ኃይለማ ርያም ወንድሙ
በዛሬው አዲስ ዘመን ድሮ ዓምዳችን በ1960 የወጡትን አይተናል። በዘመን ዳሰሳችን ከተፈቀደላቸው በላይ ትርፍ ጭነው የነበሩ አሽከርካሪዎች እንደተቀጡ ፤ ባለንበት በኮረና ዘመን ተራራቁ እየተባለ ተሽከርካሪዎች ሰው ጠቅጥቀው ሲያሳፍሩ የሚቀጣቸውም የሚቆጣቸውም ሲጠፋ እያየን ነው። በድሬዳዋ የንጽሕና መመሪያ ያልተከተሉ ዘጠኝ ልኳንዳ ቤቶች መዘጋታቸውንም ይነግረናል። አሁን እኮ በተመሳሳይ ምግብ ቤቶች ንጽህናን በሚመለከት ኃላፊዎች “እያየነው ነው እርምጃ እንወስዳለን “ሲሉ እንሰማን አንጂ እርምጃውን ማየት አልቻልንም። ሌሎች ተመሳሳይ ዘገባዎች አሉት ተከታተሉት።
ከተፈቀደላቸው በላይ ሰዎች ያሳፈሩት ተቀጡ
አቶ በቀለ ደገፉ የተባሉት ሰው መጋቢት ፲፬ ቀን ፷ ዓ.ም ከቀኑ ፲ ሰዓት ከ፲፭ ደቂቃ ሲሆን ፤ በአርበኞች መንገድ ቁጥር ፲፪ ሺ ፮፻፺፭ አ.አ ሊዊንቺና መኪና እየነዱ በሕግ የተፈቀደላቸውን ከ፳ ሰው በላይ አሳፍረው ፭ ሰው ትርፍ ስለጫኑ በትራፊክ ተቆጣጣሪነት ክስ ቀርቦባቸው መጋቢት ፳፫ ቀን ፷ ዓ.ም፤ ፩ኛ ወረዳ ፍርድ ቤት ቀርበው ጥፋታቸውን ስለአመኑ የፍርድ ቤት አስተያየት
አድርጎላቸው ፩፻፳ ብር (አንድ መቶ ሐያ ብር )መቀጫ እንዲከፍሉ ተፈርዶባቸዋል ሲል የትራፊክ ምርመራና መቆጣጠሪያ ፖሊስ ጽሕፈት ቤት ገለጠ።
እንዲሁም አቶ ኃይሉ ታደሰ የተባሉት ሰው መጋቢት ፲፬ ቀን ፷ ዓ/ም ከቀኑ ፲፩ ሰዓት ከ፴፭ ደቂቃ ሲሆን፤ በአርበኞች መንገድ ቁጥር ፷ሺ፯፻፴፱ አ/አ ፎርድ ታኖስ ሊዎንቺና የሆነ መኪና እየነዱ ፩ኛ በሕግ ከተፈቀደላቸው ከ ፲፬ ሰው በላይ ፬ ሰው ትርፍ ስለጫኑ ፤ ፪ኛ ያለመንጃ ፈቃድ ስለነዱ በትራፊክ ፖሊስ ክስ ቀርቦባቸው ፩ኛ ወረዳ ፍርድ ቤት ቀርበው ጥፋታቸውን ስለአመኑ ፶ ብር መቀጫ እንዲከፍሉ መደረጋቸውን በድጋሚ አብራርቷል።
(ሚያዝያ 10 ቀን 1960 የወጣው አዲስ ዘመን)
፱ የድሬዳዋ ልኳንዳዎች ተዘጉ
ድሬድዋ፡-(ኢ-ዜ-አ) የድሬዳዋው ማዘጋጃ ቤት ያወጣውን የንጽሕና መመሪያ ያልተከተሉ ፱ የድሬዳዋ ልኳንዳ ቤቶች እንዲዘጉ ተደረገ።
በድሬዳዋ ከተማ ከሚገኙት ፳፰ ልኳንዳ ቤቶች ውስጥ ዘጠኙ እንዲዘጉ የተደረጉት ከ፫ ወር በፊት የድሬዳዋ ማዘጋጃ ቤት የሰጣቸውን መምሪያዎች በሚገባ አሟልተው ያልተገኙ በመሆናቸው ነው ሲሉ የድሬዳዋ ማዘጋጃ ቤት የጤና መኰንን አቶ አብርሃም ዮሴፍ ገለጡ።
አንድ የልኳንዳ ቤት ለሥጋው ማኖሪያ በደንብ የተሠራ የዝንብ መከላከያ ቁም ሳጥን ፤ በንጹሕ ቆርቆሮ የተለበደ ጠረጴዛ ፤በደንብ የተሠራ የሲሚንቶ ወለል ክዳን ያለው የጥራጊ ማጠራቀሚያ ፤ ለሠራተኞች ንጹሕ ቆብና ሽርጥ እንዲሁም የጤንነት መረጃ የምስክር ወረቀት ፤ የንጽሕና ቤት ፤ የእጅ መታጠቢያና ፎጣ ክፍሉ በቂ ብርሃንና አየር እንዲኖረው ሉኳንዳ ቤቱ ከመኝታ ቤቱ ጋር ግንኙነት እንዳይኖረው የማዘጋጃ ቤቱ መምሪያ ከማስረዳቱም ሌላ ፤ በሉኳንዳ ቤት ውስጥ ሥጋ አብስሎና ጠብሶ መሸጥ አጥብቆ የተከለከለ መሆኑን ያስጠነቅቃል።
የተዘጉት የ፱ ልኳንዳ ቤቶች አላፊዎች፤ የድሬዳዋ ማዘጋጃ ቤት ያወጣውን መመሪያ አሟልተው ከተገኙ የሚከፈትላቸው መሆኑን አቶ አብርሃም በተጨማሪ አስረድተዋል።
(ሚያዝያ 14 ቀን 1960 የወጣው አዲስ ዘመን)
የዱር አራዊት የገደሉት ተቀጡ
ጐሬ፡-(ኢ-ዜ-አ) በሕግ የተከለከለውን የዱር እንስሳት የገደሉት ፰ ሰዎች እያንዳንዳቸው ፣ ፩፻ ብር መቀጫ እንዲከፍሉ የጎግና ጀር አውራጃ ፍርድ ቤት መጋቢት ፲፩ ቀን በዋለው ችሎት ፈረደ።
እነርሱም ፤ አቡቶ ኡቶው ፤ እኩት አቡላ ፤ አቡላ ኪዱ ፤ ኢጆር አቡላ ፤ኡማን ኡጋኤ፤ አደር ጉይ፤ ቦም ጊሎ ፤ኡጋት አበነ የተባሉት ናቸው።
ተከሳሾቹ የተፈረደባቸውን ገንዘብ ለመክፈል ባይችሉ እያንዳንዳቸው የ፮ ወር እሥራት እንዲቀጡ ሲበየንባቸው ፤ በእጃቸውም የተገኘው ፫ ጠመንጃና የልዩ ልዩ አውሬዎች ቆዳ ለመንግሥት በውርስ ገቢ እንዲሆን የተፈረደባቸው መሆኑን የኢሉባቡር ጠቅላይ ግዛት ዋና ጸሐፊ አቶ አበራ ወልደሩፋኤል ገለጡ።
(ሚያዝያ 6 ቀን 1960 የወጣው አዲስ ዘመን)
በ፩ የጥድ ዛፍ የ፰ ወር እስራት ተፈረደባቸው
ደሴ (ኢ.ዜ.አ)፡-በወሎ ጠቅላይ ግዛት በዋግ አውራጃ ከተተከለለው የመንግሥት ደን ውስጥ በመግባት ፩ የጥድ ዛፍ ቆርጠው ሸጠዋል በመባል የተከሰሱት በ፰ ወሮች እስራት እንዲቀጡ የወብላ ወረዳ ፍርድ ቤት ፈረደ።
በወሎ ጠ/ግዛት በዋግ አውራጃ ጎንብረዳ በተባለው ቀበሌ ጥድ እንጨት ቆርጠው የተያዙት ቸኮል ፋንታዬ ፤መርሣ በረሄ፤ ተፈራ ጫለው ፤ተገኝ በረሄ ፤እንግዳ ብሩ፤ ብርሃኑ ፋንታዬ ፤ሐዲስ ንጉሠ፤ ትኩ ይርዳ የተባሉ ናቸው።
እነዚህ ሰዎች አጥፊ መሆናቸው በሕግ ስለተመሰከረባቸው መጋቢት ፳፬/፷ ዓ/ም/ ወብላ ወረዳ ፍ/ቤት ቀርበው ፤ እያንዳንዳቸው በአንዳንድ ወር እንዲቀጡ የተፈረደባቸው መሆኑን የአውራጃው ፖሊስ አዛዥ የመቶ አለቃ ካሣ በዳኔ ገለጡ።
(ሚያዝያ 1 ቀን 1960 ዓ.ም የወጣው አዲስ ዘመን)
አዲስ ዘመን የካቲት 08 /2013