዘንድ ተስፋ ሰጪ ሀገራዊ ስሜትና የአንድነት ድባብን ማሳየት ጀምሯል።
ጠባቡ የፖለቲካ ግንባታ አካሄድ እየሰፋ መምጣቱና ሀገራዊ ገፅታ እየተላበሰ መምጣቱ በትውልዱ ዘንድ የአስተሳሰብ ለውጥ ማሳየት ጀምሯል።በሚዲያዎችና በተለያዩ መንገዶች እየተላለፉ ያሉ ኢትዮጵያዊነትን የሚገነቡ መልዕክቶች መጠናከር አለባቸው።
በቅርቡ በኦሮሚያ ክልል በአንድ አካባቢ በእግር እየተንቀሳቀስኩ ሕፃናት ተሰባስበው እየተጫወቱ ኢትዮጵያ ሀገራችን እያሉ ሲዘምሩ መስማቴ የግንባታውን ለውጥ እንድገነዘብ አስችሎኛል።ላፍታም ቢሆን ልጅነቴን አስታውሶኛል።ትናንትን ናፋቂ ብቻ ሳንሆን ዛሬ ላይ ነገን መስራት እንደምንችል አመላክቶኛል።
በዘረኝነትና ማንነት ዙሪያ የተከበቡ ሰበካዎች እያበቃለት መምጣቱን ታዘብኩ።ሀገራዊ አንድነትን በትውልዱ ለማስረፅ የአድዋ ድል ላይ ብቻ ማጠንጠን በቂ አያደለም።
የመልዕክት አሰጣጥ ዘዴያችንን ማስፋት ይጠበቅብናል።የጽሑፌ ትኩረት የአድዋ ድል ላይ በመሆኑ የድሉን እልፍ ቱሩፋቶችን ትውልዱን በማስተማሪያነት እንዴት መጠቀም አለብን በሚለው ነጥብ ላይ ብቻ አተኩራለሁ።
የአድዋ ድል የአርበኞቻችን ጀግንነትን፣ አይበገሬነትንና ለሉዓላዊነታቸው መከበር ያላቸውን ቁርጠኝነት አንዱ የማስተማሪያ ዘዴ የዘንድሮው የበዓሉ አከባበር አቅጣጫ ነው።ሌላው በትምህርት ካሪኩለም ተካቶ በተለይ የነገ ሀገር ተረካቢው ዜጋ ሊቀረፅበት ይገባል።የአድዋ ድል በዓለማችን ከፍተኛ የአስተሳሰብ ለውጥን አምጥቷል።ድሉ የጥቁር ሕዝቦች ኩራት ነው።
የሀገራችን መላ ሕዝቦች ተሳትፎ የተረጋገጠበት፣ በጣሊያን ወራሪ ኃይል ላይ አንፀባራቂ ድል የተጎናፀፉበትና አንድነታቸውን ይበልጥ ያረጋገጡበት አውደ- ግንባር ነው አድዋ።እናም ይህን እና ሌሎች የድሉ ትሩፋቶችን በሚዲያዎች የተለያዩ ፕሮግራሞችና ዘገባዎችን በመስራት፣ በመደበኛ ትምህርት፣ በክፍሎችና በትምህርት ቤቶች መካከል የጥያቄና መልስ ውድድሮችን በማካሄድ፣ በፓናል ውይይቶች፣ በተለያዩ ስፖርታዊና ኪነ-ጥበባዊ ክንውኖች፣ በዓሉን ምክንያት ያደረጉ ባዛርና ሲምፓሲየሞችን . . . ወዘተ በመጠቀም የበዓሉን ትርጉም፣ ፋይዳውን፣ በድሉ የተገኙ ውጤቶችንና የመሳሰሉ ተያያዥ ቁም ነገሮችን ለትውልዱ ማስተማር ይቻላል።
ሌላው የአድዋ ድልን ምክንያት በማድረግና አርበኞቻችንን ለመዘከር የዛሬ 8 ዓመት ገደማ የተጀመረው ከአዲስ አበባ – አድዋ የእግር ጉዞ በርካታ መልዕክት ለማስተላለፍ አንዱ ግብአት ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል።የእግር ጉዞው በሌሎች አካባቢ አቅጣጫም ቢታከልበት፤ በተለይም ተጓዦች በሚያርፉባቸው ከተሞችና የገጠር አካባቢዎች ታዳጊዎች ላይ ያተኮረ ትምህርትና ቅስቀሳ ቢደረግ የጎላ ጠቀሜታ አለው።
በአጠቃላይ የአድዋ ድል ካለው ትርጉምና ጠቀሜታ አንፃር ወደትውልድ በማሸጋገር በኩል ብዙ አልተሰራበትም።ድሉ የማንነታችን መገለጫ ነው።ለትውልዱ የነገ የቤት ሥራዎች የላቀ ፋይዳ አለው።እናም ድሉ እልፍ ቁም ነገሮች ይሰነቁበታል።የዘንድሮው የበዓሉ አከባበር አቅጣጫም ተጠናክሮ መቀጠል አለበት።መልዕክቶቻችን ወቅትን የጠበቁ ብቻ መሆን የለባቸውም።ቀጣይነት ያለው ትውልድን መገንቢያ መሣሪያ አድርገን ልንጠቀምበት ይገባል፡፡
አዲስ ዘመን የካቲት 23/2013