ዳግም ከበደ
በተለምዶ የፋሽን ሳምንት እየተባሉ የሚጠሩ ዝግጅቶች በዓለማችን ላይ በበርካታ አገራት ይካሄዳሉ። ከእነዚህ ዝግጅቶች መካከል አንዳንዶቹ ዓለም አቀፍ ይዘት ሲኖራቸው ቀሪዎቹ ደግሞ በየአገራቱ ውስጥ ተወስነው የሚደረጉ ናቸው።
በዛሬው የፋሽን አምዳችን በዓለም አቀፍ ደረጃ የዘርፉን ተከታዮችና የመገናኛ ብዙኃን ቀልብ መሳብ የቻሉ ዝግጅቶችን እንቃኛለን።
በፋሽን ሳምንቶቹ ላይ አልባሳት፣ አዳዲስ የዝነጣ የፈጠራ ውጤቶች፣ ባህልን፣ ልማድን፣ ወግን የሚያንፀባርቁ ቁሳቁስን ጨምሮ የመዋቢያ ጌጣጌጦችና ሜካፖች ለእይታ ይቀርባሉ። በዘርፉ ላይ ለዓመታት የቆዩ ባለሙያዎችና አዳዲስ ራሳቸውን ከሚያስተዋውቁበት አጋጣሚ ባሻገር በደማቁ ትእይንት ላይ ተውበው የመታየት አጋጣሚው ይፈጠርላቸዋል።
በተለይ ይህን መሰል ዝግጅቶች የመገናኛ ብዙኃን ቀልብን በሰፊው ከመሳባቸው የተነሳ ለቀናት ለፋሽን ተከታዮች ይፋ የሚሆኑ ሥራዎች አነጋጋሪነታቸው ይጨምራል። በፋሽን ሳምንቶች ውስጥ ታዋቂ ግለሰቦች፣ አርቲስቶች፣ የፊልም ተዋንያን የሚደምቁበት አጋጣሚም አለ፡፡
ይህ ብቻ ሳይሆን በውበት እና በተለያዩ ቁሳቁስ ላይ ዲዛይነሮችና የሥነ ውበት ባለሙያዎች የተጠበቡበትን የፈጠራ ውጤት የሞዴሊንግ ክህሎት ያላቸው ቆነጃጅት ይዋቡበትና ዝግጅቱን ይበልጥ ልብ አንጠልጣይና ተወዳጅ ያደርጉታል።
በዓለማችን ላይ እጅግ ከሚታወቁ የፋሽን ሳምንታት ውስጥ በቀዳሚነት የሚጠቀሱት በፓሪስ፣ ሚላን፣ ሎንዶንና ኒውዮርክ ከተማዎች የሚዘጋጁት ናቸው። እነዚህ የታላላቁ አገራት ዋና ከተማዎች ተወዳጅ የፋሽን ሳምንታትን በማዘጋጀት የሚታወቁ ናቸው።
ለዛሬ በዓለማችን አንፀባርቀው የሚታዩ ውብ የፋሽን ሳምንቶች እንዲስፋፉና የተለመደ ዘመናዊ ባህል የሆኑበትን አጋጣሚ ለመመልከት እንሞክራለን። በዋናነት ግን የፋሽን ሳምንቶች እንዴት ተጀመሩ የሚለውን ጉዳይ ለማንሳት በርካታ ዓመታትን ወደኋላ መመለስ ያስፈልጋል።
ጥቂት ወደ ኋላ
የፋሽን ሳምንቶች ለሕዝብ ክፍት በሆኑ ቦታዎች ላይ የተለያዩ አልባሳትና ጌጣጌጦችን በማሳየት የሚደረጉ ዝግጅቶች ናቸው። ይህ ዓይነት ፅንሰ ሃሳብ በይፋ መተዋወቅ የጀመረው በፈረንሳይ ፓሪስ ከተማ ነበር። በዋናነት አዳዲስ አልባሳትና የመዋቢያ ጌጣጌጦች ለገበያተኛው ማቅረብ በሚያስፈልግበት ወቅት ዲዛይነሮችና የፈጠራው ባለቤቶች በፓሪስ ጎዳናዎች ላይ ቆነጃጅቶች ሥራዎቻቸውን እንዲያሳዩላቸው መመልመል ጀመሩ። በዚህ አጋጣሚ በአደባባዮችና ለእይታ ምቹ በሆኑ ስፍራዎች ላይ በዲዛይነሮች የተሰሩ የመዋቢያ ቁሳቁስን በይፋ አስተዋወቁ። ይሄ እንቅስቃሴ ቀስ በቀስ
የፋሽን አብዮት በመፍጠር እነዚህን ተወዳጅ ሳምንታት መፍጠር ቻለ። ከፈረንጆቹ የዘመን አቆጣጠር ከ1900 እና ከዚያ በፊት ያለው ጊዜም የፋሽን ሳምንታት ቀስ በቀስ እያደገ የመጣበት በሚል ይታወቃል።
የፋሽን ሳምንታት በኢትዮጵያ
ባህላዊ ሀብቶቻችንን ለቀሪው ዓለም ከምናስተዋውቅበት መንገድ አንዱ የፋሽን ኢንዱስትሪው ነው። ይህ ዘርፍ በዓይነተ ብዙ መንገዶች እድገት አሳይቶ ስኬት ላይ የሚደርስ ከሆነ በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ባህላዊ እሴቶቻችንን ሳንበርዝ ለቀሪው ዓለም ማስተዋወቅ ያስችለናል። ከዚህ ባለፈም አገራችን ኢትዮጵያ የፋሽን ቱሪዝም ተደራሽ ሆና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት እንዲኖራት ያስችላል።
ከላይ ያነሳነውን ጥረት ከስኬት ለማድረስ ደግሞ ልክ ዓለም አቀፍ የፋሽን ሳምንቶች እንደሚካሄዱት ሁሉ በአገራችንም በስፋት ሊለመዱ ይገባል። ያን ጊዜ የተፈለገው ግብ ላይ ለመድረስ ሰፊ መንገድ ማበጀት ይቻላል። ለመሆኑ በኢትዮጵያ ውስጥ የፋሽን ሳምንት
የማዘጋጀት ተሞክሮ ምን ይመስላል?
የተለያዩ የፋሽን ሳምንቶች በኢትዮጵያ ውስጥ ሄድ መለስ እያሉ ቢታዩም ያን ያህል ዘርፉን ለማሳደግ በሚያስችል ሁኔታ ግን ተጠናክረው ሲቀጥሉ አይስተዋልም፡፡ ለዚህ በዋናነት እንደ ችግር የሚጠቀሰው ደግሞ የፋይናንስ አቅምና በዘርፉ በቂ ባለሙያ አለመኖር ነው።
በአዲስ አበባ የዲዛይን ሳምንት የማስተናገድ ሀሳብ ከተጀመረ አምስት ዓመታት ተቆጥረዋል። ዲዛይን ዊክ አዲስ አበባ የሚል መጠሪያም ስም የተሰጠው አንድ እንቅስቃሴ አለ። የዲዛይን ሳምንቱ በፈጠራ ዘርፍ ያለውን እንቅስቃሴ ለማስተዋወቅና ለማጠናከር እንደተወጠነ የዲዛይን ዊክ አዲስ አበባ መስራቾች ከዚህ ቀደም በተዘጋጀ የፋሽን ሳምንት ላይ መግለፃቸው ይታወሳል።
በዲዛይን ዊክ አዲስ አበባ ከተካተቱ ዘርፎች ውስጥ የሥነ ሕንፃና የከተማ ዲዛይን፣ ፋሽንና ጨርቃ ጨርቅ፣ ቴክኖሎጂ፣ ግራፊክ ዲዛይን፣ የምግብ አዘገጃጀት ይገኙበታል። ይህን መሰል ዝግጅቶች በኢትዮጵያ ውስጥ ሊበረክቱ ይገባል።
ፓሪስ ዲዛይን ዊክ፣ ኒው ዮርክ ዲዛይን ዊክ፣ ኢስታንቡል ዲዛይን ዊክ፣ ዱባይ ዲዛይን ዊክ የሚባሉት ዓለም እውቅናን ካተረፉ የዲዛይን መሰናዶዎች ቀዳሚ መሆናቸው ይጠቀሳል። በኢትዮጵያ የሚካሄዱ ጅምር የዲዛይንና የፋሽን ሳምንቶች እዚህ የማይደርሱበት አጋጣሚ ስለማይኖር ጫንቃን ደደር አድርጎ ለስኬት መስራት ያስፈልጋል።
ቢያንስ ለአንድ ሳምንት በሚካሄዱት የዲዛይን መሰናዶዎች ሥነ ሕንፃ፣ ሥነ ጥበብ፣ ቴክኖሎጂና ፋሽንን ጨምሮ በርካታ ዘርፎች ይዳሰሳሉ። የፈጠራ ባለሙያዎች ሥራዎቻቸውን ያሳያሉ፤ ግብይት፣ ውይይትና የልምድ ልውውጥም ይደረጋል። እነዚህ ዓለም አቀፍ የዲዛይን መድረኮች ከሚሰናዱባቸው ሀገሮች ባለፈ ከሌሎች አገራትም ታዳሚዎችን መሳብ ይቻላል።
ከዚህ መነሻ የፋሽን ሳምንታት መስፋፋት አስፈላጊ መሆን እንዳለባቸው ሊሰመርበት ይገባል። የዝግጅት ክፍላችን በቀጣይ ጊዜያት የፋሽን ዊክ አዘጋጆችን በመጋበዝ ዘርፉ ላይ ያሉ ክፍተቶችን መልካም አጋጣሚዎችን እንዲሁም አሁን ላይ የሚገኙበትን ደረጃ ይዳስሳል። ቸር እንሰንብት!
አዲስ ዘመን የካቲት 15/2013