ወርቁ ማሩ
አገራችን ካለፉት ሶስት ዓመታት ወዲህ በለውጥ ሂደት ውስጥ ትገኛለች። ይህ ለውጥ በአንድ በኩል በህብረተሰቡ ውስጥም ሆነ በመላው ዓለም በርካታ ተስፋዎችን ያጫረ ሲሆን፤ በአንጻሩ ደግሞ በርካታ ተግዳሮቶችንም እያስተናገደ ያለ ነው።
በተለይ ለውጡን የማይፈልጉ የውስጥና የውጭ ኃይሎች ይህ ለውጥ እንዳይመጣ ሴራ ከመሸረብ ጀምሮ ከለውጡ በኋላም ለውጡን ለመቀልበስ ያልፈነቀሉት ድንጋይ፣ ያልማሱት ጉድጓድ ያለም። በተለይ በህወሓት ጁንታ የሚመራው የለውጥ አደናቃፊ አካል ስልጣን ካልያዝኩ አገር ትፍረስ በሚል ግልፅ ፕሮፖጋንዳ አገርን የማተራመስና የማፍረስ ጥረቱን ሌት ተቀን ሰርቷል። ለዚህ የተጠቀመው ዋነኛ ስልት ደግሞ ለዓመታት በአንድነትና በፍቅር የኖሩ ሕዝቦችን እርስ በርስ ማጋጨትና በመካከላቸው መተማመን ማጥፋት ነው።
ከዚህ አንጻር የነዚህ አካላት ሰለባ ከሆኑ አካባቢዎች አንዱ የቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል መተከል ዞን ነው። በዚህ አካባቢ ህብረተሰቡ ለዘመናት አብሮ የኖረ፣ የተዋለደና በአገራዊ አንድነት የሚያምን በመሆኑ ይህን አካባቢ ማበጣበጥ ከተቻለ አገር ማበጣበጥ ይቻላል የሚል ዕቅድ ይዞ ሲሰራ እንደነበር ብዙዎች ይናገራሉ። በዚህም በርካታ ዜጎች በግፍ ተገድለዋል፤ በሺዎች የሚቆጠሩት ደግሞ ተፈናቅለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ያዋቀሩት የተቀናጀ ግብረሃይል ችግሩን ለመፍታት በአካባቢው ከተሰማራ ከአንድ ወር በላይ ሆኖታል። እኛም በዚሁ ዙሪያ የግብረሃይሉ የፖለቲካዊና ማህበራዊ ጉዳዮች ዘርፍ አስተባባሪ የሆኑትን አቶ ተስፋዬ ቤልጂጌን በጉዳዩ ዙሪያ አነጋግረናቸዋል፤ እንደሚከተለው አቅርበነዋል።
አዲስ ዘመን፡– በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል ላለፉት 27 ዓመታት የነበረው ፖለቲካዊ ፣ ምጣኔ ሀብታዊና ማህበራዊ ሕይወት እንዴት ይገለጻል ?
አቶ ተስፋዬ፡– እንደሚታወቀው ኢሕአዴግ የአራት ድርጅቶች ግንባር ሆኖ ነው አገር ሲመራ የነበረው። ከለውጡ በፊት በነበሩት 27 ዓመታት የቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል አጋር ድርጅት ተብሎ የሚጠራ ነበር። በሌላ በኩል ደግሞ በክልሉ በርካታ ኢትዮጵያውያን በጋራ የሚኖሩበት አካባቢ ነው። በዚህ የተነሳ በብዝሃነት የሚታወቅ አካባቢ ነው። ኦሮሞ፣ አማራ፣ ሺናሻ፣ ጉምዝ፣ በርታ፣ ማኦ ኮሞ እና ሌሎችም ኢትዮጵያውያን በአንድነት የሚኖሩበት ክልል ነው። ከዚህም ባሻገር ታላቁ የህዳሴ ግድብ የሚገነባው በዚሁ ክልል በተለይም በመተከል ዞን ውስጥ ነው። አካባቢው በተፈጥሮ ሀብት እጅግ በጣም የሚታወቅ አካባቢ ነው። ለኢትዮጵያ ዕድገትም አንድ ኮሪደር መሆን የሚችል ነው። ነገር ግን በ27 ዓመታት ውስጥ የተገኙ የተወሰኑ ለውጦች ቢኖሩም ከሕዝብ ተጠቃሚነት አኳያ ብዙ ያልተሠሩ ነገሮች ነበሩ። በጣም ብዙ የሕዝብ ጥያቄዎች ያሉበት አካባቢም ነው። “አለማንም” የሚል ቅሬታ የሚያነሱ በርካታ የሕብረተሰብ ክፍሎች ያሉበት አካባቢ ነው። ስለዚህ ከለውጡ በፊት በነበሩት 27 ዓመታት የተጀመሩ የተወሠኑ ሥራዎች ቢኖሩም ብዙ ያልተመለሱ ጥያቄዎች ያላቸው የሕብረተሰብ ክፍሎች ያሉበት አካባቢ ነው።
አዲስ ዘመን፡- ከለውጡ ማግሥት ጀምሮ በክልሉ ያለው የሠላም መደፍረስ መሠረታዊ መነሻ ምንድነው ?
አቶ ተስፋዬ፡- መተከል ዞን በባህርይው ሕብረ ብሄራዊነት ከሚታይባቸው የሀገሪቱ ክፍሎች ውስጥ አንዱ ነው። ዞኑ ውስጥ ብዙ ቋንቋ ተናጋሪ ኢትዮጵያውያን ይኖራሉ። እጅግ በጣም የተሠባጠረ ዞን ነው። እዚያ አካባቢ የሚኖሩት ሕዝቦች ደግሞ ቀደም ሲል እስከ 2010 ዓ.ም ድረስ በሠላምና በአብሮነት በመኖር ነው የሚታወቁት። እንደቅርብ ጊዜው ዓይነት የተፈጠረ የጎላ ችግርም እዚያ አካባቢ አይታወቅም። ነገር ግን በለውጡ ማግሥት ብዙ ለውጡን የማይቀበሉ ሃይሎች ችግር ለመፍጠር ሲያስቡ ምቹ ነው ብለው ያሠቡት ይህን አካባቢ ነው።
በዚህ መልኩ የወሰዱበት ምክንያትም አንደኛው የተለያዩ ኢትዮጵያውያን በጋራ የሚኖሩበት አካባቢ በመሆኑ እና በቋንቋ፣ በባህልና በሌሎች ጉዳዮች የተለያየ መሆኑ በዚህ አካባቢ ልዩነቱን በመጠቀም የማጋጨት ሥራ ከተሰራ እና አንዴ ከተቀጣጠለ በቀላሉ አይበርድም የሚል ግምት ስለነበራቸው ነው ።
በሌላ በኩል ባለፉት 27 ዓመታት ከተሠሩ መጥፎ ሥራዎች ውስጥ አንዱ ዘረኝነትና ልዩነት የተሠበከበት መንገድ ነው። እንደ የትኛውም አካባቢ በተለይ መተከል ዞን ኢትዮጵያውያንን አንድ ከሚያደርጋቸውና ከሚያማክላቸው ነገር ይልቅ ልዩነቶች ሲሠበኩ የቆዩበት አካባቢ ነው። ለምሣሌ እኛ ከሄድን በኋላ እጅግ በጣም ኋላ ቀር ነው መቅረት አለበት ብለን እየሠራን ያለነው እዚያ ዞን ላይ ሰው ቀይና ጥቁር ተብሎ ይለያል። ስለዚህ ይህ ሐሳብ ቀስ በቀስ እያደገ፣ እያደገ ሄዶ የልዩነት ምንጭ ወደመሆን ሄዷል። ያን ዓይነት ዘግናኝ ጥፋት የተፈፀመውም ያንተን ልማት፣ ያንተን ዕድገት፣ ያንተን ከፍታ የከለከለህ ቀይ ነው፤ ስለዚህ ቀይ ላይ ርምጃ ውሰድ በሚል ትርክት ነው። ስለዚህ በተለምዶ ሲነገር የቆየው አነጋገር እየዳበረ መጥቶ በኋላ ለጥፋት ውሏል። አንዱ እዚያ አካባቢ የተከሰተው ችግር ለረጅም ጊዜ የተሠራበትና በልዩነት ላይ የተመሠረተው ትርክት ውጤት ነው። ከኢትዮጵያውያን አንድነትና አብሮነት ጋር የሚቃረን አስተሳሰብ ሥር እንዲሰድ መደረጉ ነው።
ሁለተኛው የተለያዩ ማህበረሰቦች አንዱ ሌላውን እንዲጠራጠር ተደርጎ የተሠራው ሥራ ነው። ለምሣሌ የጉምዝ ማህበረሰብ እንደ ሁሉም ማህበረሰብ የመልካም አስተዳደርና የልማት ጥያቄዎችና ቅሬታዎች ይኖራሉ። ነገር ግን “የጉምዝ ማህበረሰብ ያልለማው እነእከሌ ስላሉ ነው፣ እነእከሌ ያንተን ሐብት ስለወሰዱ ነው” የሚል የተዛባ ነገር በሥፋት ተሠራጭቷል።
በሦስተኛ ደረጃ ከለውጡ በኋላ እስከ ሕዝብ ድረስ እንዲሠርጽ የተደረገ አንድ በጣም የተዛባ መልዕክት አለ። ይኸውም “ብልጽግና ጨፍላቂ ነው፣ ጨቋኝ ነው፣ ለውጡ አሃዳዊ መንግሥት ይዞ ነው የመጣው፣ ስለዚህ ብሄር ብሄረሰቦች ራሳቸውን በራሳቸው የማስተዳደር ሕገመንግሥታዊ መብት ተነጥቀዋል፤ ጉምዝም በዚህ ምክንያት እንደጉምዝ ራስህን በራስህ የማስተዳደር መብትህ ከዛሬ ጀምሮ አክትሟል፤ እነእከሌ እነ እከሌ ሊውጡህ ነው፣ ስለዚህ ይህን ለውጥ መቃወም አለብህ፤ ይህንን ለውጥ በተቻለህ መጠን እስከ ትጥቅ ትግል ድረስ ተደራጅተህ መቃወምና መቃረን አለብህ” የሚል እጅግ በጣም የተሣሣተ የሐሰት ትርክት ወደህብረተሰቡ እንዲሰርጽ ተደርጓል።
ከዚህ ጎን ለጎን ደግሞ ኋላቀርነት አለ፤ ድህነት አለ፣ የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች አሉ፤ በሕዝቡ ውስጥ የሚነሱ ቅሬታዎች አሉ፤ እነዚህ ሁሉ ተደማምረው እኩይ ዓላማ ላነገቡ ቡድኖች መጠቀሚያ ሆኗል። እኛም እዚያ ስንሄድ ካየናቸው ነገሮች አንዱ ልዩነት ላይ የተመሠረቱ የሐሰት ትርክቶች በአንድ በኩል፣ በሌላ በኩል ደግሞ ለውጡና ብልጽግና ፓርቲ አሃዳዊ ጨፍላቂና መብትን አሣልፎ የሚሰጥ፣ ከዚህ ቀደም በሕገመንግሥት ያገኘኸውን መብት በሙሉ የሚያሳጣ እና ለሌላ አካል አንተን አሳልፎ የሚሰጥ ስለሆነ ርምጃ መውሰድ አለብህ። ርምጃ ስትወስድም ቀይ ማህበረሰብ ላይ ነው የሚል ስብከት እዚያ አካባቢ በተደራጀ መንገድ በሥፋት ተሰርቷል። ለአካባቢው ችግር ዋናው ምክንያት ይህ ነው ብሎ መውሰድ ይቻላል።
አዲስ ዘመን፡– በክልሉ የነበረው የሠላም ችግር ደጋግሞ እንደሚነገረው ውስብስብ ነው ?
አቶ ተስፋዬ፡– አንድ በደንብ መታወቅ ያለበት ነገር፣ እዚያ አካባቢ ያሉ ችግሮች በጣም ውስብስብ ነገሮች አሉት። ምክንያቱም ችግሮቹ ውስጣዊ ብቻ ሣይሆኑ ውጫዊም ናቸው። ስለዚህ በቤኒሻንጉልም ሆነ በመተከል አካባቢ የሚፈጠሩ ችግሮች ከውስጣዊም ከውጫዊም ነገሮች ጋር የተያያዙ ናቸው። ውስጣዊ የሆነው ችግር ለውጡን የማይፈልጉ ሃይሎች ከላይ እንዳልነው እዚያ አካባቢ በሚገባ በመሥራታቸው ነው። በተለይ እኛ ሥልጣን ካልያዝን ኢትዮጵያ የምትባል ሃገር መኖር የለባትም የሚሉ ሃይሎች፣ አሁን የፈረሠውን ህወሃት ጨምሮ እዚያ አካባቢ ትልቅ ደባ ሠርተዋል።
ለምሣሌ እዚያ አካባቢ በህወሃት ስፖንሰር አድራጊነት ጉህዴን የሚባል አንድ ፓርቲ ተቋቁሞ ነበር። የኢትዮጵያን ብልጽግና የማይፈልጉ የውስጥ ሃይሎች በሙሉ መንግሥትን ለማዳከም፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ብጥብጥ ለመፍጠር፣ ኢትዮጵያ ውስጥ አለመረጋጋት እንዲኖር፣ ቀስ በቀስም ያ አለመረጋጋት ወደብሄር እና ወደሃይማኖት ግጭት እንዲሸጋገር፣ ምቹ አካባቢ አድርገው የወሰዱት መተከል ዞንን ነው።
ሁለተኛ ደግሞ ታላቁ የህዳሴ ግድብ የሚገነባው በዚህ ዞን ነው። ታላቁ የህዳሴ ግድብ ደግሞ የኢትዮጵያውያን የልብ ትርታ እንደሆነ ይታወቃል። በታላቁ የህዳሴ ግድብ ላይ የኢትዮጵያውያን ሥነ ልቦና ምን እንደሆነ ይታወቃል። ከታላቁ ህዳሴ ግድብ ጋር የተያያዘ ጉዳይ ኢትዮጵያውያንን በሙሉ የሚነካ እንደሆነ ሁሉም ያውቃል። ይህ ግድብ ተገንብቶ ከተጠናቀቀ ደግሞ ኢትዮጵያ ምን እንደምትሆን ይታወቃል። ኢትዮጵያውያን ለዘመናት ሲመኙት የነበረውን አባይ ወንዝን ለልማት ማዋል፤ አባይ ወንዝ ላይ የልማት ሥራ ሠርቶ ከድህነት መውጣት፣ ከጨለማ መውጣት፣ ይህ ሕልም ይሳካል።
ይህንን የኢትዮጵያን ከፍታ የማይፈልጉ ሃይሎች የተለያዩ ውስጣዊ ችግሮችን እየፈለጉ አካባቢው ያለመረጋጋትና የግጭት መነሻ እንዲሆን ይሠራሉ። የመተከል ችግር የኢትዮጵያን የህዳሴ ግድብ ግንባታ የማይቀበሉ የውስጥም ሆኑ የውጭ ሃይሎች የጋራ ግንባር የፈጠሩበት ችግር ነው ።
በሦስተኛ ደረጃ ደግሞ ክልሉ ኋላ ቀርነት፣ ድህነት፣ የተለያዩ ጥያቄዎች እና ቅሬታዎች ያሉበት አካባቢ ነው። ስለዚህ ይህ ሲደመር ችግሩን ውስብስብ ያደርገዋል። ዋናው ጉዳይ ችግሩ ይህ ከሆነ እንዴት ነው የሚፈታው? የሚለውን ለማየት ሞክረናል። በጠቅላይ ሚኒስትሩ የተመደበው የተቀናጀው ግብረሃይል ወደዚያ እንደሄድ አምስት ዋና ዋና የሥራ መስኮችን ለይቷል።
አንደኛው የተፈጠረው ችግር መነሻ ፖለቲካዊ ነው፤
ስለዚህ ዝርዝር የፖለቲካ ሥራዎችን መሥራት ይገባል የሚል ነው። ከአመራሩ፣ ከመዋቅሩ እና ከማበረሰቡ ጋር የመግባባት ሥራ መሠራት እንደሚያስፈልግ ታምኖበታል። ለዚህም ከሕዝቡ ጋር መወያየት እና መግባት ያስፈልጋል ተብሎ አቅጣጫ ተቀምጧል።
ሁለተኛ የፀጥታና የሕግ ማስከበር ሥራውም ሌላው አጀንዳ ነው። ከዚህ ጋር በተያያዘ ሰው በሠላም ወጥቶ የሚገባበትን አካባቢ መፍጠር ይገባል የሚል ጠንካራ አቋም ይዘን ከፀጥታ መዋቅሩና ከሕብረተሰቡ ጋር ሥራዎችን ሠርተናል።
ሦስተኛ በነበረው ችግር ብዙ የተጎዱና የተፈናቀሉ የሕብረተሰብ ክፍሎች አሉ። ተፈናቃዮችን ለማቋቋም እንዴት እንሂድ? በሚለው ላይ የጋራ ሥራ መሥራት እንዳለብን ወስነን ወደ ሥራ ገብተናል። በዚህ መሠረት ተፈናቃች ወደነበሩበት ሥፍራ መመለስ አለባቸው። ነገር ግን እስከሚመለሱ ድረስ ባሉበት አካባቢ ሆነው የሰብዓዊ ድጋፍ የሚያገኙበት ሁኔታ ማመቻቸት ያስፈልጋል በሚል ሠፊ ሥራ ሠርተናል። በዚህ መልኩ ተፈናቃዮችን ወደቦታቸው መመለስ፣ መልሶ ማቋቋም እና ማደራጀት ሥራ መሥራት ሌላው የትኩረት መስክ ነው።
አራተኛ አሁን የተፈጠረው እውነታ እዚያ አካባቢ ብዙ ዓይነት ቅሬታ ስለቀሰቀሰ የእርቅ፣ የሠላምና የአብሮነት ግንባታ ሥራ መሰራት አለበት ብለን ወደ ሥራ ገብተናል።
አምስተኛ ችግሩ ተመልሶ እንዳይከሰት በዘላቂነት ለመፍታት ምን መሰራት አለበት ብለን በዚህ መልኩ ወደ ሥራ ገብተናል።
እስካሁን ባለው ሥራ ይህ በተለያየ መንገድ የታየው ማለትም በሐሰት ትርክት በተለይ የጉምዝን ማህበረሰብ ወደተሣሣተ አቅጣጫ ያስገባውን ነገር ማፅዳትና ሕዝብንና ሽፍታውን የመለየት ሥራ ስንሰራ ነበር። በዚህ መልኩ የተሠራው ሥራ ትልቅ ውጤት አምጥቷል። እስካሁን ባለው ሁኔታ አንድም እኩይ የሆኑ ቡድኖች ተደናግረው ወይም ተገደው ወደጫካ ከገቡት ውስጥ 36 ሺህ በላይ የሚሆኑት ከነበሩበት ጫካ ወደቤት ተመልሰዋል።
እንደሚታወቀው ሽፍታ የሚደበቀው ሕዝብ ውስጥ ነው። ርምጃ እንኳን እወስዳለሁ ብትል ሕዝብ ላይ ርምጃ መውሰድ አትችልም። ሽፍታውንና ሕዝብን መለየት ያስፈልጋል። በዚህ የተነሳም ሕብረተሰቡን የሽፍታው አስተሳሰብ እንደማይጠቅመው ማሣየት ያስፈልጋል።
በነገራችን ላይ መተከል ዞን በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ የትም መቼም መደገም የሌለበት ጥፋት የተፈፀመበት አካባቢ ነው። ሰዎች በማንነታቸው ምክንያት፣ በሚናገሩት ቋንቋ ወይም ሰዎች ፈልገው ሣይሆን በተፈጥሮ የቆዳ ቀለማቸው ምክንያት የተጎዱበት ሁኔታ ተፈጥሯል። ይህ እጅግ በጣም አሣዛኝ ነው። በማንነት ምክንያት የደረሰው ጭፍጨፋ እጅግ በጣም ዘግናኝ ነው። ይህ ያልጎዳው የሕብረተሰብ ክፍል የለም። ለምሣሌ የጉምዝ ማህበረሰብ በዚህ ድርጊት በእጅጉ ተጎድቷል። ብዙ ሺህ የጉምዝ ማህበረሰብ አባላት ተገደው ወደጫካ ሄደዋል። ጫካ ውስጥ የሚወልዱ እናቶችም አሉ፤ ጫካ ውስጥ የሚሞቱ ሰዎች አሉ፤ ሌላም በርካታ ጉዳት በጫካ ውስጥ የሚደርስባቸው የጉምዝ ማህበረሰብ አባላት አሉ።
ሽፍታው የያዘው ሐሳብ ልክ አይደለም ብሎ የተቃረነ፣ እኛ ከአማራ፣ ከኦሮሞ፣ ከሺናሻ፣ ወዘተ ማህበረሰብ ጋር በጋራ ነው ለዘመናት የኖርነው፤ በመካከላችን ምንም ችግር አልነበረም፤ ጥቃቱ በምንም መልኩ የጉምዝ ማህበረሰብን ባህሉንም፣ የኋላ ታሪኩንም አይወክልም ብለው የጮሁ አሉ።
ለምሣሌ በጉምዝ ማህበረሰብ ባህል በሆነ አጋጣሚ የሚከሰቱ ግጭቶች ቢኖሩም ይህ ጭፍጨፋ ከባድ ጉዳት ያደረሰው እናቶችና ሕጻናት ላይ ነው፤ ያውም ማንነትን ለይቶ። ቀይ አንተን ጉድቷል ተብሎ የተዛባ ትርክት ስለተነገረው ቀይ የተባለ በርካታ ሕዝብ ተጎድቷል። በርካታ የአማራ፣ የኦሮሞ እና በተወሰነ ደረጃ የሺናሻ ማህበረሰብ አባላት ተጎድተዋል፣ ይህ የኛ ባህል አይደለም፣ ትክክል አይደለም፤ እንዲህ ዓይነት ነገር መፈፀም የለብንም ብለው ሐሳብ ያቀረቡ የጉምዝ ሰዎችም ታርደዋል፤ ተገድለዋል። ስለዚህ አሁን በተፈጠረው ነገር ማንም አልተጠቀመም።
ከሩቅ የሚመለከት ሰው ምናልባት የጉምዝ ማህበረሰብ ያልተጎዳ ይመስለው ይሆናል። ነገር ግን ይህ ትክክል አይደለም። በርካታ የጉምዝ ማህበረሰብ አባላት ተገድለዋል፤ወደጫካ ተፈናቅለዋል።ጫካ ውስጥም እንዲሞቱ ተደርጓል። ስለዚህ ይህ የተፈጠረው ነገር ማንንም አልጠቀመም፤ ይህ ሽፍታ ለጉምዝ ማህበረሰብም ጠላት፣ ለሌሎች ብሄረሰቦችም በተመሣሣይ ጠላት ነው። ስለዚህ አንድ ላይ ሆነን በጋራ ይህን ሽፍታ መከላከልና ማስቆም አለብን የሚል አቋም እየተያዘ ነው። ይህ ደግሞ ትልቁ ሥኬት ነው። ይህ ከሕዝብ ጋር በተደረገው ውይይት የተገኘ ድል ነው።
እስካሁን ባለው ሂደትም በዞኑ ውስጥ ከ75 ሺህ በላይ ሰዎችን አወያይተናል። በዞኑ ሰባት ወረዳዎች አሉ፤ ከነዚህ ውስጥ ስድስቱ ችግር የነበረባቸው ናቸው። እነዚህ ስድስት ወረዳዎች ውስጥ የሚገኙ ወጣቶችን፣ የሃገር ሽማግሌዎችን የሃይማኖት አባቶችን፣ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን እና የተለያዩ አካላት አግኝተናል። ከነዚህ ጋር በየመድረኩ የተሥማማነው በዚህ የሽፍታ እንቅስቃሴ ተጠቃሚ የሆነ ማንም የለም፤ ጉምዝም ሌላውም እየተሠቃየ ነው፤ ስለዚህ በጋራ ሆናችሁ አንዳችሁ ሌላችሁን ሣትጠራጠሩ ተጋግዛችሁ ይህንን ሕገ ወጥ ቡድን ማስቆም አለባችሁ በሚል ነው።
በጉዳዩ ላይ እየተግባባን ስንመጣ ሕብረተሰቡ እየተነጠለ ከሽፍታው ሲወጣ አሁን ሽፍታውን ብዙ ቦታዎች ላይ መቆጣጠር ተችሏል። አብዛኞቹ የሽፍታ አባላትም ተሣስተናል ብለው እጅ የመስጠትና ተመልሶ ሕጋዊ መንገድ የመከተል እንቅስቃሴ ውስጥ ገብተዋል። ስለዚህ አንዱ የተሠራው ሥራ ሕብረተሰቡን ከሽፍታው የመነጠል፣ የተፈናቀሉ የጉምዝ ማህበረሰብ አባላትን ወደቀዬያቸው የመመለስ እና የማቋቋም ሥራ ነው።
ሌላው ማህበረሰብም የጉምዝ ሕዝብን የመጠራጠር፣ በመካከላቸው የጠላትነት ሥሜት ከፍ እንዲል የማድረግ፣ ነገሩን የማያባራ የሕዝብ ችግር የማድረግ ሁኔታ ነበር የታሰበው። ስለዚህ የሕዝብ ግጭት ሣይሆን በጉምዝ ማህበረሰብ ውስጥ ሁሉንም ጉምዝ የማይወክል፣ የጥፋት ሃይልን ብቻ የሚወክል የውስጥ ባንዳዎችንና የውጭ ተላላኪ የሆነ ሽፍታ ቡድን ነው የተደራጀው። ይህ ለሃገርም፣ ለጤናማው የጉምዝ ማህበረሰብም እንዲሁም እዚያ ለሚኖሩ የተለያዩ ኢትዮጵያውያንም የሚጠቅም ሃይል እንዳልሆነ የጋራ መግባባት ተይዟል። በዚህ መሠረትም ትልቅ ለውጥ መጥቷል ብሎ መውሰድ ይቻላል። ለዚህም ከ36 ሺህ በላይ ሰዎች ከጫካ ወደቤት መመለሳቸው አንድ ማሣያ ነው።
ሁለተኛው ማሣያ የተቀናጀው ግብረሃይል እዚያ ቦታ ሲሄድ ዞኑ በአጠቃላይ ካሉት 180 ቀበሌዎች ከ80 በላይ የሚሆኑት በችግር ውስጥ ነበሩ። አሁን ግን ከነዚህ በችግር ውስጥ ከነበሩ ከ80 በላይ ቀበሌዎች ውስጥ ከ19ኙ ውጭ ሌሎች ቀበሌዎች የመንግሥት መዋቅር፣ የአስተዳደር መዋቅር፣ የፀጥታ መዋቅር እንደገና እንዲደራጅ ማድረግ ተችሏል። ይህ ትልቅ ለውጥ ነው።
ሌላው ሕብረተሰቡ አሁን እንዲህ ዓይነት ራሱን የደበቀ፣ ከአንድ አካባቢ ወደሌላው የሚዘዋወር፣ ቋሚ ቦታ የሌለው፣ ፊት ለፊት ጥቃት ወይም ጦርነት የሚያካሄድ ሣይሆን ከቦታ ወደቦታ እየተዘዋወረ ጥቃት ከሚፈፅም ሃይል ሕብረተሰቡን ለመከላከል፣ አንዱ መንገድ ተደርጎ የተመረጠው ነዋሪውን የሚመስል ሁሉም ነዋሪ የሚስማማበት፣ የሚሊሻ ሃይል መልምሎ እና አሠልጥኖ መንደራቸውን፣ ሠፈራቸውን፣ ቀበሌያቸውን እንዲጠብቁ ማድረግ ነው። ከዚህ አኳያ አሁን እንዳልኩት ከ19 ቀበሌዎች ውጭ ሌሎቹ ላይ የሚሊሻ ሃይል የመመልመል፣ የአስተዳደር መዋቅሩን የማደራጀት፣ የመሪውን ፓርቲ የፖለቲካ መዋቅር የማደራጀት ይህንን በማድረግ ቀበሌው መንግሥት የሚቆጣጠረው፣ የፀጥታ ሃይል የሚቆጣጠረው የማድረግ ሥራ እየተሠራ ነው።
ከዚህ አኳያ ሚሊሻም ተመልምሎ ሲደራጅ ከሕብረተሰቡ የተውጣጣና ሕዝብን የሚመስል እንዲሆን፣ ሁሉም ሕዝብ የሚያምንበት ለምሣሌ ሕዝቡ ተሠባጥሮ ይኖራል፤ ጉምዝ፣ ሺናሻ፣ አገው፣ አማራ፣ ኦሮሞ ወዘተ አንድ ላይ ይኖራል። ስለዚህ አንድ ላይ በሚኖሩበት ክፍሎች ከሁሉም የሕብረተሰብ ክፍሎች እኛን ሊጠብቁ የሚችሉ ሃይሎች እነዚህ ናቸው ብሎ ማህበረሰቡ ራሱ እንዲመርጥ ማድረግ፣ እንዲተቹ ማድረግ፣ በጋራ የሚስማማበት ሃይል ደግሞ መንደራቸውን እንዲጠብቁ የማድረግ ሥራ እየተሠራ ነው። ይህ ደግሞ አካባቢውን በዘላቂነት ለመጠበቅ ያግዛል።
ከዚህ ውጭ የፀጥታ ሃይሉ ደግሞ የሕግ የበላይነት ለማስከበር፣ በጣም ጠንካራ ሥራ እየሠራ ነው። የፀጥታ ሃይሉ በዚህ አካባቢ ኢትዮጵያ ውስጥ ንጹሃን በመግደል፣ በሃይል ፍላጎትን ማሣካት እንደማይቻል ትምህርት በሚሰጥ መንገድ በሠላማዊ መንገድ እጅ ሠጥቶ ወደ ሠላማዊ ኑሮ መመለስ የሚፈልጉ ሃይሎችን በሠላማዊ መንገድ፣ ወንጀል ውስጥ የገቡትን በወንጀላቸው ልክ ለፍርድ ቤት በማቅረብ ተጠያቂ ማድረግ፣ ከዚያ ውጭ ንፁሃንን መግደል የሚቻል አይደለም የሚለው ነገር ጠንካራ አቋም ይዞ መከላከያ ሠራዊታችንን በጋራ ሆኖ የኦፕሬሽን ሥራ እየተሠራ ነው።
የኦፕሬሽን ሥራዎች በተለይ ጫካ የገባው ሕዝብ በሠላማዊ መንገድ ወደቤት እየገባ ያለበት ሁኔታ በመኖሩ በጣም ውጤታማ እየሆነ የመጣበት ሁኔታ እየጎላ መጥቷል። ከዚህ ውጭ ደግሞ የፖለቲካ መዋቅሩንም የማጥራት ሥራ እየተሠራ ነው። በፖለቲካና በአስተዳደር መዋቅር ውስጥ የተሣሣተ አስተሣሰብ ይዘው የተሠገሠጉ አካላትን የማስተካከል ሥራ እየተሰራ ነው። ይህም ሲባል ይህ የተፈጠረው ችግር ውስጥ ግንኙነት ያለው በተለይ በፓርቲ እና በአስተዳደር መዋቅሩ ውስጥ ያሉ አካላት ማጥራት፣ መለየት እና ለሕግ የማቅረብ፣ እና ተጠያቂ የማድረግ ሥራ እየተሰራ ነው። ባለፉት አርባ ቀናት እየተሠራ ካለው ሥራ አንዱ ይኸው ነው።
በየደረጃው ከክልል ጀምሮ ውይይት አድርገናል። ሠሞኑንም በክልሉ ላይ ኮንፈረንስ አካሂደናል። እስከ ቀበሌ ድረስ ያለውን አመራር የማጥራት፣ የመለየት፣ መልሶ የማደራጀት እና የመገንባት ሥራ ተሰርቷል።
በዚህም እስካሁን ባለን ግምገማ ችግር ውስጥ የገባውን ሃይል ማሥረጃና መረጃ የተገኘባቸውን አካላት፣ ግማሹን በሕግ የማስጠየቅ ሥራ፣ ሥራውን በአግባቡ መሥራት ያልቻለውንና ሃላፊነቱን ያልተወጣው ላይ ደግሞ ፖለቲካዊ ርምጃ ተወስዷል።
ይህ ሲባል ከሃላፊነት የማሣንት እና ከቦታ ቦታ የማሸጋሸግ ሥራ ተሰርቷል። በነሱ ምትክ አቃፊ የሆነ እይታ ያላቸው ሕዝብን በእኩል ዓይን የሚመለከቱ፣ በህብረ- ብሄራዊነት የሚያምኑ፣ በሕዝቦች እኩልነትና አንድነት የሚያምኑ፣ ሁሉም ሕዝብ የኔ ሕዝብ ነው ብሎ ማሰብ የሚችሉ አካላትን መልሶ ማደራጀት፣ ማሠልጠንና ወደ ሥራ የማስገባት ሥራም ተሰርቷል። ስለዚህ እስካሁን በተሰራው ሥራ አካባቢው ላይ በተነፃፃሪ ሠላም ሰፍኗል፤ የነበረው ሁኔታ እየተቀየረ መጥቷል፤ የነበረው ችግርም እየቀነሰ፣ መጥቷል፤ ሕዝቡም ወደ ሠላማዊ መንገድ እየገባ ነው።
ከላይ እንዳነሳሁት ጉዳዩ ብዙ ሃይሎች ያሉበትና በጣም ውስብስብ ነው። ለምሣሌ የታጠቀ ሁለትና ሦስት ሰው አንድ መንደር ሄዶ እየተጫወቱ ያሉ ሕጻናትን ወይም ቤት ውስጥ የተቀመጡ አዛውንቶች ላይ ርምጃ የመውሰድ ሁኔታ ነበር። የታጠቀ ሃይል ከታጠቀ ሃይል ጋር የሚደረገው ውግያ ቢሆን ምንም ችግር አልነበረውም። ስለዚህ እንዲህ ዓይነት ነገር እንዳይፈፀም ነዋሪው አካባቢውን እና ሠፈሩን የሚጠብቅበትን ሁኔታ እያመቻቸን ነው።
አዲስ ዘመን፡– ይህ ችግር የተከሰተው ችግሩ በመዋቅር የተሠራ ስለሆነ ነው የሚሉ አሉ፤ በየደረጃው ያሉ አመራሮች እንደተሣተፉበት ይነገራል። ከዚህ አንጻር ያለው ሁኔታ ምን ይመስላል?
አቶ ተስፋዬ፡– መተከል ዞን ላይ የተፈጠረው ችግር ውስጣዊም ውጫዊም ናቸው ብለናል። ከውስጣዊ ምክንያቶች ውስጥ አንዱ የፖለቲካ አመራሩ ውስጥ የተፈጠሩ ችግሮች ናቸው። ስለዚህ እስካሁን ባደረግነው ግምገማ ከችግሩ ጋር ንክኪ ያላቸው ሃይሎች እንዳሉ ታውቀዋል፤ ተለይተዋል። መዋቅሩ ውስጥ ችግር ፈጣሪዎች አሉ። ለምሣሌ የዞኑ አስተዳዳሪ ከዚህ ችግር ጋር ንኪኪ እንዳለው ተጠርጥሮ ታሥሮ ምርመራ እየተካሄደ ነው። የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር የነበረው እና ቀደም ሲል የቤጉህዴፓ ፓርቲ ሊቀመንበር የነበረው ሰው በዚህ ችግር ውስጥ እንደገባ ተጠርጥሮ በሕግ ቁጥጥር ሥር ውሏል። የክልሉ አፈ ጉባዔም በተመሣሣይ በዚህ ውስጥ እጁ እንዳለ ተጠርጥሮ ከቦታው ተነስቷል። ከዚህም ውጭ ሌሎች በርካታ የወረዳ አመራሮች፣ የዞን አመራሮች፣ በአጠቃላይ 45 በየደረጃው ያሉ አመራሮች በሕግ ቁጥጥር ሥር ውለው ምርመራ እየተካሄደባቸው ይገኛል። ይህ የሚያሣየው በመዋቅር ውስጥም ሆነው ይህንን እጅግ በጣም ዘግናኝ የሆነና አሰከፊ ጉዳት ያስከተለ ሐሳብ የተሸከመ ወይም የሚደግፍ ሃይል እንዳለ በተጨባጭ ተረጋግጧል። ለዚህ ነው የፖለቲካ ሥራችን አንዱ ማዕከል ያደረገው መዋቅሩን ማጥራት፣ መለየት እና ተጠያቂ ማድረግ ላይ ትኩረት ያደረገው።
ሁለተኛ የፀጥታ መዋቅር ላይ ችግር እንዳለም አይተናል። ለምሣሌ ሰሞኑን ሁሉም የፀጥታ መዋቅር ወደ ተሃድሶ እንዲገባ ተደርጓል። ይህ የተቀናጀ ግብረሃይል ከሄደ በኋላ አንዱ የሰራው ሥራ የፀጥታ መዋቅሩ ውስጥ ያለውን ችግር መለየት ነው። እዚህ ላይ ግን ሁሉም በጅምላ ችግር አለባቸው ተብሎ እንዳይወሰድ ለሕዝብ ሲባል የፀጥታ መዋቅሩ ውስጥ ከፍተኛ ዋጋ የሚከፍሉ፣ ሕይወታቸውን የሰጡ፣ አካላቸው የጎደለ፣ ቀንና ማታ የሚሰሩ አሉ።
አንዳንድ ወገኖች ደግሞ የፀጥታ መዋቅሩ ውስጥ ሆነው ከሽፍታው ጋር የሚገናኙ አሉ። መሣሪያ ጭምር ለሽፍታው የሚያስረክቡ አካላት አሉ፤ ተይዘው ርምጃ ተወስዷል። የታሰሩ ምርመራ እየተጣራባቸው ያሉ፣ የፀጥታ መዋቅሩ አባላት አሉ። ስለዚህ በፖለቲካ መዋቅሩም፣ በአስተዳደሩ መዋቅር ሆነ በፀጥታ መዋቅሩም ውስጥ ለሕዝብ አብሮነትና አንድነት ዋጋ እየከፈሉ ያሉ አመራሮች አሉ፤ የፀጥታ መዋቅሩ የልዩ ሃይል አባላት፣ የፖሊስ አባላት አሉ። እንዲሁም ሁለት ቦታ የሚረግጡ፣ በሁለት ቢላዋ የሚበሉ አመራሮችም፣ አባላትም አሉ። ስለዚህ እነዚህ ላይ ተለይቶ ርምጃ እየተወሰደ ነው። ችግሩ ውስጣዊ ነው ሲባል ይህንን ለማመላከት ነው።
አዲስ ዘመን፣ ሰሞኑን የአራት ቀና ኮንፈረንስ ተካሂዶ ነበር፤ የኮንፈረንሱ ዓላማ ምን ነበር? ምን ውጤት አመጣ?
አቶ ተስፋዬ፡– ሰሞኑን የተካሄደው የአራት ቀን ኮንፈረንስ እጅግ በጣም ውጤታ ኮንፈረንስ ነው። ይህ ኮንፈረንስ ማዕከል ካደረጋቸው ነገሮች አንዱ የዚህ ችግር ዋንኛ መነሻ ውስጣዊ ነው ወይስ ውጫዊ ነው የሚለውን ማየት ነው፤ ይህም ማለት መዋቅሩ ራሱን ያየበት ነው ማለት ነው። ለምን እኛ እየመራን ባለንበት ዞንና ክልል ይህ ተፈጠረ? የሚለውን ማየት ነው። ከዚህ በመነሳት ሰው በፀፀት፣ በቁጭት፣ ይህ ነገር መፈጠር አልነበረበትም በሚል እያንዳንዱ አካል ራሱን እንዲያይ አድርጓል። በሌላ በኩል ደግሞ እንዲህ ዓይነት ነገር ተመልሶ እንዳይመጣ ምን መሥራት አለብን? ችግሩን በዘላቂነት እንዴት መፍታት አለብን፣ የሚሉ ጉዳዮች ተለይተው ውይይት ተደርጎባቸዋል። ይህንንም ተከትሎ እንደግለሰብ የግምገማ ማለትም የኮንፈረንስ መድረክ ላይ ችግር ያለባቸው አካላት ላይ የውሣኔ ሐሳቦች ቀርቦባቸዋል። የሚመለከተው አካል ያፀድቃል።
ከዚህ አንጻር አንዱ የመንግሥትንም የፓርቲንም ሥራ የሚያስተባብሩ የክልሉ ቁልፍ ቁልፍ አመራሮች ከባድ ማስጠንቀቂያ ውስጥ ሆነው ክልሉ ከገባበት ችግር ውስጥ ማውጣት አለባቸው የሚል የውሣኔ ሐሳብ ቀርቧል።
በኮንፈረንሱ መደረግ የኮንፈረንሱ ተሳታፊ አንድ ስለተላለፈው ውሣኔ እስካሁን ለተፈጠረው ነገር ሕዝቡን ይቅርታ እንጠይቃለን፣ የክልሉን ነዋሪ ይቅርታ እንጠይቃለን፣ ኢትዮጵያውያንን ይቅርታ እንጠይቃለን፤ እንዲህ ዓይነት ነገር በየትም ቢሆን መቼም መደገም እንደሌበት አውቀን ሕዝብን ለመካስ እንሰራለን። ይህንን ቁስል የሚሽር ምንም ነገር የለም፣ የሚመጥንም ነገር የለም። ነገር ግን ቢያንስ እንዲህ ዓይነት ነገር ተመልሶ እንዳይመጣ በክልላችንም እንዳይፈጠር ለማድረግ ከትናንት ተምረን ነገን የተሻለ ለማድረግ ይቅርታ እንጠይቃለን ብሎ ወደ አንድነት የመጣበት መድረክ ነው።
አዲስ ዘመን፡– የክልሉ ሕገ መንግሥት በራሱ ችግር አቀጣጣይ እንደሆነ ከዋናው የሀገሪቱ ሕገ መንግሥትም ጋር የሚቃረን እንደሆነ ይነገራል፤ በዚህ ላይ ምን የሚሉት አለ ?
አቶ ተስፋዬ፡– የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥትን በተመለከተ የተለያዩ ጥያቄዎች ይነሳሉ። አንዳንድ ምሁራንን ጨምሮ አንዳንድ ወገኖች የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት የግጭት፣ የመከፋፈል፣ የጥላቻ ምንጭ ነው፤ ሙሉ ለሙሉ ተቀዶ ተጥሎ ሌላ ሕገ መንግሥት መዘጋጀት አለበት ይላሉ፤ ይህ አንድ ጫፍ ነው። በሌላ በኩል ደግሞ ከዚህ በተቃራኒ ሕገ መንግሥቱ በጣም ቅዱስ ስለሆነ እንደ መጽሃፍ ቅዱስ ወይም እንደ ቅዱስ ቁርአን መነካት የለበትም ብለው የሚያምኑ አሉ። ይህም ትክክል አይደለም። በሕገ መንግሥቱ ውስጥ የሚሻሻሉ፣ የሚስተካከሉ ነገሮች ይኖራሉ፤ አሉ። ይህ ደግሞ በዓለም ላይም የታወቀ ነው። ሕገ መንግሥት የሆነ ጊዜ ይረቀቃል፤ ከዚያ ሕብረተሰቡ በደረሰበት የዕድገት ደረጃ ልክ እየታየ የዕድገት ደረጃውን በሚመጥን መልኩ እየተስተካከለ ይሄዳል።
በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል ስናይ የክልሉ ሕገ መንግሥት ውስጥ በዚሁ መሠረት የሚሻሻሉ ነገሮች ሊኖሩ እንደሚችሉ ታሳቢ ማድረግ ያስፈልጋል። እኛ ሕገ መንግሥቱን ታሳቢ በማድረግ አልተወያየንም። ነገር ግን ያለው ነባራዊ ሁኔታ ከዚህ የተለየ አይደለም። የተፈጠሩ ነገሮችን ሥናይ ለምሣሌ በመተከል እስከ 2011 ዓ.ም ድረስ በጣም ሠላማዊ ቀጣና ነበር። በለውጡ ጊዜም ጭምር በሃገሪቱ በርካታ ግጭቶች በነበሩበት ወቅት ይህ ቀጠና በጣም ሠላማዊ ነበር። ኢትዮጵያውያን በጋራ የሚኖሩበት አካባቢ ነው። አሁን ስንሄድ ብዙዎቹ በመድረክ ጭምር የሚያቀርቡት ሐሳብ እኮ “እስከ 2011 ድረስ በሠላም፣ በተረጋጋ አካባቢ በመኖር ለኢትዮጵውን ምሣሌ ነን። ጉዳዩ መፈጠር የጀመረው ለውጡ ከመጣ በኋላ ነው” የሚል ነገር ነው።
ከዚህ አንጻር ስንመለከት ከዚያ በፊትም የክልሉ ሕገ መንግሥት ነበር። ታዲያ በ2011 ለውጡን ተከትሎ የተከሰተው ጭፍጨፋ በቀጥታ ከዚህ ጋር የተገናኘ ነው ማለት አያስችልም። ከዚያ ይልቅ ዋናው የችግሩ ምንጭ ቅድም ያነሳናቸው ጉዳዮች ናቸው። ብሄርና ብሄርን፣ ሕዝብና ሕዝብን የሚያለያዩ ትርክቶች፣ አንዱን በዳይ፣ ሌላውን ተበዳይ አድርጎ የመሣል፤ አንዱ ደሃና ኋላቀር የሆነበት ምክንያት እነእከሌ እነእከሌ ያንተን ሐብት ስለወሰዱ ብሎ መስበክ እና ኢትዮጵያውያን የራሳችን ባህል፣ ቋንቋ፣ ወግ፣ የመኖራቸውን ያህል ደግሞ የጋራ የሚያደርጉንን ነገሮች ክዶ በመነሳት በሕዝብ ውስጥ ያልሆነ ነገር መርጨት ወዘተ ናቸው።
መተከል ዞን ውስጥ አገው፣ አማራ፣ ኦሮሞ፣ አለ። ማኦ ኮሞ፣ ጉምዝ፣ ሺናሻ አለ። ፓዌ ወረዳ ላይ ደግሞ በ1977 ዓ.ም በነበረው የሠፈራ ፕሮግራም ከደቡብ ብሄር ብሄረሰቦች የመጡ ብሄረሰቦች አሉ። ስለዚህ መተከልን ትንሿ ኢትዮጵያ ናት ብሎ መውሰድ ይቻላል።
ጤናማ የጉምዝ ሽማግሌዎች እና እናቶች ጋር ቁጭ ብለን ስንወያይ እኛ እኮ “አንዳችን ከሌላችን ጋር ተጋብተናል፣ ተዋልደናል፤ በደም ተዋህደናል፤ ማንም ሊያለያየን አይችልም። አሁን የተፈጠረውን ነገር እኛ የጉምዝ ማህበረሰብ አናውቀውም። ከኛ ጋር ያለው ሌላው ብሄረሰብም አያውቀውም፤ ባዕድ ነገር ነው፣ ውስጣችሁን ፈትሹ” ነው ያሉት። ስለዚህ ከዚህም በላይ የሚገርመው ለምሣሌ እኛ ከመሃል አገር የሄድን ሰዎች እንደመሆናችን መጠን መድረኮችን የምንመራው በአማርኛ ነው። በዚህ ጊዜ ታዲያ አማርኛ የማይችሉ አባቶችና እናቶች ሲኖሩ የሚያስተረጉሙት የአማራ፣ የኦሮሞ፣ የሺናሻ ወዘተ ሰዎች ናቸው። ልትለያቸው አትችልም።
የሚገርው ፈረንጆች ሁላችንንም ጥቁር ነው የሚሉን፣ አይለዩንም። እዚያ አካባቢ ግን እኛን ለሁለት ከፍለው ጥቁርና ቀይ ብለው ከፍለውናል። ስለዚህ ዋናው የግጭቱ መነሻ ውስጣዊ ብልሽትና ውጫዊ ፍላጎቶች ናቸው። ከውጭ ሃይሎች ጋር በመሆን ሕዝብን አጋጭተው ከግጭት እናተርፋለን፤ በግጭት እንኖራለን፡ የሚሉ የግጭት ነጋዴዎች የፈጠሩት ነው። የሕገ መንግሥቱ ጉዳይ ሲነሳ የሚታዩ ነገሮች የሉም ማለት አይደለም። ነገር ግን አሁን የተፈጠረውን ግጭት በተመለከተ ዋናው መነሻ እነዚህ ነገሮች አይደሉም።
አዲስ ዘመን፡– ከዚህ ቀደም በአካባቢው ያለውን ማህበረሰብ ማስታጠቅ እንደ አንድ መፍትሄ ተወሰዶ ነበር። ከዚህ አንጻር ያለው ሂደት ምን ይመስላል?
አቶ ተስፋዬ፡– ለዚህ እንግዲህ ማስታጠቅ ሲባል ምን ማለት ነው የሚለውን መረዳት ያስፈልጋል። የተቀናጀ የግብረሃይል ከሠራቸው ሥራዎች ውስጥ አንዱ ቀበሌ ላይ ሕዝቡን የሚመስሉ የቀበሌ አመራሮች እንዲኖሩ ማድረግ ነው። በሌላ በኩል ሽፍታው አንድ ቋሚ ቦታ የለውም፤ ከአንድ ቦታ ወደሌላ ቦታ ይንቀሳቀሳል። በየትኛው ቦታ ላይ ምን ጊዜ እንደሚንቀሳቀስ አይታወቅም። እንዲህ ዓይነት ነገር ሲኖር የተደራጀ ሕዝቡን የሚጠብቅ ሚሊሻ ያስፈልገዋል። ይህ ሚሊሻ ደግሞ በተለይ እዚያ ካለው ነዋሪ የተመለመለ መሆን አለበት። ስለዚህ ይህንን ማዕከል በማድረግ ሚሊሻዎችን የመመልመል፣ የማደራጀትና ጎጥን፣ መንደርን፣ ሠፈርን እንዲሁም ቀበሌን የሚጠብቅ ሃይል እንዲኖር የማድረግ ሥራ ተሰርቷል። ከዚያ ቀደም ሲል የነበሩት አንዳንድ መፍትሄ ናቸው የተባሉ ሥራዎች በአግባቡ ባለመሠራታቸው ጉዳት ደርሷል። ስለዚህ ማስታጠቅ ሲባል ግለሰብን ሣይሆን በተደራጀ መልኩ ሕብረተሰቡ ራሱን የሚጠብቅብበት የፀጥታ መዋቅር ማደራጀት ማለት ነው።
በዚህ መሠረት እነዚህ ሚሊሻዎች ከሕዝቡ ውስጥ በሕዝብ ይመረጣሉ፣ ይመለመላሉ፤ የቀበሌው እና የመንደሩ ነዋሪ የሚያምንባቸው አካላት ይሠለጥናሉ። ከዚያ እነዚህ አካላት የአካባቢያቸውን ፀጥታ ያስከብራሉ። ይህ ነው ማስታጠቅ ማለት። ይህ ሥራ ተጀምሯል።
አዲስ ዘመን፤ ከግምገማ በኋላ አመራሩ እውን ጠርቷል ማለት ይቻላል? ምን ዓይነት የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች ተከናውነዋል?
አቶ ተስፋዬ፡– እንግዲህ ቀሪ ሥራዎችን ብንወስድ አንደኛው የተፈናቀሉ፣ ነገር ግን ወደቀዬያቸው ያልተመለሱ ወገኖቻችን አሉ። እነዚህ ወደ ቀዬያቸው ያልተመለሱ ወገኖቻችን 124 ሺህ ይደርሳሉ። እነዚህን ወደነበሩበት ለመመለስ የተለየ ጥረት እየተደረገ ነው።
እያንዳንዱ ተፈናቃይ ወደነበረበት ቀዬ ከመመለሱ በፊት ግን የቅድመ ዝግጅት ሥራ አለ። አንደኛውና የመጀመሪያው ቅድመ ዝግጅት ሥራ ቅድም ያልነውን የፀጥታ ችግር ተመልሶ እንዳይከሰት፣ ከመጡ በኋላ ደግሞ ሌላ ጥፋት እንዳይፈፀም የሚፈፅመውም አካል እፈፅማለሁ ብሎ ካሠበ እንኳን ለመከላከል የሚችል ታጣቂ እንዲኖር ማድረግ ነው። ሚሊሻዎችን መመልመል፣ ማሰልጠንና ማስታጠቅ ሥራ ሁሉ እንደቅድመ ሁኔታ እየተሰራ ነው። ይህ ተፈናቃዮቹ ከመመለሳቸው በፊት እየተሰራ ያለ ነው። ሰው ከተፈናቀለበት ቦታ አገር ሠላም ብሎ ወደቤቱ ከመጣ በኋላ ተመልሶ ሌላ ጉዳት ቢደርስበት ሌላ ፀፀት ነው።
ሌላው ቅድመ ዝግጅት ሥራ ደግሞ እነዚህ ሰዎች ተፈናቅለዋል፤ ቤታቸውን ጥለው ወጥተዋል፤ አሁን ሲመለሱ “ቤታቸው ምን ይመስላል፤ መልሶ ሊያስገባቸው ይችላል፣ አይችልም” የሚለውም ማየት ነው። በዚህ መካከል መጠራጠሮች ተፈጥረዋል፤ ቁርሾዎች ተፈጥረዋል። ስለዚህ ሕዝብ ምን ይላል የሚለው መታየት አለበት። እዚያ አካባቢ እኮ ሕዝቡ የሚገርም ባህል አለው። ጥፋተኛ የሚጠየቅበት፣ ያጠፋ ሰው ይቅርታ የሚጠይቅበት፣ ትናንት የተበላሸ ነገር ካለ የብቀላ ነገር ውስጥ ከገባን መጠፋፋት ነው የሚሆነው። ሰለዚህ ከትናንት ለቅሶ የሆነ ነገር ወስደን እንዴት ወደተሻለ ነገር ወደፊት መሄድ እንችላለን የሚለውን ማየት ነው። ስለዚህ ከዚህ በመነሳት የእርቅና የአብሮነት ነገሮች የሚሰሩበት ሁኔታ አለ። ከዚህ በመነሳት ከሕዝቡ ጋር የውይይት፣ የእርቅ፣ የአብሮነት፣ ቁስል የማከም፣ ወዘተ ቅድመ ዝግጅት ሥራዎች እየተሰሩ ነው። ይህ ከሆነ በኋላ በአጭር ጊዜ ውስጥ ተፈናቃዮች ወደ ቀዬያቸው የሚመለሱ ይሆናል።
ሌላኛው ደግሞ ተቋም መገንባት ነው። የተቀናጀው ግብረሃይል ሁሌ እዚያ መኖር አይችልም። ተቋም ገንብቶ መሄድ ያስፈልጋል። ስለዚህ የተነሳው ጥያቄ በዚህ ማዕቀፍ የሚነሳ ነው። አመራር ጠርቷል ወይ፣ የፀጥታ መዋቅሩ ጠርቷል ወይ፣ በመዋቅር ውስጥ ሆኖ ክፉ የሚያስብ የለም ወይ፣ የሚሉ ጥያቄዎችን በተመለከተ አንዱ እስካሁን በሰራነው ሥራ ሰው በጣም እየተፀፀተ ነው፤ እየተቆጨ ነው። በኛ ዘመን መሆን የለበትም እያለ ነው። ባካሄድነው ኮንፈረንስ ላይ ብዙ አመራሮች አልቅሰዋል። ይህንን ከምናይ እንደ አባቶቻችን ትናንት ብናልፍ ይሻለን ነበር ያሉ ጭምር ነበሩ። ቁጭትና እልህ ተፈጥሯል። ሕዝብን እክሳለሁ የሚል ቁጭት ተፈጥሯል። ይህንን ደግሞ በተግባር ተናግረዋል።
ይህ ማለት ግን ሌላ ጥፋት የሚያስብ አንድም ሰው የለም ማለት አይደለም። ስለዚህ እንዳይኖር ክትትል ማድረግ፣ መገንባት፣ እዚያ አካባቢ ያለው መዋቅር እንዲህ ዓይነት ሰው እንዳይሸከም ማድረግ ዋናው ሥራ ነው። የትም ቦታ ጥፋት የሚያጠፋ ወጣ ያለ ሰው ሊኖር ይችላል። ነገር ግን ያንን የማይሸከም ነባራዊ ሁኔታ ሲኖር ወይ ይተዋል፤ አልያም ለቆ ይወጣል። ስለዚህ አካባቢው ይህንን እንዳይቀበል ማድረግ ነው ዋናው ነገር።
ክትትላችን፣ ድጋፋችን፣ ተጠያቂነት ሥርዓት የማስፈን ሥራችን እንዲህ ዓይነት ነገር የሚሰራ ሃይል በፈለገበት መንገድ የሚንቀሳቀስበት ነገር እንዳይኖር ማድረግ ያስፈልጋል። ስለዚህ በኛ እምነት ሕዝባዊ የሆነ እይታ ያላቸው፣ የለውጥ እይታ ያላቸው፣ የለውጥ ሐሳብ ያላቸው፣ ሕዝብን ለመካስ የሚፈልጉ፣ አመራሮችን ከመቼውም ጊዜ በተሸለ ሁኔታ ወደመዋቅሩ እየሰበሰብን እያሰለጠንን እያስገባን ነው። ሾልኮ የሚገባ አካል ካለ ደግሞ እያጠራን ተጠያቂ የማድረግ ነገርም የምንሰራ ይሆናል። አሁን ግን በዋናነት ሲታይ አብዛኛው ሰው ቢያንስ…ቢያንስ ይህ የተፈጠረው ጥፋት ዳግም እንዳይከሰት ቆርጦ የሚሰራ ሃይል ነው ብሎ መውሰድ ይቻላል።
እዚያም እዚህም የሚፈጠሩ ችግሮች ካሉ ተጠያቂም ማድረግ፣ ክትትልም ማድረግ እንደ ከዚህ ቀደሙ ጥፋት ከጠፋ በኋላ ሣይሆን ሳይፈፀም አስቀድመን የማወቅና የመከላከል ሥራን ማዕከል አድርገን እንቀሳቀሳለን ማለት ነው።
አዲስ ዘመን፡– አሁን የተፈናቀሉ ዜጎቻችን እስከመቼ ድረስ ወደነበሩበት ይመለሳሉ?
አቶ ተስፋዬ፡– የተቀናጀው ግብረሃይል ሥራ ከጀመረ ወዲህ የመጀመሪያዎቹን አርባ ቀናት ሥራ ገምግሞ ለሚቀጥለው 15 ቀናት የሥራ ዕቅድ አውጥቷል። ስለዚህ እስከ የካቲት 20 ድረስ ያለው ሥራ እንደገና ተከልሷል። እስከዚያ ድረስ አብዛኞቹ ሥራዎች መልክ መያዝ አለባቸው ተብሎ በዚያ መሠረት እየተሰራ ነው። ለምሣሌ የአካባቢውን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት አንዱ ስትራቴጂ ተቋም መገንባት ነው። የፀጥታና የአስተዳደር መዋቅር፣ ሕብረተሰቡ ጋር ተቀናጅቶ መሥራት የሚችል የአመራር ሥርዓት እየገነባን ነው። ሕዝብን እየቀረበ፣ እያማከረ የሚሄድ የአመራር ሥርዓት እየተገነባ ነው።
ሁለተኛው በአካባቢው 42 የተጀመሩ ፕሮጀክቶች በተፈጠረው የፀጥታ ችግር ምክንያት ቆመዋል። የመንገድ፣ የመስኖ፣ የጤና ፣ የትምህርት ወዘተ ፕሮጀክቶች ግንባታ ቆመዋል። በዚህ አካባቢ አንዱ ችግር መንገድ ነው። ይህ ይታወቃል። እነዚህን ፕሮጀክቶች ሙሉ ለሙሉ ወደሥራ ብናስገባ ከአንድ መቶ ሺህ በላይ የሥራ ዕድል ይፈጠራል። ይህ ደግሞ በአካባቢው ላይ ያለውን የልማት ጥያቄ፣ የመሠረተ ልማት ጥያቄ፣ ለመፍታት ያስችላል። በሌላም በኩል የሕብረተቡን የኢኮኖሚ ጥያቄ ይመልሳል።
ሌላኛው ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት የምንሰራው ሥራ በጉምዝ ማህበረሰብ ላይ የምንሰራው ነው። የየራሳቸው አጀንዳ ያላቸው የተለያዩ አካላት እንደ ምሽግ ለመጠቀም የፈለጉት የጉምዝን ማህበረሰብ ነው። በጉምዝ ማህበረሰብ ውስጥ ደግሞ እውነተኛ ጥያቄዎች አሉ። የኋላ ቀርነት፣ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች፣ የልማት ጥያቄዎች፣ የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ወዘተ አሉበት።
ዞኑ ውስጥ ካለው ሕብረተሰብ ጋር በሙሉ ተቀራርቦ የመስራት ሥራ እንደ አንድ የትኩረት መስክ የሚታይ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ የጉምዝን ማህበረሰብ ቅሬታ ውስጥ ያስገቡ ጉዳዮች ምንድናቸው የሚለውን ለይቶ ከድህነትና ከኋላ ቀርነት የሚያላቅቁ ፕሮጀክቶችን ቀርጾ መሥራት ይገባል።
በመተከል ውስጥ ያየነው ችግር ሁለት ነገሮችን በማድረግ መፈታት አለበት። የአብሮነትና የአንድነት እሴቶቻንንን የበለጠ በማጎልበት ሁሉም የዞኑ ነዋሪዎች ዞኑ የኛ ነው፤ መዋቅሩ የኛ ነው፤ እኛ ኢትዮጵያውያን ነን፤ ይህም ኢትዮጵያ ነው የሚል እምነት እንዲይዙ አስተዳደሩ ጠንክሮ መሥራት አለበት። የአብሮነትና የአንድነት ግንባታ ሥራችን በዚህ መልኩ ተጠናክሮ መጠቀል አለባቸው።
ይህ አካባቢ ኢትዮጵያውን በአንድነት እና በሕብረ ብሄራዊነት አብረው የሚኖሩበት አካባቢ ስለሆነ ይህንን መገንባት ካልቻልን በተለይ ደግሞ የብቀላ ነገር ውስጥ ከተገባ መንቀሳቀስ አይቻልም። ጥፋት ሌላ ጥፋት ይጨምራል።
ሁለተኛው ችግሩን ለመፍታት በጉምዝ ማህበረሰብ ውስጥ ያሉ ችግሮችን ለቅሞ መፍታትና የሐሰት ትርክቶችን ማረም ያስፈልጋል። የብልጽግና የለውጥ ጉዞ ለሁሉም ኢትዮጵያዊ እንደሚጠቅም መግባባትና መረዳዳት፣ በዚያ አካባቢ በጣም ወሣኝ ነው። ከዚህ አንጻር አሁን ሥራው በጣም ተስፋ ሰጪ ደረጃ ላይ ደርሷል። በቀጣዩ ሁለት ሣምንት ደግሞ ምን…ምን መሠራት እንዳለበት ዕቅዱ ተከልሷል፤ ከየካቲት 20 በኋላ ደግሞ የሚኖረውን ሥራ ገምግመን ቀጥሎ የሚኖረንን ሥራ ማጠናከር እንችላለን ማለት ነው።
አዲስ ዘመን፡– በአጠቃላይ በክልሉ በተለይ በመተከል ዞን የደረሰው ሰብዓዊ ቀውስ ምን ይመስላል ?
አቶ ተስፋዬ፡– ብዙ ትላልቅ ጥፋቶች በአካባቢው ተከስተዋል። አንዱና ዋነኛው አሣዛኝ ጥፋት ንፁህና ምንም የማያውቁ ኢትዮጵያውያን ከግጭት እናተርፋለን በሚሉ አካላት ሕይወታቸውን አጥተዋል፤ አካላቸው ጎድሏል፤ ንብረታቸው ወድሟል፤ አጠቃላይ ማህበራዊ ሕይወታቸው ተናግቷል።
መተከል ላይ የተፈጠረው ጥፋት በመተከል ሕዝብ ላይ ብቻ ያለመ አይደለም። ከዚያም አልፎ ግጭቱ የብሄር ብሄረሰቦች እንዲሆን ታስቦ የተሠራ ነው፤ ለምሣሌ ግጭቱ የአማራና የኦሮሞ እንዲሆን ከፍተኛ ሥራ ተሠርቷል። ይህ ሲሆን ደግሞ ሁሉም ቦታ እሣቱ ሊቀጣጠል እንደሚችል፤ በዚህም ምክንያት ኢትዮጵያ መረጋጋት እንደማትችል፣ ኢትዮጵያ ከፈረሠች እነዚህ ሃይሎች የሚፈልጉትን ሥራ መሥራት እንደሚችሉ ጭምር አቅደው ለማስፈፀም ተንቀሳቅሰዋል። በዚህ እኩይ ዓላማቸው ብዙ ዜጎች ተጎድተዋል። 124 ሺህ የሚሆኑ ዜጎች ተፈናቅለዋል።
ሌላው ግጭቱ ያስከተላቸው የሥነ ልቦና ቀውሶች አሉ። በማህረሰቡ መካከል መጠራጠር እንዲኖር የማድረግ ሠፊ ሥራ ተሠርቷል። ስለዚህ ይህንንም የሚያርም ሥራ መሥራት ያስፈልጋል። በአንድ በኩል የተፈናቀለውን ዜጋ ወደቤት የመመለስና የማቋቋም፣ በሌላ በኩል እስካሁን ለተፈጠረው ሞት፣ ግድያ፣ እና ጭፍጨፋ ያጣናቸውን ውድ ዜጎቻችንን መመለስ ባችልም ቢያንስ ይህ ቁርሾ ሆኖ እንዳይቀጥል የእርቅ፣ የአብሮነትና ዘላቂ ሠላም በሚያሰፍን መንገድ የአካባቢውን ባህልና ወግ ተከትለን ሥራ እንሰራለን። እነዚህና የመሣሠሉ ሥራዎችን ሠርተን ሕዝብን ለመካስ መንግሥት በጣም በቁርጠኝነት እየሠራ ነው።
እዚያ አካባቢ የተፈጠረውን ነገር ሙሉ ለሙሉ ተቆጣጥረን ሕብረተሰቡ ላይ እንዲህ ዓይነት ጥፋት በተለይ የጅምላ ጭፍጨፋ የማይከሰትበት ደረጃ ላይ ለማድረስ ማንኛውንም መስዋዕትነት ለመክፈል መንግሥትና ብልጽግና ፓርቲ ዝግጁ ነው።
አዲ ዘመን፡– በአካባቢው ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን ምን አይነት ተጨባጭ ስራዎች ታቅደዋል?
አቶ ተስፋዬ፡– ግብረሃይሉ ወደአካባቢው ሲሄድ አካባቢው ከፍተኛ የሥጋት ድባብ የነገሠበት አካባቢ ነበር። በሠላም መውጣትና መግባት ከባድ የሆነበት ሁኔታ ነበር። በሕዝቦች መካከልም ከፍተኛ መጠራጠር የነገሠበት ሁኔታ ነበር። ስለዚህ የኛም የመጀመሪያው ሥራ ሠላምና ፀጥታ እንዲከበር የማድረግ ነበር። መዋቅሩን መፈተሽና ማስተካከል፣ የፀጥታ ሃይሉን መፈተሸና ማስተካከል፣ መዋቅሩን እንደገና ማደራጀት፣ ቀበሌዎችን እንደገና ማደራጀት፣ የሚሊሻ ሃይሉን እንደገና ማደራጀት እነዚህ ቅድመ ዝግጅት ሥራዎች ናቸው።
በሠላም መንገድ ቁጭ ብሎ መነጋገር የማይፈልገው ሃይል ደግሞ የፀጥታ ሃይሉ በተሠጠው ሕገ መንግሥታዊ ሥልጣን መሠረት ሕግ የማስከበር ሥራ እየሰራ የነበረበት ሁኔታ ነበር። የተፈናቀሉ አካላት ወደነበሩበት ሲመለሱ የአካባቢው ሠላምና ፀጥታ አስተማማኝ እንዲሆን ቀበሌውን ሊጠብቁ የሚችሉ ታጣቂዎች ተመልምለው ወደሥራ ሲገቡ፣ አሁን ቁጭ ብሎ መነጋገርና ያለፉ ጉዳዮች ላይ ይቅር የሚባባሉበት፣ ወደእርቅ የሚገቡበት ነገር መፍጠር ይቻላል። አሁን አካባቢው እየተረጋጋ መጥቷል፤ ቅድም ባልኩት መንገድ ፀጥታውም እየተሻሻለ መጥቷል፤ ተፈናቃዮችን ለመመለስ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች እየተጠናቀቁ ነው፤ የነዚህ ሥራዎች በሙሉ ማለቅ ለእርቅና ዘላቂ ሠላም ጠቃሚ ናቸው።
አዲስ ዘመን፡– አንዳንዶች ችግሩ ሕወሀት የተከለው የሠዓት ቦንብ ነው ይላሉ ፤ ይህ ምን ማለት ነው ? ለምንስ ይህንን ቦንብ በቀላሉ ማክሸፍ አልተቻለም ?
አቶ ተስፋዬ፡– በትክክል፤ የችግሩ አንዱ መነሻ ባለፉት 27 ዓመታት የልዩነት ማዕከላት ተደርጎ የተሠበከው ሥብከትና የተዛቡ ትርክቶች ናቸው። አብሮነትና አንድነት ዝቅ ተደርጎ ወይም እንዲጠፋ ተደርጎ ልዩነት ከፍ እያለ እንዲሄድ የተደረገበት ሁኔታ ነው የፈጠረው። ለዚህም ነው ረጅም ጊዜ የተዘራ ዘር አሁን በቅሎ ፍሬ እያፈራ ያለው። ችግሩ ትናንት ወይም ከትናንት በስቲያ የተፈጠረ አይደለም። ለረጅም ጊዜ ሲዘራ የነበረ ያልተገባ ትርክት እና ሴራ ውጤት ነው። ቀደም ሲል የተዘራ ዘር አሁን ደርሶ፣ በቅሎ፣ አድጎ፣ አብቦ፣ ፍሬውን ነው እየለቀምን ያለነው። አንዱ ውስብስብ የሚያደርገውም ይኸው ነው።
ይህንን ችግር ለዘለቄታው የሚፈታ መፍትሄ ያስፈልጋል። አሁን የተጀመሩ ሥራዎች በተሟላ መንገድ ተግባራዊ ሲሆኑ፤ ችግሩ የሚፈታ ነው። ለምሣሌ የፀጥታ አካላት ዋነኛ ሥራቸው ሃገርን መጠበቅ ነው፤ ሕዝብን መጠበቅ ነው። የሃገር እና የሕዝብ ደህንነትን መጠበቅ ነው። ፓርቲን አይደለም የሚጠብቁት። የሃገር አንድነት፣ የሕዝብ ደህንነት ነው። ለዚህ ደግሞ ሁሉንም ሕዝብ በእኩል ማየት፣ ሁሉም ሰው በሕግ ፊት እኩል ነው ብሎ ማመን፣ የሚችል የፀጥታ መዋቅር መገንባት ያስፈልጋል ።
አዲስ ዘመን፡- አሁን ለተፈናቀሉ ዜጎች የሚደረገው ሰብዓዊ ድጋፍ በምን ሁኔታ ላይ ነው?
አቶ ተስፋዬ፡- ተፈናቃዮችን በተመለከተ ሁለት ሥራ እየተሠራ ነው። አንዱ ጊዜያዊ የሰብዓዊ ዕርዳታ መስጠት ነው። ይህንን በተመለከተ በማዕከል ደረጃ በሠላም ሚኒስቴር የሚመራ የአደጋ ሥጋት አመራር ኮሚሽን የሚባል አንድ ቡድን አለ። ይህ ቡድን ሰብዓዊ ድጋፍን የማድረስ ሥራ ይሠራል፤ ቀጥሎ ደግሞ በቋሚነት ወደነበሩበት እንዲመለሱ ማድረግ ይሠራል። ይህ አሁን እየተሠራ ነው።
ብዙ ሰው ከቤቱ ሲፈናቀል የሚደርሰው ችግር ብዙ ነው። በቤት ውስጥ ሆኖ እንኳን ንፁህ ውሃ የሚያገኘው ሕዝብ ምን ያህል እንደሆነ ይታወቃል። መንግሥት በተቻለ መልኩ ወሣኝ የሆኑ ሰብዓዊ ድጋፎችን ለማድረስ እየሠራ ነው። ነገር ግን በቂ ነው ማለት አይደለም። የተለያዩ ቅሬታዎች ሊኖሩ ይችላሉ። ያም ሆኖ ግን እንዲህ ዓይነት ቀውስ ከተፈጠረ በዋናነት ችግሩ የሚፈታው ዜጎችን ወደነበሩበት በመመለስ ነው። እኛ ብዙ ተፈናቃዮችን ዞረን አነጋግረናቸዋል። የሚሉት “እኛ እኮ ከሰው ዕርዳታ የምንፈልግ ሣንሆን ለሰው ዕርዳታ የምንሰጥ ነን። ስለዚህ ቶሎ ብላችሁ ወደቦታችን መልሱን” ነው። ይህንን ተጨባጭ እውነታ ታሣቢ በማድረግ በቋሚነት ወደነበሩበት ለመመለስ እየሠራን ነው።
አዲስ ዘመን፡– ስለሰጡኝ ማብራሪያ በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ሥም አመሠግናለሁ፡–
አቶ ተስፋዬ፡– እኔም አመሠግናለሁ።
አዲስ ዘመን የካቲት 08 /2013