መርድ ክፍሉ
አንድ ሰው የተሳካለት ሥራ ፈጣሪ (አዲስና የተለየ የቢዝነስ ሃሳብ ወይም ዘዴ ይዞ የተነሣ) ለመሆን፣ የያዘው ሃሳብና ሃሳቡን ተግባራዊ ማድረጊያ ገንዘብ ወሳኝ መሆናቸው አይጠረጠርም። ሆኖም እነዚህ ሁለቱ ብቻ የስራ ፈጣሪ የተሳካለት የቢዝነስ ሰው እንዲሆን አያስችሉትም።
የስራ ፈጣሪነት ስኬትን መቀዳጀት እንዲችል ወይም ጉዞው ወደ ስኬት የሚገሰግስ እንዲሆን ዓይነተኛ የሆኑ የሰብዕና መገለጫዎች ያስፈልጉታል። እንደ ሰራ ፈጣሪ እነዚህ የሰብዕና መገለጫዎች ወይም ጠባዮች ካሉ ሊዳብሩ፣ ከሌሉን ደግሞ እንደ አዲስ በውስጣችን ኮትኩተን ልናሳድጋቸው ይገባል።
የራስ ተነሳሽነት ወደ ስኬት ለመድረስ፣ አንድ የስራ ፈጣሪ ቆስቋሽ ሳያስፈልገው የራሱ ተነሳሽነት ሊኖረው ያስፈልጋል። ከዚሁ ጋር ተያይዞ የበለጠ ኃላፊነትን መሻትም እንዲኖረው ይጠበቃል። በዙሪያችን የሚያበረታቱን፣ ጎሽ የሚሉን ሰዎች ቢኖሩ መልካም ነው። ሆኖም፣ ከማንም በላይ ራሳችንን ‹‹ሞራል የምንሰጠው›› እና የምናነሳሳው ራሳችን መሆን ይኖርብናል።
አደጋን የመጋፈጥ ፈቃደኝነት አደጋን (ሪስክ) ለመጋፈጥ ፈቃደኛ መሆን የስኬታማ ስራ ፈጣሪ ቁልፍ መለያ ነው። አዲስ ቢዝነስ ጀምሮ ስኬት ላይ ለመድረስ፣ ወይም ያለንን ቢዝነስ ለማሳደግ እየፈለግን በሌላ በኩል ደግሞ ምንም ዓይነት አደጋ መሰል ነገር ማሰብ አንፈልግም ማለት አብሮ አይሄድም።
በእርግጥ አደጋ መጋፈጥ ማለት በቅጡ ሳያስቡ በዘፈቀደ እርምጃ መውሰድ ፈፅሞ መሆን የለበትም። ይሁን እንጂ በሚገባ አሰላስሎ፣ አውጠንጥኖ፣ ግራ ቀኙን ተመልክቶ አዲስን ነገርን የመጀመርና የመሞከር አደጋን ለመጋፈጥ ፈቃደኛ መሆን ያስፈልጋል።
በችሎታ የራስ መተማመንን ማዳበር ልንሰማራ ባሰብንበት መስክ፣ አስተማማኝ የሆነ ችሎታ እንዳለን በራሳችን መተማመን ያስፈልገናል። በጠራ አእምሮ ስናስብ የሚታየን የችሎታ ክፍተት ካለብን፣ ራሳችንን ከማታለል ይልቅ ችሎታችንን ለማዳበር መነሣት ወይም ሌላ የሚስማማንን የሥራ መስክ መምረጥ ይኖርብናል።
ነገር ግን፣ ችሎታው እንዳለን እያወቅን እየመላለሰ ብቅ የሚል የመተማመን ጉድለትን “አናት አናቱን” ብለን ማስወገድና በራስ መተማመንን መገንባት አለብን።
ከሌሎች ምላሽን (ግብረ መልስን) መፈለግ ስኬታማ ስራ ፈጣሪ ወይም የቢዝነስ ባለቤት ለመሆን፣ “ነገሮች ከሌላ አንፃር ሲታዩ ምን ይመስላሉ?” ብሎ መላልሶ መጠየቅ ያስፈልጋል። ለዚህ ዋነኛው ምክንያት፣ አንድ መስክ ውስጥ ስንዘፈቅ “ከውጪ” በቀላሉ ሊታዩ የሚችሉ ዕድሎች ወይም ክፍተቶች ላይታዩን ስለሚችሉ ነው።
ስለዚህ የሌሎችን አስተያየትና ግብረ መልስ መላልሶ መጠየቅ ወሳኝ ነው። ታዲያ የምናገኘውን ምላሽ በቀና አስተሳሰብ መመልከትና ስሜታዊ ሳይሆኑ አሠራርን ለማሻሻያ ግብዓት አድርጎ የመጠቀም ሰብዕናም አብሮ ያስፈልገናል።
ከፍተኛ የሚንቀለቀል መሻት/ ኃይል ስኬታማ ስራ ፈጣሪዎች ስለሚሠሩት ሥራ ውስጣቸው የሚንቀለቀል “እሳት” ያላቸው ናቸው። ስለምናመርተው ምርት ወይም ስለምንሰጠው አገልግሎት፣ ወይም ተያይዞ ስለምንፈጥረው ተፅዕኖ በቀላሉ የማይበርድ ውስጣዊ ትኩሳት ሊኖረን ያስፈልጋል።
ይህ ስሜት ከሌለን፣ ሥራችን ሲሳካ የሚፈጥርብንን ስሜት በማሰብ ራሳችንን መቆስቆስ፣ ወይም ደግሞ እንዲህ ዓይነት ስሜት ሊፈጥርብኝ የሚችለው እንዴት ያለ የሥራ መስክ ነው ብሎ ራስን መጠየቅ ያስፈልጋል። በቢዝነስ ጉዟችን ብዙ ውጣ ውረድ ሊገጥመን ስለሚችል፣ እንዲህ ያለ ውስጣዊ ኃይል እንደ ነዳጅ ውጣ ውረዱን እንድንወጣ ኃይል የሚሰጠን ይሆናል።
ስለወደፊቱ ማሰብ ስኬታማ ስራ ፈጣሪዎች ከዛሬው እንቅፋት፣ ውጣ ውረድ ወይም ጊዜያዊ ድል ይልቅ የወደፊቱ ጊዜና የሚደርሱበት ከፍታ የሚታያቸው ናቸው። ሁልጊዜም ከወራት፣ ከዓመታት በኋላ ሥራችን የት እንደሚደርስ በማሰብ መቃኘት ይኖርብናል። ራዕይና ዓላማችንን ስናስብና የወደፊት ግባችንን መላልሰን የምናስብ ስንሆን፣ ዛሬ የሚገጥሙንን እንቅፋቶችም ሆነ “ማታለያዎች” ለማለፍ አቅም ይኖረናል።
ነገሮችን የማቀናጀት ክህሎት አዲስ ሥራ ስንጀምር፣ እየሠራንም ከሆነ ሥራችንን ለማስፋት ስናስብ ነገሮች ሁሉ አልጋ በአልጋ ይሆኑልናል ብሎ መጠበቅ ዘበት ነው። ያለን ገንዘብ፣ የሰው ኃይል፣ የሥራ ቦታ፣ የገበያ ትስስር ወዘተ በምንፈልገው “ሃሳባዊ” ልክ የመሆን ዕድሉ አነስተኛ ነው።
ስለዚህ ያሉንን ነገሮች ቅደም ተከተል በማስያዝና በሁነኛ መንገድ በማቀናጀት መሥራት መቻል አለብን። እንዲህ ማድረግ እንድንችል ደግሞ ነገሮችን የማቀናጀትና ውጤት የማምጣት ክህሎትን ማዳበር ያስፈልገናል።
ከገንዘብ ይልቅ እሴትን ዋጋ መስጠት በእርግጥ አንድ ቢዝነስ ህልውናው ሊቀጥል የሚችለው አትራፊ ከሆነ፣ በሌላ አባባል ከወጪው ይልቅ ገቢው ከበለጠ ነው። የዚህ ዋናው መለኪያ ደግሞ የተስተካከለ የገንዘብ ፍሰት ነው። ይሁን እንጂ፣ አንድ ቢዝነስ ትርፋማ ለመሆንና ላለመክሰር መጠንቀቅ ያለበትን ያህል ዋና ግቡን እንደው ዝም ብሎ ገንዘብ ማጋበስ እንዳይሆን መጠንቀቅ ያስፈልጋል።
ስለዚህም፣ “በፍጥነት” ከምንሰበስበው ገንዘብ ይልቅ፣ በምርታችን ወይም በአገልግሎታችን ለምንጨምረው እሴት ዋጋ መስጠት ይኖርብናል። ለጥራት፣ ለአገልግሎት እርካታና ለመሳሰሉት እሴቶች ከፍተኛ ዋጋ የምንሰጥ ከሆነ፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ ተዓማኒነታችን ከፍ እያለና ትርፋችን እየጨመረ መሄዱ አይቀሬ ነው።
ስለ ስራ ፈጣሪነት እንዲህ ከተመለከትን ከስራ እድል ፈጠራ ኮሚሽን ድረገፅ ያገኘነውን ስራ ፈጣሪ የዳንኤል ታደሰ ታሪክ እንደሚከተለው አቅርበነዋል። ዛሬ ሙሉ ለሙሉ ለውጭ ገበያ የሚቀርቡ የቆዳ ቦርሳዎች አምራች ድርጅት ባለቤት የሆነው ዳንኤል ታደሰ ትናንት የቱንም አይነት ስራ ሳይንቅ ማደጉ ለዚህ እንዳበቃው ይናገራል።
ዳንኤል ስራ መስራት የጀመረው የዩኒቨርሲቲ ትምህርቱን ከጨረሰ በኋላ ሳይሆን ገና ከልጅነቱ ጀምሮ በመኖሪያ አካባቢው ያሉ ስራዎችን በመስራት ነበር።
“ህይወቴን ያሳለፍኩት በብዙ ሞያዎች ውስጥ ነው። ጋራዥ ውስጥ ሰርቻለው። የእንጨት ስራም እሰራ ነበር። ምንም አይነት ስራ ቢሆን ሳልንቅ ከትምህርቴ ጋር ጎን ለጎን እሰራ ነበር። ከልጅነቴ ጀምሮ በስራ እንዳድግ ያደረገኝ የኑሮ ሁኔታችን ዝቅተኛነት ቢሆንም የስራ ፍቅር እና የመለወጥ ጉጉት ወትሮም ውስጤ ነበረ። ነገር ግን የትኛውንም አይነት ስራ ለመስራት እና ለመለወጥ
አእምሮዬ ክፍት ስለነበረ የስራ ፍቅር አብሮኝ አድጓል።›› ይላል። ከተመረቀበት የትምህርት ዘርፍ በተለየ ዘርፍ ላይ ስራ ፈጣሪ የሆነበት ምክኒያት ለየትኛውም ስራ አእምሮውን ክፍት በማድረጉ በፈጠረው በጎ ተፅዕኖ ነው።
ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በፖፑሌሽን ሪሶርስ ኤንድ ዴቨሎፕመንት 2ኛ ዲግሪ ድረስ እንደተማረ የሚናገረው አቶ ዳንኤል፣ ለተወሰኑ ዓመታትም ተራድዖ ድርጅት ውስጥ ተቀጥሮ ሰርቷል።
ትልቁን የስራ ፈጣሪነት ልምድ እና እውቀት ያገኘው በተለያዩ ኮሌጆች የኢንተርፕረነርሺፕ እና ቢዝነስ ማኔጅመንት ትምህርቶችን ባስተማረበት ወቅት ነበር። ዳንኤል የልብ ጓደኛው ከሆነው አዱኛ ጋር በመሆን በቲዮሪ ጠንቅቀው የሚያውቁትን የስራ ፈጠራ እውቀት እንዴት ወደ ተግባር መቀየር እንዳለባቸው ሁሌም ያስቡ ነበር።
‹‹በእርግጥ ስራ ፈጣሪነት የሚለው ሀሳብ ሁሌም ውስጤ የነበረ ነገር ነው። ከጓደኛዬ ጋር በምንገናኝበት ጊዜም ምን እንስራ? ምን እንፍጠር? እንዴት ነው ወደ ራሳችን ስራ መግባት የምንችለው? ሀገር ውስጥ ያለው ጥሬ ሀብት ምንድን ነው? እንዴትስ ነው ያንን ለውጠን ገበያ መፍጠር የምንችለው? ሀገራችንንም ማስተዋወቅ የምንችለው›› እያሉ ይነጋገሩ ነበር።
በቆዳ ምርት ዘርፍ ላይ ብዙ የሚሻሻሉ ነገሮች እንዳሉ አስተዋሉ። መጀመሪያ የወሰዱት እርምጃ ግንኙነቶችን መፍጠር እና ማጠናከር እንዲሁም ሊያግዙን የሚችሉ ሰዎችን መፈለግ ነበር። ካላቸው የስራ ፍቅር እና ፍላጎት አንፃር ዘርፉ ላይ ቢገቡ ለውጥ ማምጣት እንደሚችሉ አመኑ። ከዚያም የቆዳ ቦርሳዎችን እያመረቱ ሙሉ ለሙሉ ለውጭ ገበያ የሚያቀርበውን ኮት ኬት ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበርን መሠረቱ።
‹‹እኛ ይሄንን መስራት እንችላለን። ሰርተን ደግሞ ስራ መፍጠር እንችላለን።›› ብለው ከነሱ ጋር ደግሞ ማን አብሮን ሊሰራ ይችላል የሚለውን ማሰብ ጀመሩ። ሁለቱም መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ውስጥ ሰርተው ነበር እና እዛ የነበሩ ፕሮጀክቶች ላይ በተለይ ሴቶች ስራ ፈላጊዎች ብዙ እንደሆኑ አውቀው
ነበር። ስለዚህ ለእነሱ የተሻለ የኑሮ ሁኔታ ለመፍጠር በማሰብ የሥራ ዕድል አመቻቹላቸው። በሦስት ሰራተኞች የተጀመረው ኮት ኬት አሁን 62 ሰራተኞች ያሉት ሲሆን 95 በመቶ ያህሉ ደግሞ ሴቶች ናቸው።
የምርት ስራው ላይ ብቻም ሳይሆን የአስተዳደር ስራዎች ላይ ድርጅታቸው ውስጥ የሚሰሩት ሴት ሰራተኞች ናቸው። ኮት ኬትን በዙሪያቸው ካሉ ሰዎችና ከራሳቸው ኪስ በማዋጣት በ20ሺህ ብር መነሻ ካፒታል ነበር የተቋቋመው። በወቅቱም ሁለት ማሽን ብቻ ነበራቸው። መስሪያ ቦታ ደግሞ በኪራይ ነበር የሚጠቀሙት። እንደተጀመረ አካባቢ ሁሉም ነገር በጣም አስጨናቂ ሆኖባቸው ነበር። በስራ ፈጣሪነት ዓለም ውስጥ ሁሌም ውጣ ውረድ እና ፈተና እንዳለ አምነው በብርታት ሰርተዋል።
‹‹ስራ ፈጣሪነት ማለት በሚቻለው መንገድ ብቻ ሳይሆን በማይቻለውም ማለፍ መቻል ነው። የቆዳ ኢንዱስትሪው ዘርፍ ሰፊ ሰንሰለት ያለው በመሆኑ ከስር ጀምሮ በሚፈጠሩ ግድፈቶች ምክኒያት ጥራቱን የጠበቀ ሌዘር ማግኘት አለመቻሉ በዘርፉ የሚያጋጥም ዋና ተግዳሮት ነው።
ደረጃውን የጠበቀ ያለቀለት ሌዘር ማግኘት በጣም ፈታኝ ነው። እኛ ጋር ከመድረሱ በፊት ያለው እያንዳንዱ ሂደት ከከብት አያያዝ ጀምሮ እርድ እንዲሁም የቆዳ አቀማመጥ ላይ ከጥንቃቄ ጉድለት ብዙ ችግር ያጋጥማል።
በየጊዜው የሚደረገውም የዋጋ ጭማሪ ሌላ ፈተና ነው። ለዚህ ደግሞ ከአቅራቢዎች ጋር በቅርበት ሆኖ ከመነጋገር ባለፈ ሌላ መፍትሄ የለም። ሌላው በዘርፉ የሚያጋጥመን ፈተና የሰለጠነ የሰው ሀይል አለማግኘት ነው። የምንሰራበት ዘርፍ ፋሽን መር በመሆኑ በየጊዜው የሚቀያየረውን ፋሽን ተከትሎ አብሮ ስራውን የሚያዳብር ሰራተኛ እምብዛም አይገኝም። ለዚህ ደግሞ ድርጅታችን ምንጊዜም ቀጣይነት ያለውን ትምህርት እና ስልጠና እየሠጠን እንገኛለን።›› ይላል።
በስራ ፈጣሪነት ዓለም ውጣ ውረዶች በዝተው ተስፋ አስቆራጭ ነገር ቢያጋጥም እንኳን ዋናው ነገር አላማን ማሰብ እና ተስፋ አለመቁረጥ ተገቢ መሆኑን ይናገራል። አሁን ትልቅ እክል የሆነባቸው በቅርቡ የተከሰተው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ቢሆንም ለነገ አላማቸው ፀንተው እንዲቆሙ ያደረገ አጋጣሚን ነበር። ኮሮና በተከሰተበት ወቅት ተደናግጠው እንደነበር የሚናገረው አቶ ዳንኤል፤ አብዛኞቹ መዳረሻዎቻቸው ሎክዳውን ላይ ሲሆኑ ኤክስፖርት ቆመ፤ 80 በመቶ የሚሆኑ የታዘዙ ምርቶቻችን ተሰረዙ።
በጣም ግራ የሚያጋባ እንደነበር ያስታውሳል። አስቀድመው የሰራተኞቻቸውን ደህንነት ጥበቃ እርምጃ የወሰዱት እነ ዳንኤል ለተወሰኑ ቀናት ቤታቸው እንዲቀመጡ ማድረጋቸውንም ይናገራል።
‹‹ሰራተኞቹን ለ20 ቀን ቤት እንዲቀመጡ ካደረግን በኋላ እንዴት ይህንን ችግር መወጣት እንደምንችል፣ በምን መልኩ ማለፍ እንደምንችል እና ማን ሊረዳን ይችላል የሚለውን ማሰብ ጀመርን። በዚያን ጊዜ እንዲረዱን ካናገርናቸው ተቋማት መሃል የሥራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽን አንዱ ነበር። ወዲያው ከማስተርካርድ ፋውንዴሽን ጋር አገናኙን። የማስተር ካርድን ፋውንዴሽን ድጋፍ በቃ! ነፍስ አድን ነበር።
በመጀመሪያ 12 ሰራተኞቻችንን ለመቀነስ ተገድደን የነበረ ቢሆንም በተደረገልን ድጋፍ ሌሎች ሰራተኞችን ጨምረን ለወቅቱ የሚያስፈልገውን የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል እያመረትን እንገኛለን።›› በማለት ይናገራል።
በአላማቸው ፀንተው ለመቆየትና ተረጋግተው የመፍትሄ ሃሳብ ለማምጣት በመንቀሳቀሳቸው ይሄን ድጋፍ አግኝተዋል። በዚህም ከመውደቅ ድነዋል። ‹‹በዛ ተስፋ አስቆራጭ ወቅት ድሮ አብሪያቸው እየሰራሁ ያሳደጉኝ ሰፈር ውስጥ ያሉ ትናንሽ ንግዶች ጋር በመሄድ እነሱ እንዴት ሊቋቋሙት እንደቻሉ አዋራቸው ነበር። ያ ትልቅ የመንፈስ ጥንካሬ ይሰጠኝ ነበር።›› ይላል።
እንደነዚህ አይነት መካሪዎች በዙሪያው ስለመኖራቸው አመስጋኝ እንደሆነ የሚገልፀው ዳንኤል” በስራ ያሳደጉት ሰዎች ባለውለታዎቹ እንደሆኑ ይናገራል። በአሁኑ ጊዜ አንዳንድ የዓለም ክፍሎች ሱቆቻቸውን በድጋሚ እየከፈቱ መሆኑ ጎን ለጎን ወደ ዋናው ስራቸው ለመመለስ አሁን መልካም ጊዜ መሆኑን ይጠቅሳል።
ህይወት ከኮሮና ጋር እንኳን ቢቀጥል የቀድሞ ስራቸውን እና ህይወታቸውን ለማስቀጠል ዝግጁ ሆነው በመንቀሳቀስ ላይ እንደሚገኙ ይጠቁማሉ። በተጨማሪም ጊዜውን አዳዲስ ምርት ዲዛይን ለማፍለቅ እየተጠቀመበት መሆኑን ያስረዳል።
አዲስ ዘመን የካቲት 19/2013