
አብርሃም ተወልደ
ይህ ወር የአድዋ ድል ወር በመባል ይታወቃል። ሣምንቱ ደግሞ የወሩ መጀመሪያ ነው። ታዲያ በዚህ ሣምንት በአድዋ ድል ዋዜማ ምን ተከናወነ ለሚለው ታሪክ ከትቦ ከያዛቸው መካከል ከድሉ አንድ ዓመት ቀድሞ ማለትም በየካቲት 7 ቀን 1887 የተከናወነው ተግባራት ይጠቀሳል፤ ይህም ንጉሰ ነገሥት ምኒልክ ከትግራዩ ራስ መንገሻ እንዲሁም ከታዋቂው ጄኔራል ራስ አሉላ እና ከጎጃሙ ንጉሥ ተክለሀይማኖት ጋር ስለ አድዋ ጦርነት እና ስለተለያዩ ልማቶች የተወያዩበት በዚሁ ሣምንት ነበር።
አጼ ምኒልክ እና ሠራዊታቸው በዝዋይ ደሴቶች የነበራቸውን ቆይታ አጠናቀው ወደ አዲሰ አበባ ሲመለሱ አገራቸውን ከ16ኛውን ክፍለ ዘመን ወደ 19ኛው ክፍለ ዘመን የመሸጋገሯ ምልክቶች የተባሉ ተግባራትን በአማካሪያቸው አልፍሬድ ኢግል መሪነት በሥራ ላይ እንዲውል ማድረግ ጀመሩ።
ከእነዚህ በምኒልክ ከተወሰዱት የሥልጣኔ ርምጃዎች መካከል አንዱ ለመጀመሪያ ጊዜ የመገበያያ ገንዘብን አስቀርፀው በመላው አገሪቱ የተቀረጹት በፓሪስ ፈረንሣይ ሲሆን፤ የገንዘብ ዓይነቶቹም ብር አንድ ሩብ መሃለቅ ተሙንና ግርሻ ይባላሉ።
በገንዘቡ ላይ በአንደኛው ገጽ የአጼ ምኒልክ ምስል ዘውዳቸውን እንደጫኑ ተቀርጾበታል። በዙሪያውም “ዳግማዊ ምኒልክ ንጉሰ ነገሥት ዘ ኢትዮጵያ” የሚል ጽሑፍ ይገኛል። በሌላ በኩል ደግሞ ዘውድ የጫነ አንበሣ የኢትዮጵያን ሠንድቅ ዓላማ በትከሻው አንግቦና በፊት እግሩ ደግፎት ይታያል። በዙሪያው “ሞአ አንበሣ ዘእምነገድ ይሁዳ” የሚል ጽሁፍ ይገኝበታል። በሁሉም የገንዘብ ዓይነቶች ላይ “ኢትዮጵያ ታብጽሃዊ አብ እግዚያብሔር” የሚል ጽሑፍ ሠፍሮባቸዋል።
ሚኒልክ ገንዘቡን አስቀርፀው ወደ አገር እንደገባ ካደረጉ በኋላ የሚከተለውን አዋጅ አወጡ።
“ከዚህ ቀደም ነጋዴም ሆነ ባላሀገር ወታደርም የሆንክ ሰው ሁሉ በየገቢያውና በመንገዱ በየሥፍራው ሁሉ በጥይት ስትገበያይ ትኖር ነበር። አሁን ግን በእኔ መልክ እና ሥም የተሠራ ብር አላድ፣ ሩብ ተሙን ፣ መሃለቅ አድርጌሃለው እና በእሱ ተገበያዩ እንጂ እንግዲህ በጥይት መገበያየት ይቅር ብየሃለው።”
ከዚህም ሌላ በአልፍሬድ ኢግል ሐሳብ አቅራቢነት እና ዕቅድ አውጪነት በአዲስ አበባ ከተማ ከአውሮፓ በሰባት ሺህ ማርትሬዛ ገንዘብ የተገዛ ቧንቧ ቤተ መንግሥት ድረስ ዝርጋታው እንዲካሄድ ተደረገ።
በየቦታው የውሃ ማጠራቀሚያ የኮንክሪት ገንዳዎችንም በመገንባት ለመጠጥ የተጣራ እና ለልብስ ማጠቢያ ለሌሎች አገልግሎት የሚውል ውሃ እንደ ልብ ተገኘ። እነዚህን መሠል እንቅስቃሴዎች ሲጀመሩ የሀይማኖት አባቶች የቤተ ክርስቲያን መሪዎች በሙሉ በዝምታ ሲመለከቱ ነበር።
ነገር ግን የጎጃሙ ንጉሥ ተክለሃይማት ተከታዮቻቸውን ይዘው ለአሥራ ሰባት ቀናት ምክክር ወደ አዲስ አበባ ሲመጡ በተደረገው የአቀባበበል ሥርዓት ላይ የፍራንኮ አፍሪካ ትሬዲንግ ካምፓኒ ወኪል የነበረው ጎሥቶን ቫንደርማይም ምኒልክ እና ተክለሃይማት ሲገናኙ ፎቶ ሲያነሳቸው በሥፍራው የነበሩ ቀሣውስት “ተው! ተው! ይህን የሠይጣን ሥራ” እያሉ መጮህ ጀመሩ።
ይህ መጯጯህና በሥሜት እየገሠገሱ ፎቶ ግራፉን ወደሚያነሳው ጎስቶን ቫንደርማይም የሚጠጉ ቀሣውስትን በመገረም ሲያዩ የነበሩት ምኒልክ በቁጣ “እናንተ የማትረቡ! ወደ ቤታችሁ ተመለሱ፤ ከአሁን ወዲያ የሠይጣን ሥራ ነው! ተው! የሚል ቃል ስትናገሩ ብሰማ ወታደሮቼን አዝዤ ነው የማስገርፋችሁ… አርፋችሁ ተቀመጡ። አላበዛችሁትም ወይ” ሲሉ ገሠጿቸው። ቀሣውስቱም በዝምታ ወደነበሩት ቦታ ተመልሰው ተቀመጡ።
ቫንደርማይም ፎቶግራፍ ማንሣት የጀመረው ገና አቴጌ ጣይቱ ብጡል ከምኒልክ ጋር በተጋቡበት ዓመት ነበር። በወቅቱም ጣይቱ ቫብደርማይምን ጠርተው ለአንድ ሰዓት ያህል ከደንገጡሮቻቸው ከልዕልት ዘውዲቱ ፣ ሚኒልክ ከሌሎች የተከበሩ የቤተ መንግሥት ቅርብ ወይዘሮዎች ጋር መሆን ፎቶ ተነስተው ነበር።
ቫንደርማይም በርካታ ፎቶ ግራፎችን ካነሣቸው በኋላ በእቴጌ ጣይቱ ጋባዥነት በቤተ መንግሥት በክብር እራት ተጋብዞ እንደተሸኘ ፈረንሣዊ ወደ ሀገሩ ከተመለሠ በኋላ በጻፈው ማስታወሻ ላይ አሥፍሯል።
የካቲት 7 ቀን 1887 ተከታዮቻቸውን አስከትለው አዲስ አበባ የመጡት የጎጃም ንጉሥ ተክለሀይማኖት ከአራት ዓመት በፊት ምኒልክ ንጉሠ ነገሥት መሆናቸውን ሲያውጁ በሥራቸው እንደሚተዳደሩ ካሣወቋቸው በኋላ አሁን ከሚኒልክ ጋር የተገናኙት ለመጀመሪያ ጊዜ ነበር።
ምኒልክ ከጎጃም ንጉሥ ተክለሀይማኖት በነበራቸው ቆይታ የሚኒልክ ቤተ መንግሥት ታላላቅ የግብር አዳራሾች በቅርቡ የተገነባው የቧንቧ ውሃ መስመር ዝርጋታ እና የሚሰጠው አገልግሎት በአጠቃላይ የንጉሠ ነገሥቱ መንግሥቱ እንቅስቃሴን በሚገባ ተመለከቱ።
ከዚያ በላይ በግብር ማስገበሪያ አዳራሽ በቤተ መንግሥት እልፍኝ ጣሪያዎች ላይ የተንጠለጠሉት ባለግርማ ሞገሶቹ አርባ ስምንት ሻማዎች የሚይዟቸው የመብራት መቅረዞች እና መብራቶች ምሽቱን ወደ ቀን የሚቀይሩበት አቅም አሥገርሟቸው ነበር።
ከምኒልክ ጋር በአዲስ አበባ እና በተለያዩ አካባቢዎች እየተከናወኑ ያሉት ግንባታዎችን ተዘዋውረው ከመጎብኘታቸው በተጨማሪ ወደ አቃቂ ወንዝ ወርደው በወንዙ ዳር ያለ ተራራ በድማሚት ሐይል ሲናድ እና ወደ ቁልቁለት ድንጋይነት የሚቀየርበት ሂደትን ታዝበዋል።
በቤተ መንግሥት በሠነበቱባቸው ቀናት ለክብራቸው በየቀኑ በእቴጌ ጣይቱ ልዩ ትዕዛዝ ታላቅ ድግስ እየተደገሰ ከነተከታዮቻቸው በአክብሮት እና በታላቅ ክብር የተስተናገዱት ንጉሥ ተክለሀይማኖት በተገኙበት ምኒልክ ከሥዊዛዊው አማካሪያቸው ከአልፍሬድ ኤግል ጋር ለረዥም ዓመታት ሲመክሩበት የነበረውን የባቡር ትራንስፖርት መሥመርን የመዘርጋት ሥራ ለመጀመር የሚያስችላቸውን ውል ለመዋዋል መወሠናቸውን ይፋ አደረጉ።
ይሁንና ለለበርካታ ዓመታት ሲያብላሉት እና ሲያንከባልሉት የቆዩት የባቡር መሥመር ዝርጋታ እና ባቡር ትራንሥፖርት የመጀመር ሐሳብ በሁሉም ኢትዮጵያውያን ዘንድ በበጎ ዓይን የሚታይ አልነበረም። ሌላው ይቅር ዘመናዊነትን አውሮፓ ድረስ በመሄድ ጥቅሙን በሚገባ ያውቃሉ፤ ተራማጅ ናቸው የሚባሉት ራስ መኮንን እንኳን አይደግፉትም ነበር።
ራስ መኮንን በእርግጥ ሸቀጦችንና የግብር ምርቶችን ከቦታ ቦታ ሲያጓጉዝ በወደብ በኩል ወደ ባህር ማዶ ተሻግሮ እንዲሸጥ ሊያደርግ እንደሚችል ሁሉ ወራሪ ጦሩን ጭኖ ለማስገባት ያገለግላል ብለው እንደሚያምኑ በመግለጽ ተቃውሟቸውን አሠምተዋል።
ኢትዮጵያውያን እንዲህ ዓይነት አቋም ማንፀባረቃቸው አይፈረድባቸውም። ምክንያቱም የእንግሊዝ ጦር አጼ ቴዎድሮስን ለመውጋት ሲመጣ ለሠራዊቱ ሥንቅ ማመላለሻ የሚሆን ሐዲድ ዘርግቶ በባቡር እያጓጓዘበት እንደነበር ለማየት ችሏል።
በተጨማሪም ኢጣሊያ በ1888 ወደ ተራራማው የሀገሪቱ ክፍል ጦሩን ያዘመተው እና እንዲሠፍር ያደረገው ከምጽዋ እስከ ሠቲት የባቡር ሀዲድ በመዘርጋት እና በባቡር በመጓጓዝ ነው። ይህንን በሚገባ ተመልክተዋልና ፀረ ባቡር ትራንሥፖርት አቋም መያዛቸው አያሥገርምም።
በ1894 ምኒልክ የውጭ ወራሪዎች ሥጋት ውስጥ መሆናቸውን በመገንዘብ አብዛኛው የባቡር መሥመር የሚያልፍባቸው አካባቢዎች በንጉሱ ጠንካራ ቁጥጥር ሥር መሆናቸውን ማረጋገጥ ነበረባቸው።
ይህንንም ከፈፀሙ በኋላ የባቡር መሥመር የመጨረሻ መዳረሻ የሆነችው የባህር ወደቧ ጅቡቲ በኢጣሊያ መንግሥት እጅ ሣትሆን የኢትዮጵያ ወዳጅና የምኒልክ አጋር በሆነችው ፈረንሣይ መንግሥት ይዞታ መሆኑን ተከትሎ ፕሮጀክቱን ለማስጀመር የሚስችለውን ሥምምነት በማርች 9 ቀን 1887 ፈረሙ።
ታዲያ የሁለት ሣምንት የቤተ መንግሥት ቆይታቸውን ጨርሰው ከተመለሱት ከንጉሥ ተክለሃይማኖት ቀጥሎ የቤተ መንግሥቱ እና እቴጌ ጣይቱ እንግዳ የትግሬው ራስ መንገሻ ዮሐንስ እና ወደ ስድስት ሺህ የሚደርሱ ተከታዮቻቸው ነበሩ። ራስ መንገሻ ዮሐንስ ስድስት ሺህ የሚጠጋ ጦራቸውን እና የጦሩን አዛዞች አስከትለው ከመቀሌ በኤፕሪል ወር ተነስተው ጉዞ የጀመሩ ሲሆን፤ አዲስ አበባ ለመድረስ ሁለት ድፍን ወራት ይፈጅባቸዋል።
ራስ መንገሻ ዮሐንስ እና ሌሎች የትግራይ መኳንንት ከስድስት ሺህ ከሚበልጠው ጦር ጋር ወደ አዲስ አበባ ሲደርሱ የተደረገላቸውን አቀባበል በተመለከተ የምኒልክ ዜና መዋዕል ፀሐፊ ትዕዛዝ ገብረሥላሴ ባሠፈሩት ሐተታ “አጼ ምኒልክ በሥርዓተ መንግሥት ሆነው ከዙፋንዎ ተቀምጠው ራሶችም፣ ራስ ዳርጌ፣ ራስ ሚካኤል፣ ራስ ወሌ፣ የራስ ወርቅ አድርገው ሊቀ መኳሶችም እንደ ሥርዓታቸው ሆነው ካህናቱም ካባ ለብሰው በቀኝና በግራ ሆነው መንበረ መንግሥቱን ያጥናሉ።
በዙፋኑም በድንኳኑም ያለወርቅ ምንጣፉ የወርቁ ምከዳ ያስፈራል። በዙፋኑም ሠይፈ ጅግሬዎች ባለወርቅ ማክዳ ሠይፍ መዘው ግራ እና ቀኝ ቆመዋል። ደጃዝማቹም መኳንንቱም አጊጠው የነደደ እሣት መስለው በአዳራሹ ሞልተው ቆመዋል።
“የውጭ ሠራዊት እንደ ማዕረግ ማዕረጉ የጦር መሣሪያውን እየለበሰ ሠንደቅ ዓላማውን እየያዘ ከአዳራሹ ደጃፍ ጀምሮ የመዋቱ ወንዝ (አዋሬ አጠገብ) ተሻግሮ እየተጨነቀ ተሠልፎ ነበር።
“ይህ ሁሉ ከተፈፀመ በኋላ ራስ መንገሻ በኋላ ነበሩ። መኳንንቶቹ እነ ራስ ሐጎስ፣ አጼ ዮሐንስ ከሞቱ በኋላ ከአጼ ሚኒልክ ፊት አልደረሱም ነበር እና ድንጋይ ተሸክመው የቀረውም መኳንንት እንደዚሁ ሆኖ ወደ አዳራሹ ገባ።
ድንጋዩን እንደተሸከሙ ወደቁ፤ አጼ ምኒልክም “ምሬያችኋለሁ” አሏቸው። አጋፋሪዎችም ድንጋዩን ከላያቸው ላይ አነሱላቸው። እነዚያ እጅ ነስተው መሬቱን ሥመው ቆሙ፤ በዚህም ጊዜ 31 ጊዜ መድፍ ተተኮሠ።
በቀጣይ ቀናትም ራስ መንገሻ እና የትግራይ መኳንንቶች ከአጼ ሚኒልክና ከሹማምንቶቻቸው ጋር ባደረጓቸው ውይይቶች መላ ትግራይ ለንግሠ ነገሥቱ ታማኝቱን በቃለ መሐላ አረጋገጡ።
በራስ መንገሻ የተራመራው የትግራይ ጦር እና መኳንንት አዲስ አበባ በቆዩባቸው ሃያ ቀናት ከአጼ ምኒልክም ሆኑ ከእቴጌ ጣይቱ ጋር በፍቅር እና በደስታ እንዲሁም በታላቅ መስተንግዶ እና እንክብካቤ አሣለፉ።
ምኒልክ ራስ መንገሻን ከዘመድ በቀር ለንጉሥ የሚገባውን ሙሉ ሽልማት ሸልመውና ሹመታቸውን አጽድቀው አስደሰቷቸው። ወደ ትግራይ ከመጓዛቸው እና ከመሠነባበታቸው በፊት በኢጣሊያ ጦር እንቅስቃሴ ዙሪያ ሹማምነቱ ከራስ መንገሻ እና ከራስ አሉላ ጋር ሰፊ የሆነ ምክክር ያካሄዱ ሲሆን፤ በምንም መልኩ ቢሆን ጣሊያኖች ቢቆሰቁሷቸው እንኳን በእልህ ወደ ጦርነት እንዳይገቡና እያንዳንዱ እንቅስቃሴን እያማከሯቸው ይወስዱ ዘንድ ራስ መንገሻን አሣሰቧቸው።
ራስ መንገሻም ዮሐንስም ከነሠራዊታቸው ምኒልክን እቴጌይቱን ተሠናብተው ወደ መቀሌ ጉዞ ሲጀምሩ ታዋቂው ጄኔራል ራስ አሉላ አባነጋ አዲስ አበባ ምኒልክ ዘንድ ክረምቱን ለማሳለፍ ወስነው እዚያው ቀሩ።
(ለዚህ ጽሑፍ አንደ ምንጭነት “እቴጌ ጣይቱ ብርሃን ዘ ኢትዮጵያ” በብሩክ መኮንን የተጻፈውን እንዲሁም የኢትዮጵያ ታሪክ በባህሩ ዘውዴ እና አጤ ሚኒሊክ በጳውሎስ ኞኞ ተጠቅመናል።)
አዲስ ዘመን የካቲት 7/2013