አዲስ አበባ፡- የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን በቅርቡ ያከናወነውን የንግድ ቤቶች ኪራይ ማሻሻያ ተከትሎ 3ሺህ 204 ተከራዮች ውል ማደሳቸውን ገለጸ፡፡ በመጨረሻዎቹ ቀናት የተፈጠረውን መጨናነቅ ምክንያት በማድረግም የውል ማደሻ ቀኑን እስከ የካቲት 5 ቀን 2011 ዓ.ም ማራዘሙን በመጠቆም ደንበኞቹ በተቀመጠው ጊዜ ውስጥ ቀርበው ውላቸውን እንዲያድሱ አሳስቧል፡፡
የኮርፖሬሽኑ ኮርፖሬት ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ክብሮም ገብረመድህን ትናንት ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገሩት፤ ኮርፖሬሽኑ ያከናወነውን የንግድ ቤቶች ዋጋ ጭማሪ ተከትሎ ውል መፈጸም ከሚገባቸው 5ሺህ 947 ተከራዮች ውስጥ እስከ ትናንት በስቲያ በነበረው ሂደት 3ሺህ 204 ተከራዮች (57 ነጥብ 7 በመቶዎቹ) ውል ፈጽመዋል፡፡
እንደ አቶ ክብሮም ገለጻ፤ በተቀመጠው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት ተከራዮች እስከ ጥር 25 ቀን 2011 ዓ.ም ውል ፈጽመው ማጠናቀቅ ቢኖርባቸውም፤ የኪራይ ጭማሬውን እንዲቀየር ወይም እንዲሻሻል እናስደርጋለን በሚል የተሳሳተ ግንዛቤ ዘግይተው ቀኑ ሊጠናቀቅ አራት ቀናት ሲቀሩት ነው በሺዎች የሚቆጠሩ ተከራዮች መምጣት የጀመሩት፤ ይህ ደግሞ አንድ ቅርንጫፍ እስከ 600 እና 700 ሰው እንዲያስተናግድ በማድረግ በአገልግሎት አሰጣጣቸው ላይ ተጽዕኖ ፈጥሯል፡፡ ችግሩን ለማቃለልም ሰዎችን በውስጥ አቅም በማሰልጠን ጭምር በቅርንጫፎች ሄደው እንዲያግዙ ቢደረግም በተቀመጠው የጊዜ ገደብ ውስጥ ማጠናቀቅ አልተቻለም፡፡ በመሆኑም የውል ማደሻው ቀን እስከ የካቲት 5 ቀን 2011 ዓ.ም እንዲራዘም ተደርጓል፡፡
የቀኑን መራዘም ለደንበኞች ያሳወቁና ማስታወቂያም የለጠፉ መሆናቸውን የጠቆሙት አቶ ክብሮም፤ ሰሞኑን በነበረው መጨናነቅ የታዩ ክፍተቶችን በመለየት ደንበኞች ተገቢውን አገልግሎት እንዲያገኙ የሚያስችል አሠራር የዘረጉ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡ ደንበኞችም ቀደም ሲል በተለያየ ምክንያት በመዘግየታቸው የተፈጠረውን መጨናነቅ ዳግም እንዳይፈጠር በተቀመጠው ጊዜ ውስጥ ቀርበው ውል እንዲፈጽሙም አሳስበዋል፡፡ ይሁንና፤ በተጠቀሰው ቀን ውስጥ ውል የማይፈጽሙ ግለሰቦች ካሉ ኮርፖሬሽኑ በቤቶች አስተዳደር መመሪያ ቁጥር 2/2010 አንቀጽ 52 መሰረት የኪራይ ውላቸውን አቋርጦ ለሌሎች የንግዱ ማህበረሰብ አባላት በጨረታ የሚያስተላለፍ መሆኑን አበክረው ገልጸዋል፡፡
በተያያዘ ዜና፣ ኮርፖሬሽኑ ማህበራዊ ኃላፊነቱን ለመወጣት ለመቄዶንያ የአረጋውያንና የአዕምሮ ሕሙማን መርጃ ማዕከል ድጋፍ ማድረጉን አቶ ክብሮም ገልጸዋል፡፡ እንደ አቶ ክብሮም ገለጻ፤ ኮርፖሬሽኑ ከተጣለበት አገራዊ ተልዕኮ ባለፈ ማህበራዊ ኃላፊነቱን ለመወጣት ለመቄዶንያ የአምስት ሚሊዮን ብር ድጋፍ ማድረጉን በመጠቆም፤ በተመሳሳይ ማዕከሉ ለሚያከናውነው ግንባታ ግብዓት የሚውል 500 ሜትር ኪዩብ ጠጠር፤ 200 ሺህ ብር የሚገመቱ በተቋሙ ውስጥ የነበሩ የቢሮ ቁሳቁስ፤ እንዲሁም በማዕከሉ የሚመረቱ ለተለያዩ ቁሳቁስ መሸጫ የሚሆን ፒያሳ ላይ አንድ የንግድ ቤት መስጠቱን አብራርተዋል፡፡ በቀጣይም ማህበራዊ ኃላፊነቱን ለመወጣት ተመሳሳይ ተግባራትን እንደሚያከነውን ገልጸዋል፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 29/2011
ወንድወሰን ሽመልስ