ዳንኤል ዘነበ
ራስ ምታት በሁሉም ፆታ እና እድሜ ላይ ሊያጋጥም የሚችል እና ብዙዎቻችንን የሚያጠቃ ህመም አይነት ነው። ራስ ምታት በተለያዩ ምክንያቶች ሊከሰት ይችላል። የራስ ምታታችንን ምክንያት ስናውቀው ለመታከም እና ለመዳን ቀላል ይሆንልናል።
የራስ ምታት ደረጃዎች
- ፕራይመሪ (የመጀመሪያ ደረጃ) የራስ ምታት፡- እንደ ማይግሬን ያሉ የራስ ምታቶች በጭንቅላታችን ውስጥ ባሉ የደም ቧንቧዎች፤ ነርቮች እና ጡንቻዎች ላይ በሚፈጠር ጫና ምክንያት የሚመጡ ናቸው። በተጨማሪም በአዕምሯችን ውስጥ ባለው የኬሚካል መቀያየር የሚመጡ ናቸው።
- ሰከንደሪ (ሁለተኛ ደረጃ) የራስ ምታት፡- ይህ ራስ ምታት የሌላ በሽታ ምልክት ሲሆን ሰከንደሪ ራስ ምታት ይባላል። ለምሳሌ ጉንፋን ሲይዘን፤ ታይፈስና ታይፎይድ ስንታመም፤ በደም ግፊት ምክንያት፤ መጠጥ አብዝተን ስንጠጣ፤ ሳይነሳችን ሲነሳብን፤ እና በመሳሰሉት ምክንያት ራሳችንን ያመናል። ይሄ አይነት ራስ ምታት ነው ሁለተኛ ደረጃ ራስ ምታት የሚባለው።
መቼ ነው ሃኪም ማማከር ያለብን?
ራስ ምታት በማስታገሻ መድሃኒቶች ስለሚታገስ ማስታገሻ በመውሰድ ልንድን እንችላለን። ነገር ግን ራስ ምታታችን የሚደጋገም ከሆነ፣ በሳምንት ከሁለት ጊዜ በላይ በራስ ምታት ምክንያት የማስታገሻ መድሃኒት የምንወስድ ከሆነ፣ እየተደጋገመ የሚያመን ከሆነ እና ህመሙ እየጨመረ ከመጣ፣ ህመሙ የጀመረን ራሳችንን ከተጋጨን ወይም አደጋ ከደረሰብን በኋላ ከሆነ፣ ስራችንን በራስ ምታት ምክንያት መስራት የሚያቅተን ከሆነ፣ በማስታገሻ መድኃኒት አልድንም ካለ፣ ከራስ ምታት ጋር አብሮ ግራ መጋባት፤ ማቅለሽለሽ፤ ማስመለስ፤ ድንዝዝ ማለት፤ የአንገት ህመም፤ ማዞር፤ የጆሮ ወይም የአፍንጫ ህመም፤ ራስን መሳት፤ እይታ መከልከል፤ ድካም እና የመሳሰሉት ምልክቶች ካሉ ወደ ሃኪም ቤት እንድንሄድ ይመከራል።
ራሳችንን ሲያመን በቤት ውስጥ ምን ማድረግ እንችላለን?
ብዙዎቹ መድሃኒቶች የራሳቸው የሆነ የጎንዮሽ ጉዳት ይኖራቸዋል። ለምሳሌ የህመም ማስታገሻዎችን መውሰድ ካበዛን የጨጓራ ቁስለት ወይም የኩላሊት ችግሮችን ሊያስከትሉ ይችላሉ። ስለዚህ ቶሎ መድሃኒት ከመውሰድ በቤት ውስጥ ተፈጥሯዊ የሆኑ መፍትሄዎችን መጀመሪያ ብንሞክር ይሻላል። ካልሆነ ግን ማስታገሻ መድኃኒት መውሰድ ነው።
1. ውሃ መጠጣት፡- በሰውነታችን ውስጥ ያለው ውሃ ሲቀንስ የራስ ምታት ይነሳል። ስለዚህ ውሃ መጠጣት መፍትሄ ሊሆን ይችላል ማለት ነው። ከውሃ እጥረት የተነሳ ከሆነ ራሳችንን ያመመን ቶሎ ውሃ መጠጣት ያለብን ሲሆን ህመሙም ከሰላሳ ደቂቃ እሰከ ሦስት ሰዓት ድረስ ባለው ጊዜ ይለቀናል።
2. ቀዝቃዛ ወይም ሙቅ ነገር ጭንቅላታችን ላይ ማድረግ፡- ይሄ መፍትሄ ከሰው ሰው ይለያያል። አንዳንድ ሰዎች በረዶ ወይም በቀዝቃዛ ውሃ ውስጥ የተነከረ ጨርቅ ጭንቅላታቸው ላይ ማድረግ ራስ ምታትን ያስታግስላቸዋል። አንዳንድ ሰዎች ደግሞ ሙቅ ሻወር መውሰድ ወይም በሙቅ ውሃ ውስጥ የተነከረ ጨርቅ ጭንቅላታቸው ላይ ማድረግ ራስ ምታት ያስታግስላቸዋል።
- በማግኒዚየም የበለፀገ ምግብ መመገብ፡- ማግኒዚየም ለጤናችን በጣም ጠቃሚ የሆነ ንጥረ ነገር ሲሆን በሰውነታችን ውስጥ ያለውን የስኳር መጠን እንዲሁም ነርቮቻችን የሚያስተላልፉትን መልዕክቶች ይቆጣጠራል። ማግኒዘይም ማይግሬንን ጨምሮ ሌሎችን ራስ ምታቶች ማዳን ይችላል።
ስለዚህ ሃይለኛ ራስ ምታት ካለን ሃኪም አማክረን የማግኒዚየም ክኒኖችን መውሰድ እንችላለን። ወይም ደግሞ እንደ ሙዝ፤ አቮካዶ፤ አጃ፤ ቡኒ ሩዝ፤ ቦሎቄ፤ ኬል፤ ስፒናች፤ አተር እና ባቄላ የመሳሰሉትን በማግኒዚየም የበለፀጉ ምግቦች በመመገብ በሰውነታችን ውስጥ ያለውን የማግኒዚየም መጠን ማሳደግ እንችላለን።
4. ጠንካራ መአዛ ያላቸውን ነገሮች አለመጠቀም፡- ራስ ምታት ባለባቸው 400 ሰዎች ላይ የተደረገ አንድ ጥናት እንዳሳየው ከሆነ እንደ ሽቶ ወይም ለፅዳት የሚውሉ ኬሚካሎች ያሉ ጠንካራ መአዛዎች ራስ ምታት እንደሚያስነሱ ታይቷል።
5. የዝንጅብል ሻይ መጠጣት፡- ዝንጅብል በሰውነታችን ውስጥ ያሉ አላስፈላጊ ወይም መርዛማ ንጥረ ነገሮችን ማስወገድ እና ሰውነታችን እንዳይቆጣ ማድረግ ይችላል። በዛ ላይ ማቅለሽለሽን እና ማስመለስን ያስታግሳል። ስለዚህ የዝንጅብል ሻይ መጠጣት የራስ ምታታችንን ሊያስታግስልን ይችላል።
ምንጭ፦ ጤናችን በእጃችን
አዲስ ዘመን የካቲት 18/2013