ወንድወሰን መኮንን
ኢትዮጵያ በየዘመኑ በርካታ ጀግኖችን አፍርታለች። የጀግኖቿንም ታሪክ ከትውልድ ትውልድ አስተላልፋለች። ይህ ደግሞ በየዘመኑ ጀግኖችን ለማፍራት በእጅጉ ያግዛል። ለዚህም ማሳያው በደርግ ጊዜ የተቋቋመው ብሔራዊ የጀግኖች አምባ ሲሆን፤ በየዘመኑ ብዙ ጀግኖች እንዲፈሩ አግዟል።
በአገራዊ ግዳጆች ላይ ተሰማርተው ወላጆቻቸውን በሞት የተነጠቁና ድጋፍ ማግኘት ያልቻሉ ህጻናትን በመሰብሰብ አስተምሯል፤ ለቁምነገርም አብቅቷል። ይሁን እንጂ የደርግ ውድቀትን ተከትሎ ህጻናት ተገቢው ትኩረት ሳያገኙ ቀርተው አምባው ቀስ በቀስ እስከመፍረስ ደርሷል።
በቅርቡ ግን ሁለት ማህበራትን በማጣመር ብሔራዊ የጀግኖችና የህፃናት አምባ በማለት በአዲስ መልክ ተቋቁሟል። እኛም ከማህበሩ የቦርድ ሰብሳቢ ከዶክተር አዳሙ አንለይና ከምክትል ሰብሳቢው ሻለቃ ተስፋዬ ወንድሙ ጋር ስለማህበሩ አጠቃላይ እንቅስቃሴና ወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ቆይታን አድርገናልና ተጋበዙልን። መልካም ቆይታ።
አዲስ ዘመን፡- የት አካባቢ ተወለዱ፤ አስተዳደግዎትስ ምን ይመስላል?
ዶክተር አዳሙ፡– የተወለድኩት በቀድሞው ጎጃም ክፍለሀገር መተከል አውራጃ ድባጤ ወረዳ ነው። አንደኛ ደረጃ ትምህርቴን ድባጤ ውስጥ ተከታትያለሁ። ከዚያ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴን ደግሞ ፍኖተ ሰላም አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማርኩ። በመቀጠል አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ነበር የገባሁት። ነገር ግን አንድ ዓመት ተኩል ተምሬ አቋረጥኩት። ምክንያቱም ወቅቱ የኢትዮጵያ ተማሪዎች አብዮታዊ ትግል የተጋጋመበት ስለነበር በዚያ ለመሳተፍ ነው።
አዲስ ዘመን፡- የት ላይ ተሰለፉ? በማን ወገን ሆነው?
ዶክተር አዳሙ፡– አፍላ የወጣትነት ዘመን ላይ ያለ ሰው የወቅቱን የተሻለ መምረጡ አይቀርም። ስለዚህም እኔም የዩኒቨርሲቲ ትምህርቴን ትቼ በኢሕአፓ ውስጥ ተሰልፌ ትግል ለማድረግ ወደ በረሀ ነው የሄድኩት። በዚህ ደግሞ ፈታኙ የበረሀ ላይ ትግልን አይቻለሁ። ሱዳን የገባሁትና በመልሶ ማቋቋም እድል ለከፍተኛ ትምህርት ሀገረ ስዊድንን የዛሬ 32 ዓመት አካባቢ የተቀላቀልኩትም ለዚህ ነው።
ለረጅም ዓመት ትምህርቴን በስዊድን ተከታትያለሁ። ውጤታማም በመሆን ሦስተኛ ዲግሪዬን እንድይዝ ሆኛለሁ። ከዚህ በተጨማሪ የስዊድን ነዋሪ እንድሆንም እድል አግኝቼበታለሁ። በሙያዬ ባዮ ሜዲካል ኢንጂነሪንግ ያጠናሁ ሲሆን፤ የተለያዩ አለም አቀፍ ተቋማትና ሀገራት ውስጥ መስራት ችያለሁ።
አዲስ ዘመን፡- የት የት አገራት ላይ ሰሩ?
ዶክተር አዳሙ፡- ብዙ ናቸው። ግን ጥቀስ ከተባልኩ በምስራቅ አውሮፓ፤ በዩጎዝላቪያ፤ሀንጋሪ ሩማኒያ ሰርቻለሁ። በተለይም ደግሞ በዩጎዝላቪያ ጦርነት ወቅት በአውሮፓ ሕብረት የመልሶ ማቋቋም፤ በቤት ስራ ግንባታ ተሳትፎ አድርጌያለሁ። በሩማኒያ ሕጻናት ማሳደጊያም እንዲሁ መስራት ችያለሁ።
አፍሪካ ውስጥ ደግሞ ሩዋንዳ ፣ ቡሩንዲና ኡጋንዳ ውስጥ አገልግያለሁ። አሁን ደግሞ የስዊድኖች ድርጅት በሆነው ‹‹ሂዩመን ብሪጅ ኢንተርናሽናል ›› እያገለገልኩ እገኛለሁ። በዚህ ድርጅት ውስጥ ለ18 ዓመታት አገልግያለሁ። አሁን ደግሞ የድርጅቱ የአፍሪካ ዋና ስራ አስፈጻሚ በመሆን እየሰራሁ ነው የምገኘው።
አዲስ ዘመን፡- ስለ ድርጅቱ ትንሽ ቢሉን?
ዶክተር አዳሙ፡- ድርጅቱ የሕክምና መሳሪያዎችን ለዩኒቨርስቲዎች፤ለዩኒቨርስቲ ሆስፒታሎች ይሰራል። ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴርና ከደብረማርቆስ ዩኒቨርስቲ ጋር በመተባበር ባዮ ሜዲካል ቴክኒሽያኖችን ደብረማርቆስ ላይ ያሰለጥናል። ተማሪዎቹ የሚማሩት ከፍለው ሳይሆን ድርጅቱ የኪስ ገንዘብ እየተሰጣቸው ነው።
ከጨረሱ በኋላ መንግሥት በየሆስፒታሉ፣ በየጤና ጣቢያው ይመድባቸዋል። ስለዚህም ለባዮ ሜዲካል ቴክኒሽያንነት መንግስት ራሱ መልምሎ የሰጠንን ተማሪዎች በማሰልጠንና ብቁ በማድረግ ለራሱ ለመንግስት የፈለገው ቦታ ላይ እንዲመድባቸውም የማድረግ ሥራ ይሰራል።
አዲስ ዘመን፡— በሙያዎ ባዮ ሜዲካል ኢንጅነሪንግ እንዳጠኑ ነግረውናል። ለመሆኑ ባዮ ሜዲካል ቴክኒሽያን ማለት ምን ማለት ነው ?
ዶ/ር አዳሙ፡-ባዮ ሜዲካል ቴክኒሽያን ማለት የሕክምና መሳሪያ ጥገና ተከላ እንደገናም ካሊብሬሽንም ያደርጋሉ፡ እነዚህን ሶስት ስራዎች ነው በዋናነት የሚሰሩት።
አዲስ ዘመን፡- ይሄ ሙያ በሀገራችን አዲስ ነው ወይስ የቆየ ?
ዶ/ር አዳሙ፡– ባዮ ሜዲካል ኢንጂነሪንግ በኢትዮጵያ የተጀመረው በቅርብ ነው ። ጅማ ዩኒቨርስቲ ነው የጀመረው ። የዲፕሎማ ፕሮግራሙን ግን እኛ ነን ከመንግስት ጋር ሁነን የጀመርነው ። የመጀመሪያዎቹ ነን ማለት ይቻላል ።
አዲስ ዘመን፡- እስከአሁን ምን ያህል ተማሪዎች አስተምራችሁ አስመርቃችኋል ?
ዶ/ር አዳሙ፡– እስከዛሬ ወደ 480 ተማሪዎች አስመርቀናል። አሁን ደግሞ ወደ 500 የሚሆኑ ተማሪዎች እናስመርቃለን ። ትምሕርት ቤቱ የሚገኘው ደብረማርቆስ ከተማ ሲሆን፤ ስልጠናው የሚሰጠው ለ3 ዓመት ነው ።
አዳሪ ትምህርት ቤት አይደለም። የኪስ ገንዘብ ስለምንሰጣቸው እዛው ትምህርት ቤቱ አቅራቢያ በግላቸው ተከራይተው ይኖራሉ ። ትምህርታቸውን እንደጨረሱ እኛ ዝርዝራቸውን ለጤና ጥበቃ ሚኒስቴር እንልካለን። ከዚያ መንግስት በሚፈልገው ቦታ ይመድባቸዋል ። ሲመለመሉ መንግስትን ለማገልገል ቃልኪዳን ገብተው ነው የሚመጡት። ስለዚህ ስራ አላቸው ማለት ነው ።
አዲስ ዘመን፡- ሀገራችን ውስጥ የት የት ቦታዎች ላይ ቢሮ ከፍታችኋል ?
ዶ/ር አዳሙ፡- ኢትዮጵያ ውስጥ ያለን ቅርንጫፍ ቢሮ ደብረማርቆስ ላይ ነው። ያው ግን ፓርትነራችን መንግስት ነው። ስለዚህ ከዩኒቨርሲቲዎች ጋር ከሆነ እኛ የምናደርገው ምንድነው ለምሳሌ የሕክምና እቃ ስናስመጣ ኮንሳይነሩ ዩኒቨርስቲው ወይ ሆስፒታል ከሆነ በቀጥታ ነው የምንልከው ። መጋዘን የለንም ። መጋዘን ላይ አናስቀምጥም ።
አዲስ ዘመን፡-ከብሪጅ ሪጅናል የአፍሪካ ዳይሬክተርነትዎ በተጨማሪ ፈርሶ የነበረውን የጀግኖች አምባና የሕጻናት አምባ ማሕበር በሕጋዊነት በማቋቋም ቦርዱን በሊቀመንበርነት እየመሩ እንዳሉ ሰምተናል። ለመሆኑ ይህ ማህበር ምንድነው ስራው? በአዲስ መልክ የጀግኖችና የሕጻናት አምባ በሚል ለማቋቋም ምን አነሳሳችሁ?
ዶክተር አዳሙ ፡- እንደሚታወቀው ሁሉ በሀገራችን በ1969 ዓ.ም የሶማሊያው የዚያድ ባሬ መንግስት ኢትዮጵያ ላይ ጦርነት ከፍቶ እስከ አዋሽም ድረስ ዘልቆ የመግባት ሁኔታዎች ተፈጥሮ ነበር።
በልጅነት እድሜያችን የምናስታውሰው በዚያን ወቅት ኢትዮጵያ ምንም አይነት ዝግጅት ባላደረገችበት፤ሶማሊያ ደግሞ ኢትዮጵያ ተዳክማለች ብላ ባሰበችበት ወቅት ነበር ቅጽበታዊ ጦርነት የከፈተችብን ። እናም በዚያን ጊዜ ብዙ የሠራዊታችን አባላት በምስራቁ ጦርነት ከፍተኛ ውጊያ ስለነበር የአካል ጉዳት አጋጥሞአቸዋል ።
የእግር፤ የእጅ ሌላም እንደዚሁ ጉዳት ገጥሟቸዋል ። እንደገናም በሰሜኑ ጦርነት በተለይም ኤርትራና ትግራይ ላይ በነበረው ውጊያ በጣም ብዙ ሚሊሽያዎችና መደበኛ ሠራዊት አባላት በጦርነቱ ተመሳሳይ ችግር አጋጥሟቸዋል ።
ሶማሊያ ለከፈተችብን ጦርነት ሚያዚያ 4 ቀን 1969 ዓ.ም ነበር ብሔራዊ የክተት የእናት ሀገር ጥሪ የታወጀው ። ያኔ ሚሊሽያው ወደ ጦር ግንባር ሲዘምት የ20 ብር ደመወዝተኛ ነበር ። የቀረበለትን የእናት ሀገር ጥሪ ተቀብሎ ሲዘምት ቤቱን ልጆቹን ትቶ ነው ።
እርሻ ላይ የጠመደውን በሬም ትቶ ወደ ቤቱ ሳይመለስ የሄደ አርሶ አደር አለ ። እህል ለመሸጥ አህያ ጭኖ ገበያ የሄደ አርሶ አደር በዛው አህያውን ጥሎ የዘመተም ነበር ። የእናት ሀገር ጉዳይ ስለነበረ ማለት ነው ።
እነዚህ የሠራዊታችን አባላት የአካል ጉዳት ሲያጋጥማቸው ከሠራዊቱ ለአገልግሎት ብቁ አይደሉም ተብለው ሲቀነሱ ሲሰናበቱ በቀጥታ የሚሄዱት ወደየቤታቸው ነው ። ቤታቸው ሲሄዱ ደግሞ የአካል ጉዳተኞች ስለሆኑ እንደ ድሮአቸው እርሻ ማረስ መነገድ ተንቀሳቅሰው መስራት አይችሉም ።
በወቅቱ የነበረው የኢትዮጵያ መንግስት ደብረዘይት ላይ ጀግኖች አምባን በማቋቋም ዘለቄታዊ እንክብካቤ ይደረግላቸው ነበር ። በተለይ የተወሰነ መንቀሳቀስ የሚችሉትን ደግሞ በመዝገብ አያያዝ በተለያየ ሙያ በማሰልጠንና በማስተማር በየመሥሪያ ቤቱ ኮታ እየተሰጠ ይመደቡ ነበር ።
በቀድሞው የጀግኖች አምባ የነበሩትን ለሀገራቸው መስዋዕትነት የከፈሉ የጦር ጉዳተኞችን ላለፉት አስር ዓመታት በየዓመት በአሉ አስፈላጊውን በማድረግ አብረዋቸው ያሳልፉ እንደነበር ሰምቼአለሁ ። ስለዚህም ያንን ለማድረግ ነው እኔም ይህንን ያቋቋምኩት ። ዓላማውን በተመለከተ ለሀገር ክብር የቆሰሉ፣ የደሙ በጦር ሜዳ የተጎዱ ጀግኖች ተገቢ እንክብካቤ እንዲያገኙ ማገዝና መርዳት ነው ።
አዲስ ዘመን፡- የቀድሞው የጀግኖች አምባ መቼ ነበር የተቋቋመው ?
ዶ/ር አዳሙ፡- ከ1970—71 ዓ.ም አካባቢ ሊሆን ይችላል ብዬ እገምታለሁ ። የቆየው የመንግስት ለውጥ እስከተደረገበት እስከ 1983 ዓ.ም ድረስ ነበር። በተጓዳኝም ወላጆቻቸው በጦር ሜዳ የሞቱባቸው የወታደር ልጆች ሕጻናት አምባ ይገቡ ነበር ። ከመንግስት ለውጥ በኋላ እነሱም እንዲበተኑ ተደርጓል። በተለይ የእነሱ ሕይወት በጣም አስከፊ ነበር ።
አሁን ልደታ አካባቢ ዘለቄታዊ እንክብካቤ ተብሎ ጀግኖች አምባ የሚለው ስም ተቀይሮ የአካል ጉዳተኞች ክብካቤ ማእከል ውስጥ ነው ያሉት። ስማቸውንም መጥቀስ አልተፈለገም ።
ይሄ የሆነው በኢሕአዴግ ግዜ ነው ። የጦር ጉዳተኞቹ በጣም ይከፋቸው ነበር ። ለሀገር መስዋዕትነት ከፍለን ስማችን ተቀይሮ እንዴት እንደዚህ እንባላለን ይላሉ ። እኔ በግሌ የምችለውን አግዛቸው ነበር ። ለሀገር መስዋዕትነት የከፈሉ ጀግኖችን መርዳትና መንከባከብ ይገባል።
አዲስ ዘመን፡- ለሀገር መስዋዕትነት የከፈሉ ግን ደግሞ ተገቢው እንክብካቤ ያልተደረገላቸውንና ባለውለታነታቸው የተረሱትን ጀግኖች አስበው ለማገዝ የተነሱበትን ምክንያት ቢገልጹልን ?
ዶ/ር አዳሙ፡– እኔ የኋላ ታሪኬ ሲታይ የወታደር ልጅ ነኝ። አባቴ ለሀገሩ ሲዋጋ ጦር ሜዳ ነው የሞተው ። የወታደርን ሕይወት እናውቀዋለን። ለግዳጅ ይወጣል ። ላይመለስ ይችላል ። ከተመለሰ ደግሞ ወይ በጤናው አሊያም ተጎድቶ ይመጣል ።
ስለዚህ እንደ ሀገርና ሕዝብ ትልቅ ኃላፊነት አለብን ። ይሄ ሠራዊት ዛሬ እኛ ቆመን እንድንሄድ፤ በሰላም እንድንኖር ፤ ሀገራችን ታፍራ ተከብራ እንድትኖር ያደረገ ሠራዊት ነው ። እንደ ዜጋ ይሄንን ሠራዊት የግድ መንከባከብ አስፈላጊ ነው ብዬ አምናለሁ ። ዋናው መነሻዬም እሱ ነው።
አዲስ ዘመን፡- የጀግኖች አምባ አባላት የነበሩትን ከመቼ ጀምሮ ነበር መርዳት የጀመሩት ?
ዶ/ር አዳሙ ፡– 10 ዓመት ይሆናል።
አዲስ ዘመን፡- በራስዎ ተነሳሽነት ሄደው እገዛ ሲያደርጉ ተቃውሞ አያጋጥምዎትም ነበር ?
ዶ/ር አዳሙ፡- በአንድ ወቅት የሚኖሩበትን ቤት እያደስኩላቸው ነበር ። ምን ፈልጎ ነው መንግስት እኮ በጀት አለው የመሳሰሉትን ነገር በዛ ግዜ ይሉ ነበር ። እኔም እነግራቸው ነበር ። እነዚህ ሰዎች ከዚህ በኋላ ዊልቸራቸውን ጥለው ለእናንተ የጸጥታ ስጋት ሊሆኑ አይችሉም ። ቢያንስ ሰብዓዊ የሆነ እገዛና እርዳታ አድርጉላቸው ነበር የምለው ።
አንግባባም ነበር ። አሁን በተለይ ይሄ ለውጥ ከመጣ በኋላ መንግስትም ትኩረት ሰጥቶት እኔም በግሌ የማደርገውን ነገር በጋራ እያደረግን ድሮ አይተዋቸው የማያውቁትም የመከላከያ ጄኔራሎች ቦታው ድረስ ሄደው ጎብኝተዋቸው አበረታተዋቸዋል ። ይሄ የሆነው ከለውጡ በኋላ ነው ። አሁን በጣም ጥሩ ግንኙነት ነው ያለን ።
አዲስ ዘመን፡- በቅርቡ የመሰረታችሁት ማሕበር ስሙ ማነው ?
ዶ/ር አዳሙ፡– አሁን ያቋቋምነው ማሕበር ብሔራዊ የጀግኖችና ሕጻናት አምባ ነው የሚባለው ። እኛ እስከመጨረሻው ልናስተዳድረው አይደለም ። በቅርብ ጊዜ የመንግስት አዋጅ ይወጣል ተብሎ ይጠበቃል ። አዋጁ ከታወጀ በኋላ የሚሆነውን እንጠብቃለን ። ምክንያቱም ሥርዓት በተቀየረ ቁጥር ወታደር ሁነው በተለያዩ ጦር ሜዳዎች ሀገራዊ ግዳጃቸውን የተወጡ የቆሰሉ የተጎዱት እንደ ወንጀለኛ መቆጠር የለባቸውም፤ አይገባም ።
እንደ ዜጋ መታየት ስላለባቸው አዋጅ በአዋጅ እስካልተሻረ ድረስ እንክብካቤአቸው ይቀጥላል ማለት ነው ። እኛ ድጋፍ ሰጪዎች ነን ። ለእነሱ የሚሆን ሀብት ነው የምናፈላልገው። ሀብት ካፈላለግን በኋላ ተቆጥሮ የተሰጠን ስራ አለ። አምባው ላይ እሱን እንጨርሳለን።
አዲስ ዘመን፡- የበፊቱ ጀግኖች አምባ ከፈረሰ በኋላ በማን ስር ነበር የሚተዳደረው ?
ዶ/ር አዳሙ፡– በአዲስ አበባ ማሕበራዊ ጉዳይ ቢሮ ስር ነበር የሚተዳደረው።
አዲስ ዘመን፡- ኢሕአዴግ ከመግባቱ በፊት የነበሩት የጦር ጉዳተኞች እዛ ውስጥ አሉ ?
ዶ/ር አዳሙ፡- የድሮዎቹ አሁንም ወደ 160 የሚሆኑ አሉ ። በጣም ጉዳተኞች ናቸው ። ከዛ ውጭ ወጥተው ወደየትም መሄድ አይችሉም ። ምግባቸውን ያገኛሉ ። ጡረታ ያገኛሉ ። ሀገሪቱ በአቅሟ መሰረት እያገዘቻቸው ነው ። በባድመ ውጊያ ላይ የቆሰሉም አሉ ። ገብተዋል ። አሁንም በሆስፒታል ሁነው ቦታ አጥተው እየተጠባበቁ ያሉ አሉ።
አዲስ ዘመን፡- የቢሾፍቱ ጀግኖች አምባ ሰፊ ነበር ። ብዙ ቤቶችም ነበሩት ። አሁን እንዴት ነው ያለው ?
ዶ/ር አዳሙ፡- አሁን እሱ ቦታ የለም ። ሙሉ በሙሉ ተለቋል ። ያ ቦታ የቢሾፍቱ ጀግኖች አምባ የነበረው ግቢ የመከላከያ ኢንጂነሪንግ ኮሌጅ ሆኗል። የአላጌው (ዝዋይ) የጀግኖች ልጆች ማሳደጊያ የነበረውን ደግሞ ግብርና ሚኒስቴር ነበር የያዘው።
አዲስ ዘመን፡- አባቶቻቸው በጦር ሜዳ የሞቱባቸውና ሕጻናት አምባ የነበሩትስ ልጆች ወዴት ሄዱ ?
ዶ/ር አዳሙ፡- ልጆቹን ያኔ አዲስ አበባ አምጥተው እንደበተኑአቸው ነው የሰማሁት ። ከባድ የጦር ጉዳተኞቹ ግን አዲስ አበባ ልደታ ነው ያሉት ። የአካል ጉዳተኞች ዘለቄታዊ እንክብካቤ የሚባለው ቦታ ላይ ናቸው ።
አዲስ ዘመን፡- የጦር ጉዳተኞችን በተመለከተ አሁን መንግሥት ያወጣል ያሉት አዋጅ ምን ላይ ያተኮረ ነው የሚሆነው ?
ዶ/ር አዳሙ፡– አንድ ድርጅት ሲቋቋም በአዋጅ ነው የሚቋቋመው ። ተጠሪነቱ ለማን እንደሆነ ይገልጻል። የእኛ ድርሻችን እንዳልኩህ በአጋዥነት መሰለፍ ነው ። ውል እንፈራረማለን ። እንቀጥላለን ። ሕጻናት አምባ ግን የት እንደሚሆን፤ ምን እንደሚሆን ገና የወሰነው ነገር የለም ። የመንግሥትን አቅጣጫ ነው የምንጠብቀው።
አዲስ ዘመን፡- አዲሱን የድርጅታችሁን ቢሮ የት የት ከፍታችኋል ?
ዶ/ር አዳሙ፡- ሕጻናት አምባን በተመለከተ እንደ ሀሳብ እያሰብን ያለነው አራት ቦታ ለመክፈል ነው። ሰሜን፤ ደቡብ ፤ምስራቅና ምእራብ ። ምክንያቱም ሕጻናት ከወላጆቻቸው በጣም መራቅ የለባቸውም ። አባታቸው በጦር ሜዳ ቢሰዋ ቢያንስ እናት አላቸው ።
እንደዚህ አይነት ሀሳብ አለን። ይሄ ተቀባይነት ካገኘ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት አሉ ። ከእነሱ ጋር እንወያያለን ። የአዋጭነት/የፊዚቢሊቲ ስቴዲ ጥናት ይደረጋል። በኃላም ወደ ተጨባጭ ስራ የምንገባበት ይሆናል።
አዲስ ዘመን፡- በአሁን ሰአት ምን ያህል ደጋፊ አባላት አላችሁ ?
ዶ/ር አዳሙ፡– እስከአሁን እያደረግን ያለነውን በተመለከተ የክልል መንግሥታት እየረዱን ነው ያሉት። 3 ሚሊዮን 2 ሚሊዮን ብር የረዱን አሉ። 500 ሺህ ብር የረዱን አሉ። ዩኒቨርሲቲዎች ይረዱናል ። ማቴሪያልም ጭምር ።
እውነት ለመናገር ከምንጠብቀው ካሰብነውም በላይ ብዙ እርዳታ አግኝተናል ። እኛም ሥርዓቱን ተከትለን የተጣለብንን ኃላፊነት ለመወጣት እየሰራን እንገኛለን።
አዲስ ዘመን፡- በተገኘው እርዳታ ምን ለመስራት አስባችኋል ?
ዶ/ር አዳሙ፡– አሁን ለምሳሌ ጀግኖች አምባ ላይ አንድ ላይብረሪ፤ አንድ አይሲቲ ሴንተር፤ የስፖርት ማዘውተሪያ፤ ፊዚዮቴራፒ ማእከል፤ ዳቦ መጋገሪያ፤ ላውንደሪዎች፤ ኪችን እቃዎች እንደገናም ከከተማ ወጣ ብለው ስለሚኖሩ ጥሩ ፊልም ቤት ማታ ሲሆን ወጥተው እዛው የሚያዩበት እነዚህ ስራዎችን እንሰራለን ብለን እናስባለን።
አዲስ ዘመን፡-በቀጣዩ ምን እንጠብቅ?
ዶ/ር አዳሙ፡- በቀጣዩ የሚጠበቀውን እድሜና ግዜ ከሰጠን በጋራ እዛው አላጌ የድሮ ሕጻናት አምባ ሄደን እናየዋለን ። ቦታውን ግብርና ሚኒስቴር ነበር የያዘው አሁን ግን አንዱ መንደር ተለቋል ። አንዱ መንደር ነው እየተሰራ ያለው ። መንግስት አስፋልትና የውስጥ ለውስጥ መንገድና ራምፕ ለጉዳተኞች እንዲመች አድርጎ እየሰራ ነው።
አዲስ ዘመን፡- ከጦር ሜዳ ጉዳተኞች ውጭ በእድሜያቸው የገፉ፤ ረዳት የሌላቸው፤ ቤተክርስቲያን የወደቁ የሠራዊት አባላት የነበሩ አሉ ። አስፍታችሁ እንዲህ አይነቶቹንም ለማካተት ለመርዳት አስባችኋል ?
ዶ/ር አዳሙ፡- አዎን ። መጀመሪያ አዋጁ ምን ይላል የሚለውን ነገር እናያለን ። የጀመርነውን ከጨረስን በኋላ በቀጣዩ እነዚህን ልናስብ እንችላለን። አዋጁ ይሄንንም የሚያካትት ይመስለኛል ።
ባላየውም የሠራዊት አባል እስከነበሩ ድረስ ሕክምና የተለያዩ ጥቅማ ጥቅሞች የሚያገኙበት ሁኔታ የሚኖር ይመስለኛል ። ምክንያቱም በየትኛውም ዘመን ይሁን የሠራዊት አባል የሠራዊት አባል ነው ። አሁን ያለው የመንግስትም አቅጣጫ ይመስለኛል ። እኛም እንደሱ ነው የምናስበው።
አዲስ ዘመን፡- እርስዎ ስዊድን ሀገር ወደ 30 ዓመት ኖረዋል። በሌላው ሀገር የጦር ጉዳተኞችና ለሀገር ዋጋ የከፈሉ ወታደሮች አያያዝ እንዴት ነው?
ዶ/ር አዳሙ፡– በየትኛውም ባደጉ ሀገሮች ውስጥ ላይ የጦር ጉዳተኞችን በተመለከተ መንግስት በጀት መድቦ የጦር ጉዳተኞች ኮሚሽን በሚኒስቴር ወይም በኮሚሽን ደረጃ ያንን የሚከታተል ሊያቋቁም ይችላል ።
በጤናቸው በሕይወታቸው ለአገልግሎታቸው ውለታ የሚመለስበት፤ የተለያየ ጥቅማ ጥቅሞች የሚያገኙበት፤ ትራንስፖርት ላይ ቅድሚያ የሚሰጥበት 40 ወይም 50 ብቻ ፐርሰንት የሚከፍሉበት አይነት ብዙ ነገሮች ይደረግላቸዋል ። አይደለም ሕይወቱን ለሀገር የሰጠው ወታደር በእድሜ የገፉ ዜጎች እንደነዚህ አይነት እንክብካቤ ይደረግላቸዋል።
አዲስ ዘመን፡- እንደነገሩኝ ክልላዊ መንግስታት ትልቅ ትብብር እያደረጉ ነው። ቅርንጫፍ ቢሮዎችን የመክፈቱ ነገርስ ?
ዶ/ር አዳሙ፡- አሁን የጀመርነውን የመጀመሪያውን እንሞክረው ። ኋላ ላይ ከዚህ የምንወስደው ጠንካራና ደካማ ጎን ብለን የምንፈትሸው ይኖራል። ከዚያ ጥናት ተነስተን ነው የት ላይ ነበር ድክመቱ፤ ለምንስ በተለያየ ቦታ አይሆንም የሚለውን በኋላ የምናየው። አሁን ያተኮርነው ሥራውን የበለጠ ለማሳካት ሀብት ማሰባሰቡ ላይ ነው ። አቅማችን እንዳይበታተን ጥንቃቄ እናደርጋለን።
አዲስ ዘመን፡- ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴያችሁ ምን ያህል ሰው አለው ?
ዶ/ር አዳሙ፡- በቦርድ ነው የሚመራው ። የቦርዱ የበላይ ጠባቂ ክብርት ፕሬዚዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ ናቸው ። ቀጥሎ የእለት ተእለት ስራውን የሚመሩ የሚከታተሉ የማኔጅመንት አካላት አሉ። አሁን ቢሮአችን ያለው መስቀል አደባባይ ነው ። ስራችን ሀብት ማሰባሰብ፤ በየቦታው ጉዞ ማድረግ፤ በጣም ከፍተኛ ግንኙነቶችን መፍጠር ላይ ነው ያተኮርነው ።
በተለይ አሁን በቅርቡ ከህወሓት ጋራ በተደረገው ጦርነት የተጎዱ የጦር ጉዳተኞች አሉ ። የቀድሞዎቹም አሉ ። እነዚህ አንድ ላይ ወደ ጀግኖች አምባ ከገቡ በኃላ በቀጣዩ ደግሞ የት አካባቢ ነው በብዛት እንዲህ አይነት ችግር ያለው የሚለውን እናየዋለን ።
በስፋት እናጠናለን ። አሁን አብዛኛውን ግዜያችንን ለዚህ ስራ ሰጥተን እየሰራን ነው ። የድርጅቱን ሕጋዊ ፈቃድ ከወሰድን ሁለት ወይ ሶስት ወር አካባቢ ይሆናል ። በጣም ፈጣን እንቅስቃሴ እያደረግን ነው ። መንግስትም የተገነዘበው ይሄንኑ ነው።
አዲስ ዘመን የካቲት 15/2013