ዳንኤል ዘነበ
የስነ-አዕምሮ ሳይንስ በዓለም በተለይም በአፍሪካ ገና በማቆጥቆጥ ላይ እንዳለ በስነ-አዕምሮ ህክምና ዙሪያ የተፃፉ የተለያዩ መዛግብት ያስረዳሉ።በሃገራችን ኢትዮጵያ የአዕምሮ ሕመምን በተመለከተ በተለምዶ የሚሰነዘሩ የተለያዩ አባባሎች ያሉ ሲሆን በሕክምናው ደረጃ አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማት ቁጥርም በጣም ውስን ነው።
ከ1930 ዓ.ም ጀምሮ በሃገራችን ውስጥ በብቸኝነት የአዕምሮ ሕክምና አገልግሎቱን እየሰጠ የሚገኘው የአማኑኤል አዕምሮ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ‹‹አንድ ለእናቱ›› ነው።የአዕምሮ ሕመም ማለት፡-
- ከተለመደውና ትክክለኛ ከሚባለው ውጭ የአስተሳሰብ፤ የስሜት ወይም የባህሪ ለውጥ ሲኖር እና ከባድ የአዕምሮ ጭንቀት ሲያስከትል ለራሱ ጭንቀትን የሚፈጥር ከሆነ፣
- በሕመም ምክንያት የሚፈጠረው የግለሰቡ ባህሪ ለውጥ በማህበራዊ ግንኙነት ወይም ከሰዎች ጋር በመግባባት አብሮ ለመኖር እንቅፋት ከሆነ፣
- በተጨማሪም ከነባራዊ እውነታዎች መውጣትና ሌሎች ሊጋሯቸው በማይችሉት የራስ አለም ውስጥ መገኘት፣
- እንዲሁም ከህመም የተነሳ ሌሎች ማህበራዊ ግንኙነቶች ሲዛቡ የአዕምሮ ሕመም ተከሰተ እንላለን፡፡
የአዕምሮ ጤና ማለት ምን ማለት ነው?
የአዕምሮ ጤና ማለት እንደ የዓለም ጤና ድርጀት አገላለጽ ‘’የራስን ማንነት አውቆ ራስን መምራት መቻል፤ ሃላፊነትን ማወቅና መወጣት፤ ምክንያታዊ ካልሆነ ጭንቀት ነጻ የሆነ ህይወት መምራት መቻል እንዲሁም ካለበት ማህበረሰብ ጋር በመግባባት ተግባርን ማከናወንና በማህበረሰቡ ተቀባይነት ያለው የኑሮ ዘይቤን የመከተልን ሁኔታ’’ ያመለክታል፡፡
በተቃራኒው የአዕምሮ ሕመም ክስተቶች ዙሪያ ሳይንሳዊ የሆነና ተጨባጭ መረጃ ላይ የተመሰረተ ትምህርት ያልተስፋፋ በመሆኑ አብዛኛው የህብረተሰብ
ክፍል ስለ አዕምሮ ህመም ያለው ግንዛቤ በጣም አነስተኛና በባህል ሲወርድ ሲዋረድ በመጡ አባባሎች ላይ የተመሰረተ ነው፡፡
የአዕምሮ ህመም አባባሎች እንደሚሉት ልክፍት ወይም ቁጣ ሳይሆን ማንኛውም የሰው ልጅ አካል እንደሚታመም ሁሉ አዕምሮኣችንም ይታመማል፤ በተለያዩ ምክንያቶችም መረበሽ ይደርስበታል።ስለ አዕምሮ መረበሽ ሦስት ዋና ዋና እውነታዎች ይጠቀሳሉ፡፡
- 1የአዕምሮ ሕመም የርኩስ መንፈስ ውጤት ሳይሆን እንደ ማንኛውም የሰውነት ሕመም በተወሰነ የክፍሉ አካል (አንጎል) መታመም የተነሳ የሚፈጠር ነው፣
- አብዛኛው የእርስ በእርስ ሰላም ማጣት፤ ካለመከባበር እና ካለመተባበር ጋር ይያያዛል፣
- የአዕምሮ ሕመም እንደማንኛውም የአካል ሕመም በአብዛኛው በህክምና ሊድን ይችላል፡፡
የአንድ ሰው አዕምሮ ጤነኛ አይደለም የሚባለው መቼ ነው?
አዕምሮን ጤነኛ ወይም ሕመምተኛ ብሎ ለመፈረጅ የሚያስችል መስፈርት ወይም መመዘኛ ግልፅ በሆነና ሁሉም ሰው ሊስማማበት በሚችል መልኩ የተቀመጠ አይደለም።
የአንድ ሰው አዕምሮ ጤነኛ ወይም ሕመምተኛ ለማለትና ለመገምገም እንደየህብረተሰቡና እንደየአካባቢው ባህልና ግንዛቤ እንደሚወሰን የህክምና ባለሙያዎች ያስረዳሉ።በዚህም የአንድ ሰው አዕምሮ ጤነኛ አይደለም ለማለት ከሚያስችሉ አጠቃላይ መስፈርቶች ከሚከተሉት አንዱ ወይም ከአንድ በላይ ሲኖረው እንደሆነ አብዛኞች ምሁራን ይስማማሉ፡፡
ሀ/ የግለሰቡ አዕምሮ ለራሱ ጭንቀትን የሚፈጥር ከሆነ፤
ለ/ የግለሰቡ አዕምሮ ለማህበራዊ ግንኙነት ወይም ከሰዎች ጋር በመግባባት ለመኖር እንቅፋት የሚሆን ከሆነ፤
ሐ/ በራሱ በግለሰቡ ወይም በሌሎች ላይ የአካል፤ የመንፈስ ወይም ማህበራዊ ቀውስን የሚያስከትል ከሆነ፤
መ/ ግለሰቡ የሚጠበቅበትን ቤተሰቡን፤ የመንግስት ስራን፤ ትምህርትን ወይም ማህበራዊ ኃላፊነቱን በአግባቡ እንዳይወጣ ባህሪው እንቅፋት ከሆነውና የመሳሰሉት ሲከሰቱ/ሲታዩ የግለሰቡ አዕምሮ ጤነኛ አይደለም ለማለት ያስችላል።
የአዕምሮ ሕመም መንስኤ
የአዕምሮ ሕመም መንስኤዎች በሶስት ዋና ዋና ክፍሎች ሊመደቡ ይችላሉ። አንደኛው አካላዊ ወይም ስነ-ፍጥረታዊ (Biological)፣ ሁለተኛው ስነ-ልቦናዊ (Psychological) እና ሶስተኛው ደግሞ ማህበራዊ (Social factors) መንስኤዎች ናቸው።
የአዕምሮ ሕመም ምልክቶች/Symptoms
የአዕምሮ ሕመም ምልክቶች የምንላቸው የአካል ችግር (የእንቅልፍ፣ የወሲብ፣ የምግብ ፍላጎቶች መብዛት ወይም ማነስ)፤ የባህሪ ችግሮች (ከዚህ በፊት በግለሰቡ ላይ የማይታዩና እንግዳ የሆኑ ባህሪያት መታየት)፤ ማህበራዊ ችግሮች (በማህበራዊ ግንኙነት ላይ ያለምክንያት የተለያዩ ጠባዮችን ማንፀባረቅ)፤ በስራ ላይ ችግር መፍጠር (የስራ ምርታማነትና የፈጠራ ችሎታ መቀነስ፣ ፍላጎት ማጣትና የማስታወስ ችግር) ናቸው።
የአዕምሮ ሕመም ሊድን ይችላል?
የአዕምሮ ሕመም መዳን የሚችል ሲሆን ሙሉ ለሙሉ መዳን የማይችሉ ጥቂት ዓይነት የአዕምሮ ሕመም ዓይነት መኖራቸውን ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ከዓለም ጤና ድርጅት ጋር በጋራ በመሆን በ1993 ዓ.ም ‘’የአዕምሮ ደህንነት’’ በሚል ባሳተመው መፅሐፉ ላይ ያትታል።ነገር ግን እነዚህን ሕመሞችንም ቢሆን በአብዛኛው ለታማሚውና ለቤተሰብ ተጨማሪ ጉዳት እንዳይፈጥሩ በህክምና መቆጣጠር እንደሚቻልና ለአዕምሮ ሕመም ችግሮች እንደ ሕመሙና ታማሚው ልዩ ስብዕና የተለያዩ የህክምና ማስተካከያ ዘዴዎችና መድኃኒቶች እንደሚገኙ ያስቀምጣል።
ከአዕምሮ ሕመም ዓይነቶች ጥቂቶቹ፡-
• ስኪዞፍሬኒያ (Schizophrenia/Psychosis)
- ድባቴ (Depression)
- የሁለት ተቃራኒ ጫፍ ተለዋዋጭ ስሜት (Bipolar Disorder)
- በአደንዛዥ እጽ ሱስ ሳቢያ የሚመጣ የአእምሮ ህመም (Mental illness due to substance use disorder)
- አንድን ነገር ለማድረግ ከውስጥ የሚወጣ አስገዳጅ ነገር ግን ተገቢ ያልሆነ ከፍተኛ ፍላጎት(Obsessive Compulsive Disorder)
- የጭንቀት ህመም (Anxiety Disorder)
- ከእርጅና ጋር ተዛማጅ የሆኑ የመርሳትና የማገናዘብ ችግሮች (Old age related cognitive disorder) የሚጠቀሱ ሲሆን የአዕምሮ ህመም ምልክቶች በጣም የተለያዩ ሲሆኑ ልዩነቶቹ እንደ የሕመሙ ዓይነትና ደረጃ የሚወሰኑ ናቸው።
በአጠቃላይ ሁሉም ሰው ያለአዕምሮ ጤና ጤንነት ያለመኖሩን ተገንዝቦ የአዕምሮውን ጤና መጠበቅና መንከባከብ ይኖርበታል። በመሆኑም የአዕምሮ ጤና ጉዳይ የሁላችንም ጉዳይ ነውና ለአዕምሮ ሕሙማን ተገቢውን እንክብካቤ ልናደርግ ይገባናል፡፡
አዲስ ዘመን የካቲት 11/2013