አስመረት ብስራት
መጀመሪያ ከእኛ ልጀምር ወይስ ከነሱ? ምን እየተሰማኝ እንደሆን እንጃ። ከእኛ ልጀመር፤ የፍቅር ቄጠማ ጎዝጉዘን የተዋቡ ጊዜያት በቀጨንባቸው በፍቅረኝነት ዘመናችን የማያልቅና ጥግ የሌለው በሚመስሉ የፍቅር ባህር ውስጥ የሰመጥንባቸው ውብ ዓመታት፤ ሙሽርነት ጫጉላ ትዳር በልጅ ያልታጀቡ አስር ዓመታት ከፍቅር ሙቀት የዕለት ከዕለት ልምምድ ውስጥ ራስን ማመላለስ የእኛ መጀመሪያም እስካሁንም ይህ ብቻ ነው።
የነሱ፤ የባሌና የሷን ማለቴ ነው። መጀመሪያ ረዘም ያለ የፀጉር ዘለላ ከኮቱ ስር መዘዝ አድርጌ አወጣሁ፤ በጥርጣሬ ራሴን ዳበስኩ በዛ ቁመት ልክ ፀጉሬን አይቼው አላውቅም:: ስለዚህ የመጀመሪያው ቀን መረጃዬ ከነቀኑ ከነሰዓቱ ተቀምጧል። ሁለተኛ የከንፈር ቀለም በሸሚዙ ኮሌታ ላይ፤ ሦስተኛ እኔ የማላቀው ሽቶ አራተኛ አምስተኛ… እያለ ቀኑ ተከታተለ። ምንም አዲስ ነገር እንዳልሆነ ሆኖ ድግግሞሹ ቀጥሏል።
እንደሁልጊዜው ጠዋት ቀድሞኝ የተነሳው እሱ ነው፡፡ ከኩሽናው ቁርስ እያበሰለ የሚያማስለው የመጥበሻ ድምፅ ይሰማኛል:: ስልኩ መልዕክት ሲቀበል ድምፅ አሰማ። ለወትሮው ስልክ ማየት ማገላበጥ ብዙም ውስጤን ምቾት ስለማይሰጠው አላደርገውም፡፡ ዛሬ ግን ግማሽ ልቤ ተይ ቢለኝም ከግማሽ ልቤ ጋር ተስማምተን ስልኩን አነሳሁት::
«የተለመደው ቦታ በተለመደው ሰዓት እጠብቅሃለሁ፤ አፈቅርሃለሁ!» የሚል መልዕክት ነው። በየዕለቱ ያጠናቀርኩት መረጃ ውጤት ይሁን የቅናት ውስጤ ያለው መረጋጋት ዛሬ ከስሜት በላይ ሆኖብኝ አላውቅም:: ውስጤም ደስ በሚል ሞቅታ ለመሞላቱ ምክንያት ግራእየተጋባሁ እጠይቃለሁ እኔና እሱ የተለመደው የምንለው ቦታ ኖሮን አያውቅም!!
ከቤታችን ውጪ ሁለተኛ የተለመደ ሰዓት አላቸው:: እኔና እሱ ለምንም የተለመደም ወይም የተመደበ ቦታም ይሁን ሰዓት የለንም:: የልደት ቀኖቻችንን እንኳን እረስተነው አልፎ «ለካ ትናንት ነበር» የምንባባልበት ጊዜ አለ:: ማንም ሰው ሊረሳው ይከብደዋል የሚባለው የጋብቻ ቀናችንንም እንኳን የምናስታውሰው በወሬ ተነስቶ «በስመ አብ ጊዜው እንዴት ይሮጣል አስር ዓመት ሞላን» ስንባባል ነው።
ከሁሉም የገረመኝ ደግሞ ታፈቅረዋለች:: ይሄ ሲሰላ ቀመሩ እሱም ከኔ በላይ ያፈቅራታል ማለት ነው ወይስ ወረት ሆኖበት? ምንድነው እየተሰማኝ ያለው? እኔ.ጃ ….. ቁርሱ ደርሷል። ከዚያን ቀን ቀድሞ አልጋዬ ላይ የምጠብቀውን ቁርስ በፍጥነት ተጣጥቤ በልኬ ተቆነጃጅቼ መመገቢያው ጠረጴዛ ላይ ተቀምጬ አገኘኝ፡፡ «ምን ተገኘ?» ሲለኝ፤ ትከሻዬን ሰበቅ አደረኩኝ በግዴለሽነት፡፡
ዓይን ዓይኔን ያየኛል። አቀርቅሮ ቀና ሲል «ምን ተገኘ?» ይለኛል አስሬ የሰራልኝን ቁርስ እያጎረሰኝ «ምነው?» «በጣም ደስ ብሎሻል! ይሄን ፈገግታ ካየሁት የማላስታውሰውን ያህል የጊዜ ርዝመት ያህል ዘመን ሆኖ ነበርኮ!» አለኝ በፈግታ።
ዝም አልኩ «እያመነዘርክብኝ እንደሆነ ሳውቅ ነው ደስ ያለኝ! ልበል ወይስ ቅናት አናቴን አዙሮኝ የሚባለው ጠፍቶኝ ነው ደስ ያለኝ ልበል። ቁርሱ ተጠናቆ «አንድ ቦታ ደርሼ መጣሁ» ብሎ ለመውጣት ይለባብሰ ጀመር።
«እሱን ሸሚዝ ቀይረው:: ሰንበተ አይደል? ፈካ ያለ ነገር ልበስ.. ቆይ እኔ ልምረጥልህ!» ብዬው ቄንጠኛ ሸሚዝ እፈልግ ጀመር … ምን እያደረኩ ነው? ለምን አልተናደደኩም? ለምን መዘነጡን ፈለኩ ብቻ እንጃ ራሴን እየፈራሁት ነው።
አንዴ ፀጉሩን አንዴ ጫማውን … ደግሞ ኮሌታውን ሳስተካክልለት ግራ ተጋብቶ ያየኛል:: ይባሰ ብዬ የምሰስትለትን ሽቶ አውጥቼ ራሱ ላይ አርከፈከፍኩት። ባሌ ሊያመነዘርብኝ እየሄደ እንደሆነ እያወኩኝ ለምን አልከፋኝም። ለምን ጭርሱኑ ውስጤ በደስታ ተሞላ ስለተደራቢዬ ዝም ብዬ አስባለሁ።
ለምን አልከፋኝም የአስር ዓመት ትዳሬ ነው እኮ፡፡ የመጀመሪያው ትሆን እንዴ? እንዳገባስ ታውቅ ይሆን? ሄዶ ሲስማት የኔን ትራፊ እንደምትስም ታውቅ ይሆን? እቤቱ ሲገባ የሚያስኮንን አፍቃሪ መሆኑን ታውቅ ይሆን? የመጽሐፉን ቃል ስለማስፈረሱስ ይገባት ይሆን? ዛሬም ከ10 ዓመት በኋላ እያጎረሰኝ እንደምበላ ታውቅ ይሆን? ወይስ እሷም ጋ ዝንፍ የማይል የማይጎልበት ተንከባካቢ የፍቅር ሰው ይሆን ይሆን?
በሀሳብ እየተላጋሁ ከተቀመጥኩበት ሳልነሳ የቀኑ እኩሌታ ላይ ተመልሶ መጣ «የሄድክበት ጥሩ ነበር?» ጥያቄዬን ሳይመልስ ደግሜ «ቆየህ» አልኩት። «ፍቅር ከተለያየን ግማሽ ቀን አልሆነም እኮ» አለኝ ከሷ ጋ እንደመጣ «ቢሆንስ» አልኩት «እሺ ቆንጆ ነበር!» አለኝ መገረም ሳይለየው
ምነ አውርተው ይሆን? ተጣልተው ይሆን? ተጨቃጭቀው? ለምንድነው የተለየ ፊት የማያሳየው? ምን ዓይነቷ ናት? ለምን በደስታ ጎርፍ እንዲወሰድ አላደረገችውም? ወይስ እሷም እንደኔ መፈቀር ደከማት? እንክብካቤ ሁሌ ምቾት አንገሸገሻት?
ይሄን እያሰብኩ አጠገቡ እንደ አሻንጉሊት ቀጥ እንዳልኩ ጉብ አልኩኝ። ጎተት አደረገኝ!! «እንዳትነካኝ!» አልኩት ኮስተር ብዬ «እንዴ? ለምን?» «የራሴው ገላ አይደል?» «አዎ»«እንደገና ደግሞ የራሴው ሰውነት አይደል? ራሴው አይደል ይዤው የምዞረው?»
«እንዴ ፍቅር ምን ሆነሻል?»
«ሌላ ደግሞ አንዳንድ ጊዜ ተሸከምልኝ ብዬ አላስቸገርኩህም አይደል? ደሞም በገቡ በወጡ ቁጥር ምንደነው መጎነታተል?» ቅናት አቅሌን ሊያስተኝ ነው መሰል ሳላውቀው እየጮህኩ ነው።
«ምንድነው ጉዱ?»
«የምን ጉድ? እ? አትንካኝ ማለት ምንድነው ጉዱ ያስብላል? መልሰ ከሌለህ አበቃሁ!!» ብዬው ማሳረጊያ የተለመደ ፈገግታ ፈገግ ብዬ ከአጠገቡ ተነስቼ ጥዬው ሄድኩ::
ተከተለኝ፡፡ መኝታ ቤት ገብቼ በሩን ቆልፌ ተቀመጥኩ። ምን እያሰበ ነው? ከኔ ያጣ የመሰለውን ልጅ ፍለጋ ሊሄድ ይሆን? መውለድ እያማረኝ ችግሩ ከእሱ እንደሆነ እያወኩኝ እንኳን የሆዴን በሆዴ ይዤ እንደተቀመጥኩ ያውቅ ይሆን?
የሱ መሄድ ልቤን ጮቤ ያስረገጣት በራሴ ላይ የጠመጠምኩትን የፍቅር ሰነሰለት በጣጥሶ የሚያስጥል ክህደት ስለገጠመኝ ይሆን?
አስቦት የሄደው ነገር ሳይሳካለት ሲቀር፤ እኔ ለሱ ስል ዝም እንዳልኩ ሲያስበውስ እራሱን በምን ይቀጣ ይሆን? ወይስ ምንም እንዳልተፈጠረ እሱም በተለመደው መንገድ ያቀና ይሆን?
ብቻ እንጃ ለዛሬው የቅናት ዛር ይሁን የደስታ ባህር እንጃ!!!! የተዘፈኩበትን ሳላውቀው በሩን ተደግፌ እንደተቀመጥኩኝ ሰዓታት ነጎዱ።
እየተመላለሰ በሩን ሲሞክር እየሰማሁ ዝም ብያለሁ። መልካም ትዝታው ሁሉ ከውስጤ ድርግም ብሎ ሲጠፋ የነፃነት ንፋስ በራሴ ላይ ሽው ሲል እየተሰማኝ አሁንም ዝም ብያለሁ። ለዓመታት የተዳፈነው ቁስል ባልተገባ ሁኔታ ስለተነካ ይሆን ወይስ እንጃ…….
ለፍቅር የተከፈለው የሰው ልጆች ሁሉ ዘር የመተካት ፍላጎት እንደትንሽ መስዋእት እንደ አልባሌ ስለተቆጠረ ይሆን ብቻ እንጃ….. አሁንም እያሰብኩ ነው።
አዲስ ዘመን የካቲት 12/2013